በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በማዳመጥ እውቀት አግኝ

በማዳመጥ እውቀት አግኝ

በማዳመጥ እውቀት አግኝ

ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ “ከምናውቃቸው ነገሮች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑትን የተማርነው በማዳመጥ ነው” በማለት ገልጿል። አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋው በማዳመጥ ቢሆንም ትኩረታችን ይሰረቃል፣ ስለ ሌሎች ነገሮች እናስባለን ወይም ከሰማነው ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነውን እንረሳዋለን። እነዚህ ትኩረት የሚስቡ አኃዛዊ መረጃዎች የማዳመጥ ችሎታችንን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎሉ ናቸው።

በዘገባው መሠረት “በኅብረተሰብ ውስጥ ለሚታዩት ብዙ ችግሮች መንስኤው ደካማ የሆነ የማዳመጥ ልማድ ነው።” ስለ ሰው የንግግር ችሎታ የሚያጠኑትና የሐሳብ ልውውጥ ባለሙያ የሆኑት ሪቤካ ሻፈር ደካማ የሆነ የማዳመጥ ልማድ በአብዛኛው ራስን መግደልን፣ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅን፣ የቤተሰብ መፈራረስንና አደገኛ ዕፅ መውሰድን ለመሳሰሉት ችግሮች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያምናሉ።

ስለ ማኅበራዊ ሕይወት የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች ሰዎች የተለያየ ዓይነት የማዳመጥ ዘይቤ እንዳላቸው አስተውለዋል። አንዳንዶች ከባለ ታሪኩ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መስማት የሚያስደስታቸው ሲሆን በሚነገረው ነገር ዙሪያ ያሉትን ዝርዝር ሁኔታዎች በሙሉ ማወቅ ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ መስማት የሚፈልጉት ስለተከናወነው ነገር ብቻ ስለሆነ ተናጋሪው በቀጥታ ወደ ነጥቡ እንዲሄድ ይሻሉ። መጽሔቱ “እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እርስ በርስ ሲነጋገሩ በቀላሉ መግባባት ይቸግራቸዋል” ብሏል።

ኢየሱስ “እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” በማለት የጉዳዩን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ያለ ምክንያት አልነበረም። (ሉቃስ 8:18፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ጥሩ አድማጭ መሆን መልካም ምግባር ነው። ውጤታማ የሆነ ውይይት ለማድረግም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በውይይት ወቅት እንዴት ማዳመጥ እንደሚቻል ከቀረቡት ተግባራዊ ሐሳቦች መካከል ትኩረትን ከሚሰርቁ ነገሮች መቆጠብ፣ በመጠኑ ወደፊት ዘመም ብሎ ማዳመጥ እንዲሁም የሚናገረውን ሰው ትኩር ብሎ በመመልከትና ጭንቅላትን በመነቅነቅ ምላሽ መስጠት ይገኙበታል። እውቀት መቅሰማችን በአብዛኛው የተመካው ውጤታማ በሆነ መንገድ በማዳመጣችን ላይ ስለሆነ ትኩረት ሰጥቶ የማዳመጥ ልማድ ሁላችንም እያሻሻልነው ልንሄድ የሚገባ ነገር ነው።