ሞባይል ስልክ ያስፈልገኛልን?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ሞባይል ስልክ ያስፈልገኛልን?
“ሞባይል ስልክ ካልያዝኩ ስጋት ያድርብኛል፤ መንፈሴ ሁሉ ይረበሻል።”—አኪኮ *
ሞባይል ስልኮች በብዙ አገሮች ውስጥ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ነው። ለአጠቃቀም በጣም አመቺ ናቸው። ጓደኞችህና ወላጆችህ በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ሊያነጋግሩህ የሚችሉ ሲሆን አንተም እንደዚያው ማድረግ ትችላለህ። አንዳንድ የስልክ ሞዴሎች አጠር ያለ የጽሑፍ መልእክት ለመለዋወጥም ያስችላሉ፤ የለንደኑ ዘ ታይምስ ጋዜጣ ይህንን ሞዴል “ወጣቶች ከሌሎች ጋር የመነጋገር ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚጠቀሙበት አዲሱ መሣሪያ” ብሎታል። ከኢንተርኔት ጋር የሚያገናኙና በዌብ ገጾችና በኤሌክትሮኒክስ መልእክት መለዋወጫ መስመሮች አማካኝነት ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ሞባይል ስልኮችም አሉ።
አንተ ራስህ ሞባይል ስልክ ይኖርህ አሊያም ለመግዛት ታስብ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ እያንዳንዱ ነገር መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ መጥፎ ጎንም ሊኖረው እንደሚችል ልብ ማለቱ
ጠቃሚ ነው። ሞባይል ስልክ የተወሰኑ ጥቅሞች ይኖሩት ይሆናል። ይሁን እንጂ መጥፎ ጎኑንም መመልከቱ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ሞባይል ስልክ ለመግዛት ብትወስን እንኳን ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን አንዳንድ ችግሮችን በሚገባ መገንዘብህ በአጠቃቀምህ ረገድ ጠንቃቃ እንድትሆን ይረዳሃል።‘ኪሳራውን አስላ’
ኢየሱስ አንድ ከበድ ያለ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከራችን በፊት ‘ኪሳራውን እንድናሰላ’ በማሳሰብ ጥበብ የተሞላበት መመሪያ ሰጥቶናል። (ሉቃስ 14:28) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለሞባይል ስልኮችም ሊሠራ ይችላል? አዎን፣ ይሠራል። እርግጥ ነው፣ ስልኩን በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ልትገዛው ወይም ደግሞ በነፃም ጭምር ልታገኘው ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የ17 ዓመቷ ሄና እንደተገነዘበችው “በየጊዜው የሚከፈለው የአገልግሎት ሂሳብ ሳይታሰብ በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።” ከዚህም በላይ ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን እንድትገጥምለትና የበለጠ ውድ የሆኑ የስልክ ሞዴሎችን እንድትገዛ የማያቋርጥ ግፊት ይደረግብህ ይሆናል። ሂሮሺ የተባለው ወጣት “በየዓመቱ አዳዲስ ሞዴሎችን ለመግዛት እንድችል የትርፍ ሰዓት ሥራ እየሠራሁ ገንዘብ አጠራቅማለሁ” ብሏል። ብዙ ወጣቶችም እንደዚህ ያደርጋሉ። *
ወላጆችህ የስልክ ሂሳቡን ሊከፍሉልህ ቢስማሙም እንኳን ወጪውን ማስላቱ አስፈላጊ ነው። በጃፓን የሚኖር አንድ ክርስቲያን ተጓዥ አገልጋይ “አንዳንድ እናቶች መጀመሪያውኑም አስፈላጊ ያልነበረውን የልጆቻቸውን ሞባይል ስልክ ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ተጨማሪ የትርፍ ሰዓት ሥራ መስራት ጀምረዋል” ብሏል። በወላጆችህ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሸክም መጫን እንደማትፈልግ የታወቀ ነው።
“የጊዜ ሌባ”
መጀመሪያ ላይ ስልካቸውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት የቆዩ ብዙ ወጣቶች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ካሰቡት በላይ ጊዜያቸውን ሊሻማባቸውና የበለጠ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ሊያሳጣቸው ይችላል። ሚካ በእራት ሰዓት ከቤተሰቧ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ታሳልፍ ነበር። “አሁን ግን ከእራት በኋላ ሁላችንም [ስልኮቻችንን] ይዘን ወደየክፍላችን እንበታተናለን” ብላለች።
የለንደኑ ዘ ጋርዲያን መጽሔት “በ16 እና በ20 ዓመት ዕድሜ መካከል ከሚገኙት ወጣቶች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከየትኛውም ሌላ የጽሑፍ መገናኛ መሥመር ይልቅ በሞባይል ስልኮቻቸው የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥን ይመርጣሉ” ብሏል። በሞባይል ስልክ አማካኝነት በጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ የሚጠይቀው ወጪ በቀጥታ ከመነጋገር ያነሰ ሊሆን ቢችልም መልእክቱን በጽሑፍ ማስፈሩ የበለጠ ጊዜ ይወስድብሃል። ሚኤኮ እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “‘ደህና እደሪ’ የሚል መልእክት ከደረሰኝ እኔም ‘ደህና እደሪ’ ብዬ እመልሳለሁ። ከዚያም ለአንድ ሰዓት ያህል መልእክት መላላካችንን እንቀጥላለን። የምንለዋወጠው መልእክት ግን ዝም ብሎ የማይረባ ወሬ ነው።”
ብዙ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች በስልክ መልእክት በመለዋወጥ በአንድ ወር ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንዳጠፉ ቆም ብለው ቢያሰሉት በጣም ይገረማሉ። የ19 ዓመቷ ቴጃ “ሞባይል ስልክ ለብዙ ሰዎች ጊዜ ቆጣቢ ሳይሆን የጊዜ ሌባ ነው” በማለት ሐቁን ተናግራለች። ሞባይል ስልክ ለመያዝ በቂ ምክንያት ቢኖርህም እንኳን በስልኩ በመጠቀም በምታጠፋው ጊዜ ረገድ ጠንቃቃ መሆን ይገባሃል።
ማርያ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብላለች:- “በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ወጣቶች ተራ መልእክቶችን ለሌሎች ይልካሉ። ይህ በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል።” አንዳንድ ወጣቶች በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይም እንደዚህ እንደሚያደርጉ ተስተውሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ጊዜ እንዲዋጁ ይመክራል። (ኤፌሶን 5:16) ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች የመደብነውን ውድ ጊዜ በስልክ ጭውውት ብናባክነው እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል!
ምስጢራዊ ግንኙነት
ማሪዬ ሌላም አደጋ እንዳለ ትናገራለች:- “ስልኩን የሚያነሳው ራሱ ግለሰቡ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከማን ጋር እያወሩ እንዳሉ፣ እንዲያውም በስልክ እያወሩ ይሁን አይሁን እንኳን ማወቅ አይችሉም።” በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወጣቶች በሞባይል ስልኮቻቸው በመጠቀም ከተቃራኒ ጾታ ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ይመሠርታሉ። አንዳንዶች በሌላ ጊዜ ከሰዎች ጋር ሲጫወቱ የሚያከብሯቸውን ሥርዓቶች በመጣስ ገደባቸውን አልፈዋል። ይህ የሆነው እንዴት ነው?
የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ “[ወጣቶች] በሞባይል ስልክ አማካኝነት የሚለዋወጡትን የጽሑፍ መልእክት ማንም ሰው ሊከታተለው አይችልም” ብሏል። የምታነጋግረውን ሰው ፊት ለፊት አለማየትህ ወይም ድምፁን አለመስማትህ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ቲሞ እንዲህ ይላል:- “አንዳንዶች በጽሑፍ የሚደረግ ውይይት ነጻ እንደሚያደርጋቸው ይሰማቸዋል። ፊት ለፊት ቢሆን ለመናገር የማይደፍሩትን ነገር ጽፈው ይልካሉ።”
ኬይኮ የተባለችው የ17 ዓመት ክርስቲያን ወጣት በሞባይል ስልክ መጠቀም ስትጀምር የስልክ ቁጥሯን ለብዙ ጓደኞቿ ነገረቻቸው። ብዙም ሳይቆይ በጉባኤዋ ከሚገኝ አንድ ወጣት ጋር በየቀኑ መልእክት መለዋወጥ ጀመረች። ኬይኮ እንዲህ ትላለች:- “መጀመሪያ ላይ እንዲሁ ስለ ዕለታዊ ጉዳዮች እናወራ ነበር፤ በኋላ ግን ስለሚያስጨንቁን ነገሮችም ማውራት ጀመርን። በሞባይል ስልኮቻችን አማካኝነት የራሳችንን ዓለም ፈጥረን ነበር።”
የሚያስደስተው ነገሮች ሳይባባሱ በፊት ከወላጆችዋና ከክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታ አገኘች። አሁን እንዲህ ስትል *
ሐቁን ትናገራለች:- “ወላጆቼ ስልኩን ሳይሰጡኝ በፊት ከተቃራኒ ጾታ ጋር መልእክት ስለመለዋወጥ በሚገባ አስጠንቅቀውኝ የነበረ ቢሆንም በየዕለቱ መልእክት እልክለት ነበር። ስልኩን ለዚህ ዓላማ ልጠቀምበት አይገባም ነበር።”መጽሐፍ ቅዱስ “በጎ ሕሊና ይኑራችሁ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 3:16) ይህ ማለት ኮኢቺ የተባለው ወጣት እንደተናገረው በሞባይል ስልክ ስትነጋገር ሌላ ሰው ቢሰማህ ወይም የላክኸውን መልእክት ቢመለከተው “የሚያሳፍርህ አይሆንም” ማለት ነው። ምንጊዜም ቢሆን ከሰማያዊው አባታችን የተደበቀ ነገር እንደሌለ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እኛን በሚቈጣጠር በ[አምላክ] ዓይኖ[ች] ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብራውያን 4:13) ይህ ከሆነ እንግዲያው ምስጢራዊ ግንኙነት ለመመሥረት መሞከር ዋጋ የለውም ማለት ነው።
ገደብ አብጅ
ሞባይል ስልክ ለመግዛት እያሰብክ ከሆነ በእርግጥ ስልኩ ያስፈልግህ እንደሆነ ለማወቅ ለምን መጀመሪያ ሁኔታህን በጥንቃቄ አትመረምርም? ጉዳዩን ከወላጆችህ ጋር ተወያይበት። አንዳንዶች ዬና የተባለችው ወጣት እንደተሰማት ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸዋል:- “ለብዙ ወጣቶች ሞባይል ስልክ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ኃላፊነት ነው።”
ሞባይል ስልክ ሊኖርህ እንደሚገባ ብትወስንም እንኳን በአጠቃቀምህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን ይገባሃል። ይህንን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አግባብነት ያላቸው ገደቦች አብጅ። ለምሳሌ ያህል፣ የሞባይል ስልክ ብዙ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን በአጠቃቀምህ ላይ ገደብ ልታበጅ ወይም ለሞባይል ስልክ የምታውለውን ጊዜና ገንዘብ አስቀድመህ ልትወስን ትችላለህ። ብዙ የስልክ ድርጅቶች ስልኩን በምን መልኩ እንደተጠቀምክበት በሂሳብ መጠየቂያ ደረሰኙ ላይ ዝርዝር መግለጫ ስለሚያቀርቡ ከወላጆችህ ጋር ሆነህ በየጊዜው ወጪህን ልትመረምር ትችላለህ። አንዳንዶች በቅድሚያ በመክፈል በሞባይል ስልክ አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ ማበጀት ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
ከዚህም በላይ ጥሪ ሲደረግልህና መልእክት ሲላክልህ ምላሽ የምትሰጠው መቼና እንዴት እንደሆነ በጥሞና አስብ። ሊሠሩ የሚችሉ ተገቢ የሆኑ ደንቦችን አውጣ። ሺንጂ እንዲህ ይላል:- “መልእክት መቀበያውን የምከፍተው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ምላሽ የምሰጠውም አስፈላጊ ለሆኑ መልእክቶች ብቻ ነው። በመሆኑም ጓደኞቼ ተራ መልእክቶችን መላክ አቁመዋል። በእርግጥ አጣዳፊ የሆነ ጉዳይ ከገጠማቸው መደወላቸው አይቀርም።” ከሁሉ በላይ ደግሞ ከእነማን ጋር ግንኙነት እንደምትመሠርት አስብበት። የስልክ ቁጥርህን ለሌሎች በምትሰጥበት ጊዜ ጠንቃቃ ሁን። መልካም ባልንጀርነትን በተመለከተ ሁል ጊዜ የምትጠቀምበትን መሠረታዊ ሥርዓት እዚህም ላይ ተጠቀምበት።-1 ቆሮንቶስ 15:33
መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉ ዘመን አለው . . . ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 7) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሞባይል ስልኮችም ‘ዝም ማለት’ የሚገባቸው ጊዜ አለ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በአገልግሎታችን ላይ ስንሆን ‘ጊዜያችንን’ በስልክ ለማውራት ሳይሆን አምላክን ለማምለክ መድበነዋል። አብዛኛውን ጊዜ የሬስቶራንቶችና የቲያትር ቤቶች አስተዳዳሪዎች ደምበኞቻቸው ሞባይል ስልኮቻቸውን እንዲያጠፉ ይጠይቃሉ። እንደዚህ ዓይነቶቹን መመሪያዎች በአክብሮት እንታዘዛለን። የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዢ ከዚህ የላቀ አክብሮት ሊሰጠው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም!
ብዙዎች በጣም አስፈላጊ የሆነ የስልክ ጥሪ እየጠበቁ ካልሆነ፣ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በሚያከናውኑበት ወቅት ስልካቸውን ያጠፉታል። ሌሎች ደግሞ ሞባይል ስልኮቻቸውን ከአካባቢያቸው አርቀው ያስቀምጧቸዋል። ደግሞስ አብዛኞቹን መልእክቶች ቆየት ብለን ልናያቸው አንችልምን?
ሞባይል ስልክ ለመያዝ ከወሰንክ ስልኩ እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ አንተ ልትቆጣጠረው ይገባል። ጠንቃቃ በመሆን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያውን መስጠት ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ጥበበኞች . . . እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” በማለት ይመክረናል። (ኤፌሶን 5:15) ሞባይል ስልክ ለመያዝ ከወሰንክ በአጠቃቀምህ ረገድ ጥበበኛና አስተዋይ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.7 ከትምህርት ሰዓት በኋላ መሥራትን በተመለከተ በመስከረም 22, 1997 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ—ገንዘብ ለማግኘት መሞከር ስህተት ነውን?” የሚል ርዕስ ተመልከት።
^ አን.18 ከተቃራኒ ጾታ ጋር አዘውትሮ በስልክ ማውራት ወይም መልእክት መለዋወጥ ተቀጣጥሮ እንደመጫወት ሊቆጠር ይችላል። “የወጣቶች ጥያቄ—ያለ ዕድሜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ጉዳቱ ምንድን ነው?” የሚለውን በጥር 8, 2002 የንቁ! እትም ላይ የወጣ ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንዳንድ ወጣቶች በሞባይል ስልኮች አማካኝነት ምስጢራዊ ወዳጅነት ይመሰርታሉ