እንስት ድብ በእንቅልፍ የምታሳልፋቸው ወራት
እንስት ድብ በእንቅልፍ የምታሳልፋቸው ወራት
ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ በርካታ ዝርያ ያላቸው ወፎች የክረምቱን ብርድና ቅዝቃዜ ለማምለጥ ሲሉ መኖሪያቸውን እየለቀቁ ወደ ደቡብ ይፈልሳሉ። በዚሁ አካባቢ የሚኖሩ ቡናማ ድቦችም በጣም የሚቀዘቅዘው የክረምት ወቅት ችግር ይፈጥርባቸዋል። ዕፅዋት ይደርቃሉ፣ መሬቱም ሆነ በአካባቢው ያለው ነገር ሁሉ በበረዶ ይሸፈናል። በዚህ ጊዜ ክንፍ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ በቀላሉ እየበረሩ አካባቢውን ለቅቀው ይሰደዳሉ። ቡናማዎቹ ድቦች ግን እንዲህ በቀላሉ ጫካውንና ምድረ በዳውን አቋርጠው ሞቃታማ ወደሆነ ክልል መሰደድ አይችሉም። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን?
ይህን ችግር የሚቋቋሙበት የራሳቸው የሆነ ብልሃት አላቸው። ለክረምት ወራት ጭምር የሚበቃቸውን ያህል ምግብ በበጋ ይመገቡና የክረምቱን ወቅት ተኝተው ያሳልፋሉ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ እንዲህ እንደምንናገረው ቀላል አይደለም። አንተ ለግማሽ ዓመት ያህል ምንም ነገር ሳትበላና ሳትጠጣ ብትቆይ ምን ልትመስል እንደምትችል መገመት ትችላለህ። አንዲት እንስት ድብ የክረምቱን ወራት እንዴት በእንቅልፍ እንደምታሳልፍ እስቲ ደረጃ በደረጃ ለመመልከት እንሞክር።
በጣም ሥራ የሚበዛበት የበጋ ወቅት
አንዲት እንስት ድብ የሚላስ የሚቀመስ የማታገኝባቸው ወራት ከመምጣታቸው በፊት ከወዲሁ ብዙ ምግብ በመመገብ በቂ ጉልበት ማጠራቀም አለባት። ዋናው ዓላማዋ በሰውነቷ ውስጥ ብዙ ስብ ማከማቸት በመሆኑ በጣም መወፈሯ ብዙም አያሳስባትም። በዚህ ወቅት በአንዳንድ የሰውነቷ ክፍሎች ላይ የሚከማቸው ስብ እስከ ስምንት ሴንቲ ሜትር ይደርሳል። ዋነኛው ምግቧ በስኳር የበለጸገ እንጆሪ ቢሆንም ሥራ ሥሮችን፣ ትናንሽ አጥቢ እንስሳትን፣ ዓሦችንና ጉንዳኖችን ጨምሮ ያገኘችውን ሁሉ ትበላለች። በመጨረሻ የክረምቱ ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ ክብደቷ ከ130 ኪሎ ወደ 160 ኪሎ ሊደርስ ይችላል።
ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ስብ ነው (በዚህ ጊዜ ወንዱ ድብ ክብደቱ እስከ 300 ኪሎ ሊደርስ ይችላል)። ወደ እንቅልፍ ዓለም የምትሄድበት ጊዜ ሲደርስ ከማንኛውም ዓይነት ምግብ የምትታቀብ ከመሆኑም በላይ አንጀቷ ውስጥ የቀረውን ሁሉ በእዳሪ መልክ ታስወግዳለች። ከዚያ በኋላ ግማሽ ዓመት ያህል ሳትበላ፣ ሳትሸና ወይም ኩሷን ሳትጥል ትቆያለች።የእንቅልፍ ጊዜዋን የምታሳልፈው በዋሻ፣ በኩይሳ ወይም ከዛፍ ሥሮች በታች ባለ ጉድጓድ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ፀጥታ የሰፈነበት እስከሆነ ድረስ ሁሉም ይስማማታል። ማንም ቢሆን ሲተኛ የሚረብሸው ነገር እንዲኖር እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። እንስቷ ድብ ዋሻዋ በተቻለ መጠን ምቾትና ሙቀት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ትልልቅ የዛፍ ቅርንጫፎችን፣ የድንጋይና የእንጨት ሽበቶችን፣ በከፊል የበሰበሱ ተክሎችንና ሌሎች ጉዝጓዝ ሆነው የሚያገለግሉ ነገሮችን ትሰበስባለች። ዋሻው ከድቧ ግዙፍ ሰውነት ብዙም የሚበልጥ አይሆንም። ክረምት ሲመጣ አየር ለማስገባት ከምታገለግል በጣም ትንሽ ቀዳዳ በስተቀር ዋሻው ጥጥ በሚመስል አመዳይ በረዶ ሙሉ በሙሉ ይሸፈናል።
በእንቅልፍ የምታሳልፈው ጊዜ
እንደ ጃርት፣ የሌሊት ወፍና አይጠ መጎጥ ያሉ አጥቢ እንስሳት የክረምት ወራትን ከሞት ባልተናነሰ ሁኔታ ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ያሳልፋሉ። የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከአካባቢው የሙቀት መጠን ጋር ተቀራራቢ እስኪሆን ድረስ በጣም ይቀንሳል። የድቧ የሰውነት ሙቀት መጠን ግን የሚቀንሰው እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ ብቻ በመሆኑ ድብን ያለ እንቅልፍ አይወስዳትም። “ራሷን እስከማታውቅ ድረስ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ አይወስዳትም። በየቀኑ ማለት ይቻላል፣ ራሷን ቀና ታደርግና ትገላበጣለች” ሲሉ በፊንላንድ የሚገኘው የኦውሉ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑትና ድቦች የክረምት ወራትን እንዴት በእንቅልፍ እንደሚያሳልፉ ለበርካታ ዓመታት ጥናት ሲያደርጉ የቆዩት ፕሮፌሰር ራይሞ ሂሳ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው ድቧ በክረምቱ ወራት ከዋሻዋ አትወጣም።
ተኝታ በምታሳልፈው በዚህ የክረምት ወቅት በሕይወት ለመቆየት አስፈላጊ ከሆኑት በስተቀር በሰውነቷ ውስጥ የሚካሄዱት ተፈጥሯዊ ሂደቶች በአብዛኛው ይቆማሉ። የልብ ምቷ በጣም በመቀነስ በደቂቃ ከአሥር ያነሰ ይሆናል። የምታቃጥለውም ጉልበት እንዲሁ ይቀንሳል። አንዴ እንቅልፍ ከወሰዳት በኋላ ስቡ መቃጠል ስለሚጀምር ሰውነቷ የሚያስፈልጋትን ጉልበትና ውኃ በበቂ ሁኔታ ያገኛል። በሰውነቷ ውስጥ የሚካሄዱት ተፈጥሯዊ ሂደቶች መጠን ቢቀንስም እንኳ ኬሚካላዊ ለውጦች መካሄዳቸው ስለማይቀር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቆሻሻ ይፈጠራል። ታዲያ ዋሻዋን ሳትበክል ቆሻሻውን ማስወገድ የምትችለው እንዴት ነው? ሰውነቷ ቆሻሻውን ከማስወጣት ይልቅ መልሶ ይጠቀምበታል!
ፕሮፌሰር ሂሳ እንደገለጹት “በመጨረሻ የሚፈጠረው የናይትሮጅን ውሁድ ከኩላሊትና ከፊኛ ውስጥ ወጥቶ በደም አማካኝነት አንጀት ውስጥ ይገባል። ከዚያም አንጀት ውስጥ በሚገኙ ባክቴሪያዎች አማካኝነት ወደ አሞኒያ ይለወጣል።” ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ነገር አሞኒያው ተመልሶ ጉበት ውስጥ የሚገባ መሆኑ ነው። ጉበት ውስጥ ከገባ በኋላ ፕሮቲን ለማዘጋጀት አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ አሚኖ አሲዶችን ለመሥራት ያገለግላል። በዚህ መንገድ የድቧ ሰውነት ቆሻሻዎችን መልሶ ጠቃሚ ወደሆኑ ንጥረ ነገሮች በመቀየር ድቧ በዋሻዋ ውስጥ ተኝታ በምታሳልፈው ረጅም ወቅት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያሟላል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ሰዎች ዋሻ ውስጥ የተኙ ድቦችን አድነው ይገድሉ ነበር። በእርግጥም የተኙ ድቦችን ማደን ቀላል ነው። በመጀመሪያ ድቡ ያለበት ዋሻ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ የበረዶ መንሸራተቻ ያጠለቁ ሰዎች ዋሻውን ይከብቡታል። ከዚያ ድቡን ከተኛበት ይቀሰቅሱትና ይገድሉታል። ይሁን እንጂ በክረምት ወራት ድቦችን በተኙበት ማደን ጭካኔያዊ ድርጊት በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በመላው አውሮፓ ማለት ይቻላል፣ በሕግ ታግዷል።
ግልገሎች መውለድ
ተባዕቱ ድብ ክረምቱን በሙሉ እየተገላበጠ ከመተኛት በስተቀር የሚሠራው ነገር አይኖርም። እንስቷ ድብ ግን የሚጠብቃት ሥራ አለ። የድቦች የስሪያ ወቅት በበጋ ወራት መጀመሪያ ላይ ሲሆን የወንዱ ዘር ከሴቷ እንቁላሎች ጋር ከተገናኘ በኋላ ድቧ በእንቅልፍ የምታሳልፈው የክረምት ወቅት እስኪደርስ ድረስ ጽንሶቹ ምንም ዕድገት ሳያደርጉ ይቆያሉ። ከዚያም ወቅቱ ሲደርስ በማኅጸኗ ውስጥ ማደግ ይጀምራሉ። ጽንሶቹ በማኅጸኗ ውስጥ የሚቆዩት ለሁለት ወር ብቻ ሲሆን በታኅሣሥ ወይም በጥር የእናትየው የሰውነት ሙቀት መጠን በትንሹ ይጨምርና ሁለት ወይም ሦስት ግልገሎችን ትወልዳለች። ከዚያ የሰውነቷ ሙቀት መጠን ከመውለዷ በፊት የነበረውን ያህል ባይሆንም እንደገና ይቀንሳል። የግልገሎቹ አባት ሲወለዱ የማየት አጋጣሚ አያገኝም። ቢመለከትም እያንዳንዳቸው ከ350 ግራም ያነሰ ክብደት የሚኖራቸው እነዚህ ትናንሽ ግልገሎች የራሱ ልጆች መሆናቸውን ማመን ስለሚቸገር ለእሱ ብዙም ትርጉም አይኖረውም።
እናትየው ግልገሎቿን የምታጠባ በመሆኑ ጉልበቷ ይበልጥ ይሟጠጣል። ግልገሎቹ ከእናታቸው የሚያገኙትን ገንቢ ወተት እየጠቡ
በፍጥነት ስለሚያድጉ የጸደይ ወቅት ሲጠባ ክብደታቸው አምስት ኪሎ ግራም ይደርሳል። በመሆኑም በእናትየው አነስተኛ መኖሪያ ውስጥ ውር ውር ማለታቸው አይቀርም።ጸደይ
የክረምቱ ቅዝቃዜ አልፎ መጋቢት ጠብቷል። በረዶው እየቀለጠ በመሄዱ ወፎቹ ከሄዱበት ይመለሳሉ። ወሩ እየተገባደደ ሲሄድ ወንዶቹ ድቦች የክረምቱን ወራት ካሳለፉባቸው ዋሻዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ። እንስቶቹ ድቦች ግን ግልገሎቻቸው ጉልበታቸውን ስላሟጠጡባቸው ሊሆን ይችላል፣ ተጨማሪ እረፍት ለመውሰድ ሲሉ ለጥቂት ሳምንታት እዚያው ዋሻቸው ውስጥ ይቆያሉ።
ከዚህ ሁሉ በኋላ እንስቷ ድብ ተኝታበት ከነበረው ዋሻ ብቅ ትላለች። የክረምቱ ወቅት ከመምጣቱ በፊት ከነበራት ግዙፍ ሰውነት አንጻር ሲታይ አጽሟ ብቻ ነው የቀረው ማለት ይቻላል። ሰውነቷ ላይ ተከማችቶ የነበረው ስብ እንደ በረዶው ሟምቷል። ከዚያ በተረፈ ግን ብዙ በመተኛቷም ሆነ ለረጅም ጊዜ ሳትመገብ በመቆየቷ በሰውነቷ ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት የለም። በሚያስገርም ቅልጥፍና እንደ ልቧ ትንቀሳቀሳለች። ከዋሻዋ ከወጣች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘እንደ እበት ያለ እዳሪ’ ትወጣለች። አብዛኛውን ጊዜ የአካል ክፍሎቿ ወደ ወትሮው ሁኔታቸው ተመልሰው እንደገና በትክክል መሥራት እስኪጀምሩ የተወሰነ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ መብላት የምትጀምረው ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ ነው። ከዚያ በኋላ ግን የሚቀራት ነገር አይኖርም። ይሁንና ዕፅዋት ገና እያቆጠቆጡ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ በጫካው ውስጥ ብዙም የሚበላ ነገር አታገኝም። በመሆኑም እጮችን፣ ጥንዚዛዎችንና የሞቱ እንስሳትን የምትመገብ ከመሆኑም በላይ የደጋ አጋዘኖችንም እያደነች ትበላለች።
እንስቷ ድብ እንደ ዓይኗ ብሌን አድርጋ የምትመለከታቸውን ግልገሎቿን የድብ ባሕርይ ይዘው እንዲያድጉ ተንከባክባ ታሳድጋቸዋለች። አንድ የጥንት ምሳሌ “ሰነፍን በስንፍናው ከመገናኘት ልጆችዋ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 17:12) በሌላ አባባል ሁለቱንም መገናኘት የሚመረጥ ነገር አይደለም። “እናትየው ግልገሎቿን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የምታደርገው ጥረት ቀላል አይደለም። አንድ ወንድ ድብ ከመጣ አባታቸው ሆነም አልሆነ ጉዳት ሊያደርስባቸው ስለሚችል ወዲያውኑ ዛፍ ላይ እንዲወጡ ታደርጋለች” ሲሉ ሂሳ ገልጸዋል።
በቀጣዩ ዓመት ክረምት ሲገባ እናትየው ግልገሎቿን ወደ ራሷ ዋሻ ይዛቸው ትሄዳለች። ከዚያ በኋላ ባለው ዓመት ግን ሌሎች ግልገሎች የምትወልድ በመሆኑ ጡት የጣሉት ግልገሎች የየራሳቸውን ዋሻ መፈለግ ይኖርባቸዋል።
ድቧ የክረምቱን ወቅት ተኝታ እንድታሳልፍ የሚያደርጓትን በጣም ውስብስብ የሆኑና የረቀቁ ክስተቶች በተመለከተ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ማግኘት የተቻለ ቢሆንም በእንስሳዋ ላይ የሚታዩት ብዙዎቹ ባሕርያት አሁንም ድረስ ምስጢር እንደሆኑ አሉ። ድቧ የክረምቱ ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ የሚጫጫናትና የምግብ ፍላጎቷን የምታጣው ለምንድን ነው? ለረጅም ጊዜ ምግብ ሳትበላ መቆየቷ በሰውነቷ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም እክል የማያስከትለው ለምንድን ነው? እንዲህ እንዲህ ያሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ሁሉ ማወቅ ቀላል አይደለም። ድብም የራሷ የሆነ ምስጢር አላት!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ድቦች በእንቅልፍ የሚያሳልፉትን ጊዜ በተመለከተ የተካሄደ ጥናት
የኦውሉ ዩኒቨርሲቲ የሥነ እንስሳት ክፍል በእንስሳት ሰውነት ውስጥ የሚፈጠረውን ቅዝቃዜን ለመቋቋም የሚያስችል ተፈጥሯዊ ለውጥ በርከት ላሉ ዓመታት ሲያጠና ቆይቷል። አውሮፓ ውስጥ በሚገኘው ቡናማ ድብ ላይ ጥናት መካሄድ የጀመረው በ1988 ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ በድምሩ በ20 ድቦች ላይ ምርምር ተካሂዷል። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለእንስሳት ተብሎ በተዘጋጀ የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ለዚሁ ምርምር የሚያገለግል የድቦች መኖሪያ ተገንብቷል። ድቦቹ በክረምት ወራት በሚተኙበት ጊዜ የሙቀት መጠናቸውን እንዲሁም በደማቸውና በሆርሞናቸው ውስጥ የሚካሄዱትን ለውጦች ጨምሮ በሰውነታቸው ውስጥ የሚኖረውን ኬሚካላዊ ሂደት የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለማግኘት ተመራማሪዎቹ ኮምፒውተሮችን፣ የላቦራቶሪ ምርመራዎችንና የቪዲዮ ካሜራ ተጠቅመዋል። ምርምሩ ሲካሄድ የቆየው በሌሎች አገሮች ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ነው። በጃፓን የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳ ሳይቀሩ በምርምሩ ተሳትፈዋል። ተመራማሪዎቹ በዚህ ጥናት አማካኝነት የሚገኘው መረጃ በሰው አካል ክፍሎች ላይ ለሚያጋጥሙ እክሎች እንኳ ሳይቀር መፍትሔ ለማግኘት ሊረዳ ይችላል የሚል እምነት አላቸው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእንስት ድብ ዋሻ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስኳር የበለጸገ እንጆሪ