አምላክ የሚሰማቸው ጸሎቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ የሚሰማቸው ጸሎቶች
“ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፣ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛል፣ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።”–ሉቃስ 11:9, 10
ብዙ ክርስቲያኖች ከላይ በተጠቀሱት የኢየሱስ ቃላት ሙሉ በሙሉ በመተማመንና አምላክ እንደሚወዳቸውና እንደሚንከባከባቸው እርግጠኞች በመሆን ለችግሮቻቸውና ለሚያስጨንቋቸው ነገሮች መፍትሔ ለማግኘት ወደ አምላክ ይጸልያሉ። ሆኖም አንዳንዶች ጸሎቶቻቸው ምላሽ እስኪያገኙ መጠበቅ ተስፋ አስቆራጭ ይሆንባቸዋል። ጸሎቶችህ ተሰሚነት እንደሌላቸው ይሰማሃልን? አምላክ ጸሎትህን ይሰማልን?
ጸሎቶቻችን ምላሽ ያላገኙ ቢመስለንም እንኳን ይህ ማለት አምላክ ያቀረብነውን ጸሎት አልሰማም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ጴጥሮስ 3:12) ስለዚህ ይሖዋ አምላክ ጻድቃን ድምፃቸውን እያሰሙም ይሁን በልባቸው የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። (ኤርምያስ 17:10) ይሖዋ ጸሎቱን የሚያቀርበው ሰው ራሱ በሚገባ ያልተገነዘበውን ወይም ያላወቀውን ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን ጭምር ይመረምራል።—ሮሜ 8:26, 27
ሆኖም ጸሎቶቻችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከተፈለገ የተወሰኑ ብቃቶችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ጸሎት መቅረብ ያለበት ለኢየሱስ፣ ለአንድ “ቅዱስ” ወይም ለምስል ሳይሆን ለአምላክ ብቻ ነው። (ዘጸአት 20:4, 5) ከዚህም በላይ ጸሎት መቅረብ ያለበት የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። (ዮሐንስ 14:6) ይህ ማለት ኢየሱስ ጸሎቶቻችንን ከሰማ በኋላ መልእክቱን ለአምላክ ያስተላልፈዋል ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። ከዚያ ይልቅ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ በኢየሱስ ስም መቅረባችን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እንደተገነዘብንና ወደ አምላክ መቅረብ የቻልነው በእሱ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ መሆኑን አምነን እንደተቀበልን የሚያሳይ ነው።—ዕብራውያን 4:14-16
ጸሎት ስናቀርብ እምነት ሊኖረን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።” (ዕብራውያን 11:6) አንድ ሰው እንደዚህ ዓይነት እምነት እንዳለው እንዴት ማወቅ ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ያዕቆብ 2:18) አዎን፣ እምነታችን በሥራ ሲገለጽ ሥራችን ደግሞ በተራው አምላክን እንደምንወድና ልናስደስተው እንደምንፈልግ ያሳያል።
የአምላክ አገልጋዮች በጸሎታቸው እንዲጸኑም ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ በመግቢያው ላይ በተጠቀሰው የሉቃስ 11:9, 10 ሐሳብ ይህንን ግልጽ አድርጎታል። ደግሞስ አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ አንድ ጊዜ ብቻ ጸልዮ ካቆመ ይህ ሰው ጉዳዩ በጣም አሳስቦታል ማለት ይቻላል?
አምላክ ቃል የገባው ምን ለማድረግ ነው?
የቱንም ያህል ደጋግመንና አጥብቀን ብንጸልይም የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆኑት የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ደስተኞች እንደሚሆኑ ቢናገርም ሕይወታቸው ከችግር ነጻ ይሆናል አላለም። (ማቴዎስ 5:3-11) ይሁን እንጂ ሐዘን፣ ረሃብ፣ ጥማት ወይም ስደት ቢደርስባቸውም እንኳን ደስተኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል።
ኢየሱስ የጠቀሰው ደስታ የተመቻቸ ሁኔታ በማግኘታችን ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን በማገልገላችን የምናገኘው ውስጣዊ እርካታ ነው። በመሆኑም ችግሮች እያሉም እንኳን በተወሰነ መጠን ደስተኞች መሆን እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 12:7-10
የግል ችግሮችን መቋቋም
ይህ ማለት ታዲያ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ስለማግኘት ወይም የቤተሰብ፣ የሥራ ወይም የጤና ችግሮችን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ወደ አምላክ መጸለይ ዋጋ የለውም ማለት ነው? አይደለም። አምላክ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለመለወጥ ቃል ባይገባም እንኳን ሁኔታዎቹን ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ጥበብ ይሰጠናል። ያዕቆብ ፈተናዎችን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) ስለዚህ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ይመራናል። ይህም ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድንገነዘብና ተግባራዊ እንድናደርጋቸው ይረዳናል።
እርግጥ ነው፣ የአምላክ መንፈስ በእኛ ቦታ ሆኖ ውሳኔ አያደርግልንም። ከዚህ በተቃራኒው የግል ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ችግር ሲያጋጥመን በጉዳዩ ላይ ምርምር በማድረግ ሁኔታውን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለመመልከት ጥረት እናደርጋለን? ይህ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ተግባር ነው። (ያዕቆብ 2:18) አምላክ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚያስችለን መመሪያ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ በመጠየቅ መፍትሔ ለማግኘት የማያቋርጥ ሙከራ እናደርጋለን? (ማቴዎስ 7:7, 8) ከጉዳዩ ጋር በተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በጥንቃቄ ምርምር አድርገናል? የአምላክ ቃል “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ[ን]” እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
አምላክ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ችግሮቻችንን በሙሉ ማስወገድ ቢችልም ነፃ ምርጫ ሰጥቶናል። የሚያሳዝነው ብዙዎች ነፃነታቸውን ሌሎችን በሚጎዳ መንገድ ይጠቀሙበታል። በመሆኑም የምንጸልይባቸው አንዳንዶቹ ችግሮች አምላክ አዲስ ሥርዓት እስከሚያቋቁምበት ጊዜ ድረስ ላይወገዱ ይችላሉ። (ሥራ 17:30, 31) እንዲወገድልን የምንፈልገው ችግር እንደ ወንጀል ወይም ጦርነት ያለ እኛ በምንኖርበት አካባቢ የሚገኝ ሁኔታ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ተቃዋሚዎች የሚያመጡትን ተጽዕኖ መቋቋም ይኖርብን ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 4:4) አምላካዊ ፍርሃት በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ አንዳንድ ሁኔታዎች ላይስተካከሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል።
ያም ሆኖ ግን አምላክ አገልጋዮቹን ይወዳቸዋል እንዲሁም ሊረዳቸው ይፈልጋል። መንግሥቱ አለተቀናቃኝ በምድር ላይ በሚገዛበት ወቅት በዓለም ላይ የሚገኙትን አሳዛኝ ችግሮች በሙሉ ያስወግዳቸዋል። (ራእይ 21:3, 4) ያ ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችለን መመሪያ እንዲሰጠን አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል። እንደዚህ ካደረግን ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኢሳይያስ 41:10 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።”