በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያሳየችው ድፍረት ክሷታል

ያሳየችው ድፍረት ክሷታል

ያሳየችው ድፍረት ክሷታል

ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብዙ ወጣቶች ስለ እምነታቸው በድፍረት በመናገር መልካም ምሳሌ ሆነዋል። ስቴላ የተባለችውን በግሪክ ተሰሎንቄ ከተማ የምትኖር በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ወጣት ምሳሌ ተመልከት። ስቴላ እንዲህ ትላለች:- “ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ማኅበሩ ያዘጋጃቸውን ቪዲዮዎች እንዴት መጠቀም እንደምንችል ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን በአንዱ ላይ ተብራርቶ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች​​—⁠⁠ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን ቪዲዮ እንዴት ልጠቀምበት እንደምችል አሰብኩ። ከዚያም በሚቀጥለው ቀን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር ሄጄ ቪዲዮው በትምህርት ቤቱ እንዲታይ ሐሳብ አቀረብኩ። ሌሎቹ አስተማሪዎች እስከ ተስማሙ ድረስ እርሳቸው ምንም እንደማይቃወሙ ሲነግሩኝ ተደነቅኩ።

“በዚያው ዕለት ትንሽ ቆይቶ ርዕሰ መምህሩ ቪዲዮው በሚቀጥለው ሳምንት ሊታይ እንደሚችል ግን የሚታየው ከትምህርት ክፍለ ጊዜ በኋላ ብቻ እንደሆነ ነገሩኝ። ይህን ስሰማ የክፍል ጓደኞቼ ቪዲዮውን ለማየት ሲሉ ትርፍ ጊዜያቸውን መሥዋዕት አያደርጉም ብዬ ስላሰብኩ ቅር ተሰኘሁ። ቢሆንም በቀጣዩ ቀን ሁሉም እንዲገኙ ጋበዝኳቸው። እነርሱም ግብዣዬን ተቀብለው መምጣት ብቻ ሳይሆን የሌላ ክፍል ተማሪዎችንም ጋብዘው ነበር። በሃይማኖታዊ ትምህርት የተመረቀውን አንድ መምህር ጨምሮ ስድስት አስተማሪዎችም ቪዲዮውን ለማየት መጡ።

“ሁሉም ሰው በጥሞና ይከታተል ነበር። ፊልሙ እንዳለቀ ርዕሰ መምህሩ የጥያቄና መልስ ውይይት እንዳካሂድ ጋበዙኝ። ብዙ ተማሪዎች በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚያከናውኑትን ሥራ ሲያዩ ተገርመው ነበር። አንድ ተማሪ ‘ደመወዝ የማይከፈላቸው ቢሆንም ተግባራቸውን የሚያከናውኑት በደስታ ነው!’ በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

“ፊልሙን ለማየት ለመጡት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረቱት ጽሑፎቻችን ነገርኳቸው። እንዲሁም ‘አዲሱ ሺህ ዓመት​​—⁠⁠የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?’ የሚል ርዕስ ያለውን የመንግሥት ዜና ቁጥር 36 አደልኳቸው። ርዕሰ መምህሩ በዚያ ላልተገኙ አስተማሪዎች የሚሰጠው ተጨማሪ ቅጂዎች እንድሰጠው ጠየቀኝ።

“ከዚያ ወዲህ ብዙ ተማሪዎች ስለ ቪዲዮው ለጓደኞቻቸው ያወሩ ነበር። ምስክርነቱን ለመስጠት ይህን አጋጣሚ በመጠቀሜ ደስተኛ ነኝ። የክፍል ጓደኞቼ ለእኔ ከበፊቱ የበለጠ አክብሮት አላቸው። ከሁሉም በላይ ግን የማመልከውን አምላክ እንዲያከብሩት አድርጓቸዋል!”