በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ ዛሬም ከባርነት አልተላቀቀም

የሰው ልጅ ዛሬም ከባርነት አልተላቀቀም

የሰው ልጅ ዛሬም ከባርነት አልተላቀቀም

ባርነት የቀረ ነገር ነው? ብዙ ሰዎች ቀርቷል ብለው ያስባሉ። ባርነት የሚለው ቃል ሲነሳ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ግፍና ጭካኔ ነው። ብዙዎች ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ከቀሩ ብዙ ዘመን አልፏቸዋል ብለው ያስባሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ባርነት ሲነሳ ወዲያው ትዝ የሚሏቸው ቀደም ባሉት መቶ ዘመናት በፍርሃት የተዋጡ ሰዎችን እንደ ሰርዲን አጭቀው እየተንቋቁ ይጓዙ የነበሩ የእንጨት መርከቦች ናቸው።

ባሁኑ ጊዜ እንደነዚህ ያሉ መርከቦች በባሕሮች ላይ ሲቀዝፉ እንደማይታዩ አይካድም። እንዲህ ያለው ባርነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲታገድ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ባርነት ፈጽሞ የቀረ ነገር አልሆነም። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ዓለም አቀፋዊው የፀረ ባርነት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ አሁንም ቢሆን 200 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በባርነት እንደሚኖሩ ይገመታል። እነዚህ ሰዎች የሚሠሩበት የሥራ ሁኔታ በቀደሙት መቶ ዘመናት ይኖሩ የነበሩ ባሮች ይሠሩበት ከነበረው የከፋ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ተንታኞች “ባሁኑ ጊዜ በባርነት የሚኖሩ ሰዎች ብዛት ከየትኛውም የታሪክ ዘመን ይበልጣል” ብለዋል።

እነዚህ የዘመናችን ባሮች የሚደርስባቸውን ሁኔታ መስማት በእጅጉ ያሳዝናል። ካንጂ * ገና አሥር ዓመቱ ሲሆን ቀን በቀን ለሚደበድቡት ጨካኝ ጌቶቹ ከብት ይጠብቃል። “ዕድለኛ ከሆንኩ የደረቀ ዳቦ አገኛለሁ። አለበለዚያ ግን ጦሜን እውላለሁ። ባሪያ ስለሆንኩና እንደ ንብረታቸው ስለሚቆጥሩኝ ለምሠራው ሥራ ደመወዝ ተከፍሎኝ አያውቅም። . . . በኔ ዕድሜ ያሉ ልጆች ከሌሎች ልጆች ጋር ይጫወታሉ። እንዲህ ባለው አሰቃቂ ኑሮ ከምኖር ብሞት ይሻለኝ ነበር” ይላል።

እንደ ካንጂ ያሉት ዘመናዊ ባሮች አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ወይም ሴቶች ናቸው። አለፈቃዳቸው ምንጣፍ ይሠራሉ፣ መንገድ ይገነባሉ፣ ሸንኮራ አገዳ ይቆርጣሉ አልፎ ተርፎም በዝሙት አዳሪነት ይሠማራሉ። የሚሸጡበት ዋጋ ደግሞ ከሰማንያ ብር ብዙም ያልበለጠ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ልጆች ለዕዳ መክፈያነት ሲባል በገዛ ወላጆቻቸው ይሸጣሉ።

እንዲህ ያለውን ታሪክ መስማት ይዘገንንሃል? እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ኬቪን ቤልዝ የተባሉት ደራሲ ዲስፖዘብል ፒፕል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ባርነት ትልቅ ነውር ነው። የአንድን ሰው ጉልበት ብቻ ሳይሆን መላ ሕይወቱን መዝረፍ ማለት ነው” ብለዋል። ሰዎች በሰዎች ላይ ይህን የመሰለ አረመኔያዊ ተግባር የሚፈጽሙ ከሆነ ታዲያ ባርነት ፈጽሞ የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣል ብለን ለማመን ምን ምክንያት ይኖረናል? ይህ ጥያቄ ከምታስበው በላይ አንተን በግል የሚመለከት ነው።

ወደፊት እንደምንመለከተው ባርነት አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም። የባርነት ዓይነቶች ብዙ ሲሆኑ አንዳንዶቹ በሁሉም የሰው ዘሮች ላይ የሚደርሱ ናቸው። ስለዚህ ሁላችንም የሰው ልጅ እውነተኛ ነጻነት ያገኝ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ግን ስለ ባሪያ ፍንገላ አጭር ታሪክ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ትክክለኛ ስሙ አይደለም።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጎስቋላ ሴቶችና ልጆች ለባርነት ሲፈነገሉ ኖረዋል

[ምንጭ]

ከላይ ያለው ፎቶ:- UN PHOTO 148000/Jean Pierre Laffont

U.S. National Archives photo