በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ክርስቲያኖች ለሌሎች መስበክ ይኖርባቸዋልን?

ክርስቲያኖች ለሌሎች መስበክ ይኖርባቸዋልን?

ምናልባት ከአስተዳደግህ ወይም ከኖርክበት ባሕል የተነሳ ሃይማኖት ከቤተሰብ ክልል ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ መነሳት የሌለበት ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። በመሆኑም አንድ ሰው ድንገት ቤትህ መጥቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊነግርህ ሲሞክር ልትበሳጭ ትችላለህ። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲያድርባቸው ያደረገው ደግሞ የነፍስ አድን ዘመቻ በሚል ሽፋን በሃይማኖት ታሪክ ሲፈጸም የኖረው ዓመፅ ነው።

በብዙ አገሮች ታሪክ ለክርስቶስ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ሳይሆን ሕይወታቸውን እንዳያጡ ፈርተው በጅምላ ሃይማኖታቸውን የለወጡ ሰዎች አሉ። ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ትተው የአሳዳጆቻቸውን ሃይማኖት ላለመቀበል ሲሉ ራሳቸውን ደብቀዋል፣ ቤታቸውንና የትውልድ አገራቸውን ትተው ተሰድደዋል አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። አንዳንዶቹ የሞቱት በእንጨት ላይ እንደተሰቀሉ በእሳት ተቃጥለው ነበር።

በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖትን በኃይል የማስለወጥ ድርጊት አይደግፍም። ታዲያ ይህ ማለት አንድ ሰው ሃይማኖታዊ እምነቶቹን ለሌሎች ማስተማር አይችልም ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መልሱን ይሰጠናል።

እንደ ባለሥልጣን ማስተማር

በመጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ምን እንዳደረገ ተመልከት። የአድማጮቹን ሕይወት መለወጥ የቻለ የተዋጣለት አስተማሪ ነበር። (ዮሐንስ 13:13, 15) በተራራው ስብከት ወቅት የሰጠው ትምህርት በቀላሉ የሚገባና ልብ የሚነካ ነበር። ከዚህ የተነሣ አድማጮቹ ‘እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበር በትምህርቱ ተገርመዋል።’ (ማቴዎስ 7:28, 29) ኢየሱስ ይህን ትምህርት ካስተማረ ወደ 2, 000 የሚጠጉ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ዛሬም እነዚህን ትምህርቶች የሚመረምሩ ሰዎች ሕይወታቸው ሊለወጥ ይችላል። ፕሮፌሰር ሃንስ ዲተር ቤትስ ከዚህ ሐሳብ ጋር በመስማማት “የተራራው ስብከት የአይሁድ እምነትን፣ የክርስትናን አልፎ ተርፎም የምዕራባዊውን ባህል ለውጧል” በማለት ተናግረዋል።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ትንሽ ቀደም ብሎ የሰጠው ትእዛዝ እርሱ የጀመረው የማስተማር ሥራ ከእርሱ ሞት በኋላም እንደሚቀጥል አልፎ ተርፎም በበለጠ ስፋት እንደሚሠራ የሚያረጋግጥ ነበር። (ዮሐንስ 14:12) ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሕዛብ ሁሉ ሄደው እርሱ ‘ያዘዛቸውን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ እንዲያስተምሩ’ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ ሲናገር የዚህን ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማ ግልጽ አድርጓል።​—⁠ማቴዎስ 28:19, 20፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ሥራ 1:8

በተጨማሪም የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተመልከት። የክርስትናን እምነት ከተቀበለ በኋላ ስለ አዲሱ እምነቱ ለሌሎች ከመናገር ወደ ኋላ አላለም። (ሥራ 9:17-19, 22) ጳውሎስ በምኩራብ ይሰብክና ‘ክርስቶስ መከራ ይቀበልና ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው’ ያስረዳ ነበር። “ከመጻሕፍት እየጠቀሰ” በማስረዳት ‘አይሁድንና የግሪክን ሰዎች ያሳምን ነበር።’ አንድ ጽሑፍ እንደሚለው “ማሳመን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘ምክንያታዊ ሐሳቦችን እያቀረቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት’ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ጳውሎስ በዚህ መንገድ ጥሩ አድርጎ ስላሳመናቸው ‘ብዙ ሰዎች አመለካከታቸውን ቀይረዋል።’​—⁠ሥራ 15:3፤ 17:1-4, 17፤ 18:4፤ 19:26 NW 

ማስገደድ ወይስ ማሳመን?

በዘመናችን በተለያየ መልኩ ያለ ውዴታ ሃይማኖትን የማስለወጥ ተግባር የተለመደ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዓይነቱን ድርጊት አይደግፍም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፣ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚመሩ የመምረጥ ነጻነት ያላቸው ፍጡራን መሆናቸውን ነው። ይህ ነፃነታቸው ደግሞ አምላክን ስለሚያመልኩበት መንገድ የመወሰን መብታቸውንም ይጨምራል።​—⁠ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15

ኢየሱስ ሰዎች የሚናገረውን ነገር እንዲቀበሉት ለማድረግ ሲል አስፈሪ ኃይሉንና ሥልጣኑን አለመጠቀሙ አምላክ የሰጣቸውን የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ መብታቸውን እንደሚያከብር የሚያሳይ ነው። (ዮሐንስ 6:66-69) ልባቸውን ለመንካት በማሰብ አሳማኝ ምክንያቶችን፣ ምሳሌዎችንና የአመለካከት ጥያቄዎችን በመጠቀም አድማጮቹን ለተግባር አነሳስቷል። (ማቴዎስ 13:34፤ 22:41-46፤ ሉቃስ 10:36) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱም የሌሎችን ምርጫ እንዲያከብሩ አስተምሯቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 10:14

ጳውሎስ በአገልግሎቱ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተል እንደነበር የታወቀ ነው። ጳውሎስ አሳማኝ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶችን እያቀረበ አድማጮቹን ለማሳመን ይጥር የነበረ ቢሆንም ስሜታቸውን ይጠብቅላቸውና አመለካከታቸውንም ያከብር ነበር። (ሥራ 17:22, 23, 32) ፈጣሪያችንን ከልብ እንድናገለግል ሊገፋፋን የሚገባው ለአምላክና ለክርስቶስ ያለን ፍቅር መሆን እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐንስ 3:16፤ 21:15-17) ስለዚህ በዚህ ረገድ የየራሳችንን ውሳኔ ማድረግ አለብን ማለት ነው።

የግል ውሳኔ

አስተዋይ የሆኑ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቤት መግዛትን፣ የሥራ ምርጫን እንዲሁም ልጆች ማሳደግን የመሳሰሉ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን የሚያደርጉት በስሜት ተነድተው አይደለም። የተለያዩ አማራጮች መኖራቸውን ካጣሩ፣ ባገኙት መረጃ ላይ በጥሞና ካሰቡበትና ሌሎችንም ምክር ከጠየቁ በኋላ ውሳኔ ያደርጋሉ።

አምላክን ማምለክ ያለብን እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ በሕይወታችን ውስጥ ውሳኔ ከሚጠይቁት ከማናቸውም ጉዳዮች የበለጠ ጊዜና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ ውሳኔ የአሁኑን ሕይወታችንን አልፎ ተርፎም ወደፊት የምናገኘውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚነካ ነው። በቤርያ ይኖሩ የነበሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይህን በግልጽ ተረድተው ነበር። ምሥራቹን ያብራራላቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ቢሆንም እየተማሩት የነበረው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር። ከዚህ የተነሣ ‘ከእነርሱ ብዙዎቹ አምነዋል።’​—⁠ሥራ 17:11, 12

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ያስጀመረውን የማስተማርና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ተያይዘውታል። (ማቴዎስ 24:14) ሌሎች ሰዎች የራሳቸውን ሃይማኖት የመምረጥ መብት እንዳላቸው ይገነዘባሉ። ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውን ለሌሎች ማካፈልን በተመለከተ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሳሌ ይከተላሉ። አዎን፣ ሕይወት አድን እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱትን ይህን ሥራ ሲሠሩ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሐቀኝነት ተጠቅመው አሳማኝ ምክንያቶችን ያቀርባሉ።​—⁠ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16