በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጆሮህን ጤንነት ጠብቅ!

የጆሮህን ጤንነት ጠብቅ!

የጆሮህን ጤንነት ጠብቅ!

“በዓለም ውስጥ ከ120 ሚልዮን የሚበልጡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይኖራሉ።”​—⁠የዓለም የጤና ድርጅት

የመስማት ችሎታ እንደ ትልቅ ሀብት ሊቆጠር የሚገባው ውድ ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ የመስማት ችሎታችንም እየተዳከመ ይሄዳል። በተለያዩ ጫጫታዎችና ውካታዎች የተሞላው ዘመናዊው ኅብረተሰብ ደግሞ ይህን ሂደት ያፋጠነው ይመስላል። በዩናይትድ ስቴትስ ሴይንት ሉዊ፣ ሚዙሪ በሚገኘው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማዕከላዊ ተቋም የሚሠሩ አንድ ከፍተኛ ሳይንቲስት “የመስማት ችግር ከሚገጥማቸው አሜሪካውያን መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ለዚህ ችግር የሚጋለጡት በእርጅና ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው ሲሰሙት በኖሩት ድምፅ ጭምር ነው” ብለዋል።

ድንገተኛ ለሆነ ከፍተኛ ድምፅ መጋለጥ በውስጠኛው የጆሮ ክፍል ውስጥ በሚገኙ ብዙ አቅም የሌላቸው ሕዋሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው የመስማት ችሎታውን የሚያጣው “ጫጫታ የሚበዛባቸው ሥራዎች፣ ከፍተኛ ድምፅ የሚሰማባቸው መዝናኛዎችና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች የሚያስከትሉት ጉዳት አንድ ላይ ሲደማመር ነው” ይላሉ የጆሮ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ማርጋሬት ቺስማን። ታዲያ የጆሮህን ጤንነት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላለህ? መልሱን ለማግኘት ጆሮህ ድምፅ የሚለየው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ጠቃሚ ይሆናል።

የምንሰማቸው ድምፆች

በምንኖርበት አካባቢ የምንሰማቸው ኃይለኛ ድምፆች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል። ብዙ ሰዎች ዕለት በዕለት በጎዳና ላይ ከሚርመሰመሱት መኪናዎች፣ አውቶቡሶችና ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በሥራ ቦታዎች ከሚገኙ መሣሪያዎች በሚወጡ ከፍተኛ ድምፆች ሲበጠበጡ ይውላሉ።

ይህ ብቻውን እንዳይበቃ ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከፍ አድርጎ በመክፈት ችግሩን የምናባብስበት ጊዜ አለ። የጆሮ ማዳመጫዎች በመጠቀም በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ሊንቀሳቀሱ በሚችሉ የሲዲና የካሴት ማጫወቻዎች ሙዚቃ ማዳመጥ የተለመደ ነገር ሆኗል። የካናዳ ሙዚቀኞች ክሊኒክ ተባባሪ መስራች የሆኑት ማርሻል ቼሰን እንደሚሉት ድምፃቸው ከፍ ብሎ በተከፈተ የጆሮ ማዳመጫዎች ምክንያት የመስማት ችሎታቸውን እያጡ ያሉ ወጣቶች ቁጥር በጣም እየጨመረ እንደሄደ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ የሚባለው ድምፅ የትኛው ነው? ድምፅ በሦስት መንገዶች ማለትም በጊዜ፣ በድግግሞሽና በኃይል መጠን ይመደባል። ጊዜ የሚያመለክተው ድምፁ የሚሰማበትን የጊዜ ርዝመት ነው። የአንድ ድምፅ ድግግሞሽ መጠን ወይም ቃና በሰከንድ ይህን ያህል ድግግሞሽ ወይም ይህን ያህል ኸርዝ ነው ተብሎ ይገለጻል። ልንሰማው የምንችለው ልከኛ ድምፅ በሰከንድ ከ20 እስከ 20, 000 ድግግሞሽ ይኖረዋል።

የአንድ ድምፅ ኃይል ወይም ጥንካሬ የሚለካው ደግሞ ዴሲቤል በሚባል አሐድ ነው። ተራ የሆነ ጭውውት 60 ዴሲቤል የሚያክል ጥንካሬ ይኖረዋል። ከ85 ዴሲቤል ለሚበልጥ የድምፅ መጠን ለረዥም ጊዜ የተጋለጠ ሰው ውሎ አድሮ የመስማት ችሎታውን የማጣት አጋጣሚው ከፍተኛ እንደሚሆን የጆሮ ሐኪሞች ይናገራሉ። ድምፁ በጣም ጮክ ባለ መጠን በጆሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ ይሆናል። በኒውስዊክ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት “ጆሮ አንድ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የመሰርሰሪያ መሣሪያ የሚያሰማውን ድምፅ (100 ዴሲቤል) ለሁለት ሰዓት ያህል መቋቋም ይችላል። በቪዲዮ ማጫወቻ ቦታዎች የሚሰማውን ውካታ ግን (110 ዴሲቤል) ከ30 ደቂቃ በላይ መቋቋም አይችልም። የድምፅ መጠን በ10 ዴሲቤል ሲጨምር ጆሮን የመጉዳት ኃይሉ በ10 እጥፍ ይጨምራል” ይላል። አንድ ድምፅ 120 ዴሲቤል ገደማ ሲደርስ ጆሮ እንደሚያሳምም ሙከራዎች አረጋግጠዋል። አንዳንድ የቤት ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከ140 ዴሲቤል የሚበልጥ ድምፅ ማውጣት ይችላሉ።​—⁠ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

በጣም ጮክ ያለ ድምፅ በጆሮ ላይ ጉዳት የሚያደርሰው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የድምፅ ሞገድ ጆሮ ላይ ሲደርስ ምን እንደሚሆን እንመልከት።

ድምፅ የምንሰማው እንዴት ነው?

ከውጭ ተንጠልጥሎ የሚገኘው የጆሮ ክፍል የሚያገለግለው የድምፅ ሞገዶችን ሰብስቦ ወደ ውስጠኛው የጆሮ ክፍል ለማስገባት ነው። ከዚያ በኋላ የድምፁ ሞገድ ወደ ጆሮ ታምቡር ይደርሳል። የድምፁ ሞገድ የጆሮው ታምቡር እንዲርገበገብ ያደርግና የጆሮ ታምቡሩ በተራው በመካከለኛው ጆሮ የሚገኙት ሦስት አጥንቶች እንዲርገበገቡ ያደርጋል። ቀጥሎ እርግብግቢቱ ፈሳሽ የተሞላ ከረጢት ሆኖ በአጥንት ወደተከበበው ውስጠኛ ጆሮ ይገባል። ከዚያም የድምፁ እርግብግቢት የቀንድ አውጣ ቅርጽ ባለው ኮክሊያ የተባለ የውስጠኛ ጆሮ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ፈሳሽ በኩል ያልፋል። በኮክሊያ ውስጥ ፀጉር መሰል ሕዋሳት ይገኛሉ። በኮክሊያ ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ የፀጉር መሰሎቹን ሕዋሳት ላይኛ ክፍል በማንቀሳቀስ የነርቭ መልእክት እንዲተላለፍ ያደርጋል። እነዚህ መልእክቶች ወደ አንጎል ይተላለፉና ድምፅ ሆነው ይሰማሉ።

ሊምቢክ ሲስተም ተብሎ የሚጠራው የአንጎል ክፍል አንጎል ለየትኛው ድምፅ ትኩረት መስጠትና የትኛውን ደግሞ ችላ ብሎ ማለፍ እንደሚኖርበት እንዲለይ ያስችለዋል። ለምሳሌ፣ አንዲት እናት ሕጻን ልጅዋ ሲጫወት የሚያሰማውን ድምፅ ነገሬ ብላ አታዳምጥም። ደንግጦ በሚጮህበት ጊዜ ግን ወዲያው ብድግ ትላለች። በሁለት ጆሮአችን የምናዳምጥ መሆናችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ድምፆችን ለመስማት ያስችለናል። ይህ ደግሞ ጠቃሚ ነው። ድምፁ ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ ለመለየት ያስችለናል። ይሁን እንጂ ንግግር የታከለበት ድምፅ ከሆነ አንጎል ሊረዳ የሚችለው በአንድ ጊዜ አንድ መልእክት ብቻ ነው። ዘ ሴንስስ የተባለው መጽሐፍ “ሰዎች ስልክ እያነጋገሩ ሳለ አጠገባቸው ሆኖ የሚያናግራቸው ሰው ምን እንዳለ መረዳት የሚያቅታቸው በዚህ ምክንያት ነው” ይላል።

ኃይለኛ ድምፅ ጆሮአችንን የሚጎዳው እንዴት ነው?

በጣም ጮክ ያለ ድምፅ እንዴት በጆሮ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ለመረዳት የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት። አንድ በሥራ ደህንነት ላይ የተደረገ ጥናት ሪፖርት በውስጠኛው የጆሮ ክፍል የሚገኙትን ፀጉር መሰል ገለፈቶች በማሳ ላይ ባለ ስንዴ፣ ወደ ጆሮ የሚገባውን ድምፅ ደግሞ በነፋስ መስሏል። ልከኛ መጠን ያለው ድምፅ ለስለስ እንዳለ ነፋስ ሲሆን ይህ ዓይነቱ ነፋስ ስንዴውን ማወዛወዝ ይቻል እንጂ በስንዴው ላይ ጉዳት አያደርስም። የነፋሱ ኃይል ከጨመረ ግን በስንዴው አገዳ ላይ የሚያሳርፈው ግፊት ከፍተኛ ይሆናል። በስንዴው ማሳ ላይ የሚነፍሰው ነፋስ ድንገተኛና ኃይለኛ ከሆነ ወይም ነፋሱ መጠነኛ ቢሆንም አገዳው በጣም ረጅም ለሆነ ጊዜ ለነፋስ ከተጋለጠ መልሶ ሊያገግም በማይችል መጠን ጉዳት ይደርስበትና ይደርቃል።

ኃይለኛ ድምፅ በውስጠኛው የጆሮ ክፍል ላይ በሚገኙት በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ፀጉር መሰል ሕዋሳት ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተመሳሳይ ነው። በድንገት የሚባርቅ ከፍተኛ ድምፅ የውስጠኛውን ጆሮ ህብረሕዋሳት ሊቀድና ሊሽር የማይችል ጠባሳ ሊያስቀር ስለሚችል ሊድን የማይችል የጆሮ እክል ያደርሳል። በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ የሚቆይ አደገኛ የሆነ መጠን ያለው ድምፅ ረቂቅ በሆኑት ፀጉር መሰል ሕዋሳት ላይ ሊድን የማይችል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እነዚህ ሕዋሳት አንድ ጊዜ ከተጎዱ እንደገና ሊያድጉ አይችሉም። በዚህ ምክንያት የጆሮ መጮህ ችግር ሊያጋጥም ይችላል።

ጆሮህን በመጠበቅ የመስማት ችሎታህን ዕድሜ አራዝም

በዘር ውርሻ ወይም ባልታሰበ አደጋ ምክንያት የመስማት ችሎታችንን ልናጣ ብንችልም በጣም ውድ የሆነውን የመስማት ችሎታችንን ለመጠበቅና ዕድሜውን ለማራዘም ልናደርግ የምንችላቸው ጥንቃቄዎች አሉ። በጆሮ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን በቅድሚያ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው። አንድ የጆሮ ሐኪም እንዳሉት “ችግር እስኪያጋጥም ዝም ብሎ ቆይቶ በኋላ አንድ ነገር ለማድረግ መሞከር ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ይሆናል።”

አብዛኛውን ጊዜ ለውጥ የሚያመጣው የምናዳምጠው ነገር ሳይሆን የምናዳምጥበት ሁኔታ ነው። ለምሳሌ፣ ሙዚቃ የምታዳምጠው ራስ ላይ በሚጠለቅ ማዳመጫ ከሆነ የድምፁን መጠን በዙሪያህ ያለውን ድምፅ ለመስማት በሚያስችልህ መጠን ዝቅ ልታደርገው ብትችል ጥሩ ነው። በመኪናህ ውስጥ ወይም እቤትህ ያለው የሙዚቃ መሣሪያ የተከፈተበት መጠን ተራ የሆነ ጭውውት ለመደማመጥ የማያስችል ከሆነ ጆሮህ ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መጠን ላይ ደርሷል ማለት ነው። ከ90 ዴሲቤል የሚበልጥ መጠን ላለው ድምፅ ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዓት መጋለጥ በጆሮ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ሊቃውንቱ ይናገራሉ። ጫጫታ በበዛበት አካባቢ ስትሆን ጆሮን መወተፍ ወይም አንድ ዓይነት መከላከያ ማድረግ ይበጃል።

ልጆች ከአዋቂዎች ይበልጥ በከፍተኛ ድምፅ የመጎዳት ዕድል እንዳላቸው ወላጆች ቢገነዘቡ ጥሩ ይሆናል። ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጡ መጫወቻዎች አደገኛ መሆናቸውን አትዘንጉ። የአንዳንድ መጫወቻዎች ድምፅ እስከ 110 ዴሲቤል ሊደርስ ይችላል።

ጆሮቻችን አነስተኛና በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ቢሆኑም በጣም አስደናቂ የሆኑ መሣሪያዎች ናቸው። በእነዚህ መሣሪያዎች በዙሪያችን ያለው ዓለም የሚያሰማቸውን የተለያዩና የተዋቡ ድምፆች እንሰማለን። በእርግጥ ለዚህ ውድ ስጦታ ተገቢ የሆነ ጥበቃ ልናደርግለት ይገባል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአንዳንድ የተለመዱ ድምፆች ግምታዊ የዴሲቤል መጠን

• መተንፈስ​—⁠10 ዴሲቤል

• ማንሾካሾክ​—⁠20 ዴሲቤል

• ጭውውት​—⁠60 ዴሲቤል

• የሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት የመኪናዎች እንቅስቃሴ​—⁠80 ዴሲቤል

• በኤሌክትሪክ የሚሠራ ምግብ መፍጫ—⁠90 ዴሲቤል

• የሚያልፍ ባቡር​—⁠100 ዴሲቤል

• በኤሌክትሪክ የሚሠራ መጋዝ​—⁠110 ዴሲቤል

• አውሮፕላን ሲያልፍ​—⁠120 ዴሲቤል

• የጠመንጃ ተኩስ​—⁠140 ዴሲቤል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሚከተሉትን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ ጆሮህ እየደከመ ሊሆን ይችላል

• ሌሎች በጣም ጮኸብን እያሉም የራዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ድምፅ ከፍ የምታደርግ ከሆነ

• ብዙ ጊዜ ሌሎች የተናገሩትን እንዲደግሙልህ የምትጠይቅ ከሆነ

• የሚያናግርህ ሰው የሚለውን ለመስማት ጆሮህን ወደርሱ ዘንበል ወይም ፊትህን ኮስተር የምታደርግ ከሆነ

• ጫጫታ ባለበት ግብዣ ላይ ወይም ሰው በሚበዛበት የገበያ ቦታ ከሌሎች ጋር መደማመጥ የሚቸግርህ ከሆነ

• ብዙ ጊዜ ምንድን ነው የተባለው እያልክ ሌሎችን የምትጠይቅ ከሆነ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ውጨኛው ጆሮ

በመካከለኛው ጆሮ የሚገኙ ሦስት አጥንቶች

የጆሮ ታምቡር

ኮክሊያ

ወደ አንጎል መልእክት የሚያስተላልፉ ነርቮች