በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብሔራት አሁንም ከታሪክ አይማሩም

ብሔራት አሁንም ከታሪክ አይማሩም

ብሔራት አሁንም ከታሪክ አይማሩም

“ሰዎች ከታሪክ ሊማሩ ቢችሉ ኖሮ እንዴት ያለ ትምህርት ይገኝ ነበር! ነገር ግን በስሜታዊነትና በወገናዊነት ታውረናል። ተሞክሮ የፈነጠቀልን ብርሃን የጋን ውስጥ መብራት ሆኖብናል!”— ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅ

እንግሊዛዊው ባለቅኔ ሳሙኤል ኮልሪጅ በሰጠው አስተያየት ትስማማለህ? ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ባለን የጋለ ስሜት ታውረን የቀደሙ ትውልዶች የፈጸሙትን አሳዛኝ ስህተት ደግመን ልንፈጽም እንችላለን?

የመስቀል ጦርነቶች

በመስቀል ጦርነት ጊዜ ሰዎች ያደረጓቸውን አንዳንድ ነገሮች በምሳሌነት እንመልከት። በ1095 እዘአ የሮማ ሊቀ ጳጳስ ዳግማዊ ኡርባን “ክርስቲያኖች” ቅድስቲቷን አገር ከሙስሊሞች ነጻ እንዲያወጡ ጥሪ አቀረቡ። በዳግማዊ ኡርባን ሥልጣን ሥር ይተዳደሩ የነበሩ ነገሥታት፣ መሳፍንት፣ መኮንኖችና ተራ ሰዎች ጥሪውን ተቀበሉ። አንድ የመካከለኛው ዘመን የታሪክ ሊቅ ይህን ዓላማ ለመደገፍ ያልተነሳሳ “በክርስቶስ ሕግ የሚኖር አንድም ሕዝብ አልነበረም” ብለዋል።

የታሪክ ምሁሩ ዞኤ ኦልደንቡር አብዛኞቹ የመስቀል ጦረኞች “ለመስቀል ጦርነት መዝመታቸው ለአምላክ አገልግሎት በቀጥታ መሰለፋቸው እንደሆነ አድርገው ያምኑ ነበር” ብለዋል። ራሳቸውን “በዲያብሎስ ልጆች ላይ የወደቁ አጥፊ መላእክት አድርገው ይመለከቱ ነበር።” በተጨማሪም ብራያን ሞይነሃን የተባሉ ደራሲ እንዳሉት “በዚህ ጦርነት የሞቱ ሁሉ በሰማይ የሰማዕታት አክሊል እንደሚጠብቃቸው” ያምኑ ነበር።

የመስቀል ጦረኞች ጠላቶቻቸውም ልክ የእነርሱን የመሰለ እምነት እንዳላቸው አላወቁ ይሆናል። ሙስሊም ወታደሮች፣ ይላሉ ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ ሾርተር ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ በተባለው መጽሐፋቸው፣ ወደ ጦር ሜዳ ይዘምቱ የነበረው የሚዋጉት ለአምላክ እንደሆነ በጽናት አምነውና ‘ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር ሲዋጉ በጦር ሜዳ ቢሞቱ በቀጥታ ወደ ሰማያዊ ገነት እንደሚገቡ’ እርግጠኛ ሆነው ነበር።

ሁለቱም ወገኖች የሚዋጉት አምላክ የደገፈውና የባረከው ፍትሐዊ ጦርነት እንደሆነ ተነግሯቸዋል። የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች እንደዚህ ያለውን እምነት ያራምዱ የነበረ ከመሆኑም በላይ የተገዥዎቻቸው ስሜት እንዲቀጣጠል ያራግቡ ነበር። ሁለቱም ወገኖች በቃላት ሊገለጽ የማይችል አሰቃቂ ድርጊት ፈጽመዋል።

ምን ዓይነት ሕዝብ ነው?

ይህን የመሰለውን አስከፊ ድርጊት የፈጸመው ምን ዓይነት ሕዝብ ነው? አብዛኞቹ በዛሬው ዘመን ካሉት ሰዎች እምብዛም የማይለዩ ተራ ሰዎች ነበሩ። ብዙዎቹ በአንድ ዓይነት ዓላማና በዘመናቸው በነበረው ዓለም ተፈጽሟል ብለው ያሰቡትን ግፍ ለማስወገድ ባላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳሱ እንደሆኑ አያጠራጥርም። ስሜታቸው በዚህ መንገድ እጅግ በመነሳሳቱ “ለፍትሕ” ሲዋጉ በጦር ሜዳ ቀጣና ውስጥ በተገኙ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ በደል፣ ሥቃይና መከራ እንዳመጡ ልብ ሳይሉ የቀሩ ይመስላል።

ይህን የመሰለው ሁኔታ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በተደጋጋሚ የታየ አይደለምን? ከፍተኛ የሆነ የማሳመንና አስተሳሰብ የማስለወጥ ችሎታ ያላቸው መሪዎች በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በጤናማ አእምሮአቸው ቢሆን ኖሮ ሊያስቡት እንኳን የማይችሉትን አረመኔያዊ ድርጊት በሃይማኖታዊና በፖለቲካዊ ተቃዋሚዎቻቸው ላይ እንዲፈጽሙ አላደረጉምን? ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች የዘመቻ ጥሪ ማድረጋቸውና አምላክም በሁለቱም ወገኖች እንደተሰለፈ መነገሩ በፖለቲካዊና በሃይማኖታዊ ተቃውሞ ላይ ለሚፈጸመው አፈናና ጭካኔ ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣል። ይህ ብዙ አምባገነኖች ለበርካታ ምዕተ ዓመታት በተደጋጋሚ የተጠቀሙበት ስልት ነው። ሞይነሃን “ይህ የናዚ ጨፍጫፊዎችና ዘመናዊዎቹ የጎሣ ምንጠራ አራማጆችም ሆኑ የመስቀል ውጊያ መሪዎች የተጠቀሙበት ስልት ነው” ብለዋል።

‘ይሁን እንጂ ዛሬ ከፍተኛ ሥልጣኔ ላይ የደረስን በመሆኑ የዘመናችን ሰዎች እንዲህ ባሉ መሪዎች ሊጠመዘዙ አይችሉም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎን፣ መሆን የነበረበት ይህ ነው። ነገር ግን በእርግጥ ከታሪክ ተምረናል? ያለፈውን የመቶ ዓመት ታሪክ መለስ ብሎ የተመለከተ ሰው በሐቀኝነት አዎን፣ ብሎ ሊመልስ ይችላል?

አንደኛው የዓለም ጦርነት

ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ የተደረገውን የሚመስል ነገር በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜም ተፈጽሟል። “በ1914 ከታዩት ለማመን የሚያዳግቱ ሁኔታዎች አንዱ በእያንዳንዱ አገር ከሁሉም ፓርቲ፣ እምነትና ዘር የተውጣጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደስ እያላቸውና በፈቃደኝነት ወደ ጦርነት መዝመታቸው ነው” ሲሉ ሮበርትስ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተራ ሰዎች “ደስ እያላቸውና በፈቃደኝነት” ለጦርነት የዘመቱት ለምን ነበር? ከእነርሱ በፊት ወደውና ፈቅደው ለጦርነት እንደዘመቱት ሰዎች አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው በዘመኑ በነበረው ፍልስፍና ተቀርጾ ስለነበረ ነው። ለነፃነትና ለፍትሕ ለመጋደል ብለው የተነሱ አንዳንድ ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም የራሳቸው ብሔር ከሌላው እንደሚበልጥና በዚህም ምክንያት ሌሎቹን ብሔራት በሙሉ መግዛት እንደሚገባው በግትርነት አምነው የዘመቱ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ አይጠረጠርም።

እነዚህ ሰዎች ጦርነት መኖር ያለበት “ተፈጥሮአዊ ግዴታ” ነው ብለው እንዲያምኑ የተደረጉ ናቸው። ፊል ዊልያምስ የተባሉት ደራሲ “ማህበራዊ ዳርዊኒዝም” ጦርነት “ለመኖር የማይበቁ ዘሮችን ለማስወገድ” የሚያስችል ትክክለኛ መሣሪያ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።

እርግጥ ሁሉም ወገኖች የየራሳቸው ዓላማ ትክክል እንደሆነ ያምኑ ነበር። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ማርቲን ጊልበርት የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ በአንደኛው የዓለም ጦርነት “መንግሥታት የዘረኝነት፣ የአርበኝነትና የወታደራዊ ጀብዱ ከበሮ ይደልቁ ነበር። ሕዝቦቻቸው ደግሞ በጭፍን ተከተሏቸው” ብለዋል። የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያ የሆኑት ጆን ኬነት ጋልብሬት በዚሁ ጦርነት ዘመን በካናዳ ገጠራማ አካባቢ ያደጉ ሰው ናቸው። በአካባቢያቸው ያገኟቸው የነበሩት ሰዎች ሁሉ “በአውሮፓ የተቀሰቀሰው ግጭት ትልቅ ድንቁርና” መሆኑን ይናገሩ እንደነበረ ገልጸዋል። “የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች . . . እንዲህ ያለውን እብደት ሊቀበሉ አይችሉም” ይሉ ነበር። ይሁን እንጂ መቀበላቸው አልቀረም። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሎ በተጠራው በዚህ ዘግናኝ ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች ከሞቱት ከዘጠኝ ሚልዮን የሚበልጡ ወታደሮች መካከል 60, 000 የሚሆኑት ካናዳውያን ነበሩ።

አሁንም አልተማሩም

ሃያ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ፋሺዝምና ናዚዝም ሲያቆጠቁጥ ይኸው መንፈስ እንደገና መታየት ጀመረ። ፋሺስቶች ‘የሕዝቦችን ስሜት ለማነሳሳት አፈ ታሪኮችንና እንደ ፋስ ያሉትን ጥንታዊ አርማዎች በፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት መጠቀም ጀመሩ’ በማለት ሂው ፐርሰል ጽፈዋል። እጅግ ውጤታማ ሆኖ ያገኙት አንዱ ዘዴ ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር መቀላቀል ሲሆን ሠራዊቶቻቸውን አምላክ እንዲባርክ ይጸልዩ ነበር።

አዶልፍ ሂትለር “የብዙሃኑን ሥነ ልቦና በመለወጥ ጥበብ የተካነና በጣም የተዋጣለት ተናጋሪ” ነበር። ዲክ ጊሪ ሂትለር ኤንድ ናዚዝም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደ ብዙዎቹ የሥልጣን ጥመኞች ሂትለርም ‘ብዙሃኑ የሚመራው በአንጎሉ ሳይሆን በስሜቱ ነው’ ብሎ ያምን ነበር ሲሉ ጽፈዋል። ይህን የሰው ልጅ ድክመት የሕዝቡ ጥላቻ በአንድ የጋራ ጠላት ላይ እንዲያነጣጥር በማድረግ ለራሱ ዓላማ ተገልግሎበታል። “ጀርመኖች በአይሁዳውያን ላይ ሥጋትና ጥላቻ እንዲያድርባቸው አድርጓል” ይላሉ ፐርሰል። ‘አይሁዳውያን የጀርመንን ብሔር ይበክላሉ’ በማለት ያንቋሽሻቸው ነበር።

ይህን ዘመን በጣም አስከፊ የሚያደርገው በሚልዮን የሚቆጠሩ ጨዋ የሚመስሉ ሰዎች ሕዝቦችን በጅምላ ለመጨፍጨፍ በቀላሉ መነሳሳት መቻላቸው ነው። “የሠለጠነ አገር የሚባል ሕዝብ አሰቃቂ የሆነውን የናዚ አረመኔያዊ ድርጊት ዝም ብሎ ከመመልከትም አልፎ እንዴት ተባባሪ ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ጊሪ ይጠይቃሉ። ይህ አገር “የሠለጠነ” አገር ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን አገር የሚባልም ነበር። እንዲህ ወዳለው እልቂት ተስበው የገቡት ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ይልቅ የሰዎችን ፍልስፍናዎችና እቅዶች ለመከተል ስለመረጡ ነው። ከዚያም ወዲህ ቢሆን ቅን የሆኑ እጅግ በርካታ ወንዶችና ሴቶች አሰቃቂ ወደሆነ እልቂት እንዲገቡ ተደርጓል።

ጌኦርግ ሄግል የተባለው ጀርመናዊ ፈላስፋ “ብሔራትና መንግሥታት ከታሪክ ምንም ነገር እንዳልተማሩ ወይም ካገኙት ትምህርት ምንም እንዳልተጠቀሙ ተሞክሮና ታሪክ አስተምሮናል” ብሏል። ሄግል ስለ ሕይወት ባለው ፍልስፍና የማይስማሙ ብዙ ሰዎች ይኑሩ እንጂ በዚህ አባባሉ የማይስማሙ ሰዎች ግን እምብዛም አይኖሩም። ሰዎች ከታሪክ ለመማር ያለመቻል ከባድ ችግር ያለባቸው መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል። ይሁን እንጂ አንተስ እንደነዚህ ሰዎች መሆን ይገባሃልን?

በእርግጥ ልንማረው የሚገባ አንድ ግልጽ ትምህርት አለ። ባለፉት ዘመናት የታዩት አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይደገሙ ከተፈለገ ሊሳሳቱ ከሚችሉት የሰው ልጆች ፍልስፍናዎች ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ መመሪያ ያስፈልገናል። ታዲያ ከሰብዓዊ ፍልስፍና ሌላ ልንመራበት የምንችል ምን ነገር አለ? የመስቀል ጦርነት ከመካሄዱ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው ብቸኛው ትክክለኛ አካሄድ ምን እንደሆነ በተግባር አሳይተዋል። በዚያ ዘመን ወደነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት ተስበው ላለመግባት ምን እንዳደረጉ እንመርምር። ይሁን እንጂ ዛሬስ ብሔራት ይህን ተምረው ከግጭት ይታቀቡ ይሆን? ብሔራት ያደረጉትን ቢያደርጉ አምላክ ይህን የሰው ልጆች መከራና ሥቃይ ለማስወገድ ምን መፍትሔ አዘጋጅቶ ይሆን?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አረመኔያዊ ድርጊትና ሥቃይ የሰው ልጆች ግጭቶች መለያ ባሕርይ ሆኗል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ:- በጦርነት ከታመሰ አካባቢ የተፈናቀሉ ስደተኞች

የሰለጠኑ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች እንዲህ ያለውን ለመናገር እንኳን የሚከብድ ድርጊት እንዴት ሊፈጽሙ ቻሉ?

[ምንጮች]

የሩዋንዳ ስደተኞች:- UN PHOTO 186788/J. Isaac;

የዓለም የንግድ ማዕከል ሲፈርስ:- AP Photo/Amy Sancetta