በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

የማትፈልገውን ዕቃ ምን ታደርገዋለህ ተብለህ ብትጠየቅ ምን ብለህ ትመ​ልሳለህ? “እጥለዋለኋ” የሚል ፈጣን ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቆሻሻን ማስወገድ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። የት ነው የሚጣለው? በኢጣሊያ የሚገኝ አንድ የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር እንደገመተው ባሕር ውስጥ የተጣለ አንድ ጠርሙስ እስኪበሰብስና ወደ አፈርነት እስኪለወጥ ድረስ 1, 000 ዓመታት ይወስዳል። በአንጻሩ ደግሞ ለስላሳ ወረቀቶች ለመበስበስ ሦስት ወር ብቻ ይወስድባቸዋል። የሲጋራ ቁራጭ በባሕር ውስጥ ሳይበሰብስ ለ5 ዓመታት ያህል የሚቆይ ሲሆን ፌስታሎች ከ10 እስከ 20 ዓመት፣

ከናይለን የሚሠሩ ጨርቆች ከ30 እስከ 40 ዓመት፣ ጣሳዎች እስከ 500 ዓመትና ማይካ ወይም ፕላስቲኮች ደግሞ እስከ 1, 000 ዓመት ድረስ ሳይበሰብሱ ሊቆዩ ይችላሉ።

በየጊዜው የሚጣለው እንዲህ ያለው ቆሻሻ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ የንግዱ ዓለም የተለያዩ ምርቶችን በገፍ እያቀረበ ሲሆን የማስታወቂያው ዓለም ደግሞ ሁሉም ነገር እንደሚያስፈልገን ሊያሳምነን ይሞክራል። ዘ ጋርዲያን የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ “የማስታወቂያ ድርጅቶች ከዚህ በፊት አስበነው የማናውቀው ነገር እንደሚያስፈልገን አድርገን እንድናስብ ያደርጉናል” ሲል ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። በእርግጥም ገበያ ላይ የዋለ አዲስ ነገር ሁሉ ሳያመልጠን ለመግዛት ልንፈተን እንችላለን። በማስታወቂያው ዓለም “አዲስ” የሚለው ቃል “የተሻለና የላቀ” ነገርን ለማመልከት የሚሠራበት ሲሆን “አሮጌ” የሚለው ደግሞ “ተራና ጊዜ ያለፈበት” ነገርን ለማመልከት ይሠራበታል።

በመሆኑም ብዙውን ጊዜ አሮጌውን ከመጠገን ይልቅ አዲስ እንድንገዛ ግፊት ይደረግብናል። አንዳንዶች ያረጀውን ከመጠገን ይልቅ በአዲስ መተካት የተሻለ እንደሆነና ወጪንም እንደሚቀንስ ይናገራሉ። አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ግን አሮጌውን መጣልና በአዲስ መተካት ወጪ የሚጨምር ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ ነው።

በዛሬው ጊዜ ለገበያ የሚቀርቡት ብዙዎቹ ምርቶች ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲያገለግሉ ተደርገው የሚሠሩ ናቸው። አንዴ ከተበላሹ ወይም ካረጁ መጠገን የማይቻል በመሆኑ ዕቃዎችን በምንገዛበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለሸማቾች የሚዘጋጅ አንድ የጀርመን መጽሔት “የምንገለገልባቸው ዕቃዎች ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠረ መጥቷል። ትናንት እንደ ‘ፋሽን’ ይታይ የነበረው ነገር ዛሬ ‘ጊዜ ያለፈበት’ ይሆንና ቆሻሻ ውስጥ ይጣላል። በመሆኑም አንዳንድ ማስተካከያ ተደርጎላቸው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ዕቃዎች በየዕለቱ ምንም ዋጋ እንደሌለው ነገር ይጣላሉ!” ሲል ገልጿል።

ገበያ ላይ የዋለውን ሁሉ መግዛት ሸማቹን ይጠቅመዋል? እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የሚጠቅመው ካዝናቸውን መሙላት ብቻ የሚታያቸውን የንግድ ተቋማት ነው። ይሁንና ዲ ቬልትዎኽ የተባለው ሳምንታዊው የስዊስ ጋዜጣ “እያንዳንዱ ሰው አንዴ የገዛውን የቤት ቁሳቁስና መኪና ዕድሜ ልኩን ቢጠቀምበት ይቅርና የዕቃውን ወይም የመኪናውን ዕድሜ በእጥፍ ቢያስረዝመው የኢኮኖሚ ውድቀት መከሰቱ የማይቀር ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። የኢኮኖሚ ውድቀት ሸማቹ ኅብረተሰብ ከሥራ እንዲፈናቀል የሚያደርግ በመሆኑ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ጥርጥር የለውም። ታዲያ በገፍ የሚጣለው ቆሻሻ ለፈጠረው ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

ቆሻሻውን ማስወገድ፣ እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ወይስ መቀነስ?

አንዳንድ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች ቆሻሻቸውን በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ማራገፍ ቀላል ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ዘገባ እንዳመለከተው “በናይጄሪያ በቆሻሻ በተሞላ አንድ ሥፍራ በዝገት ከተበሉ ከ8, 000 የሚበልጡ በርሜሎች ውስጥ እየተንጠባጠበ የወጣ 3, 500 ሜትሪክ ቶን መርዛማ ኬሚካል አፈሩንና ከመሬት በታች ያለውን ውኃ እንደበከለ ታውቋል።” በዚህ መንገድ ቆሻሻን ለማስወገድ መሞከር የማያዛልቅ ከመሆኑም በላይ አሳቢነት አለማሳየት ነው።

የማይፈለጉ ዕቃዎችን እንዲሁ ከማስወገድ ይልቅ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቢደረግስ? እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ዘዴ ሸማቾች ተጠቅመው የሚጥሏቸውን ዕቃዎች በዓይነት በዓይነት ለይተው እንዲያስቀምጡ ይጠይቅባቸዋል። በአንዳንድ አገሮች ነዋሪዎች እንዲህ የማድረግ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው። ባለ ሥልጣናት ሕዝቡ ቆሻሻ በሚጥልበት ጊዜ ወረቀቱን፣ ካርቶኑን፣ ብረት ነክ የሆነውን ዕቃ፣ ጠርሙሱንና ሌላውንም ቆሻሻ ለየብቻ እየለያየ እንዲጥል ሊያሳስቡ ይችላሉ። ጠርሙሶቹን ደግሞ እንዲሁ እንደ ቀለማቸው ዓይነት መለያየት ያስፈልግ ይሆናል።

የማይፈለጉ ዕቃዎችን እንደገና አገልግሎት ላይ ማዋል የራሱ የሆነ ጠቃሚ ጎን እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። አልሙኒየም እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ “ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የሚቆጥብ” ከመሆኑም ሌላ “የአሉሚኒየም ማዕድንን ለማውጣት በሚካሄደው ቁፋሮ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሊቀንስ” ይችላል ሲል 5000 ዴይስ ቱ ሴቭ ዘ ፕላኔት የተሰኘው መጽሐፍ ገልጿል። ይኸው መጽሐፍ አክሎ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “አዲስ ወረቀቶችን ለማምረት ከሚያስፈልገው ኃይል ላይ ግማሽ ያህሉን፣ ከውኃው መጠን ላይ አንድ አሥረኛውን ብቻ በመጠቀም ያገለገሉ ወረቀቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። . . . ብዙዎቹን ተረፈ ምርቶች እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። . . . የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የራሳቸውን ተረፈ ምርቶች እንደገና ሊጠቀሙባቸው በማይችሉበት ጊዜ እንኳን ሌሎች እንዲጠቀሙባቸው መልሰው ማምረት ይችላሉ። . . . በሆላንድ ከ1970ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ የተረፈ ምርት ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት ስልት ተቀይሶ በተሳካ ሁኔታ ሲሠራበት ቆይቷል።”

ሌሎች ባለሥልጣናት ደግሞ ቆሻሻን ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ ከማፈላለግ ይልቅ መጀመሪያውኑ ቆሻሻን በተቻለ መጠን ማስቀረት የተሻለ አማራጭ ሆኖ አግኝተውታል። ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ የሰው ልጅ “ብክነት ከሚያስከትል የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲላቀቅና . . . የሚያስወግደውን ቆሻሻም ሆነ የምርት ፍጆታውን የሚቀንስ ቆጣቢ የሆነ ኅብረተሰብ ለመፍጠር” ከተፈለገ “አሁኑኑ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት” አስጠንቅቋል።

ይሁንና “ብክነት ከሚያስከትል የኢኮኖሚ ሥርዓት” መላቀቅ የሚፈልጉ ሁሉ የሚገዟቸውን ዕቃዎች መጠገን የማይችሉበት ደረጃ ላይ እስካልደረሱ ድረስ ላለመጣልና ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም ፈቃደኞች ሆነው መገኘት አለባቸው። ሊያገለግሉ የሚችሉ ዕቃዎችን ስላላስፈለጉ ብቻ ከመጣል ይልቅ ሊጠቀሙባቸው ለሚችሉ ሌሎች ሰዎች መስጠት ይገባል። በዳርምስታት የሚገኘው የጀርመን ኦኮ ኢንስቲትዩት (የሥነ ምሕዳር ኢንስቲትዩት) ቢሮ በሰጠው ግምታዊ መረጃ መሠረት “ሳታባክን ጥቅም ላይ አውለው” የሚለውን መሠረታዊ መመሪያ አጥብቆ የሚከተል ቤተሰብ የሚጥለው ቆሻሻ ሌላው ቤተሰብ ከሚጥለው ቆሻሻ 75 በመቶ ያነሰ ነው።

ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ቤተሰቦች እንዲህ ያሉ መሠረታዊ መመሪያዎችን ሊከተሉ ይችላሉ ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል። የሰው ልጅ ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ የገጠመው ችግር ሌሎች በጣም አሳሳቢ ችግሮች እንዳሉ የሚጠቁም ነው። በዛሬው ጊዜ መጣል በሚቀናው አባካኝ ኅብረተሰብ መካከል የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች የመጣል አባዜ ተጠናውቷቸዋል ማለት ይቻላል። እስቲ እንዲህ ያለውን ዝንባሌና ዝንባሌው ሊያስከትል የሚችለውን የከፋ መዘዝ እንመርምር።

የመጣል አባዜ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ

የፍጆታ ምርቶችንም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ቶሎ የመጣል አባዜ ቀላል ከሆነ ብክነት የከፋ ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል። ሰዎች አድናቆትና አሳቢነት የጎደላቸው እንዲሆኑና ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ምንም ያልተነኩ ምግቦችንና ሌሎች ዕቃዎችንም የመጣል ልማድ እንዲጠናወታቸው ሊያደርግ ይችላል። ራስ ወዳድና ከልክ በላይ መራጭ የሆኑ እንዲሁም ፋሽን የሚከተሉ ሰዎች ያልተበላሹና ሊያገለግሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን፣ ልብሶችንና ሌሎች ዕቃዎችን በየጊዜው በአዲስ መተካት እንዳለባቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ለሚገለገሉባቸው ንብረቶች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ያላቸው አመለካከትም ሊዛባ ይችላል። የተጣሉ የቤት ቁሳቁሶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተቋቋመ አንድ የጀርመን ፕሮጀክት በቅርቡ እንዲህ ብሏል:- “ለአምስት ዓመት ተጠቅመንባቸው ለሰለቹንና በአዲስ ተክተን ለጣልናቸው የሳሎን ቤት ዕቃዎች የሚኖረን አመለካከት ለሰዎች በሚኖረን አመለካከትም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ጥያቄው ኅብረተሰባችን እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ታግሶ የሚኖረው እስከ መቼ ድረስ ነው የሚል ነው።” ዘገባው በመቀጠል “አንድ ሰው ሥራውን በከፍተኛ ብቃትና ቅልጥፍና ማከናወን እየተሳነው ሲመጣ በሌላ ሰው እንዲተካ ይደረጋል። ሠራተኛ እንደሆነ ሞልቷል!” ሲል ገልጿል።

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት አል ጎር ኧርዝ ኢን ዘ ባላንስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን አግባብነት ያለው ጥያቄ አንስተዋል:- “የምንገለገልባቸውን ነገሮች ለተወሰነ ጊዜ ተጠቅመንባቸው ልንጥላቸው እንደሚገባን ሆኖ እየተሰማን ከመጣ እንደ እኛው ላሉ ሰዎችም ያለን አመለካከት እየተለወጠ መጥቶ ይሆን? . . . እያንዳንዱ ሰው ላለው የራሱ የሆነ ባሕርይና ተሰጥኦ የነበረን ግምት ቀስ በቀስ እየጠፋ መጥቶ ይሆን?”

ሰዎች ለሌሎች ያላቸው አድናቆትና አክብሮት እየጠፋ ከሄደ ወዳጆቻቸውን ወይም የትዳር ጓደኞቻቸውን በቀላሉ ሊተዉና ይህን በማድረጋቸውም ምንም ጥፋት እንደፈጸሙ ሆኖ ላይሰማቸው ይችላል። ዙትዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “በዓመት ሁለት ጊዜ አዳዲስ ልብሶች፣ በየአራት ዓመቱ አዲስ መኪና፣ በየአሥር ዓመቱ ደግሞ ሙሉ የሳሎን ቤት ዕቃ እንገዛለን። የዕረፍት ጊዜያችንን የምናሳልፍበትን ቦታ በየዓመቱ እንቀያይራለን፤ ቤት እንለውጣለን፣ ሥራ እንቀይራለን። ታዲያ የትዳር ጓደኛችንንስ መቀየራችን ይቀራል?”

በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ማንኛውም ነገር አሰልቺ ከሆነባቸው ከመጣልና ከመተው ወደኋላ የሚሉ አይመስልም። ለምሳሌ ያህል አውሮፓ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አገር በ1999 በግምት 100, 000 የሚሆኑ ድመቶችንና 96, 000 ውሾችን ባለቤቶቻቸው እንደጣሏቸው ተነግሯል። በዚህች አገር የሚኖሩ አንዲት የእንስሳት መብት ተሟጋች የአገራችን ሰዎች “የቤት እንስሶቻቸውን ለዘለቄታው የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሆኖ አይሰማቸውም። መስከረም ላይ ትንሽ ቡችላ የገዙ እንደሆነ [ከአንድ ዓመት በኋላ ነሐሴ ላይ እረፍት ሲወጡ] ጥለውት ይሄዳሉ” ብለዋል። ከዚህ ሁሉ ይበልጥ የከፋው ደግሞ ሰዎች ለሰብዓዊ ሕይወትም ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱ ነው።

ለሕይወት አክብሮት አለማሳየት

በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ዋጋ እንዳለው አድርገው የሚያስቡ አይመስልም። እንዴት? ለምሳሌ ያህል በአውሮፓ ውስጥ እየታተመ የሚወጣ አንድ መጽሔት በቅርቡ እንዳለው ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ወጣቶች ሕይወትን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ከምንጊዜውም በበለጠ መዳፈር ጀምረዋል። ሕይወታቸውን ሊያሳጧቸው በሚችሉ አደገኛ ስፖርቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ለጥቂት ደቂቃዎች ደስታ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አሳልፈው ከመስጠት ወደኋላ አይሉም! ስግብግብ የሆኑ ነጋዴዎች ደግሞ እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ትርፍ ለማጋበስ ይጠቀሙበታል። አንድ ጀርመናዊ የፖለቲካ ሰው አደገኛ ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ ሰዎች “ብዙውን ጊዜ ከሰው ሕይወትና ደህንነት ይበልጥ የሚያሳስባቸው ገንዘብ ማግኘታቸው ነው” ብለዋል።

ፅንስ ስለማስወረድስ ምን ለማለት ይቻላል? የዓለም የጤና ድርጅት እንደገመተው ከሆነ “በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 75 ሚልዮን ሕፃናት ያለ ወላጆቻቸው ፍላጎት ይፀነሳሉ። ብዙዎቹ ሴቶች ያላቸው አማራጭ ማስወረድ ብቻ ነው።” ሕፃናት ከተወለዱም በኋላ እንኳን ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ ነው። ኦ ኤስታዶ ደ ሳኦ ፓውሎ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ “በየመንገዱ የሚጣሉ ሕፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።” አንተ በምትኖርበት አካባቢም እንዲህ ዓይነት ችግር አለ?

ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በየጊዜው ሲፈጸሙ የምንመለከታቸው ነገሮች ሰብዓዊ ሕይወት በአብዛኛው የትም እንደሚጣል ተራና አልባሌ ነገር ተደርጎ የሚታይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። ተወዳጅነት ባተረፉ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጸመው የኃይል ድርጊት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። በአንድ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ብቻ እንኳ እንደ “ጀግና” የሚታዩ ገጸ ባሕርያት “ክፉ” ተደርገው የሚታዩ በርካታ ሰዎችን ይጨፈጭፋሉ። በምድር ዙሪያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወንጀሎች ይፈጸማሉ። ሌቦችና ቀማኞች ጥቂት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ወይም አላንዳች ምክንያት ሰዎችን ይገድላሉ። እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የሽብርተኝነት ድርጊቶች፣ የጎሳ ማጥፋት ዘመቻዎችና የጅምላ ጭፍጨፋዎች ሲፈጸሙ በዜና ማሰራጫዎች እንሰማለን። በእነዚህ ሁሉ አረመኔያዊ ጭፍጨፋዎች የሰው ልጅ ሕይወት እየተቀጠፈ እንደ አልባሌ ነገር ይጣላል።

መጣል በሚቀናው ኅብረተሰብ መካከል የምንኖር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ልማድና ዝንባሌ እንዳይጠናወተን መከላከል እንችላለን። የሚቀጥለው ርዕስ በእንዲህ ዓይነት ኅብረተሰብ መካከል መኖራችን ሊያሳድርብን የሚችለውን ተጽዕኖም ሆነ የተዛባ አመለካከት ለመቋቋም ምን ሊረዳን እንደሚችል ያብራራል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ ቦታዎች፣ ያገለገሉ ዕቃዎች ዳግመኛ ተመርተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስገድድ ሕግ አለ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

በየጊዜው የሚለዋወጠውን ፋሽን ለመከተል ስትል ምንም ያልሆኑ ልብሶችን እየጣልክ አዲስ ልብስ ትገዛለህ?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማኅፀን ያለ ፅንስ በእንክብካቤ ሊያዝ እንጂ የትም እንደሚጣል ተራ ነገር ሊታይ አይገባውም

[ምንጭ]

Index Stock Photography Inc./BSIP Agency

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጥቂት ደቂቃዎች ደስታ ሲባል ራስን አደጋ ላይ መጣል ሕይወትን እንደ ማራከስ ይቆጠራል