በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባርነት የማይኖርበት ጊዜ!

ባርነት የማይኖርበት ጊዜ!

ባርነት የማይኖርበት ጊዜ!

ነጻነት! ለሰው ልጅ ከዚህ ይበልጥ የሚያስደስት ቃል የለም። ለነጻነት ሲሉ መከራ የተቀበሉና የተጋደሉ፣ መላ ሕይወታቸውን የሠዉና የሞቱ ሰዎች ብዙ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉለት ዓላማ ግቡን ሲመታ ለማየት አልታደሉም። ከባርነት ነጻ ለመሆን የሚቻልበት አስተማማኝ ተስፋ ይኖራል? አዎን፣ አለ።

ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ የገባውን ተስፋ አስመልክቶ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” (ሮሜ 8:​21) ይሁን እንጂ አምላክ እንዲህ ያለውን ‘ክብራማ ነፃነት’ እንደሚያመጣ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? አንደኛው መንገድ አምላክ ባለፉት የታሪክ ዘመናት ከሰው ልጆች ጋር ባደረገው ግንኙነት ያከናወናቸውን ነገሮች መመርመር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 3:​17) አዎን፣ የአምላክ መንፈስ እጅግ በጣም ኃይለኛ ነው። አምላክም በዚህ ኃይል አማካኝነት ለሰው ልጆች የተለያየ ዓይነት ነፃነት ሲያጎናጽፍ ቆይቷል። እንዴት? በመጀመሪያ ባርነት ዓይነቱ ብዙ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ቀደም ስንልም ብርቱው ደካማውን በጉልበት አስገድዶ ባሪያ የሚያደርግበትን አስከፊ የሆነ የባርነት ዓይነት ተመልክተናል። ሌሎቹን የባርነት ዓይነቶች ደግሞ እስቲ እንመልከት።

ሰዎች ለተለያዩ ሱሶች ራሳቸውን ባሪያ ሊያደርጉና ከያዛቸው ሱስ ለመላቀቅ በጣም ሊቸገሩ ይችላሉ። በተጨማሪም በሐሰት ትምህርቶች ተታልለው በመገዛት ለውሸትና ለማታለያ ባሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እያንዳንዳችንን፣ አወቅንም አላወቅን፣ ባሪያ አድርጎ የሚገዛን በጣም መሠሪ የሆነ ሌላ የባርነት ዓይነትም አለ። የሚያስከትለውም መዘዝ ሕይወት ሊያሳጣ የሚችል ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ማብራሪያ ላይ የተለያዩትን የባርነት ዓይነቶች በአንድ ምድብ ብንፈርጅም ሁሉም የባርነት ዓይነቶች በአስከፊነታቸው እኩል ናቸው ማለታችን አይደለም። በመካከላቸው በጣም ሰፊ ልዩነት አለ። የሆነ ሆኖ ሁሉም የባርነት ዓይነቶች የጋራ ባሕርይ አላቸው። ይዋል ይደር እንጂ የነጻነት አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ባርነት ከሰው ልጅ ጫንቃ ላይ ማውረዱ አይቀርም።

ሱስ ባሪያ አድርጎ በሚገዛበት ጊዜ

ዌን ላክ ራንስ አውት የተባለው መጽሐፍ የቁማር ሱሰኛ ስለመሆን የተናገረውን ልብ እንበል:- “አንድ ግለሰብ ሊቆጣጠር በማይችለው ግፊትና ፍላጎት ቁማር ለመጫወት የሚገደድበት የባሕርይ ችግር ነው። ይህ ግፊት እየጨመረና እየጎለበተ ሄዶ . . . በሰውዬው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ወደማበላሸት ደረጃ ይደርሳል።” ለቁማር ባሪያ የሆኑ ሰዎች ምን ያህል እንደሚሆኑ አስረግጦ የሚያውቅ ሰው የለም። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ስድስት ሚልዮን የቁማር ተገዥዎች እንዳሉ ተገምቷል።

የአልኮል ሱስም ከቁማር ያልተናነሰ፣ እንዲያውም የሚብስ ጉዳት የሚያደርስና በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝ ሱስ ነው። በአንድ ሰፊ አገር ለአቅመ አዳም ከደረሱ ወንዶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት መጠኑ ይለያይ እንጂ በአልኮል ሱሰኝነት ችግር የተለከፉ ናቸው። ከ20 ዓመታት በፊት የአልኮል ሱሰኛ የሆነው ሪካርዶ ይህን ሱስ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከእንቅልፍ ከነቃችሁበት ጊዜ ጀምሮ ሰውነታችሁን ዘና ለማድረግ፣ ችግሮቻችሁን ለመርሳት፣ ወይም ኑሮ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ወኔ ለማግኘት ሰውነታችሁ አልኮል አምጣ፣ አምጣ ይላችኋል። ከመጠጥ ሌላ ምንም ነገር ማሰብ ያቅታችኋል። እንዲህም ሆኖ ግን ራሳችሁንና በዙሪያችሁ ያሉትን ሰዎች ከሥርዓት የወጣ አመል እንደሌላችሁ ለማሳመን ትሞክራላችሁ።”

ከአልኮል በተጨማሪ ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ባሪያ አድርገው የሚገዙ ሌሎች ንጥረ ነገሮችም አሉ። በመላው ዓለም ሕጋዊ ያልሆኑ ዕፆችን የሚወስዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ከዚህም በላይ ወደ 1.1 ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች ትምባሆ የሚያጨሱ ሲሆን ይህም እጅግ ከባድ ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር የያዘ ነው። ከዚህ አመል ለመላቀቅ የሚልጉ ሰዎች በርካታ ቢሆኑም በማይወጡበት ባርነት ውስጥ እንደታሰሩ ሆኖ ይሰማቸዋል። ታዲያ ይሖዋ እንደነዚህ ላሉት ሱሶች ባሪያ የሆኑ ሰዎችን ነፃ ለማውጣት የሚችል መሆኑን አስመስክሯል? *

የሪካርዶን ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ በማለት ይተርካል:- “ከአሥር ዓመት በፊት አልኮል ሕይወቴን እየተቆጣጠረው እንዳለ ተገነዘብኩ። በትዳሬ፣ በሥራዬ፣ በቤተሰቤ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነበር። ከመዳፉ ካልወጣሁ ችግሮቼን ልፈታ እንደማልችል ተረዳሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴ ሰካራም ሰው በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ድሃ መሆኑ እንደማይቀር እንድገነዘብ ረዳኝ። (ምሳሌ 23:​20, 21) ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረኝ ፈለግኩ። አምላክ እንዲረዳኝ በመማጸን ያቀረብኩት ልባዊ ጸሎት ለራሴ ሐቀኛ እንድሆን ረዳኝ። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ጀመር። ይህ ሰው በጣም ጥሩ ወዳጅ ሆኖኛል። አገርሽቶብኝ ወደ መጠጥ ስመለስ በትዕግሥትና በጽናት አምላክ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የሰጠውን የሕይወት መንገድ ያሳየኝ ነበር እንጂ ተስፋ ቆርጦ አልተወኝም።”

ዛሬ ሪካርዶ፣ ቢያንስ በአንጻራዊ ሁኔታ ከቀድሞ ባርነቱ ነፃ እንደወጣ ይሰማዋል። አልፎ፣ አልፎ በሱሱ የተሸነፈባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አይክድም። “እንዲህ ያሉ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙኝም” ይላል “ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ባለኝ ፍላጎት ላይ የሚስቴና የሌሎች ክርስቲያን ባልደረቦቼ እርዳታ ታክሎበት ያለብኝን ችግር ለመቆጣጠር ችዬአለሁ። አምላክ ቃል በገባው መሠረት ወደፊት የሚመጣውን ‘ማንም ታምሜአለሁ የሚል የማይኖርበትንና’ የአልኮል ሱስ የተረሳ ነገር የሚሆንበትን ዓለም በጉጉት እጠብቃለሁ። እስከዚያ ጊዜ ግን ራሴን ‘ለአምላክ ሕያው፣ ቅዱስና ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት’ አድርጌ ለማቅረብ በማደርገው ዕለታዊ ትግል እቀጥላለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 33:​24፤ ሮሜ 12:​1

በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ ሱሶች ነፃ ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ አምላክ ያደረገላቸውን ድጋፍ በግል ሕይወታቸው አይተዋል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለተለያዩ ፈተናዎችና ተጽእኖዎች በማጋለጥ ራሳቸውን በራሳቸው የሱስ ባሪያ እንዳደረጉ አይካድም። ሆኖም ይሖዋ በጣም ትዕግሥተኛ የሆነ ነፃ አውጪ መሆኑን ለመገንዘብ ችለዋል። እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉትን ሁሉ ለመርዳትና ለማበርታት ፈቃደኛ ነው።

‘እውነት ነጻ ያወጣችኋል’

ለውሸትና ለማታለያዎች ባሪያ ስለመሆንስ ምን ለማለት ይቻላል? ከዚህም ቢሆን ነፃ ልንወጣ እንደምንችል ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋግጦልናል። “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:​31, 32) ኢየሱስ ይህን በተናገረበት ጊዜ ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹ በማያፈናፍነው የፈሪሳውያን ወግና ሥርዓት ተተብትበው ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በዘመኑ ስለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሲናገር “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” ብሏል። (ማቴዎስ 23:​4) የኢየሱስ ትምህርቶች ሰዎችን እንደዚህ ካለው ባርነት ነፃ አውጥተዋል። ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ከማጋለጡም በላይ የእነዚህ ውሸቶች ምንጭ ማን እንደሆነ ጭምር አስታውቋል። (ዮሐንስ 8:​44) አምላክ ከሰዎች የሚፈልጋቸውን ምክንያታዊ የሆኑ ብቃቶች በማሳወቅ ውሸቶቹን በእውነት ተክቷል።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30

ዛሬም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ልክ እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአምላክ እርዳታ በባርነት አስረዋቸው ከነበሩት ሃይማኖታዊ ውሸቶችና የተሳሳቱ ልማዶች ነፃ እየወጡ ነው። ነፍስ የሚያድሰውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ካወቁ በኋላ ሙታንንም ሆነ እሳታማ ሲኦልን ከመፍራት እንዲሁም ላባቸውን ጠብ አድርገው ያገኙትን ገንዘብ “በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ” ያለውን ክርስቶስን እንወክላለን የሚሉ ቀሳውስት ለሚያከናውኑት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከመገበር ነፃ ሊወጡ ችለዋል። (ማቴዎስ 10:​8 አ.መ.ት ) ይሁን እንጂ ከዚህም የበለጠ ነፃነት ከፊታችን ይጠብቀናል።

ከሁሉ የከፋ ስውር ባርነት

እያንዳንዱን ወንድ፣ ሴትና ሕፃን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገውንና ቀደም ሲል የጠቀስነውን የባርነት ዓይነት ኢየሱስ ምን ሲል እንደገለጸው ልብ እንበል:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።” (ዮሐንስ 8:​34) ኃጢአት አልሠራም ብሎ አፉን ሞልቶ ሊናገር የሚችል ማን አለ? ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” ሲል አምኗል። (ሮሜ 7:​19) ማንም ሰው ራሱን ከኃጢአት እግር ብረት ለማላቀቅ አይቻል እንጂ በዚህ ረገድ ተስፋ ቢሶች አይደለንም።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:​36) ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ በእርግጥም ከባርነት ዓይነቶች ሁሉ በጣም ጎጂ ከሆነው ባርነት ነፃነት እናገኛለን። ከዚህ ባርነት እንዴት መላቀቅ እንደምንችል ለመረዳት በመጀመሪያ እንዴት እዚህ ባርነት ውስጥ እንደገባን እንመልከት።

አምላክ ሰውን የፈጠረው የመምረጥ ነፃነት ያለውና የኃጢአት ዝንባሌ የሌለበት አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ራስ ወዳድ የሆነ በዓይን የማይታይ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ድርጊቱ በሰው ዘር ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ እያወቀ የሰው ልጆችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ፈለገ። ይህ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ በመባል የታወቀው ዓመፀኛ መልአክ ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የመጀመሪያ ወላጆቻችን የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን ከአምላክ እንዲርቁ አደረገ። አዳም ሆን ብሎ አምላክ አስረግጦ የነገረውን መመሪያ ከጣሰ በኋላ ራሱ ኃጢአተኛ ከመሆን አልፎ ለተወላጆቹ በሙሉ አለፍጽምናንና ሞትን አስተላለፈ። (ሮሜ 5:​12) ውሎ አድሮ ሰይጣን “የዓለም ገዥ” ሆኖ መግዛት የጀመረ ሲሆን ኃጢአት ደግሞ ከሞት ጋር በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ነገሠ።​​—⁠⁠ዮሐንስ 12:​31፤ ሮሜ 5:​21፤ ራእይ 12:​9

ታዲያ ነፃ ልንወጣ የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን “በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን [ዲያብሎስን] በሞት” ሊሽርና “በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ” ሊያወጣ የሚችለው የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት የሚያስገኘውን ጥቅም ልናገኝ እንችላለን። (ዕብራውያን 2:​14, 15) ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ መውጣት ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስቡት! እንዲህ ያለውን ነፃነት ማግኘት በጣም አያጓጓም?

በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ዓይነት ባርነትስ? ሰዎች አለፈቃዳቸው ተገድደው ባሪያ የሚሆኑበት ሁኔታ የሚያከትምበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

አስተማማኝ ዋስትና ያለው ተስፋ

እንዲህ ያለው ዘግናኝ ባርነት ፈጽሞ እንደሚወገድ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እንዴት? እስቲ የሚቀጥለውን እንመልከት:- በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተደረጉት የነፃነት ሰልፎች ሁሉ ታላቅ የሆነውን ሰልፍ ያደራጀው ይሖዋ አምላክ ራሱ ነው። ይህን ታሪክ ሳታውቅ አትቀርም።

የእስራኤል ሕዝብ ከባድ የሆነ የጉልበት ሥራ እየሠራና በጭካኔ እየተገዛ በግብጽ በባርነት ይኖር ነበር። እስራኤላውያን አምላክ እንዲረዳቸው ጮኹ። ይሖዋም በታላቅ ምህረቱ አደመጣቸውና እርምጃ ወሰደ። ሙሴንና አሮንን ቃል አቀባዮቹ አድርጎ በመጠቀም ግብጻዊው ፈርኦን እስራኤላውያንን ነፃ እንዲለቅ አዘዘ። ይህ ትዕቢተኛ ንጉሥ ግን ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ተከታታይ መቅሠፍቶች ካወረደ በኋላ እንኳን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ እምቢተኛ ሆነ። በመጨረሻ ግን አምላክ ፈርኦንን አንበረከከው። እስራኤላውያንም በመጨረሻ ነፃ ወጡ።​​—⁠⁠ዘጸአት 12:​29-32

በጣም የሚያስደንቅ ታሪክ አይደለም? ይሁን እንጂ አምላክ በዚህ በዘመናችን ተመሳሳይ ነገር የማያደርገው ለምንድን ነው? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በሰው ልጆች አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ባርነት እንዲጠፋ ያላደረገው ለምንድን ነው? የዚህ ዓለም ገዥ ሰይጣን እንጂ ይሖዋ እንዳልሆነ አስታውስ። በኤደን በተነሳው ግድድር ምክንያት ይሖዋ ይህ ክፉ ጠላት ለተወሰነ ጊዜ እንዲገዛ ፈቅዷል። ባርነት፣ ጭቆናና ጭካኔ የሰይጣን አገዛዝ ተለይቶ የሚታወቅባቸው ባሕርያት ናቸው። በሰይጣን የሚመራው የሰው ልጅ አገዛዝ ለሰው ልጅ መከራ ከማምጣት ሌላ የፈየደው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የደረሰውን ሁኔታ ጠቅለል ባለ መንገድ ሲገልጽ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ብሏል።​​—⁠⁠መክብብ 8:​9 NW

ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የምንኖረው ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት በጣም በተስፋፋበት የ“መጨረሻው ቀን” ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1, 2) ይህ ማለት ኢየሱስ እንድንጸልይለት ያስተማረው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ባርነት የሚወገድበትና ጽድቅ የሚሰፍንበት ኅብረተሰብ ያቋቁማል። (ማቴዎስ 6:​9, 10) አምላክ የሾመው ንጉሥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት እስኪወገድ ድረስ ማንኛውንም የባርነት ርዝራዥ በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል።​​—⁠⁠1 ቆሮንቶስ 15:​25, 26

ይህ ታላቅ ቀን ሲጠባ ታማኝ ሆኖ የተገኘ የሰው ልጅ በግብጽ ባርነት የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች ያገኙት ነፃነት ከዚህ ታላቅ ነፃነት ጋር ሲወዳደር ከዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ለማየት ይችላል። አዎን፣ ጊዜው ሲደርስ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት” ያገኛል። በዚያ ጊዜ መላው የሰው ዘር “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳል።​​—⁠⁠ሮሜ 8:​21

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በትላልቅ የሮማውያን ግብዣዎች ላይ ቁንጣን እስኪይዝ መብላት በጣም የተለመደ ነገር ነበር። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች ምግብም ሆነ ማንኛውም ተመሳሳይ ነገር ባሪያ እንዲያደርጋቸው እንዳይፈቅዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።​​—⁠⁠ሮሜ 6:​16፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​12, 13፤ ቲቶ 2:​3

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ለቁማር ሱስ ባሪያዎች ሆነዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደገኛ ዕፆች፣ ለአልኮልና ለትምባሆ ሱስ ባሪያዎች ሆነዋል

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ሪካርዶ ከተጠመዱበት ሱስ ነፃ ለመውጣት አምላክ እንዴት እንደረዳቸው ለማየት ችለዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የጥንቶቹ እስራኤላውያን ከባርነት ነፃ እንደወጡ ሁሉ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችም በቅርቡ ከዚያ የላቀ ነፃነት ያገኛሉ