በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በግ መቁጠር አያስፈልግም

ስር የሰደደ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በመላው ዓለም የተስፋፋና ከ10 ሰዎች መካከል አንዱን የሚያጠቃ ችግር መሆኑን ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንቅልፍ ማጣት በሚያስከትለው ሕመምና አደጋ ምክንያት በየዓመቱ 35 ቢልዮን ዶላር የሚያክል ኪሣራ እንደሚደርስ ሳይንቲስቶች ይገምታሉ። እንቅልፍ የማጣት ችግር ያለባቸው ሰዎች እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እንቅልፍ የማጣት ችግር ያለባቸውን ሰዎች በሦስት ቡድን በመከፋፈል በመጀመሪያው ቡድን ውስጥ የሚገኙት ሰዎች እንደ ፏፏቴ ወይም የእረፍት ማሳለፊያ ቦታ የመሰለ የሚያምርና የሚያስደስት አካባቢን እያሰቡ እንዲተኙ፣ በሁለተኛው ቡድን የተመደቡት ሰዎች በሐሳባቸው በግ እንዲቆጥሩና በሦስተኛው ቡድን የተመደቡት ደግሞ ራሳቸው የመሰላቸውን ዘዴ እንዲጠቀሙ አደረጉ። በሁለተኛውና በሦስተኛው ቡድን የተመደቡት እንቅልፍ ለመተኛት ከወትሮው የበለጠ ረዘም ያለ ጊዜ ሲወስድባቸው በአንደኛው ቡድን የተመደቡት ግን በአማካይ ከወትሮው 20 ደቂቃ አስቀድመው መተኛት ችለዋል። ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት አሊሰን ሃርቬ በግ መቁጠር “የሚያስጨንቁ ሐሳቦችን ለማስወገድ የማያስችል አሰልቺ ነገር” ስለሆነ ጥቅም የለውም ብለዋል።

ዝናብ የሚስቡ ደኖች

ዶክተር ፖል ሬዴል እና ዶክተር ዴቪድ ማክጃነት የተባሉት አውስትራሊያውያን ሳይንቲስቶች እንዳሉት ከ900 ሜትር በላይ ከፍታ ላይ የሚገኙ የሐሩር ክልል ደኖች “መሬት ላይ ከሚወርደው ዝናብ 40 በመቶ የሚበልጥ እርጥበት ከዳመና ውስጥ” ይስባሉ። የኮመንዌልዝ ሳይንሳዊና ኢንዱስትሪያዊ ምርምር ድርጅት እንዳለው ከሆነ “ዝቅ ብለው የሚገኙ ደመናዎች፣ ጭጋጎችና ጉሞች በደኑ ውስጥ አዘውትረው ስለሚያልፉ የያዙት እርጥበት ወደ ጤዛነት እየተለወጠ ወደ መሬት ይወርዳል።” በዚህ መንገድ በሚልዮን ሊትር የሚለካ ውሃ ወደ ወንዞች ይገባል። “ደኖች በሚመነጠሩበት ጊዜ ግን ወደ አፈር የሚደርሰው እርጥበት በእጅጉ ይቀንሳል።”

ሚዛናዊ ያልሆነ ፍጆታ

ባሁኑ ጊዜ ከምድር ነዋሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት 86 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችንን ምርቶችና አገልግሎቶች እንደሚፈጁ ዘ ስቴት ኦቭ ወርልድ ፖፑሌሽን 2001 ዘግቧል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀው ይህ ዘገባ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች በሚኖሩና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በሚኖሩ መካከል “በጣም ከፍተኛ የሆነ ‘የፍጆታ ልዩነት’ ” አለ በማለት ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ “በዛሬው ጊዜ በኢንዱስትሪ በበለጸገ አገር የሚወለድ አንድ ሕፃን ዕድሜውን በሙሉ የሚፈልገው ፍጆታና የሚፈጥረው የአየር ብክለት በታዳጊ አገሮች የሚወለዱ ከ30 እስከ 50 የሚሆኑት ሕፃናት ከሚደርሳቸው ፍጆታና ከሚፈጥሩት ብክለት የበለጠ ነው። በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩት ሕዝቦች ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ አንድ አምስተኛ ሲሆኑ በእነሱ ምክንያት የሚፈጠረው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ወደ ከባቢ አየር ከሚገባው ጠቅላላ መጠን ከግማሽ በላይ ይሆናል። አንድ አምስተኛ በሚሆኑት ድሃ ሕዝቦች ሳቢያ የሚፈጠረው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ግን ከ3 በመቶ አይበልጥም” ይላል ዘገባው። ከዚህም በላይ በበለጸጉ አገሮች አንድን ሰው ለማኖር የሚያስፈልገው ጥቅም ላይ የሚውል መሬት ወይም የባሕር መጠን ባላደጉ አገሮች የሚኖር ሰው ከሚያስፈልገው በአራት እጥፍ ገደማ ይበልጣል።

የአመጋገብ ልማድ መዛባት መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶች

የለንደኑ ዘ ታይምስ ጋዜጣ “ወላጆች ልጆቻቸው አኖሬክስያ ወይም ቡሊምያ በሚባሉት የአመጋገብ ችግሮች የመያዝ አዝማሚያ እንዳላቸው ከአመጋገባቸው ማስተዋል ይችላሉ” ይላል። በአመጋገብ ልማድ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የተቋቋመው ማኅበር ወላጆችና አሳዳጊዎች የልጆቹ የአመጋገብ ልማድ መዛባቱን ችግሩ ከመባባሱ በፊት ሊያውቁ የሚችሉበትን መመሪያ አውጥቷል። ምግብ በትናንሹ መቆንጠር ወይም እስከ አምስት ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ አፍ ውስጥ ምግብ ይዞ መቆየት ጠቋሚ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የተዛባ የአመጋገብ ልማድ ያለባቸው አንዳንዶች ሰፋ ያለ ልብስ ይለብሱና የበሉ እየመሰሉ ምግቡን ልብሳቸው ውስጥ ይደብቃሉ። በተጨማሪም የጤነኛ ሰው ውፍረት ኖሯቸው የተነሷቸውን ፎቶግራፎች እንዲያስወግዱላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ማኅበሩ ወላጆች እነዚህን ምልክቶች ችላ ብለው ከማለፍ ይልቅ ስለታዘቧቸው ነገሮች በግልጽ መወያየት እንዳለባቸው ይመክራል።

ከሙቀት መለኪያ የሚወጣ መርዝ

“በአንድ ቴርሞሜትር ውስጥ የሚገኝ ሜርኩሪ አምስት ሄክታር ስፋት ያለው ሐይቅ ሊመርዝ የሚችል ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ ከተሰበሩ ቴርሞሜትሮች እየወጣ ወደ ወንዞች የሚገባው ሜርኩሪ 170 ኩንታል ይሆናል” ይላል ናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት። ይህ ሜርኩሪ ወደ አሣዎች አካል የሚገባ በመሆኑ አሣዎቹን በሚመገቡ ሰዎች ላይ የነርቭ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ቦስተንን ጨምሮ በበርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች የሜርኩሪ ቴርሞሜትር እንዳይሸጥ ታግዷል። አንዳንድ ሱቆች የሜርኩሪ ቴርሞሜትር ሲቀርብላቸው በኤሌክትሮኒክ ቴርሞሜትሮችና ብዙም አደጋ በማያስከትሉ ሌሎች መሣሪያዎች ይቀይራሉ።

ልከኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

ሌክስፕሬስ የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት “(እንደ ሩጫ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም መዋኘት ያሉ) የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በሳምንት ሦስት ጊዜ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ለሚያክል ጊዜ ማድረግ ጠቃሚ ነው” ይላል። ከመጠን ካለፈ ግን በጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ከልክ ያለፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጋጠሚያዎችን ሊያዳክም፣ ጅማት ሊበጥስ፣ ውልቃት ሊያደርስ፣ አጥንት ሊሰብር፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የምግብ መፈጨት ችግር፣ የአጥንት መመንመንና ልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል። ሌክስፕሬስ እንደዘገበው “በፈረንሳይ አገር በከባድ የአካል እንቅስቃሴ ምክንያት 1, 500 የሚያክሉ ጠንካራ ስፖርተኞች በየዓመቱ ይሞታሉ።” በፓሪስ በፒትዬ ሳልፔትርዬር ሆስፒታል የስፖርት ሕክምና ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ስቴፋን ካስክዋ ለሆስፒታል አልጋ ለተዳረጉ በርካታ “የእሁድ ስፖርተኞች” የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- አዘውትራችሁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጉ፤ ይሁን እንጂ ከልባችሁ አቅም ከ75 በመቶ ያለፈ መሆን የለበትም።

በሕንድ አገር በትንባሆ ምክንያት የሚመጣ የልብ ሕመም

“[በሕንድ የሚገኙ] ከፍተኛ የልብ ስፔሻሊስቶች የልብና የደም ሥር ሕመሞች በጣም እየበዙ እንደመጡ ተናግረዋል” በማለት ሙምባይ ኒውስላይን የተሰኘው ጋዜጣ ገልጿል። “በጃስሎክ ሆስፒታል የካርዲዮሎጂ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር አሽዊን ሜታ እንዳሉት ከሆነ ሕንዳውያን በተፈጥሯቸው በልብ በሽታ የመያዛቸው ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው።” በተለይ ግን አሳሳቢ የሆነው “ብዙ በማጨስ ምክንያት የልብ ችግር የሚያጋጥማቸው” ወጣቶች እየበዙ መሄዳቸው ነው። በቦምቤ ሆስፒታል በልብ ሕክምና አማካሪ ሆነው የሚሠሩት ዶክተር ፒ ቲዋሪ ሥር ነቀል እርምጃ ካልተወሰደ ሕንድ አንድ ቀን በልብ በሽታ የአንደኛነቱን ቦታ መያዟ እንደማይቀር ያምናሉ። የሕንድ ጎረቤት በሆነችው ባንግላዴሽ ከ35 እስከ 49 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት አጫሾች ሲሆኑ “ገቢያቸው ባነሰ መጠን የአጫሾቹ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል” ይላል ዘ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ። እያንዳንዱ አጫሽ በአማካይ “ለሲጋራ የሚያወጣው ወጪ በአገሪቱ ውስጥ በነፍስ ወከፍ ለልብስ፣ ለቤት፣ ለጤናና ለትምህርት ከሚወጣው ጠቅላላ ወጪ በእጥፍ ይበልጣል።” በዚህች ድሃ አገር ለትንባሆ የሚወጣው ገንዘብ ለምግብ ቢውል ኖሮ 10.5 ሚልዮን የሚያክሉ ረሀብተኛ ሰዎች በቂ ምግብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገመታል።

ረዣዥም ሕንጻዎች አሁንም ተፈላጊነታቸውን አላጡም

“የመንትዮቹ ሕንጻዎች መደርመስ መሐንዲሶችና የሕንጻ ንድፍ ባለሙያዎች አዲስ ዓይነት ሥጋትና ፍርሐት እንዲያድርባቸው አድርጓል” ይላል ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት። “ይሁን እንጂ ጊዜያዊ ፍርሐትና ሥጋት ቢኖርም የሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ተፈላጊነት አልነጠፈም።” ይህ ከሆ​ነባቸው ምክንያቶች አንዱ በአንዳንድ አካባቢዎች መሬት በጣም ውድና እንደ ልብ የማይገኝ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ከተሞች የሚኩራሩበት ነገር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ መሥራት ማለት “ክብርና ዝና ማግኘት፣ ሥልጡንነትና ዘመናዊነት ነው” ይላሉ የማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ተቋም የሥነ ሕንጻና ፕላን ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዊልያም ሚቸል። ይሁን እንጂ የሕንፃ ንድፍ ባለሙያዎች ሕንጻዎችን ይበልጥ አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዴት መሥራት እንደሚቻል በመነጋገር ላይ ናቸው። ሕንጻዎች በፍንዳታ ሊናጉ በማይችሉ ጠንካራ ግድግዳዎችና መስኮቶች ሊሠሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ክብደት የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። በቻይና በአንድ ሕንፃ ላይ በየ15ቱ ፎቅ ልዩነት ባዶ የሆነ ሰፊ ክፍተት እንዲኖር የሚያስገድድ ሕግ አለ። በሌሎች አገሮችም ለእሳት አደጋ ተከላካዮች ብቻ የሚያገለግል አሳንሱር ከመሬት እስከ ሕንጻው ጫፍ እንዲኖር፣ እንዲሁም ጭስ የማያስገባ የደረጃ መውጫ እንዲሠራ የሚያስገድድ ሕግ አለ። ከዓለም በርዝመቱ አንደኛ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው የሻንጋይ የዓለም የገንዘብ ማዕከል ሕንጻ ዲዛይነሮች ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል።

የጫጫታ መብዛትና የመስማት እክል

ፖሊቲካ የተባለው የፖላንድ ሳምንታዊ መጽሔት “በተማሪነት ዕድሜ ከሚገኙ አምስት ልጆች መካከል አንዱ፣ ከሦስት ትላልቅ የፖላንድ ዜጎች መካከል ደግሞ አንዱ የመስማት ችግር አለበት” ይላል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከሆነ ከፍተኛውን ድምፅ የሚፈጥሩት የትራፊክ እንቅስቃሴ፣ የሙዚቃና የቪድዮ ማጫወቻዎች እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያ መሣሪያዎች ናቸው። ስለ አካባቢ ሁኔታ የቀረበ አንድ ሪፖርት በዋርሶ የትራፊክ እንቅስቃሴ በጣም በመጨመሩ ምክንያት በከተማይቱ ውስጥ በሚገኝ አንድ አውራ ጎዳና ላይ የሚሰማው የድምፅ መጠን ወደ 100 ዴሲቤል ደርሷል። ልጆች ሲጫወቱ የሚያሰሙት ጫጫታም እዚሁ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ዳንስ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው ድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች እስከ 120 ዴሲቤል የሚደርስ የድምፅ መጠን ሲኖራቸው የሕመም ስሜት እንዲሰማ ከሚያደርገው የ130 እና የ140 ዴሲቤል የድምፅ መጠን የሚያንሰው በትንሹ ነው። እንደነዚህ ያሉት ከፍተኛ ድምፆች የመስማት እክል እንደሚያመጡ ሊቃውንት ይናገራሉ። ኢንስቲትዩት ኦቭ ፊዚዮሎጂ ኤንድ ፓቶሎጂ ኦቭ ሂሪንግ በተባለው ድርጅት የሚሠሩትና የአንገት በላይ ሕክምና ስፔሽያሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር ሄንሪክ ስካዢንስኪ “የመስማት እክል ከባድ የሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል። የመስማት እክል ያለባቸው ሰዎች ነጭናጮች፣ ነገሮችን ቶሎ መረዳት የማይችሉና የባዕድ ቋንቋዎችን ለመማር የሚከብዳቸው ናቸው” ብለዋል።