በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ ፍቅራቸውን የሚነፍጉኝ ለምንድን ነው?

ወላጆቼ ፍቅራቸውን የሚነፍጉኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ወላጆቼ ፍቅራቸውን የሚነፍጉኝ ለምንድን ነው?

“አባትና እናቴ ከመፋታታቸው በፊት አባቴ ወደ ባሕር ዳርቻዎች፣ ወደ ሬስቶራንቶች እንዲሁም ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመኪናው ይወስደን ነበር። አባትና እናቴ ሲፋቱ ግን ሁሉም ነገር አከተመለት። የአባቴ ባሕርይ ተቀየረ። እኔንም ጭምር ሳይፈታኝ አልቀረም።”​—ካረን *

ብዙ ወጣቶች እንደዚህ ይሰማቸዋል። እንደ ካረን ሁሉ እነዚህም ወጣቶች አባታቸው ወይም እናታቸው ለእነርሱ የነበራቸው ፍቅር እንደጠፋ ወይም ቀድሞውኑም ቢሆን ይወዷቸው እንዳልነበር ይሰማቸዋል። እንዲህ ስንል በወላጆችና በወጣቶች መካከል በሚከሰት ጊዜያዊ ግጭት ምክንያት የሚፈጠረውን ቅያሜ ወይም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ወላጆቻቸው ሲገሥጿቸው የሚሰማቸውን የቅሬታ ስሜት ማለታችን አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ትኩረትና ተግሳጽ ባለመስጠት ፍቅራቸውን ይነፍጓቸዋል። አለዚያም ደግሞ ኃይለ ቃል በመሰንዘር ወይም አካላዊ ድብደባ በማድረስ ልጆቻቸውን ይበድሏቸዋል።

በአባት ወይም በእናት ችላ ከመባል የበለጠ ስሜትን የሚጎዳ ነገር የለም። ካረን “እንደማልፈለግና እንደተተውኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል” ትላለች። በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ሁኔታው የሚያስከትለውን መጥፎ ስሜት ለመቋቋም የሚረዱህ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል። ከአባትህ ወይም ከእናትህ ድጋፍ ባታገኝም እንኳን ሕይወትህ የተሳካ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ሁን።

የወላጆችህን ችግር መረዳት

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከወላጆችህ ፍቅር ለማግኘት መፈለግህ ተገቢ ነገር ነው። አንድ ወላጅ ልጁን መውደዱ በተፈጥሮ ያለና የማይጠረጠር ሐቅ ነው። አምላክ ወላጆች ለልጆቻቸው እንደዚህ ዓይነት ፍቅር እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። (ቆላስይስ 3:21፤ ቲቶ 2:4) ይህ ከሆነ ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ችላ የሚሏቸው፣ ትተዋቸው የሚሄዱት ወይም የሚበድሏቸው ለምንድን ነው?

ለዚህ አንዱ መንስኤ የራሳቸው አስተዳደግ ሊሆን ይችላል። ‘ወላጆቼ ስለ ልጆች አስተዳደግ የተማሩት ከማን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ወላጆቻቸው እነርሱን ባሳደጉበት መንገድ ነው። “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው [NW ]” ሰዎች በእጅጉ በተበራከቱበት በዚህ ደግነት የጎደለው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱ ሥልጠና ባብዛኛው እንከን አያጣውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዚህ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ወላጆች እነርሱ ራሳቸው የደረሰባቸውን በደል በልጆቻቸው ላይ ያደርሳሉ።

ከዚህም በላይ ወላጆች ደስታቸውን እንዲያጡ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። አንዳንድ ወላጆች ከሚሰማቸው ብስጭትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለማምለጥ ሲሉ በሥራቸው፣ በአልኮል መጠጦች ወይም በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ይጠመዳሉ። ለምሳሌ ያህል የዊልያምና የጆኣን አባት የአልኮል ሱሰኛ ነበር። ጆኣን “አባታችን እኛን ማመስገን አይሆንለትም ነበር” ትላለች። “ከሁሉ የከፋው ግን መጠጥ ሲቀምስ ቁጡ መሆኑ ነበር፤ ምሽቱን በሙሉ እናቴ ላይ ይጮህባታል። በጣም ያስፈራኝ ነበር።” ወላጆች በቀጥታ ልጆቻቸውን ባይበድሏቸውም እንኳን አጉል ልማዳቸው ኃይላቸውን በሙሉ ስለሚያሟጥጥባቸው ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት ሳይችሉ ይቀራሉ።

ዊልያም የአባቱ ባሕርይ የማይጨበጥ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ተገንዝቧል። እንዲህ ይላል:- “አባቴ ያደገው በጀርመን፣ በርሊን ሲሆን በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ነበር። ልጅ እያለ ይህ ነው የማይባል ሥቃይ ደርሶበታል እንዲሁም ብዙ ሰዎች ሲሞቱ ተመልክቷል። በየዕለቱ የሚበላው ነገር ለማግኘት ብቻ እንኳ ብዙ መድከም ነበረበት። ያሳለፈው ነገር በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ይሰማኛል።” በእርግጥም፣ ከባድ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስም ይናገራል።​—⁠መክብብ 7:7

ዊልያምና ጆአን አባታቸው ያሳለፈው ሕይወት አሁን በእነሱ ላይ ለሚያደርሰው በደል እንደ ሰበብ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ይሰማቸዋልን? “ፈጽሞ” ይላል ዊልያም። “እንደዚህ ዓይነት ሕይወት ማሳለፉ ኃይለኛ ጠጪ ለመሆንና ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም ሰበብ አይሆንም። ሆኖም ስላለፈው ሕይወቱ ማወቄ የአባቴን ባሕርይ የበለጠ ለመረዳት አስችሎኛል።”

ወላጆችህ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች መሆናቸውን አምነህ መቀበልህና ስለአስተዳደጋቸው ማወቅህ እነሱን ለመረዳት ያስችልሃል። ምሳሌ 19:​11 “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል” ይላል።

ስሜቶችህን መቆጣጠር

ቤታችሁ ውስጥ ባለው ሁኔታ ምክንያት ሌሎች መጥፎ ስሜቶችም ያድሩብህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ፓትሪሺያ ሁለቱም ወላጆቿ ችላ ስላሏት “ዋጋ እንደሌላትና እንደማትወደድ” ተሰምቷታል። ላኒሻ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለች አባቷ ትቷት ከሄደ ወዲህ በአጠቃላይ ወንዶችን ማመን ያስቸግራታል። ሼላ ደግሞ “የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሱሰኛ” ከሆነችው እናቷ ያጣችውን ፍቅር ከሌላ ሰው ለማግኘት ስትል ያገኘችውን ሰው ሁሉ ትኩረት ለመሳብ ትፈልጋለች።

የቁጣ ስሜትና ቅናትም ሊያስቸግርህ ይችላል። ካረን ሌላ ሚስት ያገባው አባቷ እሷ ልታገኘው ትጓጓ የነበረውን ፍቅር ለአዲሱ ቤተሰቡ ሲያሳይ መመልከቷ “በአንድ ወቅት ከፍተኛ ቅናት” እንዲሰማት አድርጓት ነበር። ሌላኒ አንዳንድ ጊዜ ለወላጆቿ የጥላቻ ስሜት እስኪያድርባት ድረስ ትበሳጫለች። “ሁልጊዜ ከወላጆቼ ጋር እጋጭ ነበር” ትላለች።

ከሁኔታዎቹ አንጻር ሲታይ እንደዚህ ዓይነት ስሜቶች ቢያድሩብህ የሚያስገርም አይሆንም። ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት አፍራሽ ስሜቶችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ልትቋቋማቸው የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

ወደ ይሖዋ አምላክ ቅረብ። (ያዕቆብ 4:8) በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ከሕዝቦቹ ጋር አዘውትረህ በመሰብሰብ ወደ ይሖዋ መቅረብ ትችላለህ። ይሖዋ ሌሎችን እንዴት እንደያዛቸው ስትመለከት ታማኝ እንደሆነና በእሱ ላይ ትምክህትህን መጣል እንደምትችል ትገነዘባለህ። ይሖዋ እስራኤላውያንን “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን?” በማለት ጠይቋቸው ነበር። ከዚያም “አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም” ሲል ቃል ገብቶላቸዋል። (ኢሳይያስ 49:15) ስለዚህ አዘውትረህ ወደ አምላክ ጸልይ። ይሖዋ ሐሳብህን ስለሚረዳልህ ትክክለኛ ቃላት ስለመናገር መጨነቅ አያስፈልግህም። (ሮሜ 8:26) ማንም ሰው የማይወድህ በሚመስልህ ጊዜ እንኳን ይሖዋ እንደሚወድህ አስታውስ።​—⁠መዝሙር 27:10

ስሜትህን ለምትተማመንበት ሰው አካፍል። በመንፈሳዊ ከጎለመሱ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርት። ስሜትህንና የሚያስጨንቅህን ነገር በግልጽ አወያያቸው። በይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ አባቶችና እናቶች ማግኘት ትችላለህ። (ማርቆስ 10:29, 30) ሆኖም ቅድሚያውን ወስደህ ምን እንደሚሰማህ መናገር ያስፈልግህ ይሆናል። አንተ እስካልነገርካቸው ድረስ ሌሎች ምን እንደሚሰማህ ማወቅ አይችሉም። ስለሚያስጨንቅህ ውስጣዊ ስሜት መተንፈስህ እውነተኛ መጽናኛ ያስገኝልሃል።​—⁠1 ሳሙኤል 1:12-18

ሌሎችን የሚጠቅሙ ተግባራት በማከናወን ራስህን በሥራ አስጠምድ። ስለ ራስህ ብቻ በማሰብ በሐዘን እንዳትዋጥ ያለህበት ሁኔታ ባስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ ላይ አታብሰልስል። ከዚህ ይልቅ ያሉህን ነገሮች ማድነቅን ተማር። ‘ለራስህ የሚጠቅምህን ብቻ ሳትመለከት ስለ ባልንጀሮችህም በማሰብ’ እንደዚህ ለማድረግ የሚያስችልህ አጋጣሚ ታገኛለህ። (ፊልጵስዩስ 2:4) መንፈሳዊ ግቦች አውጣና አዎንታዊ አመለካከት ይዘህ ግቦችህ ላይ ለመድረስ ተጣጣር። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሌሎችን መርዳት ትኩረትህን በራስህ ላይ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ስለሌሎችም ለማሰብ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ነው።

ለወላጆችህ አክብሮት ማሳየትህን ቀጥል። ምን ጊዜም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችና መሥፈርቶች በጥብቅ መከተል እንዳለብህ አትዘንጋ። ይህም ለወላጆችህ አክብሮት ማሳየትን ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:1, 2) እንደዚህ ዓይነት አክብሮት ካለህ ቂም የመያዝ ወይም የበቀለኛነት ዝንባሌ አይኖርህም። ወላጆችህ የቱንም ያህል እንደበደሉህ ቢሰማህም አንተ በክፉ ለመመለስ ሰበብ እንደማይሆንህ አስታውስ። ስለዚህ ለይሖዋ ተወው። (ሮሜ 12:17-21) ይሖዋ “ፍትሕን ይወዳል፤” ለልጆች ደግሞ በጣም ያስባል። (መዝሙር 37:28 አ.መ.ት፤ ዘጸአት 22:22-24) ለወላጆችህ ተገቢውን አክብሮት ማሳየትህን በመቀጠል የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በተለይም ፍቅርን ለማፍራት ጣር።​—⁠ገላትያ 5:22, 23

ስኬታማ መሆን ትችላለህ

ወላጃዊ ፍቅር ማጣት የስሜት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከወላጆችህ ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘትህ በምትከተለው የሕይወት ጎዳና ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የለበትም። ከላይ የተመለከትናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ሕይወትህን አስደሳችና ስኬታማ ማድረግ ትችላለህ።

ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ዊልያም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚረዱን ብዙ ዝግጅቶች አድርጎልናል። እንደዚህ ዓይነት አፍቃሪና አሳቢ ሰማያዊ አባት ማግኘት ምንኛ መታደል ነው!” እህቱ ጆአንም ወንጌላውያን ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ሆና ታገለግላለች። “እያደግን ስንሄድ ‘እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው’ መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ መመልከት ችለናል” ትላለች። (ሚልክያስ 3:18 አ.መ.ት ) “በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች እውነትን አጥብቀን ለመያዝና የራሳችን ለማድረግ ቆራጥ አቋም እንድንወስድ አድርገውናል።”

አንተም ልክ እንደዚሁ ሊሳካልህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ” ይላል። (መዝሙር 126:5) ይህ ጥቅስ እዚህ ላይ የሚሠራው እንዴት ነው? አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ትክክለኛውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከጣርክ ከጊዜ በኋላ የአምላክን በረከቶች ስታገኝ ሐዘንህ በደስታ ይተካል።

እንግዲያው ወደ ይሖዋ አምላክ ለመቅረብ ብርቱ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። (ዕብራውያን 6:10፤ 11:6) ለዓመታት በጭንቀት፣ በተስፋ መቁረጥና በጥፋተኝነት ስሜት ብትሰቃይም እንኳን እነዚህ ስሜቶች ከጊዜ በኋላ እየጠፉ ሊሄዱና ‘አእምሮንም ሁሉ በሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም’ ሊተኩ ይችላሉ።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:6, 7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦

• የከንቱነት ወይም የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማኛልን?

• ሌሎችን ማመን አደገኛ ወይም ሞኝነት እንደሆነ ይሰማኛልን?

• ዘወትር ማጽናኛና ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገኛልን?

• ቁጣዬን ወይም የቅናት ስሜቴን መቆጣጠር ይሳነኛልን?

ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ አዎን የሚል ከሆነ በተቻለ ፍጥነት የሚሰማህን ነገር ለምትተማመንበት ወላጅህ፣ ለአንድ ሽማግሌ ወይም በመንፈሳዊ ጎልማሳ ለሆነ ወዳጅህ አካፍል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሜትህን ለመቆጣጠር እንድትችል አዎንታዊ እርምጃዎች ውሰድ