በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ትምህርት ቢገኝም ምንም ለውጥ አልተደረገም

ብዙ ትምህርት ቢገኝም ምንም ለውጥ አልተደረገም

ብዙ ትምህርት ቢገኝም ምንም ለውጥ አልተደረገም

“በቅርብ ዓመታት በሳይንስ መስክ ብዙ አስደናቂ ውጤቶች ይገኙ እንጂ የሰው ልጅ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት እምብዛም አልተለወጠም። በዚህም ምክንያት አሁንም ከታሪክ መማር ግድ ሆኖብናል።”​—⁠ኬኔት ክላርክ፣ ሲቪላይዜሽን — ኤ ፐርሰናል ቪው

ለፉት ምዕተ ዓመታት በሳይንስ ዘርፍ አስደናቂ የሆኑ እድገቶች መታየታቸው አይካድም። ታይም መጽሔት እንደሚለው እነዚህ እድገቶች “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ እንዲያገኙ አስችለዋል።” አንዳንዶቹ ታላላቅ እድገቶች የታዩት በሕክምናው ዘርፍ ነው። በመካከለኛው ዘመን “ሕክምና እጅግ ኋላ ቀርና በሽተኞችን የሚያሰቃይ ነበር” ይላሉ የታሪክ ምሁር የሆኑት ዞኤ ኦልደንቡር። “ሐኪሞች የሚያድኑትን ያህል ይገድሉ ነበር።”

ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን

ሰዎች ብዙ ጊዜ ከስህተታቸው ለመማር ፈቃደኛ አይሆኑም። ለምሳሌ፣ በ19ኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ ብዙ ዶክተሮች ራሳቸው በአንድ ያልታወቀ መንገድ ወደ በሽተኞቻቸው በሽታ እንደሚያስተላልፉ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ እየታየ ችላ ብለው ለማለፍ መርጠዋል። በዚህም ምክንያት የለመዱትን አደገኛ የሆነ አሠራር የሙጥኝ በማለት ከአንዱ በሽተኛ ወደ ሌላው ሲዘዋወሩ እጃቸውን ለመታጠብ እምቢተኞች ሆነዋል።

እንዲህም ሆኖ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማደጉን አላቆመም። ስለዚህም የሰው ልጆች ካለፈ ተሞክሮአቸው ትምህርት በማግኘት ዓለማችንን ይበልጥ ምቹና አስደሳች ማድረግ ይገባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ አልቻሉም።

ለምሳሌ፣ በ17ኛው ምዕተ ዓመት በአውሮፓ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ይህ ዘመን የእውቀትና የምርምር ዘመን ተብሎ ተጠርቷል። ሐቁ ግን ኬኔት ክላርክ እንዳሉት “እነዚያን የመሰሉ ታላላቅ የሥነ ጥበብና የሳይንስ ሊቃውንት ቢነሱም ታይቶ የማያውቅ ጭካኔ የተሞላባቸው ትርጉም የለሽ ስደቶችና አረመኔያዊ ጦርነቶች መካሄዳቸው አልቀረም።”

በጊዜያችንም ከታሪክ ተምሮ ስህተቶችን ለማስወገድ ፈቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያ ይታያል። በዚህም የተነሣ በዚህች ፕላኔት ላይ የመኖር ዕድላችን አደጋ ላይ የወደቀ ይመስላል። ጆሰፍ ኒድሃም የተባሉት ደራሲ ሁኔታው በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ‘ባሁኑ ጊዜ ጽንፈኞች ተነስተው ሕይወት ያለውን ፍጡር በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ የሚያጠፋ አንድ ኃይል እንዳይለቁብን ከመመኘትና ከመጸለይ በቀር ልናደርግ የምንችለው ምንም ነገር የለም’ ብለዋል።

የሰው ልጅ ይህን ያህል በተራቀቀበትና በሰለጠነበት ዘመን በዓመፅና በጭካኔ በተሞላ ዓለም ውስጥ የምንኖረው ለምንድን ነው? ይህ ሁኔታ የሚለወጥበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ላይ ይብራራሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሽፋን፦ የአንደኛው የዓለም ጦርነት፦ U.S. National Archives photo; የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሆሎኮስት ሰለባዎች፦ Robert A. Schmuhl, courtesy of USHMM Photo Archives

ገጽ 2 እና 3፦ ቢ-17 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን፦ USAF photo; ሴት፦ Instituto Municipal de Historia, Barcelona; ስደተኞች፦ UN PHOTO 186797/J. Isaac; 23 ኪሎ ቶን የሚመዝን ፍንዳታ፦ U.S. Department of Energy photograph