የብልግና ሥዕሎችን መመልከት ምንም ጉዳት የሌለው የጊዜ ማሳለፊያ ነውን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የብልግና ሥዕሎችን መመልከት ምንም ጉዳት የሌለው የጊዜ ማሳለፊያ ነውን?
በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች በፖምፔ የሚገኙትን የጥንት ፍርስራሾች ቆፍረው ማውጣት በጀመሩ ጊዜ በጣም የሚዘገንን ነገር ተመለከቱ። በጣም በሚያማምሩት የሥዕልና የቀለም ቅብ ሥራዎች መካከል ሩካቤ ሥጋን በገሐድ የሚያሳዩ በርካታ ቅርጾችና ሥዕሎች ነበሩ። ባለሥልጣኖች እነዚህ ሥዕሎችና ቅርጾች በጣም ስለቀፈፉአቸው ድብቅ በሆነ ቤተ መዘክር ውስጥ እንዲቀመጡ አደረጉ። እነዚህን እርቃን የሚያሳዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለማመልከት ፖርኒ እና ግራፎስ የሚሉትን ሁለት የግሪክኛ ቃላት በመውሰድ ፖርኖግራፊ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የፈጠሩ ሲሆን ቃል በቃል ትርጉሙ “ስለ ዝሙት አዳሪዎች መጻፍ” ማለት ነው። ባሁኑ ጊዜ ፖርኖግራፊ “ፍትወተ ሥጋን ለመቀስቀስ በማሰብ ወሲባዊ ድርጊቶችን በመጽሐፍ፣ በሥዕል፣ በቅርጽ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልም ወዘተ ማሳየት” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል።
በዚህ ባለንበት ዘመን የብልግና ሥዕሎችን ማየት በአብዛኞቹ ዘመናዊ ኅብረተሰቦች ተቀባይነት ያገኘና በብዛት የተስፋፋ ልማድ ይመስላል። በአንድ ወቅት ወራዳ ፊልም በሚታይባቸው ሲኒማ ቤቶችና ዝሙት አዳሪዎች በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ብቻ ተወስነው የኖሩት የብልግና ሥዕሎች ዛሬ በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ ተስፋፍተው ይገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳ የሚካሄደው የብልግና ሥዕሎች ንግድ በየዓመቱ ከ10 ቢልዮን ዶላር በላይ ትርፍ ያስገኛል!
አንዳንዶች የብልግና ሥዕል በጋብቻ ኑሯቸው የተሰላቹ ሰዎችን ትዳር ለማጣፈጥ ይረዳል በማለት ይከራከራሉ። አንዲት ጸሐፊ “በአእምሮ ውስጥ ሕያው የሆነ ምናባዊ ሥዕል ይፈጥራል። ወሲባዊ ደስታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ያስተምራል” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ በወሲባዊ ጉዳዮች ረገድ ግልጽነትና አለመፈራራት እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ። ዌንዲ ማክኤልሮይ የተባሉ ጸሐፊ “የብልግና ሥዕሎች ለሴቶች ጠቃሚ ናቸው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ በዚህ አስተሳሰብ የማይስማሙ ሰዎች አሉ። የብልግና ሥዕሎች በጣም በርካታ ከሆኑ ጎጂ ውጤቶችና ዝንባሌዎች ጋር ተዛምዶ አላቸው። አንዳንድ ሰዎች የብልግና ሥዕሎች አስገድዶ ከመድፈር ጋርም ሆነ በሴቶችና በሕፃናት ላይ ከሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች ጋር ግንኙት እንዳላቸው ይናገራሉ። በርካታ ሴቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የታወቀው ቴድ በንዲ “የብልግና ሥዕሎችን የመመልከት ሱስ ተጠናውቶት” እንደነበረ አምኗል። “ይህ ሁኔታ ወዲያው በግለሰቡ የሚስተዋል ወይም እንደ ከባድ ችግር የሚታይ ነገር አይደለም። . . . ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት . . . ወሲባዊ ባሕርይ ያላቸው የኃይል ድርጊቶች ወደመፈጸም ይመራል። ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ፍላጎት መሆኑን በአጽንዖት መግለጽ እፈልጋለሁ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈጠር ነገር አይደለም” ሲል ተናግሯል።
ባሁኑ ጊዜ የብልግና ሥዕሎች እጅግ መስፋፋታቸውና በዚህም ምክንያት ማብቂያ የሌለው ክርክር መፈጠሩ ‘መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው መመሪያ ይኖራል?’ ብለህ እንድትጠይቅ ይገፋፋህ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወሲባዊ ጉዳዮች በግልጽ ይናገራል
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወሲባዊ ጉዳዮች ምንም የሚደባብቀው ነገር የለም። (ዘዳግም 24:5፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3, ) ሰሎሞን “ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። . . . ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ( 4ምሳሌ 5:18, 19) ስለ ሩካቤ ሥጋም ሆነ ሩካቤ ሥጋ ያሉትን ገደቦች በተመለከተ ግልጽ የሆነ ምክርና መመሪያ ይሰጣል። ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ሩካቤ ሥጋ የተከለከለ ነው። ከተፈጥሮ ባሕርይ ውጭ የሆነ ሩካቤ ሥጋም እንዲሁ የተከለከለ ነው።—ዘሌዋውያን 18:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9፤ ገላትያ 5:19
በእነዚህ ገደቦች ውስጥም ቢሆን እርስ በርስ መከባበርና ራስን መግዛት አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:4) ይህ ምክር ወሲባዊ ሥዕሎች ከሚያስተላልፉት መልእክትም ሆነ ዓላማ በቀጥታ ይጻረራል።
ወሲባዊ ሥዕሎች ሩካቤ ሥጋን አዛብተው ያቀርባሉ
ወሲባዊ ሥዕሎች ሩካቤ ሥጋን በተከበረ ጋብቻ በተሳሰሩ ወንዶችና ሴቶች መካከል የሚደረግ ውብ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገው ከማሳየት ይልቅ የተዛባ መልክ በመስጠት ያዋርዱታል። ልቅ የሆነና ያልተገደበ ወሲብ አስደሳችና ተፈላጊ የሆነ ነገር ሆኖ ይቀርባል። ለሌላኛው ወገን ደንታ ቢስ በመሆን የራስን ፍላጎት ብቻ ማርካት ትልቅ ትኩረት ሲሰጠው ይታያል።
ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የወሲብ ፍላጎት ለማርካት ብቻ የተፈጠሩ ተደርገው ይታያሉ። አንድ ዘገባ እንደሚለው “ቁንጅና በሰውነት ክፍሎች ቅርጽና አቀማመጥ ስለሚለካ ከእውነታ ውጭ የሆነ ምኞትና ፍላጎት ይፈጠራል።” ሌላ ሪፖርት ደግሞ “ሴቶችን የራሳቸው ስብዕና የሌላቸው፣ ለገንዘብና ለመዝናኛ ሲሉ እርቃነ ሥጋቸውን ለመግለጥ ዝግጁ የሆኑና የወንዶችን ወሲባዊ ፍላጎት ብቻ ለማርካት የተቀመጡ ባዶ አሻንጉሊቶች አድርጎ መመልከት ከእኩልነት፣ ከመከባበርና ከሰብዓዊነት ጋር ፈጽሞ ሊጣጣም አይችልም” ብሏል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ከዚህ በተቃራኒ ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶች ‘ሚስቶቻቸውን እንደገዛ ሥጋቸው አድርገው እንዲወዱአቸውና እንዲያከብሩአቸው’ እንጂ የጾታ ስሜት ማርኪያ ብቻ አድርገው እንዳይመለከቷቸው ይመክራል። (ኤፌሶን 5:28፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) አንድ ሰው የሌሎች ሰዎችን እርቃን አዘውትሮ የሚመለከት ከሆነ የማይገባውን አያደርግም ሊባል ይችላል? አክብሮት አሳይቷል ለማለትስ ይቻላል? ወሲባዊ ሥዕሎችን የሚመለከት ሰው የሚያዳብረው ፍቅርን ሳይሆን ራስ ወዳድነትን ነው።
በወሲባዊ ሥዕሎች ረገድ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ሌላ ነገርም አለ። ሰዎች ወሲባዊ ስሜትን ለመቀስቀስ አላግባብ እንደሚጠቀሙባቸው ሌሎች ነገሮች ወሲባዊ ሥዕሎችም ብዙ ሳይቆይ የሚሰለቹ ናቸው። አንድ ጸሐፊ እንዳሉት “[ወሲባዊ ሥዕሎችን የሚመለከቱ ሰዎች] ብዙ ሳይቆይ ይበልጥ ግልጽና ነውረኛ የሆኑ ሥዕሎችን መፈለግ ይጀምራሉ። . . . ተጓዳኞቻቸው ይበልጥ እንግዳ የሆኑ ወሲባዊ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙላቸው ማስገደድ ስለሚጀምሩ . . . እውነተኛ ፍቅር ማሳየት እያቃታቸው ይመጣል።” ታዲያ እንዲህ ያለ ውጤት የሚያስከትል ድርጊት ምንም ጉዳት የሌለው ጊዜ ማሳለፊያ ሊባል ይችላል? ይሁን እንጂ ከወሲባዊ ሥዕሎች መራቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላ ምክንያት አለ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍትወት ያለው አመለካከት
በዛሬው ጊዜ ወሲባዊ ቅዠቶችን ለአእምሮ መመገብ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ስህተት የለውም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ይሁኑ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ አይስማማም። ወደ አእምሯችን በሚገባውና በምናደርገው ነገር መካከል በጣም የተቀራረበ ዝምድና መኖሩን በግልጽ ያሳያል። ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ 1:14, 15) ኢየሱስም “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ብሏል።—ማቴዎስ 5:28
ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች” ብሏል። (ያዕቆብም ሆነ ኢየሱስ እንዳመለከቱት የሰዎችን ድርጊት የሚገዛው በውስጣቸው ያለው ፍላጎት ነው። ይህ ዓይነቱ ፍላጎት እንዲያድግና እንዲጠናከር ከተፈቀደለት ለመቋቋም የሚያስቸግር ግፊት ያሳድራል። ይህን ዓይነቱን ግፊት መቋቋም በጣም አስቸጋሪ ስለሚሆን ድርጊቱን ወደመፈጸም ሊያደርስ ይችላል። ስለዚህ ወደ አእምሮአችን የምናስገባው ነገር ውሎ አድሮ በድርጊታችን ላይ ኃይለኛ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
ወሲባዊ ቅዠቶች ለአምላክ የምናቀርበውን አምልኮ ሊያስተጓጉሉብን ይችላሉ። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የጻፈው በዚህ ምክንያት ነው:- “እንግዲህ . . . ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው።”—ቆላስይስ 3:5
እዚህ ላይ ጳውሎስ ፍትወትን ከመጎምጀት ጋር አዛምዶታል። * መጎምጀት ደግሞ አንድን ያልተገኘ ነገር ከመጠን በላይ መፈለግ ማለት ነው። መጎምጀት የጣዖት አምልኮ ነው። ለምን? ምክንያቱም አንድ የሚጎመጅ ሰው የሚጎመጅለትን ነገር ከማንኛውም ነገር፣ ከአምላክም ጭምር አስበልጦ ስለሚመለከት ነው። ወሲባዊ ሥዕሎች አንድ ሰው ላላገኘው ነገር የፍትወት ስሜት እንዲያድርበትና እንዲጎመጅ ያደርጋሉ። አንድ ሃይማኖታዊ ጸሐፊ “የሌላውን ሰው ወሲባዊ ሕይወት ትመኛለህ። . . . ነጋ ጠባ የምታስበው ስለዚያ ነገር ብቻ ይሆናል። . . . የምንጎመጅለትን ነገር እናመልካለን” ብለዋል።
ወሲባዊ ሥዕሎች ሥነ ምግባርን ያበላሻሉ
መጽሐፍ ቅዱስ “ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን . . . እነዚህን አስቡ” ሲል አጥብቆ ይመክራል። (ፊልጵስዩስ 4:8) ወሲባዊ ሥዕሎችን የሚመለከት ሰው ይህን የጳውሎስ ምክር አለመቀበሉን ያሳያል። ወሲባዊ ሥዕሎች ከሰው እይታ ውጭ በምሥጢር መፈጸም የሚኖርበትን ድርጊት አላንዳች እፍረት አደባባይ ስለሚያወጡ ጨዋነት ይጎድላቸዋል። ሰዎችን ስለሚያዋርዱና ሰብዓዊ ክብር ስለሚያሳጡ አስጸያፊ ናቸው። አሳቢነትንና ደግነትን ስለማያበረታቱ ፍቅር ይጎድላቸዋል። ሰዎች ራስ ወዳድነት የተሞላበት የፍትወት ስሜት እንዲያድርባቸው ከማድረግ ሌላ የሚፈይዱት ነገር የለም።
ወሲባዊ ሥዕሎች ከሥነ ምግባርና ከጨዋነት ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን ስለሚያሳዩ አንድ ክርስቲያን ‘ክፉ የሆነውን ነገር ለመጥላት’ የሚያደርገውን ጥረት ያመክኑበታል። (አሞጽ 5:15) ኃጢአት መሥራትን ስለሚያበረታቱ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፋቸውን የሚከተሉትን ቃላት በቀጥታ ይጻረራሉ:- “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም . . . ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ።”—ኤፌሶን 5:3, 4
ወሲባዊ ሥዕሎች ጉዳት የላቸውም የሚያሰኝ አንዳች ምክንያት የለም። መልካም ሥነ ምግባርን ያበላሻሉ፣ የሰዎችንም ስሜትና ፍላጎት ይቆጣጠራሉ። ሰዎች ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ማርካት የሚኖርባቸውን የወሲብ ስሜት በዓይን በሚያዩት ነገር ለማርካት እንዲሞክሩ ስለሚያደርጉ በጾታ ተጓዳኞች መካከል ሊኖር የሚገባውን ዝምድና ሊያበላሹ ይችላሉ። የተመልካቹን አእምሮና መንፈሳዊነት ይመርዛሉ። ራስ ወዳድነትንና ስግብግብነትን በማበረታታት ሰዎች ሌሎች ሰዎችን እንደ ፍትወት ማርኪያ ብቻ አድርገው እንዲመለከቱ ያደርጋሉ። መልካም ለማድረግና ንጹሕ ሕሊና ይዞ ለመኖር የሚደረገውን ጥረት ያመክናሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የሚኖረውን መንፈሳዊ ዝምድና ሊጎዱ፣ እንዲያውም ሊያጠፉ ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:17-19) በእርግጥም ወሲባዊ ሥዕሎችን እንደ ተላላፊ በሽታ መሸሽና መራቅ ይገባል።—ምሳሌ 4:14, 15
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.20 ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው ተፈጥሯዊ ስለሆነው ወሲባዊ ፍላጎት ማለትም አንድ ሰው ለትዳር ጓደኛው ስለሚኖረው ተፈጥሯዊ የጾታ ስሜት አይደለም።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወሲባዊ ሥዕሎች አንድ ሰው ስለ ተቃራኒ ጾታ የሚኖረውን አመለካከት ሊያዛቡበት ይችላሉ