በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁማር መጫወት ምን ስህተት አለው?

ቁማር መጫወት ምን ስህተት አለው?

ቁማር መጫወት ምን ስህተት አለው?

“ወደ 290, 000 የሚጠጉ አውስትራሊያውያን ልማደኛ ቁማርተኞች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች የሚያደርሱት የገንዘብ ኪሣራ በዓመት ከ3 ቢልዮን ዶላር ይበልጣል። ይህም በልማደኞቹ ቁማርተኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምክንያት በሚደርሰው የገንዘብ ኪሣራ፣ ፍቺ፣ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትና ከሥራ የመቅረት ልማድ ሳቢያ ጉዳት በሚደርስባቸው 1.5 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ላይም ከባድ ችግር ያስከትላል።”— ጄ ሐዋርድ፣ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚንስትር፣ 1999

ቀደም ባለው ርዕስ ተጠቅሶ የነበረው ጆን ልማደኛ ቁማርተኛ ሆነ። * ወደ አውስትራሊያ ከሄደ በኋላ ሊንዳን ያገባ ሲሆን እሷም ቁማርተኛ ነበረች። ጆን የቁማር ሱሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መጣ። “ሎተሪ ከመግዛት አልፌ በፈረስ ግልቢያ መወዳደሪያ ቦታዎች እስከ መወራረድና በካዚኖዎች ቁማር እስከ መጫወት ደረስኩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በየቀኑ ቁማር መጫወት ጀመርኩ። ሙሉ ደመወዜን በቁማር ተበልቼ ቤተሰቤን የማበላው ወይም የቤቴን ዕዳ የምከፍልበት ገንዘብ የማጣበት ጊዜ ነበር። አሸንፌ ብዙ ገንዘብ በማገኝበት ጊዜ እንኳን ቁማር መጫወቴን አላቆምም። እስረኛ አድርጎ የያዘኝ ማሸነፍ የሚያስገኘው ደስታ ነበር” ይላል።

እንደ ጆን ያሉ ግለሰቦች በጣም ብዙ ናቸው። መላው ኅብረተሰብ በቁማር በሽታ የተለከፈ ይመስላል። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው መጽሔት ከ1976 እስከ 1997 ባሉት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ሕጋዊ በሆኑ ቁማሮች ውርርድ የተደረገበት ገንዘብ መጠን 3, 200 በመቶ አድጓል ብሏል።

ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው የካናዳ ጋዜጣ “ሥነ ምግባራዊም ሆነ ማኅበራዊ ተቀባይነት አጥቶ የኖረው የቁማር ጨዋታ ዛሬ ተቀባይነት ያገኘ የጊዜ ማሳለፊያ ሆኗል” ይላል። ይኸው ጋዜጣ ይህንን የመሰለ የአመለካከት ለውጥ ሊኖር የቻለበትን ምክንያት ሲያመለክት “ሰዎች አመለካከታቸው ሊለወጥ የቻለው መንግሥት በካናዳ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለረጅም ጊዜ ባካሄደው የሎተሪ ሽያጭ የማስታወቂያ ዘመቻ ምክንያት ነው” ይላል። ቁማርን ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ላይ እንዴት ያለ ውጤት አስከትሏል?

የልማደኛ ቁማርተኝነት ወረርሽኝ

የሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የሱሰኝነት ጥናት መምሪያ በሰጠው ግምታዊ መረጃ መሠረት በ1996 “በአሜሪካ 7.5 ሚልዮን የሚያክሉ ለአካለ መጠን የደረሱ ልማደኛና ሱሰኛ ቁማርተኞች” ነበሩ። ከነዚህ በተጨማሪ “7.9 ሚልዮን የሚደርሱ አሜሪካውያን ጎረምሶች ልማደኛና ሱሰኛ ቁማርተኞች ናቸው።” እነዚህ አኃዞች የአገሪቱ ብሔራዊ የቁማር ጠንቅ ጥናት ኮሚሽን (ኤን ጂ አይ ኤስ ሲ) ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ የተካተቱ ናቸው። ሪፖርቱ የቁማርተኝነት ልማድ ያለባቸው አሜሪካውያን ቁጥር በዘገባው ላይ ከሠፈረው በእጅጉ ሊበልጥ እንደሚችል አክሎ ገልጿል።

በቁማር ልማደኝነት ምክንያት የሚደርሰው ሥራ ማጣት፣ የጤና እክል፣ ለሥራ አጦች የሚከፈል ድጎማና ለሕክምና የሚወጣው ወጪ በአሜሪካ ኅብረተሰብ ላይ በየዓመቱ በቢልዮን ዶላር የሚገመት ኪሣራ ያስከትላል። ይሁን እንጂ ይህ አኃዝ በልማደኛ ቁማርተኝነት ምክንያት በሚፈጸመው ስርቆት፣ ዝርፊያ፣ ራስን መግደል፣ የኃይል ድርጊትና የልጆች ሥቃይ በሚጎዱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና የሥራ ባልደረቦች ላይ የሚደርሰውን በደልና ሥቃይ አያካትትም። አንድ በአውስትራሊያ የተደረገ ጥናት በአንድ ልማደኛ ቁማርተኛ ምክንያት እስከ አሥር የሚደርሱ ሰዎች ቀጥተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል አረጋግጧል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የምርምር ጉባኤ ያወጣው አንድ ሪፖርት “50 በመቶ የሚያክሉ ባለ ትዳሮችና 10 በመቶ የሚያክሉ ልጆች የቁማር ሱሰኛ በሆነው የትዳር ጓደኛቸው ወይም ወላጃቸው አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” ይላል።

ተላላፊ ሱስ

ልማደኛ ቁማርተኝነት እንደ አንዳንድ በሽታዎች ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ ይመስላል። ኤን ጂ አይ ኤስ ሲ ያወጣው ሪፖርት “የቁማር ሱሰኛ የሆኑ ወላጆች ያሏቸው ልጆች እንደ ማጨስ፣ መጠጣትና አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች መውሰድ ላሉ መጥፎ ድርጊቶች በእጅጉ የተጋለጡ ሲሆን ልማደኛ ቁማርተኛ ወይም የቁማር ሱሰኛ የመሆን ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው” ይላል። በተጨማሪም ይኸው ሪፖርት “ለአካለ መጠን ከደረሱ ቁማርተኞች ይልቅ በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ቁማርተኞች ወደ ልማደኛ ቁማርተኛነት ወይም ወደ ቁማር ሱሰኝነት ደረጃ የመድረስ ዕድላቸው የሰፋ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል።

የሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የሱሰኝነት ጥናት መምሪያ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሃዋርድ ጄ ሻፈር “ወጣቶች የሚጫወቷቸው ሕገወጥ ቁማሮች ሕጋዊ ከሆኑ ቁማሮች ባልተናነሰ መጠን እየተስፋፉ እንደመጡ የሚጠቁሙ መረጃዎች እየተበራከቱ ነው” ብለዋል። የቁማር ሱሰኞች በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ከአግባብ ውጭ ሊጠቀሙ ስለመቻላቸው ሲናገሩ “ክራክ ኮኬይን ማጨስ የኮኬይንን ጣዕም ጨርሶ ሊለውጥ እንደቻለ ሁሉ ኤሌክትሮኒክስም በቁማር አጨዋወት ላይ ትልቅ ለውጥ ሳያመጣ አይቀርም” ብለዋል።

የቁማር ኢንዱስትሪ ማንንም የማይጎዳ ጨዋታ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይነገራል። ይሁን እንጂ ቁማር በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ከማንኛውም ሕገ ወጥ ዕፅ በማይተናነስ ሁኔታ ሱሰኛ ሊያደርጋቸው የሚችል ከመሆኑም በላይ ወደ ወንጀለኝነት ሊመራ ይችላል። በእንግሊዝ አገር የተደረገ አንድ ጥናት ቁማር ከሚጫወቱ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች መካከል ‘46 በመቶ የሚሆኑት ሱሳቸውን ለማርካት ሲሉ ከቤተሰቦቻቸው እንደሚሠርቁ’ አረጋግጧል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንድ ተደማጭነት ያለው የቁማር ማኅበር “ቁማር ከሚጫወቱ አሜሪካውያን መካከል አብዛኞቹ ምንም ዓይነት ችግር ውስጥ አይወድቁም” በማለት ቁማር ሊስፋፋ የሚገባ መሆኑን ለማሳመን ሞክሯል። ቁማር በገንዘብም ሆነ በጤና ረገድ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስብህ ቢሰማህ እንኳ በመንፈሳዊ ጤንነትህ ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል? ከቁማር የምትርቅበት በቂ ምክንያት ይኖራል? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኘውን “የቁማር ሱስ አለብኝን?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የቁማር ሱስ አለብኝን?

የአሜሪካ የሥነ አእምሮ ሕክምና ማኅበር ባወጣው መረጃ መሠረት አንድ ሰው በገጽ 23 ላይ በሚገኙት በሚከተሉት መመዘኛዎች በመጠቀም በቁማርተኝነት ሱስ መለከፍና አለመለከፉን ማወቅ ይችላል። ከመመዘኛዎቹ መካከል በርካታዎቹ የሚታዩብህ ከሆነ ልማደኛ ቁማርተኛ እንደሆንክ፣ አንዳቸው እንኳን የሚታዩብህ ከሆነ ደግሞ ልማደኛ ቁማርተኛ የመሆን ዕድልህ ከፍተኛ እንደሆነ እንደሚያመለክት ብዙ ሊቃውንት ይስማማሉ።

መጠመድ ቁማር የተጫወትክበትን ጊዜ፣ ልትጫወት ያሰብክበትን ቦታ ወይም የምትጫወትበት ገንዘብ የምታገኝበትን መንገድ ብዙ ጊዜ ታስባለህ።

በቃኝ አለማለት ከአሁን አሁን አገኛለሁ በሚል ስሜት የምታስይዘውን ገንዘብ ለመጨመር ትገፋፋለህ።

ለመላቀቅ መሞከር ቁማር መጫወት ለመቀነስ ወይም ለማቆም በምትሞክርበት ጊዜ የመበሳጨት ወይም የመቅበጥበጥ ስሜት ይሰማሃል።

ማምለጫ ቁማር የምትጫወተው ከችግር ለመሸሽ ወይም ተስፋ የመቁረጥ፣ የበደለኝነት፣ የሥጋት ወይም የጭንቀት ስሜት እንዳይሰማህ ብለህ ነው።

ማሳደድ በቁማር ገንዘብ ከተበላህ በኋላ የተበላኸውን ገንዘብ ለማስመለስ ሌላ ጊዜ ትመለሳለህ።

መዋሸት የቁማር አመልህ ምን ያህል የከፋ መሆኑ እንዳይታወቅብህ ስትል ለቤተሰቦችህ፣ ለሐኪሞችህ ወይም ለሌሎች ትዋሻለህ።

ለመቆጣጠር አለመቻል ቁማር መጫወትህን ለማቆም፣ ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ በተደጋጋሚ ሞክረህ አልሆነልህም።

ሕገወጥ ድርጊቶች ቁማር መጫወቻ ገንዘብ ለማግኘት እንደ ማጭበርበር፣ ሥርቆት ወይም ዘረፋ የመሰለ ድርጊት ፈጽመሃል።

የሚያስከትለው መዘዝ ቁማር ትልቅ ግምት ከምትሰጣቸው ሰዎች፣ ከትምህርት ወይም ከሥራ ሊያቆራርጥህ ይችላል።

ዕዳ መግባት በቁማር ምክንያት ከባድ ኪሣራ ደርሶብህ ዕዳህን ሌሎች እንዲከፍሉልህ ለመጠየቅ ተገድደሃል።

[ምንጭ]

ምንጭ:- National Opinion Research Center at the University of Chicago, Gemini Research, and The Lewin Group.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሎተሪ ማስታወቂያዎች የሚያስተላልፉት መልእክት

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው ዱክ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች ለብሔራዊው የቁማር ጠንቅ ጥናት ኮሚሽን ባቀረቡት ሪፖርት “ቁማር ማስተዋወቅ . . . ትክክለኛ እሴቶችን እንደ ማስተማር ተደርጎ ሊታይ ይችል ይሆናል። ቁማር ብዙም ጉዳት የማያስከትል፣ እንዲያውም እንደ ጥሩ ድርጊት ሊታይ የሚገባ ነገር እንደሆነ ያስተምራል” ሲሉ ገልጸዋል። ሎተሪ ማስተዋወቅ በአንድ ማኅበረሰብ ላይ ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል ይችላል? ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “የሎተሪ ማስታወቂያዎች የሚያስተላልፉት መልእክት መጥፎ ጠንቅ የሚያስከትል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የተሳካ ውጤት ማግኘት ትክክለኛ ቁጥር በመምረጥ ላይ የተመካ ነው ብለው ያስተምራሉ። ይህ ዓይነቱ የሎተሪ ድርጅቶች አጉል ‘ትምህርት’ በረዥም ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እንዲጓተት በማድረግ የመንግሥት ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል። በተለይ የሎተሪ ማስታወቂያ፣ ሰዎች የሥራ፣ የቆጣቢነትና ራስን በትምህርትና በሥልጠና የማሻሻል አስፈላጊነት እንዳይታያቸው የሚያደርግ ከሆነ ውሎ አድሮ ምርታማነት እንዲዳከም ማድረጉ አይቀርም። ያም ሆነ ይህ፣ ተአምር ይመጣል ብሎ መጠበቅ ለልጆቻችን ልናስተምረው የሚገባ አመለካከት አይደለም።”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሁሉም ቤት ካዚኖ ሊሆን ነው

ቁማር አጫዋች ድርጅቶች አዲስ የቁማር ማጫወቻ ድርጅት ለማቋቋም ከሚጠይቀው ገንዘብ በጣም ባነሰ ወጪ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ ኮምፒውተር ያለበትን ቤት ሁሉ የካዚኖ መጫወቻ ሊያደርግ የሚችል የዌብ ገጽ ሊያዘጋጁ ይችላሉ። በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ቁማር የሚያጫውቱ የኢንተርኔት ገጾች ከ25 አይበልጡም ነበር። በ2001 ገጾቹ 1, 200 የደረሱ ሲሆን በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚካሄድ ቁማር የሚገኘው ገቢ በየዓመቱ በእጥፍ እያደገ መጥቷል። በ1997 ቁማር አጫዋች የዌብ ገጾች 300 ሚልዮን ዶላር አስገብተዋል። በ1998 ያስገኙት ገቢ 650 ሚልዮን ዶላር ደርሷል። በ2000 ደግሞ 2.2 ቢልዮን ዶላር ያስገቡ ሲሆን በ2003 ይህ አኃዝ “ወደ 6.4 ቢልዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል” ይላል የሮይተርስ ዜና ዘገባ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልማደኛ ቁማርተኛ መሆን የሚላስ የሚቀመስ እስከ ማጣት ያደርሳል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቁማርተኛ ወጣቶች ቁጥር በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

$10, 000, 000

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቁማር ሱስ የተለከፉ ወላጆች ያሏቸው ልጆች ራሳቸው ልማደኛ ቁማርተኞች የመሆን አጋጣሚያቸው በጣም ከፍተኛ ነው