ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ለወፎች የተዘጋጀ “ከረሜላ”
ጌኦ የተባለው የጀርመን መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው “አንድ የብራዚል ተክል ብዙ ዘር ለማፍራት እሳካሁን ያልታወቀ ዘዴ ይጠቀማል።” ኮምብሬቱም ላንሲዮላተም የተባለው ተክል ለጎብኚዎቹ የሚጠጡት ቀሰም ሳይሆን “ከረሜላ” ያዘጋጅላቸዋል። የዚህ ቁጥቋጦ አበቦች ሌሊቱን 0.6 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው አንኳር ይሠራሉ። ይህ አንኳር ግሉኮስና ፍሩክቶስ ስላለው የከረሜላ ጣዕም እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ጀምበር ሲወጣና አበቦቹ ሲፈኩ የሚያብለጨልጩት የከረሜላ አንኳሮች ተዘጋጅተው እንደሚቆዩ ዘገባው ያብራራል። ይህ በአበቦች የተዘጋጀ ጣፋጭ ምግብ ቢያንስ “ከስምንት ቤተሰቦች የተውጣጡ 28 የአእዋፍ ዝርያዎችን” ይስባል። ወፎቹ ከቁጥቋጦ ወደ ቁጥቋጦ እየተዘዋወሩ ሲቃርሙ ብዙ ጽጌ ብናኝ ይዘው ስለሚዘዋወሩ ተክሉ በብዛት ይራባል።
ደስተኛ የኢጣሊያ ሕፃናት
ላ ሪፑብሊካ የተባለው የሮማ ዕለታዊ ጋዜጣ የኢጣሊያ የሕፃናትና የጎረምሶች መረጃዎች መገምገሚያ ብሔራዊ ማዕከል ስላደረገው አንድ ጥናት ሲዘግብ “በአውሮፓ የኢጣሊያ ሕፃናትን ያህል ደስተኛ ሕፃናት የሉም” ብሏል። ተመራማሪዎቹ ከኢጣሊያ ሕፃናት 96 በመቶ የሚሆኑት ከአባታቸውና ከእናታቸው ጋር አብረው እንደሚኖሩ ተገንዝበዋል። ይህ አኃዝ ፍቺና ተለያይቶ መኖር በጣም ተስፋፍቶ ከሚገኝባቸው የአውሮፓ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ከግማሽ የሚበልጡት አብረዋቸው የሚኖሩ ወይም ጎረቤቶቻቸው የሆኑ አያቶች አሏቸው። ስለሆነም “ከ10 አያቶች መካከል ስምንቱ” የልጅ ልጆቻቸውን “በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ” ያያሉ። ይህም ሕጻኑ “ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማውና” ብቸኝነት እንዳይሰማው ያደርጋል ይላል ሪፖርቱ። የሥነ አእምሮ ሊቅ የሆኑት አሌሳንድራ ግራሲዎቲን “አንድ ሕፃን የሚደሰተው እንደ ትላልቅ ሰዎች ብዙ ሀብት ስላገኘ ወይም ውድ የሆነ ልብስ ስለ ለበሰ ሳይሆን እንደሚወደድ በማወቁ ነው።”
የትንባሆ ኩባንያዎች አጠያያቂ ተግባር
በምሥጢር የተያዙ የትንባሆ አምራች ኩባንያዎች ሰነዶች “ኩባንያዎቹ አጫሾችን የታርና የኒኮቲን መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሲጋራ እንደሚያጨሱ በማስመሰል ሆን ብለው አታልለዋል” ይላል የብሪታንያው ኒው ሳይንቲስት መጽሔት። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የአውሮፓ ሕብረት በ1990 ባስተላለፈው መመሪያ በእያንዳንዱ ሲጋራ ውስጥ የሚገኝ ታር ከ15 ሚሊ ግራም እንዳይበልጥ ገድቧል። በኒኮቲንም ላይ ተመሳሳይ ገደብ ጥሏል። ይሁን እንጂ የአንድ ኩባንያ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት ኩባንያው ይህን ገደብ ለማሟላት በሚያመርታቸው ሲጋራዎች ላይ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ በቅመሞቹ አለካክ ላይ ለውጥ አድርጓል። ታዲያ እንዴት ሳይያዙ ቀሩ? “መለኪያዎቹን የሚያወጣው የትንባሆ ኮሚቴ በትንባሆ አምራች ኩባንያዎቹ ቁጥጥር ሥር ናቸው” ይላል ኒው ሳይንቲስት። የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ስቴላ ቢያሉስ “እነዚህ ገደቦች የሕዝብን ጤና በመጠበቅ ረገድ ምንም ዋጋ የሌላቸው መሆናቸውን ከዚህ መረዳት እንችላለን” ብለዋል።
እጅግ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ የማስታወቂያ ጽሑፍ
የቻይና የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች እስካሁን በዓለም በዕድሜው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የታተመ የወረቀት ማስታወቂያ እንዳገኙ ቻይናስ ፒፕልስ ዴይሊ ኦንላይን ዘግቧል። በቻይና ሁናን ክፍለ ሀገር በአንድ የመቃብር ቦታ 700 ዓመት የሆናቸውና ለቀለም መጠቅለያነት ያገለገሉ ሁለት የመጠቅለያ ወረቀቶች ተቆፍረው ወጥተዋል። በወረቀቱ ላይኛ የቀኝ ጠርዝ “በ70 የቻይንኛ ሆሄያት የሸቀጡን ዓይነት፣ ጥራትና ባሕርይ የሚገልጽ ጽሑፍ የሰፈረበት ሲሆን የሱቁ አድራሻም በወረቀቱ ላይ ታትሟል” ይላል ዘገባው። ማስታወቂያው የተጠቀመበት ቋንቋ ዘመናዊዎቹ ማስታወቂያዎች ከሚጠቀሙበት ጋር በጣም ይመሳሰላል። በከፊል “የምርታችን የቀለም ጥራት ከሌሎች የዘይት ቀለሞች ጋር ሲወዳደር በጣም ልዩ ነው” በማለት ይነበባል። ወረቀት ወደ አውሮፓ የገባው በ12ኛው መቶ ዘመን፣ ጉተንበርግ የማተሚያ መሣሪያ የሠራው ደግሞ በ15ኛው መቶ ዘመን ሲሆን “በቻይና ግን ወረቀት የተሠራው ጻይ ሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ወረቀት በሠራበት በ105 ዓ.ም ነው። በኅትመት ረገድም ቻይና በዘጠነኛው መቶ ዘመን እንኳን በእንጨት ላይ የተቀረጹ የማተሚያ ፊደላት ነበሯት” ይላል ዘገባው።
ንግድ በአብያተ ክርስቲያናት
በዩናይትድ ስቴትስ ወደ አብያተ ክርስቲያናት የሚሄዱት ሰዎች ቁጥርና የሚሰጡትም የገንዘብ መዋጮ እያሽቆለቆለ በመሄዱ አብያተ ክርስቲያናት ወጪያቸውን የሚሸፍኑበት ገቢ ለማግኘት ዓለማዊ የንግድ ቤቶች በመክፈት ላይ ናቸው። “ሁሉም ቤተ ክርስቲያን የሚያመራው ወደዚህ አቅጣጫ ነው” ይላሉ በሙንስተር፣ ኢንድያና የፋምሊ ክርስቲያን ሴንተር ከፍተኛ ፓስተር የሆኑት ስቲፈን ሙንሴይ። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንዳለው የአብያተ ክርስቲያናቱ የንግድ እንቅስቃሴ ቡናና ብስኩት ከመሸጥ የተሟላ የምግብ ቤት አገልግሎት እስከመስጠት ይደርሳል። አንድ በጃክስንቪል፣ ፍሎሪዳ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ አጠገብ የገበያ አዳራሽ ከፍቷል። በገበያ አዳራሹ ውስጥ የጉዞ ወኪል፣ የቁንጅና ሳሎንና የምግብ መሸጫ ይገኛል። የዚህ ቤተ ክርስቲያን መሥራችና ጳጳስ የሆኑት ቮን ማክላፍሊን “ኢየሱስ የሰጠንን ስጦታዎች እንድንቀበልና ከስጦታዎቹም ትርፍ እንድናገኝ ይፈልግብናል” ብለዋል። በማከልም በ2000 ዓመት ቤተ ክርስቲያኒቱ ካካሄደችው ንግድ ሁለት ሚልዮን ዶላር የሚያክል ትርፍ አግኝታለች።
ጉዳት የሌለው ሐሺሽ?
የለንደኑ ዚ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ “ሐሺሽ ምንም ጉዳት የለውም የሚለው ሐሳብ መሠረተ ቢስ መሆኑ በአንድ አዲስ ሪፖርት ተረጋግጧል። ይህ ዕፅ በጣም ኃይለኛ እየሆነ በመምጣቱ ከባድና ዘላቂ የሆነ የጤና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።” በእንግሊዝ የኒውካስል ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኼዘር አሽተን “ሐሺሽ የማይጎዳው የሰውነት ክፍል የለም። የአልኮልንና የሌሎቹን
አደገኛ ዕፆች ባሕርያት በሙሉ አጠቃልሎ የያዘ ዕፅ ነው” ብለዋል። መኪና የማሽከርከር ችሎታን በእጅጉ እንደሚያዳክም ታውቋል። በተጨማሪም ስኪዞፍሬንያ የተባለውን የአእምሮ በሽታ ጨምሮ ሌሎች የአእምሮ በሽታዎችን ሊያመጣ ይችላል። በሳንባም ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ሲጋራ ከሚያደርሰው በአምስት እጥፍ ይበልጣል። እምብዛም ያልተለመደ ዓይነት የጉሮሮ ካንሰር ሊያመጣ የሚችል ሲሆን በለጋ ዕድሜ ላይ በሚገኙ አጫሾች ላይ ደግሞ ለሞት የሚያደርስ የልብ ድካም ያስከትላል። በ1960ዎቹ ዓመታት በአንድ የሐሺሽ ሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ቲ ኤች ሲ የተባለ አንጎልን የሚጎዳ ቅመም መጠን 10 ሚሊ ግራም ያህል ነበር። “ባሁኑ ጊዜ ግን ተክሉን የማዳቀልና የመትከል ዘዴ በጣም በመራቀቁ በአንድ የሐሺሽ ሲጋራ ውስጥ የሚገኘው የቲ ኤች ሲ መጠን እስከ 300 ሚሊ ግራም ይደርሳል” ይላል ጋዜጣው።ከዶክተርዎ ጋር ይግባባሉ?
የብራዚሉ ፎልያ ደ ሳኦ ፓውሎ የተባለ መጽሔት “ዶክተሮችና በሽተኞች መግባባት ተስኗቸዋል” ይላል። በአንድ የሳኦ ፓውሎ የሕፃናት ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል በተደረገ ጥናት ልጆቻቸውን ይዘው ከሄዱ ወላጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ለልጆቻቸው ምን እንደተደረገላቸው እንኳን ሳይገባቸው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ሃያ አራት በመቶ የሚሆኑት ጽሑፉ በግልጽ ስለማይነበብ ምን መድኃኒት እንደታዘዘላቸው ሊያነቡ አልቻሉም። ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የዶክተራቸውን ስም ሊያስታውሱ አልቻሉም። ይህን የመሰለ አለመግባባት ለመኖሩ እንደሚከተሉት ያሉ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ሐኪሞች በሽተኞቻቸውን የሚመረምሩት በችኮላ በመሆኑና ለበሽተኞቻቸው ትኩረት ስለማይሰጡ በሽተኞች “ሐኪሞቻቸው በሚሰጡት የምርመራ ውጤት አይደሰቱም ወይም እርግጠኛ አይሆኑም።” በጣም በርካታ በሆኑ የሕክምና ቃላት ይጠቀማሉ። በዘመናዊ ምርመራዎች ምክንያት ሐኪሞች እንደ ድሮው በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቅ አያስፈልጋቸውም። አንድ ዘገባ እንዲህ ያለው ሁኔታ የተፈጠረበትን ሌላ ምክንያት ሲናገር “ራሳቸውን ከበሽታ፣ ከሥቃይ፣ ከጭንቀትና ከሞት ፍርሃት ለመጠበቅ ሲሉ” በርካታ ዶክተሮች “በስሜት መደንደንን መርጠዋል” በማለት አንድ የአእምሮ ሐኪም የገለጹትን ጠቅሶ ተናግሯል።
ጤናማ የአውሮፕላን ጉዞ
ኤል ኡኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ከተማ ጋዜጣ የአውሮፕላን ጉዞዎችን አስደሳች ለማድረግ የሚከተሉትን ምክሮች ይሰጣል:- (1) በአውሮፕላኖች ውስጥ ያለው አየር በጣም ደረቅ ሊሆን ስለሚችል ብዙ ፈሳሽ ጠጣ። (2) ደረቅ አየር ዓይን ሊያስቆጣ ስለሚችል ከኮንታክት ሌንስ ይልቅ መነጽር አድርግ። (3) ጡንቻዎችህን ለማዝናናትና የእግሮችህን የደም ዝውውር ለመጨመር እንደተቀመጥክ ቀላል የሆኑ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን አድርግ። (4) አልፎ አልፎ በመንገደኛ መተላለፊያው ላይ ተዘዋወር። (5) ለማውለቅ የማያስቸግር ጫማ አድርግ፤ እግርህን ይዘኸው እንደምትገባው ባለ ሻንጣ ላይ አሳርፍ። (6) ቆዳህ እንደልቡ መተንፈስ እንዲችል ያልተጨማደደና ሰው ሠራሽ ካልሆኑ ጨርቆች የተሠራ ልብስ ልበስ። (7) ከፍታ የአልኮልን ኃይል ስለሚያባብስ አልኮል በመጠኑ ጠጣ፣ ወይም ጨርሶ አትጠጣ። (8) ከአየር ማራገቢያው የሚወጣው ነፋስ በአንገትህ ወይም በጀርባህ ላይ በቀጥታ እንዳያርፍ አስተካክለው። (9) የዓይን መሸፈኛ አድርገህ ለመተኛት ሞክር። (10) አውሮፕላኑ በሚያርፍበትና በሚነሳበት ጊዜ በጆሮህ ውስጥ የሚፈጠረውን የአየር ግፊት ለመቀነስ አንድ ነገር አኝክ። ለሕፃናት ደረቅ ጡጦ መስጠት ይቻላል።
ቅምጥል ሕፃናት በጀርመን
የጀርመን መምህራን ማኅበር ሊቀ መንበር የሆኑት ኡዶ ቤክማን “በወላጆች ላይ ለሕፃናት የመሸነፍ አዲስ ባሕል” መታየት ጀምሯል ይላሉ። ዙድቨስት ፕረሰ የተባለው ጋዜጣ እንዳለው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ልጆች ከመጠን በላይ ተቀማጥለው ያደጉ በመሆናቸው በትምህርት ቤት ጠንክረው መሥራት እንደማይፈልጉ ቤክማን ገልጸዋል። “የቤት ሥራ በልጆች ላይ ከፍተኛ ውጥረት ያስከትላል፣ ልጆች ለፈተና በርትተው ማጥናት አለባቸው ማለት ምክንያተ ቢስነት ነው የሚሉ ወላጆች ቁጥር በጣም እየበዛ መጥቷል ብለዋል።” በተጨማሪም ሪፖርቱ ወላጆች ከመጨቃጨቅ ብለው ለልጆቻቸው ጥያቄ ሲሸነፉ “ሕይወታቸውን ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ የመምራት አጋጣሚ እንዲያጡ ማድረጋቸው ነው” ብሏል። ተቀማጥለው ያደጉ ልጆች ይላሉ ቤክማን፣ ሲያድጉ ራስ ወዳዶችና አላንዳች ልፋት ሁሉንም ነገር ማግኘት አለብን የሚሉ ሰዎች ይሆናሉ።