በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር

መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር

መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር

በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በየጊዜው የሚጥሉት ቆሻሻ ስፍር ቁጥር የለውም። በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ የሚጣለውን ቆሻሻ እንደ ምሳሌ መውሰድ ትችላለህ። በዚህች አገር ከሚጣለው ቆሻሻ ጋር ‘የሚመጣጠን ክብደት ያለው ውኃ 50 ሜትር ርዝማኔ ያላቸውን 68, 000 የዋና ገንዳዎች ሊሞላ እንደሚችል’ ተነግሯል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የተሰጠ አንድ ግምታዊ መረጃ እንዳለው ከሆነ የኒው ዮርክ ከተማ ነዋሪዎች ብቻ በየዓመቱ የሚጥሉት ቆሻሻ በከተማይቱ ውስጥ የሚገኘውን ሰፊ መናፈሻ ቦታ 4 ሜትር ያህል ወደ ታች ሊቀብረው ይችላል! *

“የፍጆታ ዕቃዎችን በብዛት በመሸመትና በመጣል” ረገድ አሜሪካውያን “ለተቀረው ዓለም ጥሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ” ይሆናሉ መባሉ ምንም አያስደንቅም። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አዝማሚያ የሚታየው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አይደለም። የጀርመን ነዋሪዎች በየዓመቱ የሚጥሉት ቆሻሻ ከዋና ከተማዋ ከበርሊን አንስቶ 1, 800 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ እስከሚገኘው የአፍሪካ የባሕር ጠረፍ የሚደርስ ርዝማኔ ያለውን ዕቃ ጫኝ ባቡር ሊሞላ እንደሚችል ተገምቷል። በተጨማሪም በአንድ ወቅት በተሰጠ ግምታዊ መረጃ መሠረት በብሪታንያ አራት አባላት ያሉት እያንዳንዱ ቤተሰብ በአንድ ዓመት ውስጥ በአማካይ ከስድስት ዛፎች የሚመረትን ከፍተኛ መጠን ያለው ወረቀት ይጥላል።

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥም እንዲህ ዓይነት ችግር ይታያል። አንድ የታወቀ የዜና መጽሔት “6 ቢልዮን ከሚሆነው የፕላኔታችን ሕዝብ መካከል አብዛኛው ዩናይትድ ስቴትስንና የተቀረውን በኢንዱስትሪ የበለጸገ ዓለም ፈለግ በመከተል ቆሻሻ በገፍ መጣል መጀመሩ በጣም የሚያሳዝን ነው” ሲል ዘግቧል። አዎን፣ ወደድንም ጠላን አብዛኞቻችን የምንኖረው መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል ነው።

ቆሻሻ መጣል በጊዜያችን የተጀመረ ነገር አይደለም። ይሁንና የታሸጉ ምግቦችና ሸቀጦች ቀደም ካሉት ዓመታት ይልቅ በዛሬው ጊዜ ይበልጥ በብዛት የሚመረቱ በመሆናቸው ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ በየቦታው የተጣሉ የቆርቆሮና የፕላስቲክ ማሸጊያዎች ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል። ከዚህም ሌላ የጋዜጦች፣ የመጽሔቶች፣ የማስታወቂያ ወረቀቶችና ሌሎች የሚታተሙ ጽሑፎች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

በኢንዱስትሪና በሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ የመጠቀው የዛሬው ዓለም ሌሎች አዳዲስ ቆሻሻዎችንም ፈጥሯል። ዲ ቬልት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ “የአውሮፓ ኅብረት አባል በሆኑ ሀገራት ውስጥ በየዓመቱ በግምት ዘጠኝ ሚልዮን መኪናዎች እንደሚጣሉ” ዘግቧል። እነዚህን መኪኖች ማስወገድ ቀላል ሥራ አይደለም። ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ የኑክሊየር ወይም የኬሚካል ዝቃጮችን ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ እንዴት ማስወገድ ይቻላል የሚለው ነው። በ1991 ዩናይትድ ስቴትስ “ከፍተኛ መጠን ያለው የራዲዮአክቲቭ ዝቃጭ እንደተከማቸባትና ይህን ዝቃጭ ልትጥል የምትችልበት ቋሚ ቦታ እንዳላገኘች” ተነግሮ ነበር። ገዳይ የሆኑ ዝቃጮችን የያዙ በሚልዮን የሚቆጠሩ በርሜሎች “ሊጠፉ፣ ሊሠረቁና በአግባቡ ሳይያዙ ቀርተው በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ በሚችሉበት ሁኔታ” በጊዜያዊ ማከማቻ ቦታዎች ተቀምጠው ይገኙ እንደነበር ተነግሯል። በ1999 ብቻ እንኳ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ 20, 000 ኩባንያዎች የወጣው ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ቆሻሻ ከ40 ሚልዮን ቶን በላይ ይሆናል።

ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ ባለፈው መቶ ዘመን በሚያስደንቅ ፍጥነት ያደገው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ነው። የሕዝቡ ብዛት በጨመረ መጠን ቆሻሻውም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል! ብዙሃኑ ሕዝብ ደግሞ የፍጆታ ዕቃዎችን በብዛት የሚጠቀም ነው። ዘ ዎርልድ ዎች ኢንስቲትዩት በቅርቡ እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር:- “ከ1950 ወዲህ የተጠቀምንባቸው የፍጆታ ዕቃዎችና [እንደ ውኃና መብራት ያሉ] አገልግሎቶች ከዚያ በፊት የነበሩት ትውልዶች በሙሉ ከተጠቀሙባቸው በእጅጉ በልጠው ተገኝተዋል።”

በበለጸጉት አገሮች የሚኖሩ ሰዎች እነዚህ “የፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች” እንዲቀሩባቸው እንደማይፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ወደ ገበያ አዳራሽ ሄዶ የተዘጋጁ ምግቦችንና ሌሎች የታሸጉ ሸቀጦችን መግዛትና በወረቀት ወይም በላስቲክ ከረጢት ይዞ መመለስ ምን ያህል ውጣ ውረድ እንደሚያስቀር አስበው። ሰዎች እንዲህ ያሉትን የታሸጉ ሸቀጦች በድንገት ገበያ ላይ ቢያጡ ኑሯቸው ምን ያህል በእነዚህ ሸቀጦች ላይ የተመካ እንደሆነ ወዲያውኑ ሊገነዘቡ ይችላሉ። በተጨማሪም እነዚህ የታሸጉ ሸቀጦች ንጽሕናቸው በሚገባ የተጠበቀ በመሆኑ ቢያንስ ቢያንስ በተዘዋዋሪ መንገድ ለጤና አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ጠቀሜታዎች ቢኖሩም እንኳ በዛሬው ጊዜ ያለው ኅብረተሰብ ቆሻሻ በገፍ የሚጥል መሆኑ ሊያሳስበን አይገባምን? ይህን ችግር ለመቅረፍ የተደረጉት የተለያዩ ጥረቶች እምብዛም ያስገኙት ውጤት ባለመኖሩ በእርግጥም ሊያሳስበን ይገባል። በተለይ ደግሞ የተጠቀመበትን ነገር ወዲያው መጣል የሚቀናው ይህ ያለንበት ኅብረተሰብ በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት ይበልጥ አሳሳቢ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ይህ መናፈሻ ቦታ 341 ሄክታር ስፋት አለው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አደገኛ የሆኑ ዝቃጮችን ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ ማስወገድ ቀላል አይደለም