በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ መፍትሄ ተገኝቶ ይሆን?

አለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ መፍትሄ ተገኝቶ ይሆን?

አለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ መፍትሄ ተገኝቶ ይሆን?

በኮሎምቢያ ቦጎታ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ አንድ ዶክተር አለጊዜያቸው ከሚወለዱት ሕፃናት መካከል በሕይወት የሚቀጥሉት በጣም ጥቂቶቹ መሆናቸውን በማስተዋል በ1979 ለዚህ ችግር አንድ መፍትሔ ይዘው ብቅ አሉ።

አለጊዜያቸው የተወለዱ ሕፃናትን በሕይወት እንዲቀጥሉ ማድረግ ለዶክተሮች ፈታኝ ሥራ ነው። ሲወለዱ ክብደታቸው አነስተኛ የሆኑ ሕፃናት አብዛኛውን ጊዜ በሙቀት መስጫ መሣሪያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል። ሕፃናቱ ክብደታቸው እስኪጨምር ድረስ በመሣሪያው ውስጥ ይቆያሉ። ይሁን እንጂ ባልበለጸጉት አገሮች ውስጥ የሆስፒታሎች መጣበብ፣ የንጽሕና ጉድለትና የሐኪሞችም ሆነ የሕክምና መሣሪያ እጥረት መኖሩ እነዚህ ሕፃናት አደገኛ ለሆኑ በሽታዎች እንዲጋለጡ ያደርጋል።

በኮሎምቢያ የሚገኙ አንድ ዶክተር ይህን ችግር ሊያቃልል የሚችል አንድ ዘዴ አግኝተዋል። ይህ ዘዴ ምንድን ነው? አንድ ሕፃን አለጊዜው ሲወለድ የጤንነቱ ሁኔታ እስኪሻሻል ድረስ እንዲህ ላሉ ሕፃናት የሚሰጠው መሠረታዊ እንክብካቤ እየተደረገለት ይቆያል። በዚህ ጊዜ እናትየዋ ሕፃኑን ስለምትንከባከብበት መንገድ ስልጠና ይሰጣታል። የሕፃኑ ጤንነት ሲሻሻል እናትየው ልክ እንደ ሙቀት መስጫ መሣሪያ ሆና ማገልገል ትጀምራለች። እንዴት? ሕፃኑን ልብሷ ውስጥ ከትታ በጡቶቿ መካከል ታቅፈዋለች። ሕፃኑ ሙቀት እንዲያገኝና እዚያው ሆኖ የእናቱን ጡት በቀላሉ እንዲጠባ የሚያስችለው ይህ ዘዴ ካንጋሮ ሆዷ ላይ ባለው ከረጢት ልጅዋን ከምትይዝበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል። ስለሆነም ይህ ዘዴ አብዛኛውን ጊዜ “የካንጋሮ እናታዊ እንክብካቤ” ተብሎ ይጠራል።

ይህን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ የተለየ መሣሪያ አያስፈልግም። እናትየው የሚያስፈልጋት ለዚህ የሚስማማ ሸሚዝ ወይም መቀነት ያለው ቀሚስ መልበስ ብቻ ነው። የሕፃኑ ክብደት ሲስተካከል እናትየው ይዛው ወደ ቤት ልትሄድና በየጊዜው ወደ ሆስፒታሉ እያመላለሰች ጤንነቱ ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እንዲታይ ልታደርግ ትችላለች።

የተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት እንደሚያሳየው ይህ ዘዴ ውጤታማና አስተማማኝ ሆኖ ተገኝቷል። በተጨማሪም በእናትየውና በሕፃኑ መካከል የጠበቀ ቅርርብ እንዲኖር አስችሏል። ይህ ዘዴ በብዙ አገሮች ውስጥ ጥቅም ላይ መዋሉ አያስገርምም። በሜክሲኮ የሕፃኑ እናት እረፍት በሚያስፈልጋት ጊዜ እንዲያግዟት ሌሎች የቤተሰቡ አባላትም ይህን ዘዴ በተመለከተ ስልጠና ይሰጣቸዋል። በሜክሲኮ የዚህ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ጉዋዳሉፕ ሳንቶስ ለንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ከ1992 ጀምሮ ይህንን ዘዴ እንጠቀም የነበረ ሲሆን ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነም መመልከት ችለናል። የሙቀት መስጫ መሣሪያ እጥረትን ከማቃለሉም በተጨማሪ ሕፃናቱ በሆስፒታል የሚቆዩበትን ጊዜ በእጅጉ ይቀንሳል።”