ከአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መማር
ከአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መማር
“እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:8
ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችን በጭፍን መከተል ስለሚያስከትለው አደጋ ያስጠነቀቃቸው እንዲህ በማለት ነበር። ኢየሱስና ሐዋርያት የሰጡትንና በርካታ ጥቅም ያስገኘላቸውን አስተማማኝ መመሪያ የሙጥኝ ብለው መያዝ ነበረባቸው። አለበለዚያ ግን በየጊዜው በሚለዋወጡት የሰዎች አስተሳሰቦች ይሸነፉና በሚልዮን እንደሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ብዙ መከራና ሥቃይ የሚያስከትልባቸውን አካሄድ ይከተላሉ።—1 ቆሮንቶስ 1:19-21፤ 3:18-20
“እንደ ክርስቶስ ትምህርት” መኖር
ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የተነሱት የመስቀል ጦረኞች “እንደ ክርስቶስ ትምህርት” መኖር ለኢየሱስ ክርስቶስ ቆሜያለሁ ብሎ ከመናገር የበለጠ ነገር እንደሚጠይቅ አልተገነዘቡም ነበር። (ማቴዎስ 7:21-23) በመንፈስ በተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው የኢየሱስ ትምህርት ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ መኖር ማለት ነው። (ማቴዎስ 7:15-20፤ ዮሐንስ 17:17) ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:31) በተጨማሪም ‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ’ ብሏል።—ዮሐንስ 13:35
እንደ እውነቱ ከሆነ የመስቀል ጦረኞቹ ‘እንደ ሰው ወግ ባለ ከንቱ ማታለያ’ ተማርከው ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው አልፎ ተርፎም ጳጳሶቻቸው “የታወቁ የጦር ሰዎች” በሚሆኑበት ጊዜ ተራ ሰዎች መታለላቸው የሚያስደንቅ ነገር አይሆንም። በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒድያ
ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክሊስያስቲካል ሊትሬቸር “በቀሳውስት መካከል የጦረኝነት መንፈስ በጣም ተስፋፍቶ ስለነበረ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ ከታያቸው ጦርነት ለማወጅ የተዘጋጁ ነበሩ” ይላል።እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው በምን ምክንያት ነው? በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ የአምላክ ቃል አስቀድሞ እንደተነበየው ከሃዲ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከክርስቶስ ትምህርት በጣም እየራቁ ሄዱ። (ሥራ 20:29, 30) የተበከለው ቤተ ክርስቲያን እያደር ከዓለማዊው መንግሥት ጋር እየተቀናጀ መጣ። በአራተኛው መቶ ዘመን የሮማው አጼ ቆስጠንጢኖስ ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ ክርስቲያን ሆነ ተባለ። ከዚያ ወዲህ፣ ይላል ሳይክሎፒድያው፣ “የጣዖት አርማዎች በመስቀል አርማዎች መለወጣቸው በእያንዳንዱ ክርስቲያን ላይ ወታደር ሆኖ የማገልገል ግዴታ እንዲጫን አደረገ።”
ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ግዴታ እንደሌለባቸው የታወቀ ነው። ክርስቶስ የቆመለትን ዓላማ እንዲጻረሩ ያደረጋቸው የሰዎች ፍልስፍና የሚያቀርበው ‘የማባበያ ቃል’ ነው። (ቆላስይስ 2:4) መዋጋት ትክክል መሆኑን ለማሳመን አንዳንድ በጣም አታላይ የሆኑ ክርክሮች ሲቀርቡ ቆይተዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አንድ ሰብዓዊነት ወይም ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው “ጥንትም ሆነ በዘመናችን በሚፈጸሙት የጦርነት ዲያብሎሳዊ ድርጊቶች” እየተካፈለ “ከክርስትና መሠረታዊ መመሪያዎች ጋር ሊታረቅ የሚችልበት አንዳች ሁኔታ የለም” ይላል ሳይክሎፒድያው።
ክርስቲያን ነን ከሚሉት ውጭ ያሉትም ሃይማኖቶች ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ውጊያ ሲያካሂዱ ኖረዋል። እንደ ሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እነርሱም በብሔር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ልዩነቶች ምክንያት የራሳቸውን ሃይማኖት አባሎችም ሆነ ሌሎችን ሲጨፈጭፉ ኖረዋል። ሰዎችን ወደራሳቸው እምነት ለመለወጥ በኃይልና በማስፈራራት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። አንዳንዶቹ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ደም እንደ ጎርፍ አፍስሰዋል። በዚህ ረገድ ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የተለዩ ሆነው አልተገኙም።
ከዓለም መለየት
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በዘመናቸው ከነበሩት ደም አፋሳሽ ጦርነቶችና ከፖለቲካ ርቀው ሊኖሩ የቻሉት ለምን ነበር? የረዷቸው ሁለት መሠረታዊ መመሪያዎች ነበሩ። በመጀመሪያ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ራሱን ለመከላከል ሰይፍ በመዘዘ ጊዜ ኢየሱስ ለጴጥሮስ የሰጠው ትእዛዝ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ማቴዎስ 26:52) ሁለተኛ፣ ጲላጦስ ስለ ኢየሱስ ንግሥና ጠይቆት ኢየሱስ በሰጠው መልስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሏል።—ዮሐንስ 18:36
ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” የሚል ነበር። (የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን መሠረታዊ መመሪያዎች ሥራ ላይ ያዋሉት እንዴት ነበር? በፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ረገድ ጥብቅ የሆነ የገለልተኝነት አቋም በመያዝ ከዓለም ሙሉ በሙሉ ተለይተዋል። (ዮሐንስ 15:17-19፤ 17:14-16፤ ያዕቆብ 4:4) መሰሎቻቸው በሆኑ የሰው ዘሮች ላይ መሣሪያ ለማንሳት እምቢተኞች ሆነዋል። የአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአይሁዳውያን የብሔረተኝነት እንቅስቃሴዎችም ሆነ በሮማ አጼያዊ ጦር ሠራዊት ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዳልነበራቸው ከታሪክ በግልጽ መረዳት ይቻላል። የፖለቲካ መሪዎችን እንዲህ አድርጉ፣ እንዲህ አታድርጉ ለማለትም አልሞከሩም። ይህ የመንግሥታዊ መሪዎች ኃላፊነት ነው።—ገላትያ 6:5
በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ሰማዕቱ ጀስቲን ስለ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ‘ሰይፋቸውን ማረሻ አድርገው ቀጥቅጠው ነበር’ ብሏል። (ሚክያስ 4:3) ተርቱልያን ክርስቲያኖች የወሰዱትን አቋም ለተቃወሙ ሰዎች መልስ ሲሰጥ “ጌታ ሰይፍ የሚያነሳ በሰይፍ ይጠፋል እያለ ሰይፍን መተዳደሪያ ማድረግ ሕጋዊ ነው ማለት ይቻላልን?” ሲል ጠይቋል።
‘ከሰዎች ይልቅ አምላክን መታዘዝ’
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ወደ ጦርነት አንዘምትም ማለታቸው ብዙ ችግር አስከትሎባቸዋል። በዘመኑ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረውን እምነት የሚጻረር አቋም ነበር። ሴልሰስ የተባለው የክርስትና ጠላት በወሰዱት አቋም ተሳልቋል። ይህ ሰው ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እስካዘዙ ድረስ ማንኛውም ሰው ለጦርነት መዝመት አለበት ብሎ ያምን ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ ቢደርስባቸውም ማንኛውንም የክርስቶስን ትምህርት የሚቃወም ሰብዓዊ ፍልስፍና ለመቀበል እምቢተኞች ሆነዋል። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ብለዋል።—ሥራ 4:19፤ 5:29
በዘመናችንም የይሖዋ ምሥክሮች የእነዚህን ክርስቲያኖች አርዓያ ተከትለዋል። ለምሳሌ በናዚዎች ትተዳደር በነበረችው ጀርመን ሂትለር በቆሰቆሰውና ከፍተኛ እልቂት ባስከተለው ጦርነት አንካፈልም በማለት ቆራጥ አቋም ወስደዋል።
ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን ከመጣስ አረመኔያዊ ስደት ለመቀበል፣ አስፈላጊም ከሆነ ለመሞት ጭምር ፈቃደኛ ሆነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ መመሪያዎች አንተላለፍም በማለታቸው ናዚዎች ከጠቅላላዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል “ግማሽ የሚሆኑትን እንዳሰሩና አንድ አራተኛ የሚሆኑትን እንደገደሉ” ሪፖርት ተደርጓል። (ኦቭ ጎድስ ኤንድ ሜን ) በዚህም ምክንያት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተገደሉት በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱም ቢሆን በይሖዋ ምሥክር አልተገደለም። ምሥክሮቹ ሌሎችን ከሚገድሉ የራሳቸውን ሕይወት ለመሠዋት ፈቃደኞች ሆነዋል። ብዙዎቹም እስከ መሠዋት ደርሰዋል።ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ታሪክ ምን ሊያስተምረን ይችላል? አንደኛው ትምህርት የሚከተለው ነው:- ሰብዓዊ ፍልስፍና በሕዝቦችና በብሔራት መካከል ጥላቻና ውጊያ ሲቀሰቅስ ኖሯል። መክብብ 8:9 [NW ] “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ማለቱ ትክክል ነው። ይህ የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ኤርምያስ 10:23 ላይ ይገኛል። የአምላክ ቃል “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ይላል። አዎን፣ አምላክ የሰው ልጆችን ከእርሱ ተነጥለው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ አድርጎ አልፈጠረም። እንዲህ ያለ ችሎታ አልተሰጣቸውም። ታሪክም ይህን ያረጋግጣል።
የቀድሞውን አሳዛኝ ታሪክ በመድገም ላይ ያሉ የብሔራት መሪዎች የሚከተሉትን አካሄድ በግለሰብ ደረጃ ለመለወጥ አንችልም። አንድ ዓይነት አካሄድ እንዲከተሉ ለማሳመን እንድንሞክርም ሥልጣን አልተሰጠንም። ይሁን እንጂ በግጭቶቻቸው ተካፋዮች ሆነን የእነርሱ ክፍል መሆን አይገባንም። ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:14) በዚህ ዓለም ግጭቶች ተካፋይ እንዳንሆን ተለዋዋጭ የሆነውን ሰብዓዊ ፍልስፍና ሳይሆን የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የሕይወታችን መመሪያ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል።—ማቴዎስ 7:24-27፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
አስደሳች የሆነ የወደፊት ጊዜ
አስተማማኝ የሆነው የአምላክ ቃል ስላለፈውና ስላለንበት ዘመን በማስተማር ብቻ አያቆምም። ስለ ወደፊቱ ጊዜም እምነት የሚጣልበት መመሪያ ይሰጣል። (መዝሙር 119:105፤ ኢሳይያስ 46:9-11) በተጨማሪም አምላክ ለዚህች ምድር ስላለው ዓላማ ግልጽ የሆነ መግለጫ ይሰጣል። የሰው ልጆች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያስገኘላቸውን ታላቅ ችሎታ አለአግባብ በመጠቀም ምድርን በእብደት እንዲያጠፉ አይፈቅድም። ይህች ምድር መጀመሪያ ላይ አውጥቶላት በነበረው ዓላማ መሠረት ገነት ወደመሆን ደረጃ እንድትደርስ ያደርጋል።—ሉቃስ 23:43
የአምላክ ቃል ይህን አስመልክቶ ሲናገር “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ” ይላል። (ምሳሌ 2:21, 22) ይህ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ምክንያቱም ይህ ሁከት የበዛበት ዘመን ራሱ በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀን’ እንደምንኖር ያረጋግጣል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ይህ የመጨረሻ ቀን የተቆረጠ ከመሆኑም በላይ እያለቀ መጥቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል።—1 ዮሐንስ 2:17፤ ዳንኤል 2:44
በቅርቡ አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን ያጠፋል።’ ይህን በዓመፅ የተሞላ ዓለም አስወግዶ በቦታው ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ምድር’ ያቋቁማል። (ራእይ 11:18፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13) በዚያ ጊዜ ከጥፋቱ የሚተርፉትን ሰዎች “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” (ራእይ 21:1-4) ኢሳይያስ 2:4 ላይ ያለው ትንቢት ሙሉ ፍጻሜውን ስለሚያገኝ ጦርነትና የኃይል ድርጊት ለዘላለም ይወገዳል:- “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” አንተም ከታሪክ ለመማር ፈቃደኛ ከሆንክ ይህን አስደናቂና ዘላለማዊ የወደፊት ጊዜ ልትወርስ ትችላለህ።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የይሖዋ ምሥክሮች ከአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተምረዋል
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነች ተናግሯል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ቃል ገነት በምትሆን ምድር ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት እንደምናገኝ ተስፋ ይሰጣል