በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አይጦችና ሰዎች በምግብ ሽሚያ ላይ

የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ የሳይንስና የኢንዱስትሪ ምርምር ድርጅት (ሲ ኤስ አይ አር ኦ) እንዳለው በዓለም አንድ ሕፃን ልጅ በሚወለድበት ጊዜ አሥር የአይጥ ግልገሎች ይወለዳሉ። በአንድ ቀን ውስጥ 360, 000 ምግብ ፈላጊ ሕፃናት ሲወለዱ በዚሁ ጊዜ ውስጥ የሚወለዱት የአይጥ ግልገሎች ግን 3, 600, 000 ይደርሳሉ። ለምሳሌ ያህል የኢንዶኔዥያ የሕዝብ ብዛት 230 ሚልዮን የሚደርስ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት በየቀኑ የሚመገቡት ሩዝ ነው። ይሁን እንጂ በዚያች አገር በየዓመቱ ከሚመረተው ሩዝ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነውን የሚበሉት አይጦች ናቸው። የሲ ኤስ አይ አር ኦ ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ግራንት ሲንግልተን እንደሚሉት “ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ኢንዶኔዥያውያንን ለአንድ ዓመት ሊቀልብ የሚችለው ሩዝ የሚበላው በአይጦች ነው ማለት ነው።”

የዶሮ ሾርባ​—⁠ተፈጥሮአዊ የጉንፋን መድኃኒት

የዶሮ ሾርባ እንደ ጉንፋን ላሉት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እንደ ባሕላዊ መድኃኒት ተደርጎ ሲወሰድ ብዙ ዓመታት አስቆጥሯል። ፉድ፣ ዩር ሚራክል ሜዲሲን በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተዘገበው በሎስ አንጀለስ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሳንባ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ኧርውን ዚመንት ይህ መድኃኒት እንዴት እንደሚሠራ አብራርተዋል:- “የዶሮ ሥጋ፣ እንደ ብዙዎቹ የፕሮቲን ምግቦች ሲስቴይን የተባለ ተፈጥሮአዊ አሚኖ አሲድ አለው። ሥጋው በሚቀቀልበት ጊዜ ይህ አሚኖ አሲድ ይወጣል። ሲስቴይን ዶክተሮች በብሮንካይትስና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ለተያዙ ሰዎች ከሚያዙት አሴትልሲስቴይን ከተባለው መድኃኒት ጋር በጣም ከፍተኛ የሆነ መመሳሰል አለው።” ቀደም ባሉት ዓመታት ከዶሮ ላባና ቆዳ ይዘጋጅ የነበረው ይህ መድኃኒት በአፍንጫ፣ በጉሮሮና በሳንባ ውስጥ የተጠራቀመውን ንፍጥ የማቅጠንና ወደ ውጭ እንዲፈስ የማድረግ ችሎታ አለው። የዶሮ ሾርባም ይህንን የማድረግ ችሎታ አለው። ሾርባው የተዘጉ የመተንፈሻ አካላትን የመክፈት ኃይሉ እንዲጨምር ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና እንደ ሚጥሚጣ የመሰሉትን ተኮስ የሚያደርጉ ቅመሞች መጨመር ጥሩ እንደሚሆን ዶክተር ዚመንት ይመክራሉ።

“እጣን ለጤና መጥፎ ሊሆን ይችላል”

ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “መዓዛው የሚያስደስተው የእጣን ሽታ በጤንነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።” ብዙ ቡድሂስቶች፣ ሂንዱዎችና ክርስቲያኖች በየቤቶቻቸውና በየአምልኮ ቦታዎቻቸው ለመድኃኒትነትና አምላካቸውን ለመለማመን ከሚያጨሱት እጣን የሚወጣው ጭስ ሰዎችን ካንሰር አምጪ ለሆኑ በርካታ ቅመሞች ያጋልጣል።” በታይናን ታይዋን የሚገኘው የቼንግ ኩንግ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት ዳ ቻንግ ሊን የሚመሩት ተመራማሪዎች “በታይናን ከተማ ከሚገኝ አንድ መቅደስ ውስጥና ውጭ የአየር ናሙናዎችን ወስደው በአንድ የበርካታ ተሽከርካሪዎች ማቆራረጫ ቦታ ከሚገኝ የአየር ናሙና ጋር አወዳድረዋል” ይላል ዘገባው። “ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ከሚገኝ አየር የተወሰደው ናሙና ከውጭ ካለው አየር በ19 እጥፍ የሚበልጥ መርዛም ንጥረ ነገሮች የተገኙበት ሲሆን ከተሽከርካሪዎች ማቆራረጫዎች ከተወሰደው ናሙና በጥቂት በልጦ ተገኝቷል።” ኒው ሳይንቲስት እንዳለው ከሆነ ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች አንዱ “ትንባሆ አጫሾች ካንሰር እንዲያዙ የሚያደርግ ነው ተብሎ የሚታሰበው ቤንዞፓይሪን ሲሆን አጫሽ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ቤቶች 45 ጊዜ እጥፍ በሚበልጥ መጠን ተገኝቷል።”

በአምላክ ስም የሚፈጸም ስርቆት

የሰሜን አሜሪካ የኢንቨስተመንት ደህንነት አስተዳዳሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዴብራ ቦርትነር “በኢንቨስትመንት ደህንነት ተቆጣጣሪነት ስሠራ 20 ዓመት አልፎኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በአምላክ ስም የሚዘረፈው ገንዘብ ከማንኛውም በሌላ ዘዴ ከሚዘረፈው እንደሚበልጥ ተመልክቻለሁ” ብለዋል። “መዋዕለ ንዋይ በምታፈሱበት ጊዜ አንድ ሰው ሃይማኖታችሁን ወይም እምነታችሁን አስታኮ ስለጠየቃችሁ ብቻ ጥንቃቄያችሁን ላላ ማድረግ አይኖርባችሁም።” ክርስቺያን ሴንቸሪ በተባለው መጽሔት መሠረት “ባለፉት ሦስት ዓመታት በ27 ክፍለ አገሮች የሚገኙ የኢንቨስትመንት ደህንነት ተቆጣጣሪዎች በመንፈሳዊ ወይም በሃይማኖታዊ እምነቶች በመጠቀም ኢንቨስተሮችን ባሳመኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። . . . አንድ የፕሮቴስታንት በጎ አድራጎት ድርጅት በአገሪቱ በሙሉ ከሚገኙ 13, 000 የሚያክሉ ኢንቨስተሮች 590 ሚልዮን ዶላር የሚያክል ገንዘብ መሰብሰቡ ከሁሉ የከፋ ሆኖ ተገኝቷል። በጎ አድራጎት ድርጅቱ በ1999 በደህንነት ተቆጣጣሪዎች የተዘጋ ሲሆን ከድርጅቱ ባለሥልጣኖች መካከል ሦስቱ ለቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።” ሌሎች ሦስት ድርጅቶች ደግሞ “1.5 ቢልዮን ዶላር መመዝበራቸውን” ክርስቺያን ሴንቸሪ ዘግቧል።

የዓለም ሙቀት መጠን ከፍ ማለት ለተፈጥሮ አደጋዎች መብዛት ምክንያት ሆኗል

የብሪታንያው ጋርዲያን ዊክሊ ቀይ መስቀል “በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት የሚደርሱ የተፈጥሮ አደጋዎች መጨመራቸውን” ሪፖርት ካደረገ በኋላ “ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪዎች በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ፈጽሞ ሊቋቋሙ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ብሏል” ይላል። “የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌዴሬሽን በዓመታዊ የአደጋዎች ሪፖርቱ ላይ የጎርፍ፣ የማዕበል፣ የመሬት መደርመስና የድርቅ አደጋዎች ቁጥር በ1996 ከነበረው 200 ተነስቶ በ2000 ወደ 392 ደርሷል ብሏል።” የፌዴሬሽኑ የአደጋዎችና የእርዳታ ኦፔረሽን ኃላፊ የሆኑት ሮዠ ብራክ የተፈጥሮ አደጋዎች ብዛት ከዚህም በጣም እንደሚጨምር በመስጋት “ሰብዓዊ እርዳታ ያለው አቅም የተወሰነ ነው። እርዳታ ልንሰጥ ከማንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ እፈራለሁ” ብለዋል። ጋርድያን እንዳለው “ባለፉት አሥር ዓመታት በተፈጥሮ አደጋዎች ከተጠቁት 211 ሚልዮን የሚያክሉ ሕዝቦች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የተጎዱት በጎርፍ አደጋ ነው። አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በድርቅ የተጎዱ ሲሆኑ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሞቱት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት የሞቱት በዚሁ በድርቅ ምክንያት ነው።”

ኤድስ​—⁠በደቡብ አፍሪካ ዋነኛው የሞት ምክንያት

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ምርምር ጉባዔ ስላደረገው አንድ ጥናት አስተያየት ሲሰጥ “በደቡብ አፍሪካ ኤድስ ዋነኛው የሞት ምክንያት ሲሆን በይበልጥ የተጠቁት ወጣቶች ናቸው” ብሏል። ተመራማሪዎች በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በደቡብ አፍሪካ በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአምስት እስከ ሰባት ሚልዮን እንደሚደርስ ገምተዋል። በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚሞቱት ሴቶች ቁጥር በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚሞቱት ሴቶች ቁጥር በእጅጉ እየበለጠ ነው። በደቡብ አፍሪካ ይላል ጽሑፉ በመቀጠል “የኤድስ አማጭ በሆነው ኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ብዛት ከማንኛውም አገር ይበልጣል። በአሁኑ ጊዜ ከዘጠኝ ደቡብ አፍሪካውያን መካከል አንዱ፣ ለአካለ መጠን ከደረሱ ደቡብ አፍሪካውያን መካከል ደግሞ ከአራቱ አንዱ ከኤች አይ ቪ ጋር እንደሚኖር የመንግሥት ባለሥልጣናት ይናገራሉ” ይላል።

በከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ብዛት

የለንደኑ ዘ ሳንዴይ ታይምስ “በ1900 ለንደን፣ ኒው ዮርክ፣ በርሊንና ቺካጎ የዓለም ትላልቅ ከተሞች” እንደነበሩ አመልክቷል። በቅርብ በተደረጉ ስሌቶች መሠረት ግን “እስከ 2015 ድረስ ምዕራባውያን ከተሞች ይበልጣሉ። በዚያ ጊዜ በግዙፍነታቸው ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት ቶኪዮ፣ ቦምቤ፣ ሌጎስ፣ የባንግላዴሿ ዳካና የብራዚሏ ሳኦ ፓውሎ ይሆናሉ።” እነዚህና ሌሎች 25 ከተሞች ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ይኖሯቸዋል። ይሁን እንጂ “እስከ 2015 ድረስ ለንደን እጅግ ብዙ ሕዝቦች ከሚኖሩባቸው 30 ከተሞች መካከል መቆጠሯ ይቀራል። በተጨማሪም ከዋነኞቹ ከተሞች መካከል የሕዝብ ብዛት ቅነሳ የሚደርስባት ብቸኛ ከተማ ትሆናለች” ይላል ታይምስ። ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ብዛት ብዙ ችግሮች ያስከትላል። በዩናይትድ ስቴትስ በፔንስልቫንያ ዩኒቨርሲቲ የሶስዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳግላስ ማሴይ “ድሆች በወንጀል፣ በዓመፅና በማኅበራዊ ቀውሶች በታወቁ ክልሎቻቸው ታጥረው ይኖራሉ። ነዋሪዎቿ አሁን ካለበት 26 ሚልዮን ዘልሎ በቅርቡ 30 ሚልዮን ይደርሳል ተብላ በምትታሰበው ቶክዮ የሕዝብ ጭማሪው ጋብ በማለቱና በቂ አገልግሎቶች ማቅረብ በመቻሉ ችግሩ ያን ያህል አሳሳቢ አልሆነም። ማሴይ እንደሚሉት ከሮማውያን እስከ ንግሥት ቪክቶሪያ ዘመነ መንግሥት ድረስ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ከ5 በመቶ በልጦ የማያውቅ ቢሆንም እስከ 2015 ድረስ ግን 53 በመቶ ይደርሳል።

እስከወዲያኛው ማጨስ አቁም!

በስቶክሆልም፣ ስዊድን የሥራ ዕድሜ ብሔራዊ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሉንድባክ “አጫሾች በሙሉ ማጨስ ማቆም አለባቸው። ያቆሙ ደግሞ ፈጽሞ ወደ አጫሽነት መመለስ የለባቸውም” በማለት ያስጠነቅቃሉ። ለምን? ምክንያቱም ማጨስ አቁመው ወደ አጫሽነት የተመለሱ ሰዎች ሳንባ ማጨስ አቁመው ከማያውቁት በበለጠ ፍጥነት ስለሚጎዳ ነው። ከ35 እስከ 68 የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 1, 116 ወንዶችና ሴቶች ላይ የተደረገ አሥር ዓመት የፈጀ ጥናት እንዳመለከተው በጥናቱ ዓመታት በሙሉ ሲያጨሱ በነበሩ ሰዎች ላይ የደረሰው የሳንባ ጉዳት 3 በመቶ ሲሆን ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ አቁመው እንደገና ማጨስ በጀመሩ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን 5 በመቶ ሆኗል።” ሉንድባክ ሲያስጠነቅቁ “በሳንባ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጣም ፈጣን የሆነው ማጨስ አቁሞ የነበረ ሰው ዳግመኛ ማጨስ በጀመረባቸው ሁለት ዓመታት ነው” ብለዋል። “ሳንባ ደግሞ አንድ ጊዜ ከተጎዳ በኋላ መልሶ ሊያገግም አይችልም።” ጥናቱ በቆየባቸው አሥር ዓመታት ማጨስ ባቆሙ ላይ የደረሰው የሳንባ ጉዳት ከ1 በመቶ እንዳልበለጠ የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል።

ገዳይ ሙቀት

ታይም መጽሔት ኮሪ ስትሪንገር የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ኮከብ ስፖርተኛ በሙቀት ምክንያት ስለመሞቱ ባሰፈረው ትችት ላይ እርጥበት አዘል በሆነ ሞቃት የአየር ሁኔታ ከሰውነት የሚወጣ ላብ ቶሎ ብሎ ስለማይተን ከባድ በሆነ የስፖርት እንቅስቃሴ ወቅት ሰውነት ለመቀዝቀዝ ይቸግረዋል። በዚህ ምክንያት የሰውነት ሙቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርስና ለሞት ሊያደርስ ይችላል። የሰውነት ሙቀት አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዴት ይታወቃል? ማዞር፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ድካም፣ አእምሮ መሳት፣ የልብ ምት መፍጠን፣ የቆዳ መድረቅና መቅላት አንዳንድ ምልክቶች ናቸው። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው ለማዳን ወዲያው በጣም ቀዝቃዛ በሆነ ውኃ በመንከር ወይም በበረዶ በማሻሸት ወይም ተመሳሳይ በሆነ ሌላ ዘዴ ትኩሳቱን ማብረድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚለው አባባልም እዚህ ላይ ይሠራል። “ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት ሰዓት ላይ አካላዊ እንቅስቃሴ አታድርግ። በሰውነትህ ውስጥ አየር ሊያዘዋውር የሚችል ለቀቅ ያለ ልብስ ልበስ። በጣም ብዙ ፈሳሽ፣” በተለይ ውኃ በብዛት ጠጣ። “አልኮል፣ ሻይና የኮላ መጠጦች ብዙ የማሸናት ባሕርይ ስላላቸው በሰውነትህ ውስጥ ያለውን የፈሳሽ መጠን ሊቀንሱብህ ይችላሉ” በማለት ታይም መጽሔት ይመክራል።