በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትናንሽ ስህተቶች የከፋ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ

ትናንሽ ስህተቶች የከፋ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ

ትናንሽ ስህተቶች የከፋ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ

በሐምሌ 6, 1988 በሰሜን ባሕር ላይ በሚገኝ ፓይፐር አልፋ የተባለ የባሕር ላይ ነዳጅ ማውጫ ጣቢያ የሚሠሩ ሠራተኞች አንድ የተበላሸ ፓምፕ ሲጠግኑ ከቆዩ በኋላ ጥገናውን ሳይጨርሱ ሄዱ። በቀጣዩ ፈረቃ የገቡት ሠራተኞች ስለተፈጠረው ሁኔታ በቂ መረጃ ባለማግኘታቸው ፓምፑን አስነሱት። ወዲያው እሳት ተነሳ። የነዳጅ ማውጫ ጣቢያው ከባሕር በላይ ከፍ ተደርጎ በመሠራቱ የተነሳ ማምለጫ ያጡ 167 የሚያህሉ ሰዎች በቃጠሎው ሕይወታቸው አለፈ።

ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ በሐምሌ 25, 2000 ኮንኮርድ የተባለ እጅግ ፈጣን የሆነ አውሮፕላን ፓሪስ ከሚገኘው የሻርል ደ ጎል አውሮፕላን ማረፊያ ለመነሳት እየተንደረደረ ነበር። አውሮፕላኑ ፍጥነት ሲጨምር በመንደርደሪያው ላይ የነበረ አንድ አነስተኛ የቲታኒየም ብረት ቁራጭ አንደኛውን ጎማ አፈነዳው። የጎማው መፈንዳት በክንፉ ላይ የነበረው የነዳጅ ማጠራቀሚያ እንዲቀደድ አደረገ። ከነዳጅ ማጠራቀሚያው የሚፈሰው ነዳጅ በአውሮፕላኑ የግራ ሞተሮች ውስጥ በመግባቱ ሞተሮቹ ከመጥፋታቸውም በላይ 60 ሜትር የሚያህል ርዝመት ያለው የእሳት ነበልባል ተፈጠረ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አውሮፕላኑ በአንድ ሆቴል ላይ ተከሰከሰና መሬት ላይ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ በውስጡ የነበሩት ተሳፋሪዎች በሙሉ አለቁ።

እንዲህ ያሉ አደጋዎችን በተመለከተ ጄምስ ቻይልስ የተባሉ አንድ ሰው አደጋን መጋበዝ—ከተራቀቀው ቴክኖሎጂ የምንማራቸው ትምህርቶች በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አንዳንድ ጊዜ ከሰው ቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ በሚችሉ ማሽኖች በተሞላው በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የተለመዱ ስህተቶች ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አምነን መቀበል ይኖርብናል።” ሳይንስ የተሰኘው መጽሔት የቻይልስን መጽሐፍ አስመልክቶ ባቀረበው ግምገማ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት ያሳዩት አስገራሚ የሆነ ፈጣን እድገት እጅግ የሚያስፈነድቅ ነው። ግዑዙን ዓለም አብጠርጥረን ለማወቅና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ እንዳለ እንዲሰማን አድርጎናል። [ቢሆንም] አሁን ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ ከስህተቶች ነጻ ነን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም።”

ሳይንስ መጽሔት በጣም አደገኛ የሆኑትን ቴክኖሎጂዎች አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በጣም ትንሹ [ስህተት] እንኳን በጣም የከፋ መዘዝ ያስከትላል። በእንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ፍጽምናን መጠበቅ ይኖርብናል።” ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በታሪክ ዘመኑ ያሳየው የሥራ ብቃት ፍጽምና ሊደረስበት የሚቻል እንደሆነ ያሳያል? በፍጹም! ስለዚህ በተለያዩ ስህተቶች ሳቢያ የሚፈጠሩ አደጋዎች ወደፊትም መከሰታቸው አይቀርም።

ይሁን እንጂ እነዚህ አደጋዎች ለዘላለም አይቀጥሉም። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ወደፊት በሰው ልጅ ስህተት ወይም የአቅም ገደብ የተነሳ ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ የማይቀጠፍበት ጊዜ እንደሚመጣ በእምነት ሊጠባበቁ ይችላሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ በሰማያዊ መንግሥቱ መስተዳደር አማካኝነት የሞትን፣ የሐዘንንና የሥቃይን መንስዔዎች በሙሉ ለማስወገድ ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/Toshihiko Sato