በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ብዛት እየጨመረ መጥቷል
በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ብዛት እየጨመረ መጥቷል
“ብዙ ጊዜ ማታ ማታ ወደ አምላክ እያለቀስኩ እጸልያለሁ። የነገውን ቀን እንዴት እንደማሳልፍ አላውቅም እለዋለሁ።”—ግሎሪያ፣ ሦስት ልጆችን ያለ አባት ያሳደገች እናት።
በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች በዛሬው ጊዜ በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ሆነዋል። * ባል፣ ሚስትና ልጆች የሚገኙበት የተለመደውና የታወቀው የቤተሰብ ኑሮ መዋቅር በሌላ ዓይነት የቤተሰብ መዋቅር እየተተካ በመምጣቱ በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የማኅበራዊ ኑሮና የሥነ ሕዝብ ተመራማሪዎች ይህ የሆነበትን ምክንያት በማጥናት ላይ ናቸው።
የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳይመን ደንከንና ፕሮፌሰር ሮዝሊንድ ኤድዋርድስ “በቤተሰብ መዋቅሮችና በወንዶችና ሴቶች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ዘላቂ የሆኑ ለውጦች በመካሄድ ላይ ናቸው” ይላሉ። ለምን? ይህ ሊሆን የቻለው ሰዎች እየተካሄደ ካለው የኢኮኖሚ፣ የባሕልና የማኅበራዊ ኑሮ ለውጥ አንጻር ኑሯቸውን እንዴት እንደሚመሩ በሚያደርጓቸው ምርጫዎች ሳቢያ እንደሆነ አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
እስቲ ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዳንዶቹንና ሰዎች እያደረጓቸው ያሉትን ምርጫዎች እንመልከት። በሰዎች አኗኗር
ላይ በዋነኛነት ተጽእኖ የሚያሳድረው ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረገው ውጣ ውረድ የሚፈጥረው ጫና ነው። የውጭው ዓለም በእያንዳንዱ ቀን የሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ አለ። ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ያሳልፈው የነበረው ጊዜ አሁን የሚያልፈው በኢንተርኔት፣ ወይም ቴሌቪዥን በማየት፣ ስልክ በመነጋገር፣ በመኪና በመጓዝ ወይም ላይ ታች በመሯሯጥ ነው።የኢኮኖሚ ተጽዕኖም የሚያስከትለው ጉዳት አለ። ዘመናዊዎቹ የቅንጦት ዕቃዎች የሚገኙት ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸው በመሆኑ ብዙ ወላጆች በሥራው ዓለም ይጠመዳሉ። የብዙ ቤተሰብ አባሎች ከቦታ ቦታ የመጓጓዝ ባሕል በዳበረበት ኅብረተሰብ መካከል የሚገኙ በመሆኑ ሊያግዟቸውና ሊረዷቸው ከሚችሉ ዘመዶቻቸው ርቀው ለመኖርና ለመሥራት ተገድደዋል። እንዲያውም ከትዳር ጓደኞቻቸው ሳይቀር የሚነጠሉበት ጊዜ አለ። በበርካታ አገሮች በብዙዎች ዘንድ ወዳጅነት እያገኙ የመጡት መዝናኛዎችም በዚህ ረገድ የሚረዱ ሆነው አልተገኙም። ብዙዎቹ መዝናኛዎች በአብዛኛው የሚያተኩሩት እንደ ትዳርና ቤተሰብ የመሰሉትን የተረጋጋ ኑሮ የሚፈጥሩ ተቋሞች በማቃለልና በማፍረስ ላይ ነው። *
በዛሬው ጊዜ ያሉት የትዳር ጓደኛ የሌላቸው እናቶች
በዛሬው ጊዜ ያሉት የትዳር ጓደኛ የሌላቸው እናቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በበለጸጉት አገሮች የመንግሥት ድጎማ እየተሰጣቸው ከጋብቻ ውጭ የወለዱትን ሕፃን ያሳድጉ ከነበሩት ወጣት ሴቶች የተለዩ ናቸው። ከጋብቻ ውጪ መውለድ አሳፋሪ ነገር መሆኑ ቀርቷል። እንዲያውም እውቅ ሰዎች የሚደግፉት ነገር ሆኗል። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሴቶች በደንብ የተማሩና ራሳቸውን ማስተዳደር የማያቅታቸው ስለሆኑ ልጅ ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ጋብቻ የግድ አስፈላጊ ነገር መሆኑ ቀርቷል።
የትዳር ጓደኛ የሌላቸው አንዳንድ እናቶች፣ በተለይ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው በመፋታታቸው ምክንያት አንደኛውን ወላጃቸውን ያጡ ከሆኑ እነሱም የሚወልዷቸው ልጆች ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርስባቸው ሲሉ ሳያገቡ መኖር ይመርጣሉ። ሌሎች እናቶች ደግሞ ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉት በምርጫቸው ሳይሆን የትዳር ጓደኞቻቸው ስለከዷቸው ነው። የብሪታንያው ጆሴፍ ራውንትሪ ፋውንዴሽን “የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉት ሆን ብለው ወይም ራስ ወዳድ ሆነው አይደለም። በአንድ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ልጆችም ቢሆኑ እንክብካቤ የተነፈጋቸውና ሥርዓት የሌላቸው አይደሉም” ብሏል።
በዚያም ሆነ በዚህ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች እየበዙ መሄዳቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ምክንያቱም የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆችም ሆኑ ልጆቻቸው የስሜት ውጥረት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ማኅበራዊ ተቀባይነት የማጣት ችግር ሊደርስባቸው ይችላል። አንዳንዶች በእርግጥ አንድ ወላጅ ብቻውን በተሳካ ሁኔታ ልጆቹን ማሳደግ ይችላል? ብለው ይጠይቃሉ። በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? አንድ ክርስቲያን ልጆቹን ለብቻው በሚያሳድግበት ጊዜ የሚገጥሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች ሊወጣ የሚችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ባል የሌላቸው እናቶች ቁጥር ‘ሚስት ከሌላቸው አባቶች ቁጥር በጣም እንደሚበልጥ’ የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ስለዚህም ይህ ጽሑፍ በአብዛኛው የሚያተኩረው ባል በሌላቸው እናቶች ላይ ነው። ይሁን እንጂ የሚብራሩት መሠረታዊ ነጥቦች ሚስት ለሌላቸው አባቶችም ይሠራሉ።
^ አን.6 እናትነት ስለሚያስከትላቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 8, 2002 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ “እናትነት—ልዩ ሴት መሆንን ይጠይቃል?” በሚል ርዕስ የቀረበውን ጽሑፍ ተመልከት።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንድ ፍቺዎች
ብቻቸውን ልጆች የሚያሳድጉ እናቶችን ለማመልከት በመላው ዓለም የሚሠራባቸው ብዙ ዓይነት አጠራሮች አሉ። በአንዳንድ አገሮች “የትዳር ጓደኛ የሌላቸው እናቶች” የሚለው ስያሜ የሚያመለክተው ሕጋዊ ጋብቻ ኖሯቸው የማያውቁ እናቶችን ሲሆን በሌሎች አገሮች ደግሞ “ብቸኛ እናት” የሚለው ስያሜ ወንድ የትዳር ጓደኛ ሳይኖራቸው ብቻቸውን ልጅ የሚያሳድጉ እናቶችን በአጠቃላይ ያመለክታል። እነዚህ እናቶች የተፋቱ፣ የተለያዩ ወይም ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይም ደግሞ እስከነጭራሹ አግብተው የማያውቁ ሊሆኑ ይችላሉ።
በእነዚህ ርዕሶች የትዳር ጓደኛ ሳይኖራቸው ብቻቸውን ልጅ የሚያሳድጉ ወላጆችን ለማመልከት “ልጆቻቸውን ያለ አባት/እናት የሚያሳድጉ ወላጆች” እና “የትዳር ጓደኛ የሌላቸው እናቶች” በሚሉት ስያሜዎች ተጠቅመናል።
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ካርታ]
ልጆችን ያለ አባት ወይም ያለ እናት ማሳደግ—በብዙ አገሮች እየጨመረ የመጣ አዝማሚያ
ዩናይትድ ስቴትስ፦ “ከ1970 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉ እናቶች ቁጥር ከ3 ሚልዮን ወደ 10 ሚልዮን ደርሷል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ልጆቻቸውን ያለ እናት የሚያሳድጉ አባቶች ቁጥርም ከ393,000 ወደ 2 ሚልዮን አሻቅቧል።”—ዩ ኤስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ
ሜክሲኮ፦ ላ ሆርናዳ በተባለው ጋዜጣ መሠረት በአገሪቱ ከሚያረግዙ ሴቶች መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
አየርላንድ፡- በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር በ1981 ከነበረው 5.7 በመቶ በ1991 ወደ 7.9 በመቶ ከፍ ብሏል። “እናቶች ልጆቻቸውን ያለ አባት ለማሳደግ የሚገደዱበት ዋነኛው ምክንያት የትዳር መፍረስ ሆኗል።”—ሲንግል ማዘርስ ኢን አን ኢንተርናሽናል ኮንቴክስት፣ 1997
ብሪታንያ፦ “በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ብዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ25 በመቶ በላይ ሆኗል። ይህም ባለፉት 30 ዓመታት ሳያገቡ የሚወልዱ እናቶችና የሚፋቱ ባልና ሚስቶች ቁጥር በጣም መብዛቱን ያመለክታል።”—ዘ ታይምስ፣ ለንደን፣ መጋቢት 2, 2000
ፈረንሳይ፦ “ከ1970ዎቹ መገባደጃ ዓመታት ወዲህ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ብዛት ከ50 በመቶ በላይ አድጓል።”—ሲንግል ማዘርስ ኢን አን ኢንተርናሽናል ኮንቴክስት፣ 1997
ጀርመን፦ “የትዳር ጓደኛ የሌላቸው ወላጆች ብዛት ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በእጥፍ አድጓል። በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ሁሉም ቤተሰቦች ማለት ይቻላል፣ . . . የሚተዳደሩት በእናቶች ነው።”—ሲንግል ማዘርስ ኢን አን ኢንተርናሽናል ኮንቴክስት፣ 1997
ጃፓን፦ ‘ከ1970ዎቹ ዓመታት ወዲህ ባል በሌላቸው እናቶች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር እያደገ መጥቷል።’ በ1997፣ 17 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች ይተዳደሩ የነበረው ባል በሌላቸው እናቶች ነው።—ሲንግል ማዘርስ ኢን አን ኢንተርናሽናል ኮንቴክስት፣ 1997፤ ዘ ወርልድስ ዊመን 2000:- ትሬንድስ ኤንድ ስታትስቲክስ
ግሪክ፦ “ከ1980 ወዲህ [በግሪክ] ሳያገቡ የወለዱ እናቶች ቁጥር በ29.8 በመቶ አድጓል። ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ አኃዛዊ መረጃ መሠረት በ1997 ከሕጋዊ ጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆች ቁጥር 3.3 በመቶ ሲሆን በ1980 ግን 1.1 በመቶ ብቻ ነበር።”—ታ ኒያ ጋዜጣ፣ አቴንስ፣ መስከረም 4, 1998
አውስትራሊያ፦ ከአራት ልጆች መካከል አንዱ የሚኖረው ከወላጅ እናቱ ወይም ከወላጅ አባቱ ጋር ብቻ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ምክንያት የሚሆነው የወላጆቹ ትዳር መፍረስ ወይም መጣላት ነው። በመጪዎቹ 25 ዓመታት በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር ከ30 እስከ 66 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል።—አውስትራሊያን ቢሮ ኦቭ ስታትስቲክስ