በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኤድስን መግታት ይቻል ይሆን? ከሆነስ እንዴት?

ኤድስን መግታት ይቻል ይሆን? ከሆነስ እንዴት?

ኤድስን መግታት ይቻል ይሆን? ከሆነስ እንዴት?

በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የኤድስን መኖር አያምኑም ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ስለ ኤድስ አንስተው መወያየት እንኳን አይፈልጉም ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ወጣቶችን ለማስተማርና በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ ውይይት የማድረግ ባሕል እንዲሰፍን ለማበረታታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። እነዚህ ጥረቶች በተወሰነ ደረጃ ውጤት ያስገኙ ቢሆንም እንኳ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤና ልማድ በጣም ሥር የሰደደ ከመሆኑ የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ሆኗል።

በሕክምናው መስክ የታየ እመርታ

በሕክምናው መስክ ሳይንቲስቶች ስለ ኤች አይ ቪ ብዙ ግንዛቤ ያገኙ ከመሆኑም ሌላ የብዙዎችን ሕይወት ማራዘም የቻሉ መድኃኒቶችን መፈልሰፍ ችለዋል። ቢያንስ ሦስት ዓይነት የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቶችን በማቀናጀት የሚሰጠው ሕክምና ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

እነዚህ መድኃኒቶች ፈውስ ማስገኘት ባይችሉም እንኳ በተለይ በበለጸጉ አገሮች በኤች አይ ቪ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ችለዋል። ብዙ ሰዎች እነዚህ መድኃኒቶች በማደግ ላይ ወደሚገኙ አገሮችም መግባት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መድኃኒቶቹ ውድ በመሆናቸው በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች እነዚህን መድኃኒቶች የመግዛት አቅም የላቸውም።

ይህ ሁኔታ፣ ገንዘብ ከሰው ሕይወት ይበልጣል? የሚል አከራካሪ ጉዳይ አስነስቷል። የብራዚል የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ፓውሎ ቴሼይራ ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል:- “መድኃኒቶቹን የሚያመርቱት ኩባንያዎች ከልክ ያለፈ ትርፍ እንዲያጋብሱ ሲባል ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚያስችሏቸውን መድኃኒቶች ማግኘት ተስኗቸው ሲቸገሩ ዝም ብለን ማየት አንችልም።” አክለውም “ግብረገብንና ሰብዓዊ ርኅራኄን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ ለንግድ ጥቅም ብቻ መሯሯጥ አይገባም” ብለዋል።

አንዳንድ አገሮች የመድኃኒት አምራች የሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎችን የባለቤትነት መብት ባለማክበር የንግድ ምልክት የሌላቸውን ተመሳሳይ መድኃኒቶች በዝቅተኛ ዋጋ ለማስገባት ወይም ለመሥራት ወስነዋል። * አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ “[የንግድ ምልክት የሌላቸው መድኃኒቶች] ዝቅተኛ ዋጋ ከዩናይትድ ስቴትስ መነሻ ዋጋ 82 በመቶ ዝቅ ብሎ ተገኝቷል” ሲል ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል ዘግቧል።

ሕክምናው ያጋጠሙት እንቅፋቶች

ይሁንና ውሎ አድሮ ትልልቆቹ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የኤድስ መድኃኒቶችን ለታዳጊ አገሮች ዝቅ ባለ ዋጋ ማቅረብ ጀምረዋል። በዚህ መንገድ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች መድኃኒቶቹን ማግኘት ይችላሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ መድኃኒቶች በታዳጊ አገሮች ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከባድ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ እንቅፋቶች መካከል አንዱ የዋጋው ጉዳይ ነው። ዋጋው በእጅጉ እንዲቀንስ ቢደረግም መድኃኒቶቹ የሚያስፈልጓቸው ብዙዎቹ ሰዎች አሁንም የመግዛት አቅም የላቸውም።

ሌላው ችግር ደግሞ የመድኃኒቶቹ አወሳሰድ ነው። በየዕለቱ ሰዓቱን በትክክል እየጠበቁ ብዙ ኪኒኖች መውሰድ ይጠይቃል። ታካሚው መድኃኒቶቹን በአግባቡ የማይወስድ ወይም በየመሃሉ የሚያቋርጥ ከሆነ መድኃኒቱን መቋቋም የሚችሉ የኤች አይ ቪ ዝርያዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ምግብ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃም ሆነ የሕክምና ተቋማት በበቂ ሁኔታ በማይገኙባቸው የአፍሪካ አገሮች ታካሚዎች መድኃኒቶቹን በትክክል እንዲወስዱ ማድረግ አስቸጋሪ ነው።

በተጨማሪም መድኃኒቶቹን የሚወስዱ ሰዎች ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ቫይረሱ መድኃኒቶቹን መቋቋም ከጀመረ የመድኃኒቶቹ ዓይነት መለወጥ አለበት። ይህ ደግሞ ልምድ ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች ማግኘት የሚጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ምርመራው የሚጠይቀው ወጪም ቀላል አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ መድኃኒቶቹ የራሳቸው የሆነ ጉዳት ያላቸው ሲሆን መድኃኒት መቋቋም የሚችሉ ቫይረሶችም እየተፈጠሩ ይሄዳሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሰኔ 2001 ኤድስን አስመልክቶ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ታዳጊ አገሮችን ለመርዳት ለጤና አገልግሎት የሚውል የእርዳታ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰባሰብ ሐሳብ ቀርቦ ነበር። ለዚህ እርዳታ ከ7 ቢልዮን እስከ 10 ቢልዮን የሚደርስ የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገምቷል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ቃል የተገባው ገንዘብ ከሚፈለገው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው።

ሳይንቲስቶች በሽታውን የሚከላከል ክትባት እናገኛለን የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸው ሲሆን የተለያዩ ክትባቶችም በተለያዩ አገሮች እየተሞከሩ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥረቶች ቢሳኩ እንኳን ክትባቱ እስኪዘጋጅ፣ እስኪሞከርና አስተማማኝነቱ ተረጋግጦ በስፋት ጥቅም ላይ እስኪውል በርከት ያሉ ዓመታት ይወስዳል።

እንደ ብራዚል፣ ታይላንድና ኡጋንዳ ያሉ አንዳንድ አገሮች በዘረጉት የሕክምና ፕሮግራም ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ብራዚል በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥቅም ላይ በማዋል በኤድስ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በግማሽ መቀነስ ችላለች። የገንዘብ አቅሙ ያላት ትንሿ አገር ቦትስዋና በአገሪቱ ውስጥ በኤች አይ ቪ ለተጠቁ ሰዎች የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቶች ለማዳረስና አስፈላጊ የሆኑትን የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለማሟላት ጥረት እያደረገች ነው።

ኤድስ ድል የሚደረግበት መንገድ

ኤድስን መከላከል የሚቻል መሆኑ ከሌሎች ወረርሽኞች የተለየ ያደርገዋል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ካከበሩ ከኤድስ ራሳቸውን መጠበቅ ይችላሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች የማያሻሙ ናቸው። ያልተጋቡ ሰዎች ከጾታ ግንኙነት መታቀብ አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:18) የተጋቡ ሰዎችም ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ መሆንና ከምንዝር መራቅ አለባቸው። (ዕብራውያን 13:4) በተጨማሪም አንድ ሰው ከደም እንድንርቅ የሚያዝዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ መከተሉ በበሽታው ከመያዝ ይጠብቀዋል።—ሥራ 15:28, 29

በበሽታው የተያዙ ሰዎች አምላክ በቅርቡ ስለሚያመጣው ከበሽታ ነፃ የሆነ ዓለም በመማርና አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች በማሟላት ከፍተኛ ደስታና መጽናኛ ማግኘት ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በሽታን ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ያሉት ችግሮች በሙሉ እንደሚወገዱ ያረጋግጥልናል። ይህ ተስፋ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጾአል:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:3, 4

ይህ ዋስትና የተሰጠው ውድ መድኃኒቶችን የመግዛት አቅም ላላቸው ብቻ አይደለም። ኢሳይያስ 33:24 “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” በማለት በራእይ ምዕራፍ 21 ላይ የተገለጸውን ትንቢታዊ ቃል ያጠናክርልናል። በዚያ ዘመን በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ የአምላክን ሕግ የሚጠብቁ ከመሆናቸውም በላይ ፍጹም የሆነ ጤና ያገኛሉ። በዚህ መንገድ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኤድስም ሆነ ሌሎች በሽታዎች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 የንግድ ምልክት የሌላቸው መድኃኒቶች በሌሎች የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የተፈበረኩ መድኃኒቶችን በማስመሰል የሚሠሩ ናቸው። የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የሆኑ አገሮች ድንገተኛና አጣዳፊ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የመድኃኒቶችን የባለቤትነት መብት ያለማክበር ህጋዊ ፈቃድ አላቸው።

[በገጽ 9 እና 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ስፈልገው የነበረው እውነተኛ ፈውስ ይህ ነው

በደቡባዊ አፍሪካ የምኖር የ23 ዓመት ወጣት ነኝ። በኤች አይ ቪ መያዜን ያወቅኩበት ቀን አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል።

በሕክምና ክፍሉ ውስጥ ከእናቴ ጋር ቁጭ ብዬ ሳለ ነበር ዶክተሩ መርዶዬን የነገረኝ። በሕይወቴ እንደዚያን ዕለት ያዘንኩበት ቀን አልነበረም። ሁሉ ነገር ተመሰቃቀለብኝ። ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም። ምርመራው ላይ ስህተት ተሠርቶ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ። የምናገረውና የማደርገው ነገር ሁሉ ጠፋኝ። አልቅሽ አልቅሽ ቢለኝም የማለቅስበት እንባ እንኳ አልነበረኝም። ዶክተሩ ስለ ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቶችና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ከእናቴ ጋር እየተነጋገረ የነበረ ቢሆንም በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ምን እንደሚል እንኳ ሊገባኝ አልቻለም ነበር።

እማርበት በነበረው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ ሰው አስይዞኝ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ። ያለሁበትን ሁኔታ ሊረዳልኝ ለሚችል ሰው ስሜቴን ለማካፈል ብፈልግም ማንም ሰው ወደ አእምሮዬ ሊመጣልኝ አልቻለም። የከንቱነትና የዋጋቢስነት ስሜት ተሰማኝ። ቤተሰቦቼ አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርጉልኝም የተስፋ መቁረጥና የፍርሃት ስሜት አደረብኝ። እንደ ሌላ ማንኛውም ወጣት እኔም ብዙ የምመኛቸው ነገሮች ነበሩ። በሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ለማግኘት ሁለት ዓመት ብቻ ቀርቶኝ የነበረ ቢሆንም ያ ሁሉ ተስፋ እንዳልነበረ ሆነ።

የታዘዙልኝን የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቶች መውሰድና ወደ ኤድስ ሕሙማን አማካሪዎች መሄድ ብጀምርም ያደረብኝ ጭንቀት ሊለቀኝ አልቻለም። ከመሞቴ በፊት እውነተኛውን ክርስትና እንዲያሳውቀኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። የጰንጠቆስጤ እምነት ተከታይ የነበርኩ ቢሆንም ሊጠይቀኝ እንኳ የመጣ አንድም የቤተ ክርስቲያን ሰው አልነበረም። ከሞትኩ በኋላ ምን እንደሚደርስብኝ በትክክል ማወቅ ፈልጌ ነበር።

በ1999 ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በሬን አንኳኩ። ያን ቀን በጣም አሞኝ የነበረ ቢሆንም ሳሎን ውስጥ እንደ ምንም ብዬ ቁጭ አልኩ። ሁለቱ ሴቶች ራሳቸውን ካስተዋወቁኝ በኋላ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ በመርዳት ላይ መሆናቸውን ነገሩኝ። ጸሎቴ በመጨረሻ መልስ በማግኘቱ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። ሆኖም አቅም አንሶኝ ስለነበር ረዘም ላለ ጊዜ ማንበብም ሆነ በትኩረት መከታተል አልቻልኩም።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደምፈልግ ነገርኳቸውና ቀጠሮ ይዘን ተለያየን። ይሁንና የቀጠሮው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ባደረብኝ የመንፈስ ጭንቀት ሳቢያ የአእምሮ ሕሙማን ወደሚታከሙበት ሆስፒታል ገባሁ። ከሦስት ሳምንታት በኋላ ከሆስፒታል ስወጣ ምሥክሮቹ እንዳልረሱኝ በማወቄ በጣም ደስ አለኝ። ከምሥክሮቹ አንዷ ዘወትር እየመጣች ትጠይቀኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በተወሰነ ደረጃ አገገምኩና ዓመቱ መገባደጃ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ የጤንነቴ ሁኔታ በየጊዜው ይለዋወጥ ስለነበረ ይህን ማድረጉ ቀላል አልነበረም። ሆኖም የምታስጠናኝ ሴት ችግሬን ትረዳልኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ታጋሽ ነበረች።

ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስማርና ይሖዋን ማወቅና የዘላለም ሕይወት ተስፋን መጠባበቅ ምን ማለት እንደሆነ ስገነዘብ ልቤ በጣም ተነካ። በተጨማሪም በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ተረዳሁ። በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን ሁሉ ስለሚተካው የአምላክ መንግሥት ያገኘሁት እውቀትም እጅግ ያስደሰተኝ ከመሆኑም በላይ አኗኗሬን ሙሉ በሙሉ እንድለውጥ አነሳሳኝ።

ስፈልገው የነበረው እውነተኛ ፈውስ ይህ ነው። ይሖዋ አሁንም እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ ማወቄ በጣም አጽናናኝ። ቀደም ሲል አምላክ እንደጠላኝና ይህ በሽታ የያዘኝም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትን ዝግጅት እንዳደረገ ሳውቅ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚለው የ1 ጴጥሮስ 5:7 ጥቅስ በሚገልጸው መሠረት በእርግጥም አምላክ የሚያስብልን መሆኑን ተገነዘብኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማጥናትና በመንግሥት አዳራሽ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የተቻለኝን ሁሉ እያደረግኩ ነው። ይህን ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እንኳ የሚያስጨንቀኝን ሁሉ ለይሖዋ በጸሎት በመግለጽ ብርታትና ማጽናኛ እንዲሰጠኝ እለምነዋለሁ። በተጨማሪም የጉባኤያችን አባላት ምንጊዜም ከጎኔ ስለሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ከጉባኤያችን አባላት ጋር በመሆን አዘውትሬ በወንጌላዊነቱ ሥራ እካፈላለሁ። ሌሎችን በተለይ ደግሞ እኔ ባለሁበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት እፈልጋለሁ። ታኅሣሥ 2001 ተጠመቅኩ።

[ሥዕል]

ስለ አምላክ መንግሥት ማወቄ እጅግ አስደስቶኛል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቦትስዋና የሚገኝ የኤድስ ሕሙማን አማካሪዎች ቡድን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሁሉም ሰው የተሟላ ጤንነት ይኖረዋል