በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመሆኑ ሣር ምንድን ነው?

ለመሆኑ ሣር ምንድን ነው?

ለመሆኑ ሣር ምንድን ነው?

ለአንዳንዶች ከቤት ውጭ እያደገ በየጊዜው እጨዱኝ እያለ የሚያስቸግር ተክል ነው። ለገበሬዎችና ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ደግሞ የሥራ ገበታቸው ነው። ለሕፃናት ምቹ የመጫወቻ ቦታ ነው። ይሁን እንጂ ሣር የሚለው ቃል የሚያመለክተው በግቢ ውስጥ፣ በከብቶች ማርቢያ ወይም በጨዋታ ሜዳ የተነጠፈውን አረንጓዴ ተክል ብቻ ነውን?

በትላልቅ ፎቆች በተጨናነቀ ትልቅ ከተማ ውስጥ የምትኖር ከሆነ ከሣር ጋር የሚያገናኘኝ ምንም ነገር አይኖርም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁላችንም ለማለት ይቻላል፣ ከአንድ ዓይነት የሣር ዘር ወይም የሣር ዘር ውጤት ጋር ሳንገናኝ የምንውልበት ቀን አይኖርም። ሣር በመሠረቱ ምንድን ነው? እንዴትስ እንጠቀምበታለን?

የሣር ዝርያዎች

ይህን እንደ አልባሌ ነገር የሚቆጠር የተክል ዝርያ እስቲ ጠለቅ ብለን እንመርምር። በሳይንሳዊ ስያሜያቸው ከሣር ከሚመደቡት እጽዋት በተጨማሪ የደንገልና የቄጠማ ዝርያዎችንም ከሣር ክፍል የሚመድቡ አሉ። እውነተኛ ሣር የሚባሉት ግን የሣር ዝርያ የሆኑ እጽዋት ብቻ ናቸው። በዚህ ዝርያ የሚመደቡት እጽዋት አብዛኛውን ጊዜ ተለይተው የሚታወቁባቸው የጋራ ባሕርያት አሏቸው። የሣር ዝርያ ነው ብለህ ወደምታስበው ተክል ቀረብ ብለህ ግንዱን ተመልከት።

ግንዱ ክብና ውስጡ ቀፎ ነው? አንጓዎችስ አሉት? ቅጠሎቹ ረዥም፣ ጠፍጣፋና ጠባብ ሆነው የማይገናኙ መስመሮች ያሏቸው እንዲሁም ግንዱ ላይ ከተጠመጠመ ብራና መሳይ ሽፋን የወጡ ናቸው? በተጨማሪም ቅጠሎቹ ጥንድ ጥንድ ሆነው ከግንዱ ግራና ቀኝ የሚወጡ ናቸው? ሥሮቹ ወደ መሬት ጠልቀው የሚገቡ ነጠላ ሥሮች ከመሆን ይልቅ እንደ ቀጫጭን ክር እየተጠላለፉ የተሠራጩና ጥቃቅን ናቸው? አበባዎቹ በጣም ትናንሽ ሆነው ሊታዩ የሚችሉ ከሆኑ እንደ እሾህ ሾል ያሉ ወይም ዘርዝረው የወጡ ናቸው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስህ አዎን የሚል ከሆነ ተክሉ ከሣር ዝርያዎች የሚመደብ ሊሆን ይችላል።

ከሣር ዝርያ የሚመደቡ ተክሎች ተመሳሳይ የሆነ መልክ ይኑራቸው እንጂ ከ8, 000 እስከ 10, 000 የሚደርሱ የተለያዩ ዝርያዎች አሏቸው። እነዚህ ዝርያዎች 2 ሴንቲ ሜትር ቁመት ካላቸው ተክሎች አንስቶ እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ርዝማኔ ያላቸውን ቀርከሃዎች ያካተቱ ናቸው። ምድርን ከሸፈኑት እጽዋት መካከል ዋነኛውን ክፍል የያዙት ሣሮች ናቸው። ይህም የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም በምድር ላይ ከሚገኙት እጽዋት መካከል የሣርን ያህል ከአካባቢ ሁኔታዎች ጋር የመላመድ ችሎታ ያላቸው እጽዋት በጣም ጥቂት ናቸው። በበረዷማ አካባቢዎች፣ በበረሐዎች፣ በትላልቅ ሸለቆዎችና ተራራዎች፣ ዝናብ በሚበዛባቸውና ነፋሻ በሆኑ አካባቢዎች ለማደግ ችለዋል። የሣር ተክሎች በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓና በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካ ሰሜናዊ ክፍል፣ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ እንዲሁም በሐሩር ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አገሮች ሰፊ መሬት ሸፍነው ይገኛሉ።

የተለያዩ የሣር ዘሮች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ጋር ለመላመድ የቻሉት በጣም ጠንካራ በመሆናቸው ነው። ሣር የሚያድገው እንደ ብዙዎቹ እጽዋት ከጫፉ ሳይሆን ከየአንጓዎቹ ነው። መሬት ለመሬት አግድም ከሚያድግ ግንድ አዳዲስ ቅጠሎች ሊያቆጠቁጡ ይችላሉ። ስለዚህ የሣሩ ጫፍ በሚታጨድበት ወይም በከብት በሚበላበት ጊዜም ሣሩ ማደጉን ይቀጥላል። ብዙ ተክሎች ግን ማደጋቸውን ያቆማሉ። ቶሎ ቶሎ ማጨድ ሌሎች እጽዋትን በማስወገድ ሣር እንዲበዛና እጅብ ብሎ እንዲያድግ የሚረዳው በዚህ ምክንያት ነው።

ከዚህም በላይ አብዛኞቹ የሣር ዓይነቶች በነፋስ ወይም በመረገጥ ምክንያት በሚጎብጡበት ጊዜ ባጎነበሱበት ጎን በኩል ፈጣን እድገት በማድረግ እንደገና ራሳቸውን ቀና የማድረግ ችሎታ አላቸው። በዚህ ምክንያት ሣር ከደረሰበት ጉዳት ፈጥኖ የማገገም ችሎታ አለው። ከሌሎች ተክሎች ጋር የፀሐይ ብርሃን ለማግኘት በሚደረገው ሽሚያ አሸናፊ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። ሣር ይህን ያህል ጠንካራ ተክል በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል። ሕልውናችን በሣር ዝርያዎች ላይ የተመካ ነውና።

ሁለገብ የሆነ ተክል

ሣር በምድር ላይ ከሚገኙት እጽዋት በሙሉ በብዛት የሚገኝ ከመሆኑ ሌላ ባለ አበባ ከሆኑ የእጽዋት ዝርያዎች መካከል የሚመደብ በጣም አስፈላጊ የሆነ ተክል ነው። አንድ የእጽዋት ተመራማሪ የሣር ዝርያዎች የምግባችን ዋና መሠረት እንደሆኑ ተናግረዋል። ‘የሣር ዝርያዎች የሰውን ልጅ ከረሐብ የሚታደጉ እጽዋት ናቸው።’ እስቲ ዛሬ ቁርስህን የበላኸው ምን እንደሆነ አስታውስ። ቅንጬ፣ በሶ ወይም ገንፎ በልተህ ይሆን? እነዚህ ሁሉ የሣር ዝርያዎች ከሆኑ የእህል ዓይነቶች የተገኙ ናቸው። አለበለዚያም ቂጣ ወይም ቁራሽ ዳቦ በልተህ ይሆናል። ቂጣው ወይም ዳቦው የተጋገረበት ዱቄት የተገኘው የሣር ዝርያ ከሆነ እህል ነው። ገብስ፣ ስንዴና ሌሎች እህሎች የሣር ዝርያዎች ናቸው። የበላኸው ከበቆሎ የተዘጋጀ ምግብ ቢሆን እንኳን ከሣር ዝርያዎች የወጣ አይደለም። በቆሎም የሣር ዝርያ ነው። በምትጠጣው ሻይ ወይም ቡና ውስጥ ስኳር ጨምረህ ይሆናል። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ስኳር የሚሠራው ከሸንኮራ አገዳ ሲሆን ሸንኮራ አገዳ ደግሞ የሣር ዝርያ ነው። ወተትና አይብ እንኳን የሣር ውጤቶች ናቸው ሊባሉ ይችላሉ። ምክንያቱም ላሞች፣ በጎችና ፍየሎች የሚመገቡት ሣር ነው።

ምሳህስ? ፓስታ ወይም እንጀራ የሚሠራው የሣር ዝርያዎች ከሆኑ እህሎች ነው። ዶሮዎች የሚመገቡት የሣር ዝርያዎች የሆኑ እህሎችን ነው። ከብቶች የተለያየ ዓይነት ሣሮችን ስለሚመገቡ የምንመገበው እንቁላል፣ ዶሮ ወይም የከብት ሥጋ በአብዛኛው የተገኘው እንስሳት ተመግበው ከአካላቸው ጋር ካዋሃዱት ሣር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከሣር ዝርያዎች የሚዘጋጁ መጠጦች አሉ። ከወተት ሌላ ብዙዎቹ እንደ ቢራ፣ ጠላ፣ አረቄና፣ ውስኪ የመሰሉት የአልኮል መጠጦች የሚሠሩት የሣር ዝርያዎች ከሆኑ እህሎች ነው።

እኔ የምወደው ምግብ አልተጠቀሰም ብለህ ቅር አይበልህ። ከሣር ዝርያዎች የሚሠሩትን ምግቦች በሙሉ ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል ነው። በመላው ዓለም ሰዎች ከሚወስዱት የካሎሪ መጠን ከግማሽ የሚበልጠው ከሣር ዝርያዎች እንደሚገኝ ይገመታል። ለእርሻ ከዋለው መሬት ከ70 በመቶ የሚበልጠው የተሸፈነው በሣር ዝርያዎች በመሆኑ ይህ የሚያስደንቅ አይደለም።

ይሁን እንጂ የሣር ዝርያዎች የሚያገለግሉት ለምግብነት ብቻ አይደለም። የቤትህ ግድግዳ ጭቃ የተመረገ ከሆነ ጭድ ባይጨመርበት ኖሮ ጠንክሮ ሊቆም አይችልም ነበር። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጣሪያዎች የሚከደኑት በሣር ነው። በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ቀርከሃ ለቤት ዕቃ መሥሪያ፣ ለቧንቧ፣ ለግድግዳና ለብዙ በርካታ አገልግሎቶች ይውላል። የሣር ዝርያዎች ከሆኑ እጽዋት ቅርጫቶችና ሰሌኖች እንዲሁም ማጣበቂያና ወረቀት የሚሠራበት ጊዜ አለ። የለበስከውንም ልብስ አትዘንጋ። ሱፍና ቆዳ የእንስሳት ውጤቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ እንስሳት ደግሞ የሚመገቡት ሣር ነው። እንደ ዋሽንት የመሰሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚሠሩት የሣር ዝርያ ከሆነ መቃ ነው። ለዋሽንት መሥሪያ ከመቃ የተሻለ ጥሬ ዕቃ ሊገኝ አልቻለም።

ሣር አብዛኛውን የምድር ክፍል ውበት ሰጥቶታል። የተንጣለለ አረንጓዴ መስክ ምን ያህል እንደሚያምር፣ እንደሚያዝናናና እፎይ እንደሚያሰኝ አስብ። ሣር በጣም ሰፊ የሆነ ቦታ በአረንጓዴ ቅጠሎች እንዲሸፈን የሚያደርግ ተክል በመሆኑ ዋነኛ የኦክስጅን ምንጭ ሆኗል። ቀጫጭን ሥሮቹ ደግሞ አፈር እንዳይሸረሸር ይጠብቃሉ። የሣር ዝርያዎች ምን ያህል ሁለገብ ግልጋሎት እንደሚሰጡ ካሰብን መመረትና ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ መሆናቸውን ማወቃችን ብዙም አያስደንቀን ይሆናል።

የሣር ዝርያዎች ታሪክ

ሣር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ስለ ፍጥረት በሚተርከው ክፍል ውስጥ ነው። አምላክ በሦስተኛው የፍጥረት ቀን “ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርን . . . ታብቅል” አለ። (ዘፍጥረት 1:​11) * ከፍተኛ ሥልጣኔ የነበራቸው ሕዝቦች በሙሉ የሣር ዝርያዎችን ለምግብነት ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ግብጻውያን፣ ግሪካውያንና ሮማውያን ዋነኛ ቀለባቸው ስንዴና ገብስ ነበር። ቻይናውያን ማሽላና ሩዝ፣ ኢንዱዎች ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ፣ ማያዎች፣ አዝቴኮችና ኢንካዎች ደግሞ በቆሎ ይመገቡ ነበር። የሞንጎል ፈረሰኞችም ለፈረሶቻቸው የሚያስፈልገውን ቀለብ ያገኙ የነበረው በጣም ሰፊ በሆኑ መስኮች ከበቀሉ ሣሮች ነበር። አዎን፣ የሣር ዝርያዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለሰው ልጅ ትልቅ ጠቀሜታ አበርክተዋል።

ከአሁን በኋላ ነፋስ የሚያወዛውዘው ሰፊ የበቆሎ ማሳ ወይም በሣር የተሸፈነ የተንጣለለ መስክ ወይም ደግሞ በመንገድ ዳር በሁለት ድንጋዮች መካከል ራሱን ብቅ አድርጎ የወጣ ሣር ስትመለከት በጣም አስደናቂና ሁለገብ ስለሆነው ስለዚህ የተክል ዝርያ ቆም ብለህ ማሰብህ አይቀርም። በተጨማሪም እንደ መዝሙራዊው ይህን ግሩም ተክል የፈጠረውን ይሖዋ አምላክን እንደሚከተለው በማለት ለማመስገን ትገፋፋ ይሆናል:- “አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ . . . እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፣ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል። . . . ሃሌ ሉያ።”​​—⁠⁠መዝሙር 104:​1, 14, 31-35

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 ይህን ጥቅስ ያሰፈረው ጥንታዊው ጸሐፊ ሣር መሰል የሆኑ እጽዋትን በዛሬው ጊዜ የሣር ዝርያዎች ተደርገው ከሚቆጠሩት ተክሎች ለይቶ አልጠቀሰ ይሆናል።

[በገጽ 15 እና 16 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሣር ተክል ክፍሎች

ዋና ዋና የሣር አበባ ዓይነቶች

እሾህ መሰል

እጅብ ያለ

ዘርዛራ

ቃጫ መሰል ሥሮች

ሽፋን

ቅጠል

ግንድ

አንጓ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዛሬ የበላኸው ከሣር ዝርያዎች የሚመደብ ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጠጣኸውስ?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነርሱም የሚመገቡት ሣር ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መኖሪያህም ከሣር የተሠራ ሊሆን ይችላል