በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፖሊስ ጥበቃ—የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የፖሊስ ጥበቃ—የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

የፖሊስ ጥበቃ—የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ፖሊሶች ባይኖሩ ምናልባት አካባቢያችን ሥርዓት አልበኝነት የነገሠበት ይሆን ይሆናል። ይሁን እንጂ ፖሊሶች እያሉስ ቢሆን ዓለማችን ከስጋት ነጻ ልትሆን ችላለች? በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ ከተሞችም ሆነ የገጠር አካባቢዎች ስለ ደህንነታቸው የሚሰጉ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ፖሊሶች ከተደራጁ ወንጀለኞችና ከልማደኛ ወንጀለኞች ይጠብቁናል ብለን ተስፋ ልናደርግ እንችላለን? የምንዟዟርባቸውን ጎዳናዎች ከወንጀል ያጸዱልናል ብለን እምነታችንን ልንጥልባቸው እንችላለን? ከወንጀል ጋር የሚያካሂዱትን ውጊያ በአሸናፊነት ሊወጡ ይችላሉ?

ዴቪድ ቤይሊ ፖሊስ ፎር ዘ ፊውቸር በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በሰጡት አስተያየት “ፖሊሶች ወንጀልን ማስወገድ አልቻሉም” ሲሉ ከመግለጻቸውም በላይ “በእርግጥም ፖሊሶች እያመረቀዘ በሚፈነዳ ትልቅ ቁስል ላይ እንደተለጠፈ ትንሽ የቁስል ማሸጊያ ከመሆን አላለፉም። . . . ወንጀልን ለማስወገድና ኅብረተሰቡን ከወንጀል ለማዳን የተቻላቸውን ሁሉ በሚያደርጉበት ጊዜ እንኳን ሙሉ በሙሉ ልንተማመንባቸው አንችልም” ብለዋል። ሦስቱ ዋነኛ የፖሊስ እንቅስቃሴ ዘርፎች ማለትም ጎዳናዎችን እየተዘዋወሩ መቆጣጠር፣ ለድረሱልን ጥሪዎች ምላሽ መስጠትና ወንጀሎችን መመርመር ወንጀልን ሊያስወግዱ እንዳልቻሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

በጣም ብዙ ፖሊሶችን በማሰማራት ወንጀልን ለማስወገድ መሞከር ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል በመሆኑ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ወጪው ቢቻል እንኳን የፖሊሶች መብዛት ወንጀለኞችን ሊገታ አይችልም። የድረሱልኝ ጥሪ ሲደርስ ፈጥኖ ቦታው ላይ መድረስም ቢሆን ወንጀልን ለመቆጣጠር አያስችልም። ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ ላይ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ካልደረሱ ወንጀለኛውን ሊይዙ እንደማይችሉ ፖሊሶች ይናገራሉ። ፖሊስ እንዲህ ባለ ፍጥነት ሊደርስ እንደማይችል ወንጀለኞች የሚያውቁ ይመስላል። የወንጀል ምርመራዎችም ቢሆኑ ብዙ ሊያግዙ አልቻሉም። መርማሪዎች ወንጀለኞችን አሳድደው ሊያገኙና ፍርድ ቤት አቅርበው ሊያሳስሩ ቢችሉም ይህን ማድረጋቸው ወንጀልን አያስወግድም። የዩናይትድ ስቴትስን ያህል ብዙ ወንጀለኞች የሚታሰሩበት አገር የለም። የወንጀሉ ብዛት ግን በፍጹም ሊቀንስ አልቻለም። በአንጻሩ ግን በጣም አነስተኛ እስረኞች ባሉባት በጃፓን የወንጀሉ መጠን ዝቅተኛ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ጓዶችን እንደማሰማራት ያሉት እቅዶችም ቢሆኑ በተለይ ወንጀል በሚበዛባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ውጤት ሊያስገኙ አልቻሉም። ዕፆችን እንደማዘዋወርና እንደ ዝርፊያ ያሉትን የተለዩ ወንጀሎች ለማስወገድ የሚደረጉ ዘመቻዎች ለጥቂት ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ሊያስገኙ ቢችሉም ይህን ዓይነቱን ዘመቻ በዘላቂነት ለማካሄድ ስለማይቻል የተገኘው ውጤት ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ይሆናል።

“ፖሊሶች ወንጀልን ሊያስወግዱ አለመቻላቸው አስተዋይ የሆኑ ሰዎችን በጣም ሊያስገርማቸው አይችልም” ይላል ፖሊስ ፎር ዘ ፊውቸር የተባለው መጽሐፍ። “በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጸመውን ወንጀል መጠን የሚወስኑት ከፖሊሶችም ሆነ ከአጠቃላዩ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ማኅበራዊ ሁኔታዎች እንደሆኑ ይታመናል።”

ፖሊሶች ባይኖሩ ኖሮ ምን ሁኔታ ይፈጠር ነበር?

የሚያይህ ፖሊስ በማይኖርበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሕገወጥ ድርጊት ትፈጽማለህ? ጨዋ ናቸው የሚባሉ በመካከለኛና በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በማጭበርበር ለሚገኝ ጥቅም ሲሉ መልካም ስማቸውንና የወደፊት ኑሯቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ይፈጽማሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡ ‘የመኪና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አጭበርብረዋል የሚል ክስ ስለቀረበባቸው 112 ሰዎች’ ዘግቧል። ‘ከተከሰሱት ሰዎች መካከል የሕግ ባለሞያዎች፣ የሕክምና ዶክተሮች፣ አንድ ወጌሻ፣ አንዲት የደረቅ መርፌ ሐኪምና አንዲት የፖሊስ መምሪያ ረዳት አስተዳዳሪ ይገኛሉ።’

የሥነ ጥበቡን ዓለም በገንዘባቸው የሚደግፉ ከበርቴዎች በቅርቡ በተፈጸመ አንድ ከባድ የማጭበርበር ድርጊት ተደናግጠዋል። በኒው ዮርክ የሚገኘው የሶትቢ እና በለንደን የሚገኘው የክርስቲ የጨረታ ሽያጭ ተቋማት የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ሕገወጥ በሆነ መንገድ የጨረታ ዋጋ እንዲወሰን አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። በመሆኑም እነዚህ አስተዳዳሪዎችና የጨረታ ሽያጭ ድርጅቶቻቸው 843 ሚልዮን ዶላር ቅጣትና ካሣ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል። ስለዚህ ገንዘብ የማጋበስ ጥማት ያልተጠናወተው የኅብረተሰብ ክፍል የለም።

በ1997 በሬሲፍ፣ ብራዚል ፖሊሶች የሥራ ማቆም አድማ ባደረጉ ጊዜ የደረሰው ሁኔታ ብዙ ሰዎች የሚቆጣጠራቸው ካልኖረ በወንጀል ድርጊት መሰማራታቸው እንደማይቀር አረጋግጧል። ሃይማኖታዊ እምነታቸው በጠባያቸው ላይ የሚያስከተለው ውጤት የለም። መልካም ሥነ ምግባርንና ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በቀላሉ ሊበርዙ ወይም አሽቀንጥረው ሊጥሉ ይችላሉ። የብዙ አገር ፖሊሶች ከባድ ሆነ ቀላል ወንጀል መፈጸም በሚቀናው ዓለም ውስጥ ከወንጀል ጋር በሚያደርጉት ውጊያ አሸናፊ መሆን አለመቻላቸው የሚያስደንቅ አይደለም።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ለሕግ የሚታዘዙት ባለሥልጣኖችን ስለሚያከብሩ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች ቢያንስ በኅብረተሰቡ ውስጥ መጠነኛ ሥርዓት እንዲሰፍን ስለሚያደርጉ አምላክ እንዲኖሩ ለፈቀደላቸው ባለሥልጣኖች መገዛት እንደሚኖርባቸው ተናግሯል። ስለ እነዚህ ባለሥልጣኖች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ስለዚህ ስለ ቊጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው።”​—⁠ሮሜ 13:​4, 5

ማኅበራዊ ሁኔታዎችን መለወጥ

የፖሊሶች ሥራ በማኅበራዊ ሁኔታዎች ላይ የሚያመጣው ጥሩ ውጤት እንዳለ አይካድም። ጎዳናዎች ሕገ ወጥ ከሆነ የዕፅ ዝውውርና ከኃይል ድርጊቶች ሲጸዱ ሰዎች የአካባቢያቸውን ስምና ዝና ጠብቀው ለመኖር ይጣጣራሉ። ይሁን እንጂ የአንድን ኅብረተሰብ ባሕርይ መቀየር በፖሊሶች አቅም ሊፈጸም የሚችል ነገር አይደለም።

እያንዳንዱ ሰው ለሕግ ካለው ከፍተኛ አክብሮት የተነሳ የፖሊስ ጥበቃ አስፈላጊ የማይሆንበት ኅብረተሰብ ይኖራል ብለህ ለመገመት ትችላለህ? ሰዎች በጣም የሚተሳሰቡ ከመሆናቸው የተነሳ ጎረቤታሞች እርስ በርሳቸው ስለሚረዳዱ የፖሊስ እርዳታ መጠየቅ አስፈላጊ የማይሆንበት ዓለም ይኖራል ብለህ ለማሰብ ትችላለህ? ይህ ሊሆን የማይችል ቅዠት ሆኖ ይታይህ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ከሌላ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተነገሩ ይሁኑ እንጂ በዚህ ረገድ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 19:​26

መጽሐፍ ቅዱስ መላው የሰው ዘር ይሖዋ አምላክ ለሚያቋቁመው መንግሥት ተገዥ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። “የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ያስነሣል፤ . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች።” (ዳንኤል 2:​44) ይህ አዲስ መንግሥት ቅን ለሆኑ ሰዎች በሙሉ የአምላክን የፍቅር መንገድ በማስተማር ለወንጀል ማቆጥቆጥ ምክንያት የሚሆኑትን ማኅበራዊ ሁኔታዎች ያስወግዳል። “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:​9) ይሖዋ የሾመው ንጉሥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም ወንጀል ማስወገድ ይችላል። “ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤ ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል።”​—⁠ኢሳይያስ 11:​3, 4

በዚያን ጊዜ ወንጀለኞችም ሆኑ ወንጀል ስለማይኖር ፖሊስ አያስፈልግም። ሁሉ ሰው “እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም” አይኖርም። (ሚክያስ 4:​4) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተገለጸው “አዲስ ምድር” ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ አምላክ በቃሉ ውስጥ የሰጠውን ተስፋ የምትመረምርበት ጊዜ አሁን ነው።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እያንዳንዱ ሰው ለሕግ ካለው ከፍተኛ አክብሮት የተነሳ የፖሊስ ጥበቃ አስፈላጊ የማይሆንበት ኅብረተሰብ ይኖራል ብለህ ለመገመት ትችላለህ?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወንጀለኞችም ሆኑ ወንጀል አይኖርም

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፖሊስና አሸባሪዎች

መስከረም 11 ቀን 2001 በኒው ዮርክና በዋሽንግተን ዲሲ ከተሞች ላይ በደረሰው ሁኔታ እንደታየው የአውሮፕላን ጠላፊዎችን፣ የአጋቾችንና የአሸባሪዎችን ያህል ፖሊሶች የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አስቸጋሪ የሚያደርግ ሁኔታ የለም። በብዙ የዓለም ክፍሎች የቆሙ አውሮፕላኖችን በድንገት በርግደው ገብተው አሸባሪዎችን በቁጥጥር ሥር የሚያደርጉ ልዩ ጓዶች ሰልጥነዋል። በተጨማሪም እነዚህ ጓዶች በሕንጻዎች ጣሪያ በኩል በገመድ ተንጠልጥለው የመግባት፣ በመስኮት ዘልሎ የመግባት፣ በንዝረት ብቻ አሸባሪዎችን አደንዝዞ የሚጥል ፈንጂ የመወርወር፣ አስለቃሽ ጭሶችን የመጠቀም ሥልጠና ስለተሰጣቸው በድንገት ገብተው በቁጥጥር ሥር የማድረግ ችሎታ አላቸው። እንደነዚህ ያሉትን ሥልጠናዎች ያገኙ ፖሊሶች በአብዛኛው በታጋቾች ላይ ብዙ ጉዳት ሳይደርስ አሸባሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ችለዋል።

[ምንጭ]

James R. Tourtellotte/U.S. Customs Service

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የማይፈለጉ ነገሮች