በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በባርነት ላይ የተካሄደ ረዥም ተጋድሎ

በባርነት ላይ የተካሄደ ረዥም ተጋድሎ

በባርነት ላይ የተካሄደ ረዥም ተጋድሎ

“ባሪያ መሆን ማለት መዋረድና ውርደትን ተቀብሎ መኖር፣ ግፍ መቀበልና ግፉን ችሎ መኖር ማለት ነው።”— በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረ ዩሪፒዲዝ የተባለ ግሪካዊ ጸሐፌ ተውኔት።

ባርነት ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ዘግናኝ ታሪክ አለው። እንደ ግብጽና ሜሶጶጣሚያ ካሉት ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ጀምሮ ኃያላን አገሮች ደካማ ጎረቤቶቻቸውን ባሪያ አድርገው ሲገዙ ኖረዋል። ከሰው ልጅ አሳዛኝ ታሪኮች አንዱ የሆነ የባርነት ታሪክ መመዝገብ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

በሁለተኛው ሺህ ዓመት ከዘአበ ግብፅ አንድ ሙሉ ብሔር፣ ምናልባትም በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በባርነት ትገዛ ነበር። (ዘጸአት 1:​13, 14፤ 12:​37) ግሪክ በሜዲትራንያን ባሕር አካባቢ የሚገኙትን አገሮች ትገዛ በነበረበት ጊዜ ብዙ ግሪካውያን ቤተሰቦች ቢያንስ አንድ ባሪያ ይኖራቸው ነበር። ባሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ቤተሰቦች መኪና እንደሚኖራቸው ማለት ነው። አርስቶትል የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ ይህ ድርጊት ትክክል እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሲል የሰው ልጅ በሁለት ክፍል ማለትም በጌታና በባሪያ የተከፈለ ሲሆን ጌቶቹ የማዘዝ ተፈጥሯዊ መብት ሲኖራቸው ባሮቹ ደግሞ የተወለዱት ለመታዘዝ ነው ሲል ተከራክሯል።

ሮማውያን ደግሞ ከግሪካውያን ይበልጥ ባርነትን አስፋፍተዋል። በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ከሮም ከተማ ነዋሪዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ማለትም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ባሮች ነበሩ። የሮማ መንግሥት በየዓመቱ ሐውልቶች የሚሠሩለት፣ ማዕድን የሚቆፍሩለት፣ እርሻ የሚያርሱለትና ትላልቅ በሆኑ የከበርቴዎች ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ግማሽ ሚልዮን የሚያክሉ ባሮች ማግኘት ያስፈልገው ነበር። * በጦርነት ላይ የሚማረኩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በባርነት እንዲያገለግሉ ይደረግ ነበር። የሮም የጦርነት ዘመቻ የማያባራ የሆነው ተጨማሪ ባሮች ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት በቀላሉ ሊረካ የማይችል በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም።

ከሮማ መንግሥት ውድቀት በኋላ የባሪያ አገዛዝ ሥርዓት እየተዳከመ ቢመጣም ባሪያ የማሳደር ልማድ ግን ቀጥሏል። በ1086 እዘአ በእንግሊዝ ንጉሥ ትእዛዝ የተደረገ ቆጠራ ውጤት የተመዘገበበት መጽሐፍ እንደሚለው በመካከለኛው ዘመን በእንግሊዝ ከነበሩት ጠቅላላ ሠራተኞች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ባሮች ነበሩ። የጦር ምርኮኞችን ባሪያ አድርጎ የመግዛት ልማድም እንደቀጠለ ነበር።

ይሁን እንጂ ከክርስቶስ ዘመን ወዲህ የአፍሪካን ያህል በባሪያ ፍንገላ የተጠቃ አህጉር የለም። ከኢየሱስ ዘመን በፊት እንኳን የጥንት ግብጾች ኢትዮጵያውያን ባሮችን ይገዙና ይሸጡ ነበር። ወደ 1, 250 ዓመት በሚጠጋ ዘመን ውስጥ 18 ሚልዮን የሚደርሱ አፍሪካውያን በባርነት እንዲያገለግሉ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ እንደተወሰዱ ይገመታል። ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ደግሞ የአሜሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ሥር መውደቅ በመጀመራቸው አዲስ የባሪያ ፍንገላ ገበያ ተከፈተ። በዚህ ምክንያት በአትላንቲክ ባሕር በኩል መካሄድ የጀመረው የባሪያ ፍንገላ በምድር ላይ እጅግ አትራፊ ከሆኑት ንግዶች አንዱ ሆነ። የታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት ከሆነ ከ1650 እስከ 1850 ባሉት ዓመታት 12 ሚልዮን የሚያክሉ ባሮች ከአፍሪካ እንደተወሰዱ ይገመታል። * ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የተሸጡት በባሪያ መሸጫ ገበያዎች ነው።

በባርነት ላይ የተካሄደ ተጋድሎ

ባለፉት መቶ ዘመናት ግለሰቦችም ሆኑ ብሔራት ራሳቸውን ከባርነት ነጻ ለማውጣት ተዋግተዋል። ከክርስቶስ በፊት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስፓርታከስ 70, 000 የሚያክሉ ሮማውያን ባሮችን በመምራት ነጻነት ለማግኘት ውጊያ ቢያካሂድም ሳይሳካለት ቀርቷል። ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ደግሞ የሃይቲ ባሮች አምፀው በ1804 ነጻ መንግሥት ለማቋቋም ችለዋል።

ከዚያ በኋላም ቢሆን ባርነት በዩናይትድ ስቴትስ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል። ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ነጻ ለማውጣት መራራ ትግል ያካሄዱ ባሮች ነበሩ። ባርነት እንዲወገድ በመሟገትና ከጌቶቻቸው የሸሹ ባሮችን በመርዳት ብርቱ ትግል ያካሄዱ ነጻ ሰዎችም ነበሩ። ሆኖም ባርነት በመላ አገሪቱ ላይ በሕግ የታገደው በ19ኛው መቶ ዓመት መጨረሻ ላይ ነበር። ዛሬስ ስላለው ሁኔታ ምን ለማለት ይቻላል?

ትግሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷልን?

ዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ “ማንም ሰው በባርነት ወይም በአገልጋይነት እንዲያድር አይገደድም። ባርነትና የባሪያ ንግድ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው” ይላል። ይህ በ1948 በጋለ ስሜት የተላለፈ ድንጋጌ በእርግጥም ክቡር ዓላማ ያለው ድንጋጌ ነበር። ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ንብረታቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ቅን አሳቢ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ይሁን እንጂ ዓላማቸው እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም።

ባለፈው ርዕስ እንደተመለከተው አሁንም ቢሆን አለምንም ክፍያ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሥር በከባድ ሥራ ሲለፉ የሚውሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ብዙዎቹም የተገዙትና የተሸጡት አለፈቃዳቸው ነው። ባርነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል የተካሄደ ከመሆኑም በላይ ባርነትን ሕገ ወጥ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ሕጎች ወጥተዋል። ይሁን እንጂ ለሁሉም የሰው ዘር እውነተኛ ነጻነት ማጎናጸፍ አልተቻለም። መላው ዓለም በኢኮኖሚ የተሳሰረ መሆኑ በስውር የሚካሄደውን የባሪያ ንግድ በጣም አትራፊ እንዲሆን አድርጎታል። እንዲያውም ባርነት በሰው ልጅ ኅብረተሰብ መካከል ይበልጥ ሥር እየሰደደ የመጣ ይመስላል። ታዲያ ሁኔታው ምንም ተስፋ የሌለው ነውን? እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አንድ የጥንት ጽሑፍ አንዳንድ ባለጠጋ ሮማውያን የነበሯቸው ባሮች ብዛት እስከ 20, 000 ሊደርስ እንደሚችል ያመለክታል።

^ አን.7 አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሰባኪዎች ይህን በሰው ሕይወት ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ንግድ አምላክ እንደሚደግፈው ይናገሩ ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ጭካኔ የሚደግፍ ይመስላቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፈውም። በጥቅምት 2001 ንቁ ! ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፦ አምላክ የባሪያ ንግድን አቅልሎ ይመለከተዋልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባሮች መጫኛ መርከቦች ተጭነው ከአፍሪካ የሚመጡ ሰዎች (ከላይ ) በአሜሪካ የባሪያ ገበያዎች ይሸጡ ነበር

[ምንጮች]

Godo-Foto

Archivo General de las Indias