በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ቸነፈር”

“በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ቸነፈር”

“በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ቸነፈር”

ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“በዓለም ላይ የኤድስ ወረርሽኝን ያህል አውዳሚ የሆነ ጦርነት የለም።”—የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ኮሊን ፓውል

ኤድስን (የሰውነትን ተፈጥሯዊ የመከላከያ ኃይል የሚያዳክም በሽታ) አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ሪፖርት የወጣው ሰኔ 1981 ነበር። የተባበሩት መንግሥታት የተቀናጀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም (ዩ ኤን ኤድስ) ዋና ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ፓዮ “የኤድስ ወረርሽኝ መጀመሪያ ላይ ሲከሰት ለችግሩ እልባት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ከነበርነው ሰዎች መካከል ወረርሽኙ አሁን ባለበት ደረጃ ይስፋፋል ብሎ የጠበቀ አንድም ሰው አልነበረም” ሲሉ ተናግረዋል። ኤድስ በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ቸነፈር ለመሆን የበቃ ሲሆን ወደፊትም ስርጭቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ያሉት ሁኔታዎች ይጠቁማሉ።

ከ36 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በኤች አይ ቪ (የሰውን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክም ቫይረስ) እንደተያዙ የሚገመት ሲሆን ሌሎች 22 ሚልዮን ሰዎች ደግሞ በኤድስ ሕይወታቸውን አጥተዋል። * በ2000 በዓለም ዙሪያ ሦስት ሚልዮን ሰዎች በኤድስ የሞቱ ሲሆን ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ሰው ሲሞት ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህ የሆነው በተለይ በበለጸጉት አገሮች የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ውለው እያለ ነው።

ኤድስ መላውን አፍሪካ አዳርሷል

በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉት የአፍሪካ አገሮች በኤድስ ወረርሽኝ ክፉኛ ተጠቅተዋል። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ አገሮች ውስጥ 25.3 ሚልዮን ሰዎች በኤች አይ ቪ እንደተያዙ ይገመታል። በ2000 በዚህ የምድር ክፍል ብቻ 2.4 ሚልዮን ሰዎች በኤድስ የሞቱ ሲሆን ይህ አኃዝ በዓለም ዙሪያ ከሞቱት ሰዎች አጠቃላይ ድምር ውስጥ 80 በመቶ ይሆናል። በእነዚህ አገሮች በዋነኛነት የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኤድስ ነው። *

ወደ 4.7 ሚልዮን የሚጠጉ የኤድስ ተጠቂዎች የሚኖሩባት ደቡብ አፍሪካ ከዓለም ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች። በዚህች አገር በኤች አይ ቪ የተያዙ 5,000 ሕፃናት በየወሩ ይወለዳሉ። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሐምሌ 2000 በደርባን በተካሄደው 13ኛው ዓለም አቀፍ የኤድስ ኮንፈረንስ ላይ ባቀረቡት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር:- “በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩት ወጣቶች መካከል ከሁለቱ አንዱ ማለትም ግማሽ ያህሉ በኤድስ እንደሚሞቱ ስንሰማ እጅግ ደንግጠናል። ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ በአኃዛዊ መረጃዎች እየተገለጸ ያለውን የበሽታውን ስርጭትም ሆነ በወረርሽኙ ምክንያት በሰው ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ . . . ቀድሞውኑ ማስቀረት ይቻል የነበረ መሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን ሊደረግ የሚችል ነገር አለ።”

ኤድስ በሌሎች አገሮችም በፍጥነት እየተዛመተ ነው

በምሥራቅ አውሮፓ፣ በእስያና በካሪቢያን አገሮችም በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። በ1999 መገባደጃ ላይ በምሥራቅ አውሮፓ የኤድስ ተጠቂዎች ቁጥር 420,000 ነበር። በ2000 ማብቂያ ላይ ግን ቁጥሩ ቢያንስ ወደ 700,000 ከፍ እንዳለ ተገምቷል።

በስድስት ትልልቅ የአሜሪካ ከተሞች የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ግብረ ሰዶም ከሚፈጽሙ ወጣቶች መካከል 12.3 በመቶ የሚሆኑት በኤች አይ ቪ ተይዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኤች አይ ቪ ከተያዙት መካከል በቫይረሱ መጠቃታቸውን የሚያውቁት 29 በመቶዎቹ ብቻ ነበሩ። የበሽታ ስርጭትና ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት የጥናቱ አስተባባሪ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በኤች አይ ቪ መያዛቸውን የሚያውቁት ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ አድርጎብናል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተያዙ ሰዎች ሳያውቁት ቫይረሱን እያሰራጩ ነው ማለት ነው።”

የኤድስ ጠበብት ግንቦት 2001 በስዊዘርላንድ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ይህን በሽታ “በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ቸነፈር” ሲሉ ጠርተውታል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ኤድስ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ክፉኛ አጥቅቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አኃዞቹ ዩ ኤን ኤድስ ባወጣው ግምታዊ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይበልጥ የሚያሳዝነው . . . የበሽታውን ስርጭትም ሆነ . . . በሰው ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ . . . ቀድሞውኑ ማስቀረት ይቻል የነበረ መሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን ሊደረግ የሚችል ነገር አለ። ኔልሰን ማንዴላ

[በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኤች አይ ቪ የተያዙ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አያውቁም

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

UN/DPI Photo 198594C/Greg Kinch