የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ይቻላል
የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ይቻላል
ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
አንሄሊካ ከአሥር የቤተሰቧ አባላት ጋር በሜክሲኮ ዋሃካ ግዛት በሚገኘው አንድ ትንሽ ገጠራማ መንደር ውስጥ ትኖር ነበር። ቤተሰቡ ደሃ ሲሆን የዘወትር ምግቡ የበቆሎ ቂጣ፣ ቦሎቄ፣ ቃሪያ የገባበት ስጎ፣ ሩዝ፣ ጣፋጭ ዳቦ እና ሻይ ነው። አንሄሊካ “ዕድገታችን በጣም ውስን ነበር” በማለት ተናግራለች። “ደቃቃዎችና ከሲታዎች ነበርን። ብዙውን ጊዜ እንደ ሆድ ሕመም፣ ጥገኛ ተውሳኮችና ጉንፋን ያሉ በሽታዎች ያጠቁን ነበር።”
አንሄሊካና ቤተሰቧ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሲሉ ወደ ሚክሲኮ ሲቲ ተዛወሩ። አሁን ዕለታዊ ምግባቸው ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ ቅባት፣ ጥቂት ቅጠላ ቅጠሎችንና የተለያዩ
የታሸጉ ምግቦችን ያካተተ በመሆኑ የአሁኑ አመጋገባቸው ከበፊቱ በጣም የተሻለ እንደሆነ ይሰማታል። ይሁን እንጂ አመጋገባቸው በእርግጥ የተመጣጠነ ሆኗልን?የተሳሳተ የአመጋገብ ልማድ —ምን ያህል ተስፋፍቷል?
በዓለም ዙሪያ ወደ 800 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጦት ሳቢያ የመሞት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። የዓለም የጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) በ1998 ባወጣው የዓለም የጤና ሪፖርት መሠረት ከአምስት ዓመት እድሜ በታች ባሉ ሕፃናት ላይ ከሚደርሰው ሞት ውስጥ ወደ 50 በመቶ የሚጠጋው ከተመጣጠነ ምግብ እጦት ጋር የተያያዘ ነው። በሕይወት መቀጠል የቻሉትም ቢሆኑ በአብዛኛው ጥሩ ጤንነት የላቸውም።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ወደ 800 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ከልክ ያለፈ የአመጋገብ ልማድ በማዳበራቸው ሳቢያ የመሞት አደጋ እንደተደቀነባቸው አንዳንዶች ይናገራሉ። የተሳሳተ የአመጋገብ ልማድ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ የስብ ክምችት መፈጠር፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ሲሮሲስ የተባለ ጉበትን የሚያጠቃ በሽታና የስኳር በሽታን የመሳሰሉ ከባድ በሽታዎች ብሎም የተለያዩ የካንሰር በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚከተለው በማለት ጉዳዩን ጠቅለል አድርጎ አስቀምጦታል:- “የተሳሳተ የአመጋገብ ልማድ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ እጦትን፣ የአንዳንድ ንጥረ ነገሮች እጥረትንና ከልክ በላይ መመገብን ያጠቃልላል። እንዲሁም ለሞት፣ ለአካል ጉዳተኝነት፣ ለአእምሮ ዘገምተኝነትና ለዓይነ ሥውርነት ይዳርጋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆችን እድገት በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል።”
በአንድ አገር ውስጥ በቂ ምግብ የማያገኙም ሆነ ከልክ በላይ የሚመገቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በአንድ ቤት ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ የማያገኙ ሕፃናትና ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሚያስቸግራቸው አዋቂዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኝ ያደገ ልጅ አዋቂ ሲሆን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያስቸግረው ይሆናል። ከገጠር ወደ ከተማ የሚዛወሩ ሰዎች እንዲህ ያለ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል።
ብዙ ሰዎች በጤንነታቸውና በአመጋገብ ልማዳቸው መካከል ያለውን ግንኙነት አይገነዘቡም። ምናልባት ይህ የሆነው የተሳሳተ
የአመጋገብ ልማድ በአንድ ሰው ጤንነት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ቅጽበታዊ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ብዙ በሽታዎችን ሊከላከል ይችላል። እንዲያውም ጤናማ የአመጋገብ ልማድ በማዳበርና የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱትን የካንሰር ሕመሞች መከላከል እንደሚቻል የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል። ታዲያ አመጋገብህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?አመጋገብህን ማሻሻል የምትችልበት መንገድ
አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ምግብ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባል። የመጀመሪያው ክፍል በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ አጃ፣ ገብስና ማሽላ የመሳሰሉትን እህሎች እንዲሁም ድንችና ስኳር ድንች የመሳሰሉትን ከመሬት ሥር የሚበቅሉ ተክሎች ያካትታል። እነዚህ የካርቦሃይድሬት ምግቦች ኃይል ይሰጣሉ። ሁለተኛው ክፍል ባቄላ፣ አኩሪ አተር፣ ምስርና ሽምብራ የመሳሰሉትን የአበባ እህሎች እንዲሁም ሥጋ፣ ዓሣ፣ እንቁላል፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ የመሳሰሉትን የእንስሳ ውጤቶች ያጠቃልላል። እነዚህ ፕሮቲን፣ ብረት፣ ዚንክና በርካታ ቪታሚኖችን ይዘዋል። ሦስተኛው ክፍል ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬን የሚያጠቃልል ሲሆን እነዚህ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑትን ቪታሚኖችና ማዕድናት ይዘዋል። አሰር ያላቸውና ኃይል የሚሰጡ ከመሆናቸውም በላይ ተፈጥሯዊ የሆነ ቪታሚን ሲ የሚገኘው ከእነዚህ የምግብ ዓይነቶች ብቻ ነው።
በሜክሲኮ የሚገኘው የሳልቫዶር ሱቢራን ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲካል ሳይንስስ ኤንድ ኒውትሪሽን (INCMNSZ) ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሄክቶር ቡርጂስ እንደተናገሩት ከሆነ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ሦስቱንም የምግብ ክፍሎች ያካተተ፣ በቂና የተመጣጠነ መሆን ይኖርበታል። “በእያንዳንዱ የመመገቢያ ሰዓት ከእያንዳንዱ የምግብ ክፍል ቢያንስ አንድ ነገር ማከልና ከየክፍሉ የምንጠቀምባቸውን የእህል ዓይነቶችም ሆነ የሚዘጋጁበትን መንገድ በተቻለ መጠን መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ” ተናግረዋል።
የማሪያን ሁኔታ ተመልከት። እርሷና ቤተሰቧ በሚክሲኮ ሂዳልጎ ግዛት በሚገኘው የአቶፒክስኮ ገጠራማ መንደር ውስጥ ይኖራሉ። በጣም ደሃ የነበሩ ሲሆን ዋነኛ ምግባቸው የበቆሎ ቂጣ፣ ቦሎቄ፣ ፓስታ፣ ሩዝና ቃሪያን ያካተተ ነበር። በመግቢያው ላይ ከተጠቀሰው ከአንሄሊካ ቤተሰብ በተቃራኒ ምግባቸው ትንንሽ ዱባዎችን፣ ቻዮታ የተባሉ ተክሎችን፣ እንጉዳይን እንዲሁም እንደ ፐርስሌንና ፒግዊድ ያሉ ቅጠላ ቅጠሎችን ያካተተ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹን በገጠራማ አካባቢዎች ማግኘት ይቻላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ወቅታቸውን ጠብቀው የሚደርሱትንና በብዛት ገበያ ላይ የሚውሉትን ፍራፍሬዎች ለመመገብ ይጥራሉ። ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ለመከተል ያደረጉት ጥረት የተሻለ ጤንነት አስገኝቶላቸዋል።
ሜክሲኮ በሚገኘው የሳልቫዶር ሱቢራን ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲካል ሳይንስስ ኤንድ ኒውትሪሽን (INCMNSZ) ሥር የአፕላይድ ኒውትሪሽን ኤንድ ኒውትሪሽናል ኤጁኬሽን ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አዶልፎ ቻቬዝ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን መጠቀም ያለብን በዋነኛነት ሳይሆን የምግቡን ይዘት ለማሻሻል እንደሆነ ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥቂት እንቁላሎችን ከድንች፣ ከአትክልት ወይም ከቦሎቄ ጋር በመቀላቀል ምግብ ማዘጋጀት ትችል ይሆናል። ዶክተር ቻቬዝ “በአመጋገብ ጥናት [መስክ] ‘የምግብን ይዘት ማሻሻል’ የሚባለው ይኸው ነው” በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በተለይ ጥሬያቸውን የሚበሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ምንጊዜም በደንብ ማጠብ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
አንድ ምግብ ለእያንዳንዱ ሰው ተስማሚ መሆንም ይኖርበታል። በዚህ ረገድ እድሜ፣ ፆታና የአኗኗር ዘይቤ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ አዋቂዎች በእያንዳንዱ የመመገቢያ ሰዓት የፍራፍሬ እና/ወይም የአትክልት እንዲሁም ያልተፈተጉ እህሎችና የጥራጥሬ ፍጆታቸውን መጨመር ይኖርባቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የእንስሳ ተዋጽኦዎችን በእጅጉ መቀነስ እንደሚያስፈልግና ከእነዚህ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ዓሣ፣ ቆዳው የተገፈፈ ዶሮና ቀይ ሥጋን መመገብ ይበልጥ እንደሚመረጥ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። የስብና የስኳር ፍጆታን መቀነስ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።
በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩና በድህነት የተጠቁ ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አመጋገባቸውን ማሻሻል ይችላሉ። እንዴት? ገንቢ የሆኑ ምግቦች በመምረጥና ዓይነታቸውን በመለዋወጥ እንዲሁም እርስ በእርስ በመቀላቀል ነው። ለምሳሌ የአገዳ እህሎችን ከአበባ አህሎች ጋር ማቀላቀል ይቻላል። የምግቡን ይዘት ለማሻሻል ጥቂት ሥጋ ወይም እንቁላል መጨመርም ይቻላል። በአካባቢያችሁ የሚያድጉትን አትክልቶችና ወቅታቸውን ጠብቀው የሚደርሱትን ፍራፍሬዎች ተጠቀሙ።
ፈጣሪያችን ለሰው ዘር ደስታ ሲል ‘ከምድር ምግብን ያወጣል።’ (መዝሙር 104:14 አ.መ.ት ) መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 9:7 [አ.መ.ት ] ላይ “ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ” በማለት ይናገራል። ፈጣሪያችን የሰጠንን ጣፋጭና ገንቢ ምግብ ሚዛናዊና ልከኛ ሆነን መመገባችን እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው ክፍል:- በቆሎና ስንዴ የመሳሰሉ እህሎች እንዲሁም ከመሬት ሥር የሚበቅሉ ተክሎች
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁለተኛው ክፍል:- የአበባ እህሎች፣ ሥጋ፣ ዓሣ፣ እንቁላል፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሦስተኛው ክፍል:- አትክልትና ፍራፍሬ