በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአክራሪ ፖለቲከኛ ወደ ገለልተኛ ክርስቲያን መለወጥ

ከአክራሪ ፖለቲከኛ ወደ ገለልተኛ ክርስቲያን መለወጥ

ከአክራሪ ፖለቲከኛ ወደ ገለልተኛ ክርስቲያን መለወጥ

ላዲስላቭ ሽሜከል እንደተናገረው

ከተፈረደብኝ በኋላ ወደታሰርኩበት ክፍል ተወሰድኩ። ወዲያውኑ ከእኔ በላይ ሁለት ፎቅ አልፎ የሚገኘው ጓደኛዬን ግድግዳውን እየቆረቆርኩ በምንግባባበት የምስጢር ቋንቋ አነጋገርኩት። ምን ያህል ዓመት እንደተፈረደብኝ ለመስማት በጉጉት እየተጠባበቀ ነበር።

“አሥራ አራት ዓመት” የሚል መልእክት አስተላለፍኩ።

ሊያምነኝ አልቻለም። “አሥራ አራት ወር?” ሲል መልሶ ጠየቀኝ።

“አይደለም፣ አሥራ አራት ዓመት” በማለት መለስኩለት።

ጊዜው 1953 ሲሆን ቦታው ሊብሬክ ቼኮዝሎቫኪያ (የአሁኗ ቼክ ሪፑብሊክ) ነበር። የዚያን ጊዜ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የምታገል የ19 ዓመት ወጣት ነበርኩ። እኛ የንቅናቄ ቡድኑ አባላት በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረውን የኮሚኒስት ፓርቲ የሚነቅፉ በራሪ ወረቀቶችን በማሰራጨት ዓላማችንን እናስፋፋ ነበር። እንቅስቃሴያችን ሀገርን እንደ መክዳት ተደርጎ ስለተቆጠረ ረጅም የእስራት ዘመን ተፈረደብኝ።

ያለ ፍርድ አንድ ዓመት በማረፊያ ቤት ቆይቼ ነበር። እስረኞች ፍርዳቸው ከመሰጠቱ በፊት በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚታሰሩ ሲሆን በየጊዜው ዓይናቸውን እየተሸፈኑ ለምርመራ ይወሰዳሉ። በታሰርንበት ክፍል ውስጥ መነጋገር አይፈቀድልንም ነበር፤ ስለዚህ የምንግባባው በመንሾካሾክ ወይም በምስጢር ቋንቋ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ በወኅኒ ቤቱ ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን አወቅሁ። በነበርንበት ወኅኒ ቤት በወር ወይም በሁለት ወር አንዴ እስረኞችን ክፍል ያቀያይሩ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት እወድ ስለነበር ከአንድ ምሥክር ጋር እንድሆን ስመደብ ደስ አለኝ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዚህ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ባይኖረንም እናደርጋቸው የነበሩት ውይይቶች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊቆጠሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ በሕይወቴ መጽሐፍ ቅዱስ አይቼ አላውቅም። ሆኖም ያስጠናኝ የነበረው ምሥክር የሚያስታውሳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች በቃሉ ሲያብራራልኝ እኔ ደግሞ የሚናገረውን በማስታወሻ እጽፋለሁ። ጥናቱ የሚካሄደው አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠን በመንሾካሾክ ነበር።

የነበሩን እቃዎች የመጸዳጃ ወረቀትና አንድ የፀጉር ማበጠሪያ ብቻ ነበሩ። በማበጠሪያው ተጠቅሜ በመጸዳጃ ወረቀቱ ላይ ማስታወሻ እጽፍ ነበር። ከተወያየንባቸው ጥቅሶች መካከል አብዛኞቹን በቃሌ ይዣቸው ነበር። ያስጠኑኝ የነበሩት ምሥክሮች የመንግሥቱን መዝሙሮችም አስተማሩኝ። አንድ ምሥክር እንዲህ ብሎኝ ነበር:- “አሁን የታሰርከው በፖለቲካ ምክንያት ነው፤ ወደፊት ግን የይሖዋ ምሥክር በመሆንህ ብቻ ልትታሰር ትችላለህ።”

ከብዙ ምርመራ በኋላ በመጨረሻ ተፈረደብኝና በያኬሞፍ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ተወሰድኩ። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክር እንደምሆን እርግጠኛ ነበርኩ።

በእስራት ያሳለፍኳቸው ረጅም ዓመታት

የዩራኒየም ማዕድን ወደሚወጣበት ካምፕ እንደደረስኩ ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ ሌላ ቦታ እንደተወሰዱ ተረዳሁ። ሆኖም አንድ የይሖዋ ምሥክር ምግብ አብሳይ ስለሆነ አልተዛወረም ነበር። ይህ ምሥክር በብዙ ቦታዎች እየደበቀ ያቆየውን አንድ በጣም ያረጀ መጽሐፍ ቅዱስ አዋሰኝ። ስለዚህ በአእምሮዬ የያዝኳቸውን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱሱ አነበብኩ። ጥቅሶቹን ሳነብ ‘አዎን፣ ልክ ወንድሞች እንዳስተማሩኝ ነው’ እል ነበር።

አንድ ወር ከሚያህል ጊዜ በኋላ በፐርሺብራም ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ ቢቲዝ ወደተባለ ካምፕ ተዛወርኩ። እዚያም ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። በቢቲዝ በድብቅ ወደ ካምፑ የሚገቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እናገኝ ነበር። የካምፑ አስተዳዳሪዎች ጽሑፎቹ እንዴት እንደሚደርሱን ለማወቅ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። አሥራ አራት የምናህል እስረኞች ለሌሎች አዘውትረን እንመሠክር ነበር። ከእነዚህ መካከል ግማሾቹ የተጠመቁ ሲሆኑ እኔን ጨምሮ የተቀረነው ደግሞ እውነትን የሰማነው በእስር ቤት ውስጥ ነበር።

አብዛኞቻችን ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት እንፈልግ ነበር። ሆኖም ብዙ ውኃ መያዝ የሚችል ገንዳ ባለመኖሩ ምክንያት መጠመቅ አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙዎች ለመጠመቅ ከእስር እስኪፈቱ መጠበቅ ነበረባቸው። በቢቲዝ ካምፕ ውስጥ ለማዕድን ማውጫው አየር ማቀዝቀዣ የሚሆኑ ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ነበሩ። በ1950ዎቹ አጋማሽ ብዙዎቻችን በነዚህ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ተጠመቅን።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመጋቢት 1960 የፖለቲካ እስረኞች ኃላፊ የነበረ አንድ የፖሊስ መኮንን አስጠራኝ። ስለ ሌሎች እስረኞች መረጃ የማቀብለው ከሆነ የእስራት ዘመኔን እንደሚያስቀንስልኝ ነገረኝ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኔን ስነግረው መጥፎ ስድቦችን ያወርድብኝ ጀመር። “የመለቀቅ ዕድልህን እየዘጋህ ነው። ፈጽሞ ወደ ቤትህ አትመለሳትም! እዚችው ትሞታታለህ” አለኝ። ይሁን እንጂ ከሁለት ወራት በኋላ ምህረት ተደረገልኝና በድምሩ ከስምንት ዓመት እስራት በኋላ ተለቀቅኩ።

ለአጭር ጊዜ የቆየ ነጻነት

ከሚያዝያ 1949 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በቼኮዝሎቫኪያ ታግዶ ስለነበር ከእስር ቤት ውጪ አምላክን ማገልገል በእስር ቤት ውስጥ ከማገልገል እምብዛም እንደማይለይ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ነጻ ተለቀቅሁ ስል ሌላ ችግር ደግሞ ከፊቴ ይጠብቀኝ ነበር። በጊዜው በአገሪቱ የሚኖር እያንዳንዱ ወንድ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ሁለት ዓመት የማገልገል ግዴታ ነበ​ረበት።

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ አንዳንድ ሰዎች ከውትድርና አገልግሎት ነጻ ይደረጉ ነበር። ለምሳሌ ያህል በከሰል ማዕድን ማውጫዎች የሚሠሩ ይህ ዓይነት ነጻነት ነበራቸው። የማዕድን ቁፋፎ ሥራ ልምድ ስለነበረኝ በአንድ የማዕድን ማውጫ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። እዚያም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልኝ። “ስለ ውትድርና አትጨነቅ። አንተን ከወታደራዊ አገልግሎት ነጻ ማድረግ አያቅተንም” ብለው ነገሩኝ።

ከሁለት ወር በኋላ መጥሪያ ሲደርሰኝ በማዕድን ማውጫው አስተዳደር ቦታ ላይ የሚሠሩት ሰዎች “ምንም አትጨነቅ፣ መጥሪያው የደረሰህ በስሕተት መሆን አለበት፤ ደብዳቤ እንጽፍና ችግሩን እናስተካክላለን” የሚል ማረጋገጫ ሰጡኝ። ይሁን እንጂ ችግሩ መፍትሔ አላገኘም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ባለ ሥልጣን መጥቶ በተፈጠረው ሁኔታ እንዳዘነ ከገለጸልኝ በኋላ እንዲህ አለኝ:- “ይህን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው ነው። ሆኖም ሄደህ ሪፖርት ማድረግ ይኖርብሃል” አለኝ። በጦርነት ለመካፈል ሕሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ ወታደር እንደማልሆን ነገርኳቸው፤ በዚህም የተነሳ ታሰርኩና በአቅራቢያው ወደሚገኝ ወታደራዊ ተቋም ተወሰድኩ።​—⁠ኢሳይያስ 2:4

ሸንጎ ፊት መቅረብ

በጥር 1961 በከላድኖ ከተማ ከታሰርኩ በኋላ ወታደር እንድሆን ለማሳመን አንዳንድ ሙከራዎች ተደርገው ነበር። በዚያ ኃላፊ የነበረው ወታደራዊ መኮንን አንድ ስብሰባ አዘጋጀ። ምቹ የሆኑ የሶፋ ወንበሮች ያሉት አንድ ሰፊ ክብ ጠረጴዛ ወደሚገኝበት የስብሰባ አዳራሽ ተወሰድኩ። ብዙም ሳይቆይ መኮንኖቹ አንድ በአንድ እየገቡ በጠረጴዛው ዙሪያ ቦታ ቦታቸውን መያዝ ጀመሩ። ኃላፊው ከሁሉ ጋር አንድ በአንድ ካስተዋወቀኝ በኋላ ተቀመጠና “እሺ አሁን ስለ እምነትህ ንገረን” አለኝ።

በልቤ አጭር ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ በትኩረት ለሚከታተሉኝ አድማጮች መናገር ጀመርኩ። ውይይቱ ወዲያው አቅጣጫውን ቀየረና ስለ ዝግመተ ለውጥ መነጋገር ጀመርን። ዝግመተ ለውጥ በሳይንስ የተረጋገጠ ሐቅ ነው የሚል ሐሳብ ቀረበ። ቀደም ሲል በነበርኩበት ካምፕ ውስጥ ኢቮሉሽን ቨርስስ ዘ ኒው ዎርልድ የተባለ ቡክሌት አጥንቼ ነበር። * ስለዚህ ዝግመተ ለውጥ ያልተረጋገጠ ጽንሰ ሐሳብ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ሳቀርብ መኮንኖቹ በጣም ተደነቁ።

ከዚያም አንድ ሻለቃ ጥያቄ አቀረበ። የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። “ለመሆኑ ስለ ድንግል ማርያም ያላችሁ አመለካከት ምንድን ነው? ስለ ቅዱስ ቁርባንስ?” ሲል ጠየቀኝ። ለጥያቄዎቹ መልስ ከሰጠሁት በኋላ እንዲህ አልኩት:- “ጌታዬ፣ ሃይማኖተኛ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ምክንያቱም ጥያቄዎችዎ ከሌሎቹ ለየት ያሉ ናቸው።”

“ኧረ በፍጹም! ሃይማኖተኛስ አይደለሁም!” በማለት ጮክ ብሎ መለሰ። በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ክብርም ሆነ የኃላፊነት ቦታ አይሰጣቸውም ነበር። ስለዚህ ከዚያ በኋላ ሻለቃው በውይይቱ ውስጥ አንዲትም ቃል ትንፍሽ አላለም። የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው እንደሚያምኑ ለእነዚያ ሰዎች የማስረዳት አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደስ አለኝ።

ለመመስከር ያስቻሉኝ ተጨማሪ አጋጣሚዎች

ከጥቂት ቀናት በኋላ ፕራግ ውስጥ ወደሚገኝ ወታደራዊ ተቋም ተወሰድኩና በወታደሮች እንድጠበቅ ተደረገ። በመጀመሪያ እንዲጠብቀኝ የተመደበው መሣሪያ የታጠቀ ወታደር የሚደረግብኝ ልዩ ቁጥጥር አስገረመው። “አንድን ሰው ብቻውን እንድንጠብቅ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያችን ነው” አለኝ። ለምን እንደታሰርኩ ነገርኩት። ይህም ትኩረቱን ስለሳበው ጠመንጃውን በጉልበቶቹ መሃል አድርጎ ተቀመጠና ማዳመጥ ጀመረ። ከሁለት ሰዓት በኋላ በሌላ ወታደር ተተካ። እሱም እንዲሁ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠየቀኝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት አደረግን።

በቀጣዮቹ ቀናት እንዲጠብቁኝ ከተመደቡት ሰዎች ጋር እንዲሁም ዘበኞቹ ሲፈቅዱልኝ ከሌሎች እስረኞች ጋር የመወያየት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ጠባቂዎቹ ከታሰርንበት ክፍል ወጥተን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቶች አንድ ላይ እንድናደርግ ይፈቅዱልን ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጠባቂዎቹ ሌሎች እስረኞችን እንዳነጋግር የሰጡኝ ነጻነት ይታወቅና የከፉ መዘዞች ይከተላሉ ብዬ ፈራሁ። ሆኖም ሁሉም ነገር በምስጢር ተይዞ ነበር።

በመጨረሻ ፍርዴን ለመስማት ወደ ፍርድ ቤት ስወሰድ እነዚህ የመሠከርኩላቸው ሰዎች ማበረታቻ ሰጥተውኛል። ከመጀመሪያው የእስራት ዘመኔ በምሕረት ተቀንሶልኝ በነበረው ስድስት ዓመት ላይ የሚደመር የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። በጠቅላላው ወደ ስምንት ዓመት በእስር እቆያለሁ ማለት ነው።

አምላክ እንደሚረዳኝ ይታወቀኝ ነበር

በቼኮዝሎቫኪያ ከካምፕ ወደ ካምፕ እና ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት ስዘዋወር አብዛኛውን ጊዜ የአምላክ እርዳታ እንዳልተለየኝ ይታወቀኝ ነበር። ቫልዲስ በሚገኘው ወኅኒ ቤት ስደርስ አዛዡ ለምን እንደታሰርኩ ጠየቀኝ። “የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው። በጦርነት እንድካፈል እምነቴ አይፈቅድልኝም” ስል መለስኩለት።

“ሁሉም ሰው ያንተ ዓይነት አመለካከት ቢኖረው ኖሮ ምንኛ ጥሩ ነበር” ሲል በአዘኔታ መለሰልኝ። ለጥቂት ደቂቃዎች በጉዳዩ ላይ ካሰበ በኋላ ግን እንዲህ አለኝ:- “በዛሬው ጊዜ ግን ብዙዎቹ ሰዎች የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የላቸውም፤ ስለዚህ መቀጣት አለብህ፤ ቅጣቱም ከበድ ያለ መሆን አለበት!”

የቅጣት ሥራ በሚሠራበት የመስታወት መቁረጫ ክፍል ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። የታሰርኩት የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኔ ምክንያት ቢሆንም እንኳ አሁንም እንደ ፖለቲካ እስረኛ ተደርጌ እታይ ነበር። ስለዚህ የሚሰጡኝ ሥራዎች ከባድ ነበሩ። ለመብራት ጌጦችና ከመስታወት ለሚሠሩ የቅንጦት እቃዎች የሚሆን መስታወት መቁረጥ አስቸጋሪ ሥራ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት እቃዎች ያለ ምንም እንከን መሠራት ነበረባቸው። እስረኞች ጨርሰናል ብለው ካስረከቧቸው ዕቃዎች መካከል ግማሹ በሚቀጥለው ቀን ለጥገና ተመልሶ መምጣቱ የተለመደ ነበር። ስለዚህ የተመደበውን የምርት መጠን ማሟላት በጣም አስቸጋሪ ነው።

ወደ መስታወት መቁረጫው ክፍል ስገባ የክፍል ኃላፊው እስኪመጣ መጠበቅ ነበረብኝ። የክፍል ኃላፊው እንደመጣ በሱ አስተያየት በትጋት በማይሰሩት ሠራተኞች ላይ መጮህ ጀመረ። እስረኞቹን አልፎ እኔ ዘንድ ሲደርስ “አንተስ? ለምንድን ነው የማትሠራው?” ሲል ጠየቀኝ።

ገና አዲስ የመጣሁ እስረኛ መሆኔን ነገርኩት። ወደ ቢሮው ወሰደኝና ለምን እንደታሰርኩና ይህን የመሳሰሉ የተለመዱ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ። የታሰርኩበትን ምክንያት ከነገርኩት በኋላ “እንግዲያው የይሖዋ ምሥክር ነህ ማለት ነው?” ሲል ጠየቀኝ።

“አዎን” ብዬ መለስኩለት።

አመለካከቱ ወዲያውኑ ተቀየረ። “አይዞህ ምንም አትጨነቅ። እዚህ የሚሠሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ሁሉም ታታሪና ጨዋ ሰዎች ስለሆኑ እናከብራቸዋለን። አንተም ልትጨርሰው የምትችለው የሥራ ድርሻ እንድታገኝ አደርጋለሁ።”

የሥራ ኃላፊው ባህሪ በቅጽበት መለወጡ በጣም አስገረመኝ። ይሖዋን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ወኅኒ ቤት ውስጥ መልካም ዝና እንዲኖራቸው ያደረጉትን እነዚያን የማይታወቁ የእምነት አጋሮቼን አመሰገንኩ። ሐቁን ለመናገር በጠቅላላው የእስር ዘመኔ የይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ እንዳልተለየኝ ይሰማኝ ነበር።

ያለሁበት ሁኔታ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን በመጨረሻ ከክርስቲያን ወንድሞቼ ጋር እንደምገናኝና አስደሳች ፈገግታቸውንና ማበረታቻቸውን እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ያለ እነርሱ እስራቴን በጽናት መቋቋም በጣም አስቸጋሪ ይሆንብኝ ነበር።

አብዛኞቹ እስረኞች የሚያስቡት ለደረሰባቸው በደል እንዴት አድርገው እንደሚበቀሉ ብቻ ነው። እኔ ግን በፍጹም እንደዚህ ተሰምቶኝ አያውቅም። መከራ የሚደርስብኝ ለአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ታዛዥ በመሆኔ ምክንያት እንደሆነ አውቅ ነበር። ስለዚህ በእስር ላሳለፍኩት ለእያንዳንዱ ቀን ይሖዋ ገነት በሚሆነው አዲስ ምድር ውስጥ ቁጥር ስፍር ለሌለው ዘመን በሕይወት ሊያኖረኝ እንደሚችል አውቃለሁ።​—⁠መዝሙር 37:29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4

ዛሬ ላገኘኋቸው በረከቶች አመስጋኝ ነኝ

ከ15 ዓመት እስራት በኋላ በግንቦት 1968 በነጻ ተለቀቅኩ። መጀመሪያ ላይ ከሰዎች ጋር መነጋገር አስፈርቶኝ ነበር። አብዛኛው ሕይወቱን በወኅኒ ቤት ላሳለፈ ሰው ይህ የተለመደ ችግር ነው። ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቼ በእገዳ ሥር እያለንም ይካሄድ በነበረው በስብከቱ ሥራ እንድካፈል ወዲያውኑ ረዱኝ።

ከተፈታሁ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከኢቫ ጋር ተዋወቅኩ። ከባድ የቤተሰብ ተቃውሞ ቢኖርባትም እንኳ እሷና ወንድሟ ላለፉት ሦስት ዓመታት በቆራጥነት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጎን ቆመዋል። ወዲያውኑ በስብከቱ ሥራ አብረን መሳተፍ ጀመርን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንም እናትም ነበር። የኅትመቱ ሥራ የሚካሄደው በድብቅ ነበር። ከዚያም በኅዳር 1969 ተጋባን።

በ1970 የመጀመሪያ ልጃችን ያና ተወለደች። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማበረታቻ ለመስጠት ቅዳሜና እሁድ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርኩ። በዚህ ሥራ ላይ እያለሁ በ1975 ተያዝኩና ወኅኒ ቤት ወረድኩ። በዚህ ጊዜ ግን የታሰርኩት ለጥቂት ወራት ብቻ ነበር። ከዚያም በ1977 ወንዱ ልጃችን ስታይፈን ተወለደ።

በመጨረሻም መስከረም 1, 1993 ቼክ ሪፐብሊክ ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሰጠች። በቀጣዩ ዓመት ሴት ልጃችን ያና ዳሊቦር ድራዛን የሚባል ክርስቲያን ሽማግሌ አገባች። የጉባኤ አገልጋይ የሆነው ወንዱ ልጃችን ስታይፈን ደግሞ በ1999 የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችውን ብላንካን አገባ። አሁን ሁላችንም ፕራግ ውስጥ የሚገኝ አንድ ጉባኤ አባላት ነን። ሁላችንም አዲሱ ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። በተለይ እኔ የወኀኒ ቤት ቅጥሮች የማላይበትን ጊዜ እናፍቃለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.24 በ1950 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማስታወሻ ላይ ለመጻፍ የፀጉር ማበጠሪያ እጠቀም ነበር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታስሬ የነበርኩበትና በኋላም የተጠመቅሁበት የቢቲዝ ካምፕ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢቫና እኔ በመሃል፣ ስታይፈንና ብላንካ በግራ እንዲሁም ያና እና ዳሊቦር በቀኝ