በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፖሊስ ጥበቃ—የሚያሳድረው ተስፋና የሚፈጥረው ሥጋት

የፖሊስ ጥበቃ—የሚያሳድረው ተስፋና የሚፈጥረው ሥጋት

የፖሊስ ጥበቃ—የሚያሳድረው ተስፋና የሚፈጥረው ሥጋት

በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ በእንግሊዝ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች የደንብ ልብስ የለበሰ፣ መደበኛ የፖሊስ ሠራዊት እንዳይቋቋም ተቃውመው ነበር። ተቃውሞ ያሰሙት ማዕከላዊው መንግሥት እንደልቡ የሚያዝዘው የታጠቀ ሠራዊት ካገኘ ነጻነታቸውን እንደሚነፍጋቸው በመፍራታቸው ነበር። አንዳንዶች በፈረንሳይ ዦዜፍ ፉሼ የፖሊስ አዛዥ ሳለ በአገሪቱ ሰፍኖ የነበረው ዓይነት የፖሊስ ሰላዮች የነገሡበት ሥርዓት ይፈጠር ይሆናል ብለው ሰግተው ነበር። ቢሆንም ‘የፖሊስ ኃይል ከሌለ እንዴት ያለ ኑሮ ልንኖር ነው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው አልቀረም።

ለንደን በትልቅነትም ሆነ በብልጽግና ከዓለም ከተሞች የአንደኛነት ደረጃ ያገኘችበት ዘመን ነው። ወንጀል ደግሞ እየተስፋፋ ሄዶ በከተማይቱ ይካሄድ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ወድቋል። የሕዝቡንና የሕዝቡን ንብረት ደህንነት መጠበቅ በበጎ ፈቃደኝነት የተሰማሩት የሌሊት ጠባቂዎችም ሆኑ መደበኛዎቹ ሌባ አዳኞች ሊወጡ የማይችሉት ከባድ ሥራ ሆነ። ክላይቭ ኤምስሊ ዚ ኢንግሊሽ ፖሊስ:- ኤ ፖለቲካል ኤንድ ሶሻል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው “ወንጀልና ሥርዓት አልበኝነት በሠለጠነ ኅብረተሰብ ውስጥ መኖር የማይገባቸው ነገሮች መሆናቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ” ብለዋል። ስለዚህም ለንደናውያን የፈሩት ሳይሆን የተመኙት እንደሚሆን ተስፋ በማድረግ በሰር ሮበርት ፒል አመራር መደበኛ የሆነ የፖሊስ ኃይል እንዲቋቋም ወሰኑ። በ1829 በመስከረም ወር የደንብ ልብስ የለበሱ መደበኛ ፖሊሶች በለንደን ጎዳናዎች ለጥበቃ ተሰማሩ።

ዘመናዊ የፖሊስ ሠራዊት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ፖሊስ ሲነሣ ሰዎች ተስፋና ሥጋት ያድርባቸዋል። ተስፋው ደህንነት ያስጠብቃሉ የሚል ሲሆን ሥጋቱ ደግሞ ሥልጣናቸውን አላግባብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ነው።

አሜሪካም የፖሊስ ሠራዊት አቋቋመች

በዩናይትድ ስቴትስ ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ የሆነ የፖሊስ ኃይል የተቋቋመው በኒው ዮርክ ከተማ ነው። ከተማይቱ እየበለጸገች ስትሄድ ወንጀሉም በዚያው መጠን እየጨመረ መጣ። በ1830ዎቹ ዓመታት እያንዳንዱ ቤተሰብ በርካሽ የሚገኙ አዳዲስ ጋዜጦች ላይ የሚወጣውን ዘግናኝ የወንጀል ዜና ማንበብ ይችል ነበር። የሕዝቡ አቤቱታ እያየለ በመምጣቱም ኒው ዮርክ በ1845 የፖሊስ ኃይል አቋቋመች። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የኒው ዮርክና የለንደን ነዋሪዎች አንዳቸው በሌላው የፖሊስ ሠራዊት ሲገረሙ ኖረዋል።

አሜሪካውያኑም ቢሆኑ እንደ እንግሊዛውያኑ መንግሥት እንደፈለገ የሚያዝዘው የታጠቀ ሠራዊት ማግኘቱ ሳያሳስባቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ ሁለቱ አገሮች ይህን ስጋት ለማስወገድ መፍትሔ ይሆናል ብለው የተጠቀሙበት ዘዴ የተለያየ ነበር። እንግሊዞቹ ረዥም መለዮና ጥቁር ሰማያዊ የደንብ ልብስ የሚለብስ ጨዋ የፖሊስ ሠራዊት ለማቋቋም መረጡ። እነዚህ ፖሊሶች ደበቅ ተደርጎ ከሚያዝ አጭር ዱላ በስተቀር ምንም ዓይነት ትጥቅ አይዙም። ዛሬም ቢሆን የብሪታንያ ፖሊሶች ለየት ያሉ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ጠመንጃ ወይም ሽጉጥ አይዙም። ይሁን እንጂ አንድ ሪፖርት እንዳለው “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ . . . የብሪታንያ ፖሊስ ሙሉ በሙሉ የታጠቀ ሠራዊት መሆኑ እንደማይቀር እየታመነበት መጥቷል።”

በዩናይትድ ስቴትስ ግን መንግሥት በፖሊስ ኃይል አላግባብ እንዳይጠቀም ለማድረግ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ተደረገ። ይህ ማሻሻያ ለሕዝቡ “የጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆንና የመታጠቅ መብት” ይሰጣል። በዚህም የተነሣ ፖሊሶች ትጥቅ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ከጊዜ በኋላ የአሜሪካ ፖሊሶች በየጎዳናው ከዘራፊዎች ጋር መታኮስ ዋነኛ ተግባራቸው ሆነ። የአሜሪካ ፖሊሶች መሣሪያ እንዲታጠቁ ሌላው ምክንያት የሆነው ነገር የመጀመሪያው የፖሊስ ኃይል በተቋቋመበት ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የነበረው ሁኔታ በለንደን ከነበረው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ መሆኑ ነበር። የኒው ዮርክ ነዋሪዎች እንደ አሸን እየፈሉ በመሄዳቸው ከተማዋ በረብሻ ተውጣ ነበር። ከ1861-65 የተደረገው የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ከአውሮፓ በመጡት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መጤዎችና በጥቁር አሜሪካውያን መካከል የከረረ የዘር ጥላቻ ተፈጥሮ ነበር። ፖሊሶች ከረር ያለ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ ተሰማቸው።

ስለዚህ የፖሊስ ኃይል ቢጠላም ያለእርሱ መኖር እንደማይቻል እየታመነበት መጣ። ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ሥርዓትና ፀጥታ ለማግኘት ሲል ፖሊሶች አልፎ አልፎ የሚፈጽሙትን ከደንብ ውጭ የሆነ ድርጊት ችሎ ለማሳለፍ ዝግጁ ሆነ። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ግን ከነዚህ ፈጽሞ የተለየ ዓይነት የፖሊስ ኃይል ማቆጥቆጥ ጀምሮ ነበር።

አስፈሪ ፖሊሶች

ዘመናዊ የፖሊስ ኃይል መቋቋም በጀመረበት በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አብዛኛው የሰው ዘር ይገዛ የነበረው ቅኝ ግዛት በሚያስፋፉ የአውሮፓ መንግሥታት ነበር። በአጠቃላይ የአውሮፓ ፖሊስ የተደራጀው ሕዝቡን ሳይሆን ገዥዎችን ለመጠበቅ ነበር። በገዛ አገራቸው ላይ የታጠቀ ፖሊስ እንዲኖር ያልፈለጉት ብሪታንያውያን እንኳን በቅኝ ግዛቶቻቸው የሚኖሩትን ሕዝቦች ለመቆጣጠር ወታደራዊ ፖሊሶችን ሲያሰማሩ ምንም ቅር አላላቸውም። ሮብ ሞውቢ ፖሊሲንግ አክሮስ ዘ ወርልድ በተባለው መጽሐፋቸው “በቅኝ ግዛቶች ውስጥ የተሰማሩ ፖሊሶች ጭካኔ፣ ሙስና፣ የኃይል ድርጊት፣ ግድያና የሥልጣን ብልግና ያልፈጸሙበት ጊዜ አልነበረም ለማለት ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል። ይኸው መጽሐፍ የቅኝ ገዥ መንግሥታት ፖሊሶች አንዳንድ ጠቃሚ ጎኖችም እንደነበራቸው ከገለጸ በኋላ “በመላው ዓለም ፖሊስ የሕዝብ አገልጋይ መሆኑ ተዘንግቶ የመንግሥት ኃይል ነው የሚል ግንዛቤ የተስፋፋው በእነዚህ ፖሊሶች ምክንያት ነው” ይላል።

ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ መንግሥታት የመንግሥት ግልበጣ ይካሄድብን ይሆናል ብለው በመፍራት ዜጎቻቸውን በድብቅ የሚሰልሉ ፖሊሶችን ሲያሰማሩ ኖረዋል። እንደነዚህ ያሉት ፖሊሶች የጠረጠሯቸውን ሰዎች ቁም ስቅል እያሳዩ ከመመርመራቸውም በላይ በግድያ ወይም አለፍርድ ቤት ትእዛዝ በማሠር ያስወግዳሉ። ናዚዎች ጌስታፖዎችን፣ ሶቪዬት ኅብረት ኬጂቢዎችን፣ ምሥራቅ ጀርመን ደግሞ ሽታዚዎችን አሰማርተው ነበር። ሽታዚ የተባለው የምሥራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት 16 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎችን ለመቆጣጠር 100, 000 የሚያክሉ መደበኛ ፖሊሶችንና ግማሽ ሚልዮን የሚያክሉ መረጃ አቀባዮችን አሰማርቶ ነበር። ሰላይ ፖሊሶች ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ የስልክ መስመሮችን እየጠለፉ ሰዎች የሚነጋገሩትን ያዳምጡ ነበር። በተጨማሪም አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ነዋሪ በተመለከተ በጽሑፍ የሰፈረ መረጃ ነበራቸው። ጆን ከህለር ሽታዚ በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “የሽታዚ ፖሊሶች ያሻቸውን ከማድረግ የማይመለሱና እፍረት የሚባል ነገር የማያውቁ ነበሩ። የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሹሞችን ጨምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ለሰላይነት ተመልምለዋል። ቢሮዎቻቸውና የኑዛዜ መቀበያ ክፍሎቻቸው በመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች የተሞሉ ነበሩ።”

ይሁን እንጂ አስፈሪ ፖሊሶች የሚገኙት ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች ብቻ አይደለም። በሌሎች አገሮችም የሚኖሩ የትላልቅ ከተሞች ፖሊሶች ሕግ በሚያስከብሩበት ጊዜ በተለይ በአናሳ ቡድኖች ላይ አግባብ ያልሆነ የኃይል ድርጊት ይፈጽማሉ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። አንድ የዜና መጽሔት በሠፊው ተወርቶለት ስለነበረ አንድ በሎስ አንጀለስ የተፈጸመ ቅሌት አስተያየት ሲሰጥ “የፖሊስ ምግባረ ብልሹነት ከፍተኛ ከሆነ አዲስ ጣሪያ ላይ መድረሱን ያመለከተ ሲሆን ወሮበላ ፖሊስ የሚል ስያሜ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል” ብሏል።

ስለዚህም የመንግሥት ባለሥልጣናት የፖሊስ መምሪያዎች እንዴት አድርገው ስማቸውን ሊያድሱ እንደሚችሉ ሲያስቡ ቆይተዋል። በርካታ የፖሊስ ሠራዊቶች ለማኅበረሰቡ የሚፈጽሙት ጠቃሚ የሆነ የአገልግሎት ገጽታ ጎልቶ እንዲታይ ለማድረግ ሞክረዋል።

መንደርን መሠረት ያደረገ የፖሊስ አገልግሎት

በጃፓን ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት የቆየው መንደርን መሠረት ያደረገ የፖሊስ አገልግሎት የበርካታ ውጭ አገሮችን ትኩረት ስቧል። የጃፓን ፖሊሶች ሥራቸውን የሚያካሂዱት አነስተኛ ከሆኑ የመንደር ፖሊስ ጣቢያዎች ሲሆን በአንድ ጣቢያ ተመድበው በተለያዩ ፈረቃዎች የሚሠሩት ፖሊሶች ቁጥር ከአሥራ ሁለት አይበልጥም። በጃፓን ለረጅም ጊዜ የኖሩትና የወንጀል ሳይንሳዊ ጥናት አስተማሪ የሆኑት ብሪታንያዊው ፍራንክ ላይሽማን “ኮባን እየተባሉ በሚጠሩት የመንደር ፖሊስ ጣቢያዎች ተመድበው የሚሠሩት ፖሊሶች የሚሰጡት ወዳጃዊ አገልግሎትና እርዳታ በሠፊው የታወቀ ነው። የጃፓን ጎዳናዎች በአብዛኛው ስም ያልተሰጣቸው በመሆኑ የሚፈልጉት አድራሻ ጠፍቶባቸው ለተቸገሩ መንገደኞች የሚፈልጉትን አድራሻ ያመላክታሉ፤ ድንገተኛ ዝናብ ለመጣባቸው መንገደኞች ጠፍተው ባለቤት ያልተገኘላቸውን ጃንጥላዎች ያውሳሉ፤ ሞቅ ብሏቸው ያመሹ የቢሮ ሠራተኞችን በባቡር ያሳፍራሉ፤ ችግር የደረሰባቸውን ዜጎች ያማክራሉ” ብለዋል። የጃፓን ከተሞች ከወንጀል የጸዱ ናቸው የሚል ዝና ሊያገኙ የቻሉት መንደርን መሠረት ያደረገ የፖሊስ አገልግሎት ስለሚሰጥ ነው።

እንዲህ ያለው የፖሊስ ሥራ በሌሎች አገሮችም ውጤታማ ሊሆን ይችል ይሆን? በወንጀል ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አንዳንድ ሰዎች ትምህርት ሊቀስሙበት ችለዋል። የዘመናዊ መገናኛ መሣሪያዎች መራቀቅ ፖሊሶችን ከሚያገለግሏቸው ሰዎች ያራቀ ይመስላል። በዛሬው ጊዜ በበርካታ ከተሞች ፖሊሶች ብቅ የሚሉት አደጋ ሲፈጠር ብቻ ነው። የፖሊስ ኃይል የተቋቋመበት ወንጀልን የመከላከል ዓላማ አንዳንዴ ቸል ሲባል ይታያል። እንዲህ ያለውን አዝማሚያ ለማስወገድ ጎረቤትን የመጠበቅ ባሕል እንደገና እንዲስፋፋ እየተደረገ ነው።

የጎረቤት ጥበቃ

ዱዊ የተባሉ የፖሊስ መኮንን በዌልስ ስላከናወኑት ሥራ ሲናገሩ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ይህ ዘዴ በእርግጥም ይሠራል፣ በእጅጉ ወንጀል ይቀንሳል። የጎረቤት ጥበቃ ሲባል ሰዎች አንዳቸው ሌላውን እንዲጠብቁ ማድረግ ማለት ነው። ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ጎረቤታሞች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ ስማቸውንና የስልክ ቁጥራቸውን እንዲለዋወጡና ወንጀልን መከላከል የሚቻልበትን መንገድ እንዲያውቁ እናደርጋለን። ይህ ፕሮጀክት በጎረቤታሞች መካከል ዳግመኛ ማህበራዊ ስሜት እንዲስፋፋ ስለሚያደርግ በጣም ያስደስተኛል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ጎረቤታቸው ማን እንደሆነ እንኳን አያውቁም። ይህ ዘዴ ውጤታማ የሆነው የሰዎችን ግንዛቤ ስለሚያሳድግ ነው።” በተጨማሪም በፖሊሶችና በሕዝብ መካከል ያለውን ዝምድና ያሻሽላል።

ሌላው እየተደረገ ያለው ጥረት ደግሞ ፖሊሶች ጥቃት ለተፈጸመባቸው ሰዎች ይበልጥ አዛኞች እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው። ጥቃት ስለተፈጸመባቸው ሰዎች ባደረጉት ምርምር የታወቁት ሆላንዳዊው ያን ቫን ዴክ “ፖሊሶች ጥቃት ለተፈጸመባቸው ሰዎች ሊያሳዩት የሚገባው ጠባይ ዶክተሮች ለበሽተኞቻቸው ከሚያሳዩት ጠባይ ባላነሰ አስፈላጊ ስለመሆኑ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል” ብለዋል። በብዙ አገሮች አሁንም ፖሊሶች አስገድዶ መድፈርንና በቤተሰብ አባል የሚፈጸም ድብደባን ከወንጀል አይቆጥሩም። ይሁን እንጂ ሮብ ሞውቢ “ፖሊሶች አስገድዶ የመድፈር ወንጀልንና በቤተሰብ አባል የሚፈጸም ድብደባን በተመለከተ የነበራቸው አመለካከት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእጅጉ ተሻሽሏል። ቢሆንም አሁንም ገና ይቀራል” ብለዋል። በሥልጣን አላግባብ በመጠቀም ረገድም የትኛውም የፖሊስ ኃይል ቢሆን ገና የሚቀረው መሻሻል አለ።

የፖሊሶች ሙስና

አንዳንድ ጊዜ በተለይ ደግሞ ፖሊሶች ስለሚፈጽሙት ሙስና በብዛት በሚወራበት ወቅት ላይ የፖሊስ ጥበቃ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ እንደ ሞኝነት ሊቆጠር ይችላል። እንዲህ ያለው ወሬ የፖሊስ ሠራዊት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲነገር የኖረ ነው። ኤን ዋይ ፒ ዲ​—⁠ኤ ሲቲ ኤንድ ኢትስ ፖሊስ የተባለው መጽሐፍ በ1855 ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “ለብዙዎቹ የኒው ዮርክ ነዋሪዎች ፖሊሶችን ከወሮበሎች መለየት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር” ይላል። በዱንካን ግሪን የተደረሰው ፌስስ ኦቭ ላቲን አሜሪካ የተባለ መጽሐፍ በላቲን አሜሪካ ያሉ ፖሊሶች “በሙስና የተዘፈቁ፣ የሙያ ብቃት የሌላቸውና ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ እንደሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል” በማለት ዘግቧል። በላቲን አሜሪካ 14, 000 አባላት የሚገኙበት የአንድ ፖሊስ ሠራዊት አስተዳዳሪ ‘በቂ ደሞዝ የማይከፈለው ፖሊስ ጉቦ ሲሰጠው ሌላ ምን እንዲያደርግ ትጠብቃላችሁ?’ ብለዋል።

ሙስና ምን ያህል ስፋት ያለው ችግር ነው? የምታገኙት መልስ እንደተጠያቂው ይለያያል። ለበርካታ ዓመታት 100, 000 የሚያክሉ ነዋሪዎች በሚገኙበት ከተማ የጥበቃ ሥራ ሲያካሂድ የኖረ አንድ የሰሜን አሜሪካ ፖሊስ “እኔ እንዳየሁት ሐቀኛ ያልሆኑ ፖሊሶች ፈጽሞ የሉም ለማለት ባይቻልም አብዛኞቹ ፖሊሶች ግን ሐቀኞች ናቸው” ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ሌላ አገር ለ26 ዓመታት የወንጀል መርማሪ ሆኖ የሠራ ፖሊስ “ሙስና የሌለበት ቦታ የለም ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር እችላለሁ። ሐቀኛ የሆኑ ፖሊሶች በጣም ጥቂት ናቸው። አንድ ፖሊስ የተዘረፈ ቤት ሲፈትሽ ገንዘብ ቢያገኝ ወደ ኪሱ መክተቱ አይቀርም። የተሰረቀ ዕቃ ቢያገኝ የተወሰነውን ለራሱ ያስቀራል” ብሏል። አንዳንድ ፖሊሶች ምግባረ ብልሹ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች ሥራውን ሲጀምሩ ከፍተኛ ሥነ ምግባር ቢኖራቸውም ውሎ ሲያድር ብልሹ የሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸውም ሆኑ በየጊዜው ሲፈጸም የሚያዩት ወንጀል በሚያሳድርባቸው ተጽእኖ ይሸነፋሉ። ኋት ካፕስ ኖው የተባለው መጽሐፍ አንድ የቺካጎ ፖሊስ የተናገረውን ጠቅሷል:- “ፖሊሶች በየቀኑ ከወንጀለኞች ጋር ስለሚገናኙ ክፋት የሕይወታቸው ክፍል ይሆናል። በዙሪያቸው የሚያዩት ነገር ሁሉ ክፋት ነው። የሚነኩት፣ የሚያሸቱት፣ የሚቀምሱትና የሚሰሙት ሁሉ ክፋት ነው።” እንዲህ ካለው ብልሹ ሁኔታ ጋር ያላቸው ንክኪ በቀላሉ መጥፎ ተጽእኖ እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል።

ፖሊሶች የሚሰጡት አገልግሎት በቀላሉ የማይገመት ይሁን እንጂ ምንም እንከን የሌለበት ነው ማለት ግን አይቻልም። አሁን ካለው የተሻለ ሁኔታ ይመጣል ብለን ተስፋ ለማድረግ እንችላለን?

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

“የብሪታንያ ፖሊሶች በጣም የሚደነቁ ናቸው!”

መደበኛ የሆነ የፖሊስ ሠራዊት በማቋቋም ረገድ ቅድሚያውን ከያዙት ሕዝቦች መካከል እንግሊዛውያን ይገኛሉ። ኅብረተሰባቸው ከሥርዓት ዝንፍ ሳይሉ የመጓጓዣ አገልግሎት ይሠጡ እንደነበሩት ሠረገሎቻቸው በሚገባ የተደራጀ እንዲሆን ማድረግ ፈለጉ። በ1829 የአገር አስተዳደር ሚንስትር የነበሩት ሰር ሮበርት (ቦቢ) ፒል የአገራቸውን ፓርላማ አስፈቅደው ዋና መሥሪያ ቤቱን ስኮትላንድ ያርድ ላይ ያደረገ የለንደን ከተማ የፖሊስ ሠራዊት እንዲቋቋም አደረጉ። ይህ ኃይል በሰካራሞችና በጎዳና ቁማርተኞች ላይ ይወስድ በነበረው ጠንካራ እርምጃ ምክንያት የተጠላ ሆኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሊሆን ቻለ።

በ1851 ለንደን መላው ዓለም ወደ ታላቁ ኤግዚቢሽን እንዲመጣና ብሪታንያ የደረሰችበትን የኢንዱስትሪ ደረጃ ተመልክቶ እንዲያደንቅ በልበ ሙሉነት ግብዣ አቀረበች። እንግዶቹ በጎዳናዎች ላይ ባዩት ሥርዓትና ሰካራሞች፣ ዝሙት አዳሪዎችና ወሮበሎች ባለመኖራቸው እጅግ ተገረሙ። ቀልጣፋ የሆኑ ፖሊሶች የጎብኚዎችን ጓዝ ይሸከሙ፣ ሰዎች መንገድ እንዲያቋርጡ ይረዱና አሮጊቶችን ደግፈው ታክሲ ያሳፍሩ ነበር። እንግሊዛውያንም ሆኑ የውጭ አገር ጎብኚዎች “የብሪታንያ ፖሊሶች በጣም የሚደነቁ ናቸው” ሲሉ መደመጣቸው የሚያስደንቅ አልነበረም።

ወንጀል በመከላከል ረገድ በጣም ውጤታማ በመሆናቸው የቼስተር ፖሊስ አዛዥ በ1873 ወንጀልን መተዳደሪያቸው ያደረጉ ሰዎች ፈጽሞ የማይኖሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለው እስከማሰብ ደርሰው ነበር። በተጨማሪም ፖሊስ የአምቡላንስና የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት ማደራጀት ጀምሮ ነበር። ለድሆች ጫማና ልብስ የሚያድል የምግባረ ሠናይ ድርጅት አቋቁሟል። አንዳንድ ፖሊሶች ደግሞ የወጣት ወንዶች ክበቦች፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችና የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ቤቶች አደራጅተዋል።

እርግጥ አዲስ የተቋቋመው የፖሊስ ኃይል ከሙስናና ከጭካኔ ድርጊት ፈጽሞ የጠራ ስላልነበረ የዲስፕሊን ችግሮች ነበሩት። ቢሆንም አብዛኞቹ ብዙ ኃይል መጠቀም ሳያስፈልጋቸው ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ችለዋል። በ1853 የዊጋን፣ ላንካሸር ፖሊሶች አድማ የመቱ የማዕድን ሠራተኞች የፈጠሩትን ሁከት ለማስቆም ተገድደው የነበረ ሲሆን አሥር ወታደሮችን ብቻ ይዞ የተሰማራው ሃምሳ አለቃ የማዕድኑ ባለቤት የሰጠውን ጠመንጃዎች ለመጠቀም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የአባቱን አርዓያ በመከተል በፖሊስነት ሙያ የተሰማራው ሄክተር ማክሊዮድ የተባለ ሰው በ1886 ደርሶት የነበረው አንድ ደብዳቤ በዘመኑ የነበረውን የፖሊሶች ዝንባሌ በግልጽ ያሳያል። ዚ ኢንግሊሽ ፖሊስ በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ይህ ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “ክፉ ከሆንክ የሕዝቡን ድጋፍና እርዳታ ታጣለህ። . . . ለጊዜውም ቢሆን እንዳገለግለው ለተመደብኩበት ማኅበረሰብ አገልጋይ በመሆኔ የሕዝቡን ፍላጎት አስቀድማለሁ። የቅርብ አዛዥህንም ሆነ ሕዝቡን ደስ የማሰኘት ኃላፊነት አለብህ።”

የለንደን ከተማ የፖሊስ መኮንን የነበሩትና ባሁኑ ጊዜ ጡረታ ላይ የሚገኙት ሄይደን እንዲህ ብለዋል:- “የፖሊስ ሥራ የሚሳካው የማኅበረሰቡን ድጋፍ ሲያገኝ ብቻ ስለሆነ ሁልጊዜ ራሳችንን መግታት እንዳለብን ተምረናል። የምንይዛትን አጭር ዱላ የምንጠቀመው ምንም ሌላ አማራጭ በምናጣበት ጊዜ ሲሆን አብዛኞቹ ፖሊሶች በሥራ በቆዩባቸው ዓመታት በሙሉ አንድ ጊዜ እንኳን አይጠቀሙበትም።” በተጨማሪም ለ21 ዓመታት በተከታታይ ሲተላለፍ የቆየውና በጥበቃ በተሰማራበት አካባቢ የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ በግል ስለሚያውቅ አንድ ሐቀኛ ፖሊስ የሚያሳየው ዲክሰን ኦቭ ዶክ ግሪን የተባለ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሕዝቡ ለብሪታንያ ፖሊሶች ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው አስተዋጽኦ አድርጓል። ፊልሙ ፖሊሶች ይህን ገጸ ባሕርይ መስለው ለመገኘት እንዲጣጣሩ አበረታቷቸው ሊሆን ይችላል። እንግሊዛውያን ፖሊሶቻቸውን እንዲወዱ እንዳደረጋቸው ግን የተረጋገጠ ነው።

በ1960ዎቹ ዓመታት የብሪታንያ ነዋሪዎች ዝንባሌ እየተለወጠ በመምጣቱ በብሔራዊ ማንነታቸው ይኮሩ የነበሩት ሰዎች ባለሥልጣናትን መጠራጠር ጀመሩ። በ1970ዎቹ ዓመታት የፖሊስ አባላት በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች አንዳቸው ሌላውን ሊጠብቁ የሚችሉበትን የአሠራር ስልት በመንደፍ የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በዘረኝነትና በሙስና የሚታሙ ፖሊሶች እየበዙ በመምጣታቸው የነበራቸውን መልካም ገጽታ እያጡ መጡ። በቅርብ ዓመታት ደግሞ ፖሊሶች ዘረኛ እንደሆኑና በወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ለማስፈረድ ሲሉ የሌለ ማስረጃ እንደሚፈጥሩ ብዙ ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ምግባራቸውን ለማሻሻል ልባዊ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ምክንያት የብሪታንያ ፖሊሶች የነበራቸውን መልካም ስምና ዝና ሙሉ በሙሉ ከማጣት ድነዋል።

[ምንጭ]

ከላይ ያለው ፎቶግራፍ:- http://www.constabulary.com

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በኒው ዮርክ የተፈጸመ እንደ ተአምር የታየ ለውጥ

ፖሊስ ልዩ ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ በጣም አስደናቂ ውጤት ይገኛል። ኒው ዮርክ በጣም አደገኛ ከሆኑ የዓለም ከተሞች መካከል መቆጠር ከጀመረች በርካታ ዓመታት አልፈዋል። በ1980ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ በከተማይቱ ውስጥ የሚፈጸመው ወንጀል ሞራሉ ከላሸቀው የኒው ዮርክ ፖሊስ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ይመስል ነበር። በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የከተማው አስተዳደር የፖሊሶችን ደመወዝ ጭማሪ ለተወሰነ ጊዜ ለማገድና ቁጥራቸውን ለመቀነስ ተገደደ። የዕፅ አዘዋዋሪዎች በዚህ ሁኔታ በመጠቀም እንቅስቃሴያቸውን በማፋፋማቸው ወንጀልና የኃይል ድርጊት ተበራከተ። የመሐል ከተማ ነዋሪዎች የተኩስ ድምፅ ሳይሰሙ የሚተኙበት ምሽት አልነበረም ማለት ይቻላል። በ1991 በዘር ልዩነት ምክንያት የተፈጠሩ ታላላቅ ረብሻዎች ከመደረጋቸውም በላይ ፖሊሶች ራሳቸው ብሶታቸውን ለማሰማት ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ አዲስ የተሾሙ የፖሊስ አዛዥ መኮንኖቻቸውን ለመቀስቀስ ፈለጉና በየጣቢያው ተገኝተው ከተራ ፖሊሶች ጋር በመወያየት ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸውን ስልቶች መንደፍ ጀመሩ። ጀምስ ላርድነርና ቶማስ ረፔቶ ኤን ዋይ ፒ ዲ (የኒው ዮርክ ፖሊስ መምሪያ) በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ያብራራሉ:- “የፖሊስ ጣቢያ አዛዦች የወንጀል መርማሪዎችን ዋና አዛዥ ወይም የአደገኛ ዕፆችና መድኃኒቶች ቁጥጥር ቢሮ ኃላፊን በጋዜጣ ላይ ካልሆነ በቀር በአካል አግኝተዋቸው አያውቁም ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ግን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለበርካታ ሰዓቶች ይወያያሉ።” የወንጀሎች ቁጥር እያሽቆለቆለ መጣ። በ1993 ወደ 2, 000 ገደማ ደርሶ የነበረው የግድያ ወንጀል እየቀነሰ መጥቶ በ1998 ወደ 633 የደረሰ ሲሆን ይህም በ35 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ዝቅተኛ ቁጥር ነው። የኒው ዮርክ ነዋሪዎች ልክ እንደ ተአምር ነበር የቆጠሩት። ባለፉት ስምንት ዓመታት ሪፖርት የሚደረጉት ወንጀሎች ቁጥር 64 በመቶ ቀንሷል።

እንዲህ ያለ መሻሻል ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በጥር 1, 2002 እትሙ የተሳካ ውጤት ሊያስገኝ የቻለው አንዱ ቁልፍ በኮምፒውተር አጋዥነት የወንጀል መረጃዎችን ማነጻጸር ነው። ይህም ኮምፕስታት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። “በዚህ ዘዴ በሳምንት ውስጥ በእያንዳንዱ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት የተደረጉ ወንጀሎች አንድ ላይ ተጠናቅረው ስለሚተነተኑ ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ ተችሏል።” የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት በርናርድ ኬርክ እንዲህ ብለዋል:- “ወንጀል የት እንደሚፈጸምና ለምን እንደሚፈጸም ከተመለከትን በኋላ በእነዚህ አካባቢዎች ይበልጥ ክትትል ለማድረግ ኃይላችንን እናሰማራለን። ወንጀልን መቀነስ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጃፓን ፖሊስ ጣቢያ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሆንግ ኮንግ ትራፊክ ፖሊስ

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእንግሊዝ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፀጥታ ማስከበር

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፖሊሶች ሥራ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳትን ይጨምራል