ፖሊሶች—አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
ፖሊሶች—አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
ፖሊሶች ባይኖሩ ኖሮ ኑሯችን እንዴት ያለ ይሆን ነበር? በ1997 ሬሲፍ በተባለችው የብራዚል ከተማ 18, 000 የሚያክሉት የከተማይቱ ፖሊሶች የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች የፖሊስ ጥበቃ ባጡበት ጊዜ ምን ሆነ?
“በባሕር ዳርቻ በምትገኘው በዚህች ሞቅ ያለች ከተማ ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖባቸው በነበሩት አምስት ቀኖች ውስጥ በየቀኑ ነፍስ ግድያ የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ አድጓል” በማለት ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። “ስምንት ባንኮች ተዘርፈዋል። ወሮበሎች ትላልቅ የገበያ አዳራሾችንና ሀብታሞች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ወርረው ጠመንጃ እየተኮሱ ከፍተኛ ዘረፋ ፈጽመዋል። የትራፊክ ሕጎችን የሚያከብር ሰው አልነበረም። . . . በዚህ የወንጀል ማዕበል የተገደሉ ሰዎች በጣም ብዙ በመሆናቸው የአስከሬን ማቆያ ቦታዎች ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልተዋል። የከተማው ትልቅ ሆስፒታል በጥይትና በጩቤ በቆሰሉ ሰዎች በመሞላቱ በሆስፒታሉ መተላለፊያዎች ሳይቀር ቁስለኞች ተኝተው ነበር።” የፍትሕ ሚንስትሩ “በዚህ ከተማ ይህን የመሰለ ሕገወጥነት ፈጽሞ ታይቶ አያውቅም” ብለዋል።
የትም እንኑር የት፣ ክፋት በሥልጣኔ መጋረጃ በመሸፈኑ የሌለ መስሎ ይታይ እንጂ በጣም ተስፋፍቷል። የፖሊሶች ጥበቃ የግድ ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን አንዳንድ ፖሊሶች ስለሚፈጽሙት ጭካኔና የሥልጣን ብልግና እንዲሁም ስለሚታይባቸው ግድየለሽነት ሰምተናል። መጠኑ ከአገር ወደ አገር ይለያይ ይሆናል። ይሁን እንጂ አለፖሊሶች እንዴት መኖር ይቻላል? ፖሊሶች ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት እንደሚሰጡ መካድ ይቻላል? ንቁ! መጽሔት በተለያዩ አገሮች ለሚኖሩ አንዳንድ ፖሊሶች ለምን የፖሊስነት ሙያ እንደመረጡ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ለማኅበረሰቡ ደህንነት የሚጠቅም ሙያ
የብሪታንያ ፖሊስ የሆነው ኢቫን እንዲህ ይላል:- “ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል። ወደ ሙያው የሳበኝ ፖሊሶች የሚያጋጥማቸው የሥራ ዓይነት የተለያየ መሆኑ ነው። ወንጀል መከላከል ከፖሊስ ዕለታዊ ተግባር ከ20 እስከ 30 በመቶ እንደማይበልጥ ብዙ ሰው አያውቅም። በአብዛኛው የፖሊስ ሥራ ማኅበረሰቡን ማገልገል ነው። ሮንድ በምዞርበት ቀን በድንገት የሞተ ሰው፣ የትራፊክ አደጋ፣ ወንጀል ወይም ችግር ላይ የወደቁ አረጋዊ ያጋጥሙኛል። በተለይ የጠፋ ልጅ አግኝቶ ወደ ወላጆቹ መመለስ ወይም ወንጀል የተፈጸመበትን ሰው ማረጋጋትና ማጽናናት በጣም ያስደስተኛል።”
ስቲቨን በዩናይትድ ስቴትስ በፖሊስነት ያገለገለ ሰው ነው። እንዲህ ይላል:- “ተጨንቀው እርዳታ ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ስታገኝ ፖሊስ በመሆንህ ካንተ የተሻለ ሊረዳቸው የሚችል ሰው አይኖርም። ወደዚህ ሙያ የሳበኝ ይህ ነበር። ሰዎችን መርዳትና ሸክማቸውን መሸከም እፈልግ ነበር። በትንሹም ቢሆን ሰዎችን ከወንጀል ለመጠበቅ እንደቻልኩ ሆኖ ይሰማኛል። በአምስት ዓመት ውስጥ ከ1, 000 የሚበልጡ ሰዎችን አስሬያለሁ። ይሁን እንጂ የጠፉ ሕፃናትን ለማግኘት፣ በአልዛይመርስ በሽታ ምክንያት ቤታቸው ጠፍቶባቸው የባዘኑ አረጋውያንን ለመርዳት፣ እንዲሁም የተሰረቁ መኪናዎችን አግኝቼ ለባለቤቶቹ ለመመለስ መቻሌ በይበልጥ አርክቶኛል። በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን አድኖ መያዝም የራሱ የሆነ እርካታ አለው።”
የቦሊቪያ ፖሊስ የሆነው ሮቤርቶ ደግሞ እንደሚከተለው ይላል:- “ድንገተኛ አደጋ የገጠማቸውን ሰዎች መርዳት እፈልግ ነበር። ወጣት ሳለሁ ፖሊሶች ሰዎችን ከአደጋ ስለሚጠብቁ አደንቃቸው ነበር። ገና እንደተቀጠርኩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚገኙበት የከተማው ክፍል ሮንድ እንድዞር ተመደብኩ። በየቀኑ ለማለት ይቻላል፣ የፖለቲካ ሰላማዊ ሰልፍ ያጋጥመን ነበር። የኔ ሥራ አምባጓሮ እንዳይፈጠር መከላከል ነበር። የሰላማዊ ሰልፉን መሪዎች በወዳጅነትና በምክንያታዊነት ከቀረብኩ አምባጓሮ ተነስቶ በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ እንደምችል ተገንዝቤያለሁ። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው።”
ፖሊሶች የሚያከናውኑት ሥራ ብዙ ዓይነት ነው። ዛፍ ላይ የተንጠለጠለችን ድመት ከማዳን አንስቶ በአሸባሪዎች የታገቱ ሰዎችን እንደማስለቀቅና የባንክ ዘራፊዎችን በቁጥጥር ሥር እንደማዋል ያሉ በርካታ ሥራዎችን ይሠራሉ። ይሁን እንጂ ዘመናዊው የፖሊስ ሠራዊት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ፖሊሶች የሚፈሩም፣ ተስፋ የሚጣልባቸውም ሆነው ቆይተዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት የሚቀጥለው ርዕስ ያብራራል።
[በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ገጽ 2 እና 3:- በቼንግዱ፣ ቻይና ትራፊክ ማስተናበር፤ የግሪክ ረብሻ በታኝ ፖሊስ፤ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች
[ምንጭ]
Linda Enger/Index Stock Photography
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሐምሌ ወር 2001 በብራዚል ሳልቫዶር ፖሊሶች የሥራ ማቆም አድማ ባደረጉ ጊዜ የተዘረፈ ሱቅ
[ምንጭ]
Manu Dias/Agência A Tarde
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስቲቨን፣ ዩ ኤስ ኤ
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮቤርቶ፣ ቦሊቪያ