መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም
መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም
“በተፈጥሮ . . . ጥቅም ላይ ሊውል የማይችል ምንም ነገር የለም።” ታይም መጽሔት እንደገለጸው ከሆነ ይህን የተናገሩት ያገለገሉ ነገሮችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ ላይ የተሠማሩ አንድ የታወቁ ባለሙያ ናቸው። ይህን አስተያየት የሰጡት በአንድ የተፈጥሮ ዑደት የሚፈጠር በድን ወይም ቆሻሻ የሆነ ነገር ምንጊዜም ለሌላ የተፈጥሮ ዑደት የሚያገለግል መሆኑን ለማመልከት ነው። እኚሁ ባለሙያ “የሰው ልጅ ቆሻሻ አልባ ከሆነው የተፈጥሮ ዑደት ትምህርት መቅሰም ይችላል። ይሁንና ይህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ማዋልና ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ይጠይቃል” ሲሉ መናገራቸውም ተዘግቧል።
አብዛኞቻችን አዲስ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ ባንችልም በአመለካከታችን ላይ ግን ለውጥ ማድረግ እንችላለን። መሠረታዊ ለሆኑ አንዳንድ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ትክክለኛ አመለካከት መያዛችን መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል መኖር የሚያስከትላቸውን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።
ቆጣቢ ሁን
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሰዎች አንዱ የሚበላው ነገር አጥቶ ጦሙን የሚያድር መሆኑን ማወቃችን ምግብን እንደ ተራ ነገር እንዳንመለከትና ቆጣቢ እንድንሆን ሊገፋፋን ይገባል። በአፍሪካ ለ28 ዓመታት በሚስዮናዊነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ወደ አውሮፓ የተመለሱ አንድ ባልና ሚስት በትውልድ አገራቸው የሚኖሩ ሰዎች “ምግብ በመድፋት ከፍተኛ ብክነት የሚፈጽሙ መሆናቸው” ስሜታቸውን በእጅጉ እንደሚረብሸው ገልጸዋል።
አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ምግብ በሚበሉበት ጊዜ ሊበሉ ከሚችሉት በላይ እንዳያወጡ ያሰለጥኗቸዋል። እንዲህ ያለ ሥልጠና መስጠታቸው ምግቡ እንዳይባክንና እንዳይጣል ለማድረግ ይረዳል። መጀመሪያ ትንሽ መውሰድና በኋላ መጨመር ይመረጣል። እርግጥ በዚህ ረገድ ወላጆች ራሳቸው ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። አምላክ ለሚሰጠን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮች እውነተኛ አድናቆት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት በተአምራዊ ሁኔታ ተትረፍርፎ የቀረበ ምግብ እንኳ እንዳይባክን ሲል ጥበብ የተሞላበት እርምጃ እንደወሰደ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይገልጽልናል።—ዮሐንስ 6:11-13
በልብስ፣ በቤት ቁሳቁስና በተለያዩ ማሽኖች አጠቃቀም ረገድም ብክነትን ማስወገድ ይቻላል። ለምንገለገልባቸው ዕቃዎች አስፈላጊውን ጥገና የምናደርግ ከሆነና ማገልገል እስከቻሉ ድረስ ረዘም ላለ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ላሉን ነገሮች አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። የማስታወቂያው ዓለም በመጠን፣ በጥራት፣ በጥንካሬም ሆነ በቅልጥፍና የተሻሉ ነገሮችን በማቅረብ ባለን ነገር እንዳንረካ ለማድረግ በሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መታለል የለብንም። አገልግሎት መስጠታቸውን ያላቆሙ ዕቃዎቻችንን በአዲስ መተካት መብታችን ቢሆንም እንዲህ ከማድረጋችን በፊት አዲስ ዕቃ ለመግዛት የተነሳሳንበትን ምክንያት ቆም ብለን መመርመራችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
የስግብግብነትን ጠባይ ማስወገድ
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በምድረ በዳ ይጓዙ በነበረበት ወቅት መና እንዲመገቡ ተደርጎ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚገልጸው መናው ዘጸአት 16:16-20) መጽሐፍ ቅዱስ ስግብግብነትን በተደጋጋሚ ጊዜያት አጥብቆ ያወግዛል።—ኤፌሶን 5:3
በበቂ መጠን ይቀርብላቸው የነበረ ሲሆን እንዳይስገበገቡና ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን ያህል ብቻ እንዲወስዱ ተነግሯቸው ነበር። ትእዛዙን ያላከበሩና ለዕለት ከሚያስፈልጋቸው በላይ የወሰዱ ሰዎች ያስተረፉት መና በመትላቱና በመሽተቱ ስግብግብነት ጥቅም እንደሌለው ተገንዝበዋል። (መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ስግብግብነትን አውግዘዋል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ሮማዊው ፈላስፋና ጸሐፌ ተውኔት ሴኔካ ስግብግብ የሆነ ሰው ፈጽሞ እንደማይረካ ተገንዝቦ ነበር። “ስግብግብ የሆነ ሰው ዓለም በሙሉ ቢሰጠው እንኳ አያረካውም” ሲል ተናግሯል። ኤሪክ ፍሮም የተሰኘው የ20ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋም በተመሳሳይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- ‘የስግብግብነት ፍላጎትን ለማርካት መሞከር የተሸነቆረን እንስራ ለመሙላት ከመሞከር ተለይቶ አይታይም። ሰውየው ፍላጎቱን ለማርካት ሲደክም ይኖራል እንጂ እርካታ የሚባል ነገር አያገኝም።’ ብዙዎች ስግብግብነትንና ብክነትን ከማስወገድ በተጨማሪ ሌሎች ጠቃሚ እርምጃዎችንም ይወስዳሉ።
ለሌሎች አካፍል
በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኙ ንብረቶችህን ከመጣልህ በፊት ለማን ብትሰጥ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ያህል ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ልብሶቻቸው ካጠሯቸው ሌሎች ልጆች እንዲጠቀሙባቸው መስጠት ይቻል ይሆን? ቀደም ሲል ስትጠቀምባቸው የነበሩና አሁን ግን ብዙም የማትገለገልባቸውን ጠቃሚ የሆኑ ንብረቶችም ለሌሎች መስጠት ትችል ይሆን? ስትጠቀምበት የቆየኸውን ዕቃ በመስጠት ሌሎች የደስታህ ተካፋዮች እንዲሆኑ ማድረግ ትችላለህ። በአዝናኝ ቀልዶቹም የሚታወቀው አሜሪካዊው ደራሲ ማርክ ትዌይን በአንድ ወቅት “ደስታህ ምሉዕ ይሆን ዘንድ ደስታህን የምታካፍለው ሰው ሊኖር ይገባል” ሲል ጽፎ ነበር። ምናልባት አንተም ደስታህን ለሌላ ሰው በማካፈል እጥፍ ድርብ ደስታ ያገኘህበት አጋጣሚ ይኖር ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ለሌሎች የማካፈል ባሕርይ ማዳበርህ ዕቃን የመጣል አባዜ የኋላ ኋላ በአመለካከትህ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን መጥፎ ተጽዕኖም እንድትከላከል ይረዳሃል።
ለሌሎች ማካፈል መጽሐፍ ቅዱስ በእጅጉ የሚያበረታታው በጎ ምግባር ነው። (ሉቃስ 3:11፤ ሮሜ 12:13፤ 2 ቆሮንቶስ 8:14, 15፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:18) በእርግጥም የምድራችን ነዋሪዎች በሙሉ ለሌሎች የማካፈል ልማድ ቢኖራቸው ዓለማችን ምንኛ የተሻለች መኖሪያ ትሆን ነበር!
መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች መርካት
ባለው የሚረካ ሰው ደስተኛ ይሆናል። ይህ በሁሉም ቦታ የሚሠራ ሐቅ ነው። “በትንሽ ነገር የማይረካ ሰው በምንም ነገር አይረካም” የሚል አንድ የግሪካውያን አባባል አለ። ጃፓናውያን ደግሞ “ባለው የማይረካ ሰው ሁልጊዜ ድሃ ነው” የሚል አባባል አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስም ባለን መርካት እንዳለብን ጠበቅ አድርጎ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8፤ ፊልጵስዩስ 4:11
እርግጥ ነው፣ ባለን መርካት እንድንችል “ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ለውጥ” ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ሱዛነ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ያለ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ተገንዝባ ነበር። “የምፈልገውን ነገር ሁሉ ማግኘት ስለማልችል ባለኝ ነገር መርካት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። አሁን በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ” ስትል ተናግራለች።
ባለን ነገር መርካታችን ደስታ እንደሚያስገኝልን የታመነ ነው። እርጅናን በተመለከተ ከፍተኛ ምርምርና ጥናት ያካሄዱት ቡልጋሪያዊው ፕሮፌሰር አርጊር ሃድጂኽሪስቴፍ “ዋናውና መሠረታዊው ችግር የሰው ልጅ ባለው ትንሽ ነገር የማይረካ መሆኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ባለን መርካታችን ለጤንነታችን የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ሲናገሩም እንዲህ ብለዋል:- “እንደ ጎረቤቱ ሳይሆን እንደ ራሱ የሚኖርና ባለው ነገር የሚረካ ሰው ከፉክክር ብሎም ከውጥረት ነፃ የሆነ ሕይወት መኖር ይችላል። ይህ ደግሞ ለነርቮች ጤንነት በጣም ጠቃሚ ነው።”
በእርግጥም የመጣል አባዜ የተጠናወተው ኅብረተሰብ እውነተኛ ደስታ ሊያገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ብዙ ሰዎች ይህን እውነታ እየተገነዘቡ የመጡ ይመስላል። አንተስ?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆች ምግብ እንዳያባክኑ ማሠልጠን ያስፈልጋል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ብክነትን በማስወገድ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማትጠቀምበትን ነገር ከመጣል ይልቅ ለምን ለሌሎች አትሰጠውም?