በቁማር ወጥመድ ላለመያዝ መጠንቀቅ
በቁማር ወጥመድ ላለመያዝ መጠንቀቅ
“ቁማር በአካላዊ ጤንነቴ ላይ ያደረሰብኝ ጉዳት የለም። በቁማር የማጠፋውንም ገንዘብ መቆጣጠር ተስኖኝ አያውቅም። ይሁን እንጂ የሎተሪ ጨዋታ በምጫወትበት ጊዜ ሁሉ ገዴ ነው የምለውን ቁጥር እንደምመርጥ ልክድ አልችልም።”— ሊንዳ
ብዙ ቁማርተኞች ገዳቸው ወይም ዕጣ ክፍላቸው የሆነ ቁጥር እንዳለ ያምናሉ። ለዚህ እምነታቸው ትልቅ ቦታ እንደማይሰጡት ይሰማቸው እንጂ በቀላሉ የሚላቀቁት እምነት አይደለም።
እንዲያውም አንዳንድ ቁማርተኞች በሚጫወቱት የቁማር ጨዋታ እንዲያሸንፉ አምላክ እንዲረዳቸው ይጸልያሉ። ይሁን እንጂ አምላክ እርሱን እናመልካለን እያሉ “እድል ለተባለ ጣዖት የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን” የሚያቀርቡትን እንደሚያወግዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 65:11) አምላክ አጉል በሆነ የዕድል እምነት ላይ የተመሠረቱ ድርጊቶችን ይጸየፋል። ቁማር በባሕርዩ በዕድል ማመንን ያበረታታል።
በተጨማሪም ቁማር ሰዎች ይሉኝታ ቢስ በሆነ መንገድ ገንዘብ ወዳዶች እንዲሆኑ ያደርጋል። በዚህ እያደር ይበልጥ ሥጋዊ አስተሳሰብ እየተጠናወተው በመጣ ኅብረተሰብ ውስጥ ገንዘብ የአምላክነት ቦታ ሲሰጠው ቁማር ደግሞ የተለመደ የአምልኮ ማከናወኛ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ትላልቅ የቁማር ቤቶች እንደ አምልኮ ቦታዎች ሆነዋል ማለት ይቻላል። በእነዚህ ቦታዎች የሚንጸባረቀው መሠረታዊ እምነት ደግሞ ስግብግብነት ጥሩ ነው የሚል ሆኗል። የቁማር መጫወቻ ቦታዎችን ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ቁማር የሚጫወቱት ለመዝናናት 1 ጢሞቴዎስ 6:10
ብለው ወይም በመጫወቻ ቦታዎች ያለውን መንፈስ ስለሚወዱ ሳይሆን “ብዙ ገንዘብ” ለማግኘት ሲሉ እንደሆነ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት ያስጠነቅቃል።—መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ “አትሳቱ፣ . . . ጣዖትን የሚያመልኩ . . . ወይም ገንዘብን የሚመኙ [“ስግብግቦች፣” አ.መ.ት ] . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት በግልጽ ይናገራል። ስግብግብነት መጥፎ ማኅበራዊ በሽታ ብቻ ሳይሆን ለሞት የሚዳርግ መንፈሳዊ በሽታ ጭምር ነው። ይሁን እንጂ ፈውስ የማይገኝለት በሽታ አይደለም።
ለመለወጥ የሚያስችል አቅም አግኝተዋል
በመግቢያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ካዙሺጌ “ቁማር መጫወቴን ለማቆም ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር” ይላል። “በፈረስ መጋለቢያ ቦታዎች ከጓደኞቼ ጋር የምጫወተው ቁማር ቤተሰቤን እየጎዳብኝ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ያሸነፍኩትን ገንዘብ በሙሉ እዚያው መልሼ አስረክቤ እገባ ነበር። ሚስቴ ሁለተኛው ልጃችን ሲወለድ ለሚያስፈልገው ወጪ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ሳይቀር ቁማር ተጫውቼበት ተበልቻለሁ። በመጨረሻም በምሠራበት ኩባንያ ገንዘብ መጫወት ጀመርኩ። በዚህ ምክንያት ራሴን ፈጽሞ ጠላሁ። ሚስቴ ብዙ ጊዜ ቁማር መጫወት እንዳቆም እያለቀሰች ለምናኛለች። እኔ ግን መተው አልቻልኩም።”
በኋላ ግን ካዙሺጌ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። እንዲህ ይላል:- “መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብኩ መጠን በእርግጥ አምላክ እንዳለና እርሱንም ብሰማ እንደምጠቀም በይበልጥ እርግጠኛ መሆን ጀመርኩ። አምላክ በሚሰጠኝ ኃይል ቁማር መጫወቴን አቆማለሁ ብዬ ቆረጥኩ። ማቆም ብቻ ሳይሆን የቁማር ጨዋታን እስከ መጥላት መድረሴ በጣም አስደንቆኛል። አሁን ቁማር መጫወቴ በቤተሰቤ ላይ ያደርስ የነበረውን ችግር ሳስታውስ በጣም ያሳዝነኛል። ይሖዋ አምላክ ከነበረብኝ የቁማር ሱስ አላቅቆ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።”—ዕብራውያን 4:12
በመግቢያው ርዕስ ላይ ተጠቅሶ የነበረው ጆንም በተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴ ያለሁበትን ሁኔታ እንዳገናዝብ ረድቶኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ ዓይኖቼ ተከፍተው ቁማርተኝነቴ በራሴና በቤተሰቤ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማየት ቻልኩ። ቁማር ሰዎች የራስ ወዳድነትና የመስገብገብ ባሕርይ እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ ተገነዘብኩ። እነዚህ ሁሉ ይሖዋ የሚጠላቸው ባሕርያት ናቸው። ጥናቴን በቀጠልኩ መጠን ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ከቁማር እንድላቀቅ የሚያስችል ብርታት ሰጠኝ። ቁማር መጫወት የጀመርኩት የተሻለ ሕይወት አገኛለሁ ብዬ ነበር። አሁን ግን ቁማር መጫወት ትቼ ይሖዋን በደስታ በማገልገል ላይ በመሆኔ ይህ ፍላጎቴ ተሟልቶልኛል።”
የጆን ባለቤት ሊንዳም ቁማር ለማቆም ወስናለች። “ቀላል አልነበረም” ትላለች። “እኔና ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመርን በኋላ ግን በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ማተኮር እንዳለብኝ ተማርኩ። አምላክ የሚወዳቸውን ነገሮች መውደድ ብቻ ሳይሆን ስግብግብነትን ጨምሮ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች በሙሉ መጥላት ቻልኩ። አሁን ሕይወቴ ይበልጥ ዓላማ ያለው ከመሆኑም በላይ ገንዘብ ይበረክትልኛል።”—መዝሙር 97:10
አንተም ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖርህ ካደረግህ ከቁማር ወጥመድ ለመራቅ የሚያስችል ብርታትና ጥበብ ልታገኝ ትችላለህ። እንዲህ ብታደርግ ኢኮኖሚያዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጤንነትህ ይሻሻልልሃል። ያን ጊዜ “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” የሚለው የምሳሌ 10:22 ቃል እውነት መሆኑን በራስህ ሕይወት ላይ ማየት ትችላለህ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ስግብግብነት መጥፎ ማኅበራዊ በሽታ ብቻ ሳይሆን ለሞት የሚዳርግ መንፈሳዊ በሽታ ጭምር ነው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ቁማርና የመናፍስት ኃይል
የዱክ ዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች የሆኑ ተመራማሪዎች ለብሔራዊ የቁማር ጠንቅ ጥናት ኮሚሽን ባቀረቡት ሪፖርት በቁማር ማስታወቂያዎችና በመናፍስት እምነት መካከል ጠንካራ ትስስር እንዳለ ገልጸዋል። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “ብዙ [የሎተሪ] ማስታወቂያዎች የሚያተኩሩት ሀብት በማግኘት ላይ ነው። . . . እነርሱ የሚለፍፉለት ሀብት ግን በጥረትና በድካም የሚገኝ ሳይሆን በምኞት፣ በቅዠትና በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ በመናፍስት ኃይል የሚገኝ ሀብት ነው። አብዛኞቹ የሎተሪ ደንበኞች የሚገዟቸውን ቁጥሮች የሚመርጡት በአጉል እምነት፣ በኮከብ ቆጠራ፣ የገዛ ሐሳባቸውን በሚናገሩ ባለ ራእዮችና ቁጥሮችን ከስሞች፣ ከቀኖችና ከሕልሞች ጋር በሚያዛምዱ ‘የሕልም መፍቻ መጻሕፍት’ እየተመሩ እንደሆነ የሎተሪ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች በሙሉ አሳምረው የሚያውቁት ሐቅ ነው። የሎተሪ ድርጅቶች ሁሉም ቁጥሮች እኩል የሆነ ባለ ዕጣ የመሆን ዕድል እንዳላቸው ከማስገንዘብ ይልቅ ተጫዋቾች ገዳቸው እንደሆነ የሚያምኑበትን ቁጥር እንዲመርጡ (እና የሙጥኝ ብለው እንዲይዙ) ያበረታታሉ።”
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ከቁማር እንድላቀቅ የሚያስችል ብርታት ሰጠኝ።”— ጆን
“አሁን ሕይወቴ ይበልጥ ዓላማ ያለው ከመሆኑም በላይ ገንዘብ ይበረክትልኛል።”—ሊንዳ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘ቁማር መጫወቴን ማቆም ብቻ ሳይሆን ቁማርን እስከ መጥላት መድረሴ በጣም አስደንቆኛል።’—ካዙሺጌ