በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሁላችንም የጋራ ፍላጎት

የሁላችንም የጋራ ፍላጎት

የሁላችንም የጋራ ፍላጎት

ምግብ ያስፈልገናል። ውኃ ያስፈልገናል። አየር ያስፈልገናል። ከቀን ሐሩርና ከሌሊት ቁር የምንከለልበት አንድ ዓይነት መጠለያና መከለያ ያስፈልገናል። እነዚህ ነገሮች ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን በዚህች ምድር ላይ ለሚኖሩ በቢልዮን ለሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ የሚያስፈልጉ ናቸው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅን ከእነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት ልዩ የሚያደርገው አንድ ብቸኛ ፍላጎት አለ። ይህ ፍላጎት ምን​ድን ነው?

ረጂናልድ ደብልዩ ቢቢ የተባሉት ካናዳዊ የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪ “ሰዎች ሃይማኖት ብቻ ሊያሟላ የሚችለው ፍላጎት አላቸው” ሲሉ ጽፈዋል። አሜሪካን ሶሲኦሎጂካል ሪቪው የተባለው መጽሔትም በየካቲት 2000 እትሙ ላይ “ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ማሰብ ሁልጊዜም የሚኖር የሰው ልጅ አመለካከት ክፍል ይመስላል” የሚል ጽሑፍ አውጥቶ ነበር።

አዎን፣ በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሰው ልጆች የማምለክ ፍላጎት እንዳላቸው ታይቷል። አብዛኞቹ የሰው ልጆችም ለበርካታ መቶ ዘመናት ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተደራጁ ሃይማኖቶች አባላት ሆነው ኖረዋል። አሁን ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ ናቸው። እንደ ሰሜን አሜሪካና ሰሜን አውሮፓ ባሉት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ በርካታ አገሮች አብያተ ክርስቲያኖቻቸውን እየተዉ የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። ታዲያ እንዲህ መሆኑ ሃይማኖት አለቀለት ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም።

ስቬንስካ ዳግብላደት የተባለው የስዊድን ጋዜጣ “ሃይማኖት እየጠፋ ነው የሚለው ዘገባ በጣም የተጋነነ ነው” ሲል ጽፏል። ታዲያ የታወቁ አብያተ ክርስቲያናት በምን እየተተኩ ነው? ጋዜጣው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አዲስ የተፈጠረው ነገር የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባል አለመሆናችን ነው። ከዚህ ይልቅ በዓለም ካሉት ሃይማኖቶች የመሰለንንና የጣመንን ቀነጣጥበን የራሳችን የሆነ ቅልቅል ሃይማኖት መያዝ እንችላለን። . . . ፈውስ ያስገኛል ከሚባል ዕንቁ እስከ ቡዲስት መነኩሴ ካባ፣ የተለያዩ ነገሮችን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። የመረጥኸው ነገር ከሰለቸህ በቀላሉና አለምንም ችግር ወደሌላው ዘወር ማለት ትችላለህ።”

የሃይማኖት ማኅበራዊ ጥናት ተመራማሪዎች ይህንን አዝማሚያ “የግል ሃይማኖት” ወይም “የማይታይ ሃይማኖት” ይሉታል። ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ቢቢ የተባሉ የማኅበራዊ ጥናት ተመራማሪ “የጣመህን ሃይማኖት ምረጥ” የሚል አባባል ፈጥረዋል። ሌሎች ደግሞ እንደነዚህ ያሉትን ሃይማኖቶች “በልክ የተሰፋ ሃይማኖት” ወይም “የጣመህን ያዝ” ይሏቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የክርስቲያን አገሮች አብዛኞቹ ሰዎች የሚከተሉት እንደነዚህ ያሉትን የግል ሃይማኖቶች ነው።

በጣም ሃይማኖተኛ ካልሆኑት አገሮች አንዷ በሆነችው በስዊድን በተደረገ አንድ ጥናት የተገኘውን ውጤት እንመልከት። ከሦስት ሰዎች ሁለቱ “በራሳቸው መንገድ” ራሳቸውን ክርስቲያን ነን ብለው እንደሚቆጥሩ አረጋግጧል። አንዳንዶቹ “የራሴ የሆነ የክርስትና አመለካከት አለኝ፣” “ቤተ ክርስቲያን ስሄድ ግራ ይገባኛል፣” “ቤተ ክርስቲያን መሄድና ቄሶች የሚሉትን መስማት አልወድም” ወይም “ክፍሌ ውስጥ ዘግቼ ብቻዬን መጸለይ እችላለሁ” ብለዋል። ብዙዎቹ ከሞት በኋላ ሌላ አካል ለብሶ መኖር እንዳለ ወይም በዕድል የማመን አዝማሚያ እንዳላቸው ታይቷል። አብዛኞቹ አንድ ዓይነት መለኮታዊ ኃይል እንዳለና ግን ይህ ኃይል ምን እንደሆነ ሊገልጹ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ሌላው ጥናት ደግሞ ብዙ ሰዎች ሃይማኖተኝነት የሚሰማቸው ከቤት ወጣ ብለው የተፈጥሮን ውበት ሲመለከቱ ብቻ እንደሆነ ደርሶበታል። አንዲት በግብርና የምትተዳደር ወጣት ሴት “ወደ አምላክ እንደቀረብክ ሆኖ የሚሰማህ ወጣ ብለህ ማሳ ውስጥ ወይም ጫካ ውስጥ ስትገባ ይመስለኛል” ብላለች። ሌላው ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ራሱን ሃይማኖተኛ እንደሆነ የማይቆጥር ሰው ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ወደ ጫካ ስሄድ ትልቅ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደገባሁ ሆኖ ይሰማኛል። . . . ያን ቦታ በበላይነት የሚቆጣጠረው ማን እንደሆነ ባላውቅም እንዲሁ ይሰማኛል።” አንዳንዶች ተፈጥሮ ቅዱስ፣ መለኮታዊና ግርማ የተላበሰ እንደሆነ ይናገሩና በተፈጥሮ ውበት ሲከበቡ ጉልበታቸው እንደሚታደስ፣ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት እንደሚያገኙ ይናገራሉ። አንድ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ሰው አስተያየቱን ሲያጠቃልል “አምላክ ወደ ጫካ ገብቷል” ብሏል።

በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያለው አዝማሚያ በብዙ የዓለም አካባቢዎች በመታየት ላይ ነው። ቶማስ ሉክማን የተባሉት አሜሪካዊ የሃይማኖት ሥነ ማኅበረሰብ ተመራማሪ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ ማኅበረሰቦች በቤተ ክርስቲያን የሚደረገው አምልኮ ወደ ጎን ገሸሽ ተደርጎ “ማኅበራዊ ቅርጽ ባለው ሃይማኖት” እየተተካ ነው ብለዋል። ይህ ማለት ግለሰቡ ከዚህና ከዚያ የለቃቀማቸውን መንፈሳዊ አስተሳሰቦች ያሰባስብና የራሱን ሃይማኖት ይፈጥራል ማለት ነው።

‘ታዲያ ታዋቂ ሆነው የኖሩት ሃይማኖቶችና አብያተ ክርስቲያናት በማኅበረሰቡ ውስጥ ገሸሽ እየተደረጉ ነውን? ከሆነስ ለምን?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኩራል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ተመራማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለሚታየው መንፈሳዊነትን ከተፈጥሮ የመፈለግ አዝማሚያ አስተያየት ሲሰጡ “አምላክ ወደ ጫካ ገብቷል” ብለዋል