በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኤድስ በአፍሪካ እየተዛመተ ነው

ኤድስ በአፍሪካ እየተዛመተ ነው

ኤድስ በአፍሪካ እየተዛመተ ነው

“ከፍተኛ እልቂት በላያችን አንዣብቧል።”

በአፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት ስቲቨን ሉዊስ የተናገሯቸው እነዚህ ቃላት ብዙዎች ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው የኤድስ ወረርሽኝ ምን ያህል እንዳሳሰባቸው የሚጠቁሙ ናቸው።

ኤች አይ ቪ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ኤድስም በበኩሉ የተለያዩ ችግሮች እንዲባባሱ ያደርጋል። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮችና ኤድስ እየተስፋፋባቸው ባሉት ሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚታየው ሁኔታ በአብዛኛው ከሚከተሉት ችግሮች ጋር የተያያዘ ነው።

ሥነ ምግባር። ኤች አይ ቪ የሚተላለፍበት ዋነኛው መንገድ የጾታ ግንኙነት በመሆኑ በግልጽ የተቀመጡ የሥነ ምግባር ደንቦች አለመኖራቸው ለበሽታው መዛመት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ብዙዎች ያልተጋቡ ሰዎችን ከወሲብ እንዲታቀቡ መምከር እምብዛም ፋይዳ ያለው ሆኖ አይታያቸውም። ፍራንስዋ ዱፉር የተባሉ ሰው ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ እየታተመ በሚወጣው ዘ ስታር የተሰኘ ጋዜጣ ላይ “ወሲባዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ በየዕለቱ የሚያዩአቸው ብዙ ነገሮች ስላሉና እነዚህም አስተሳሰባቸውንና ምግባራቸውን ስለሚቀርጹት ወጣቶችን ከወሲብ እንዲታቀቡ መምከሩ ብቻ የሚፈይደው ነገር አይኖርም” ሲሉ ጽፈዋል።

በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች ላይ የሚታየው ምግባር ለዚህ አባባል ጥሩ ማረጋገጫ ነው። ለምሳሌ ያህል በአንድ አገር የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው ከ12 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል።

በደቡብ አፍሪካ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል በአገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ሲትዝን በተባለ የጆሃንስበርግ ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ እንደገለጸው ከሆነ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል “እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ በሚኖሩ ሴቶችና ልጆች ላይ ከማንኛውም የጤና ጠንቅ የከፋ ስጋት ፈጥሯል።” ይኸው ዘገባ አክሎ ሲናገር “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በልጆች ላይ የሚፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል በእጥፍ ጨምሯል . . . እነዚህ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ኤች አይ ቪ የያዘው ሰው ልጃገረድን ከደፈረ ይፈወሳል በሚል አጉል እምነት ሳይሆን አይቀርም” ብሏል።

የአባለዘር በሽታዎች። በእነዚህ አገሮች ውስጥ በአባለዘር በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል “የአባለዘር በሽታ ያለበት ሰው በኤች አይ ቪ-1 የመያዝ ዕድሉ ከ2 እስከ 5 እጥፍ ይጨምራል” ብሏል።

ድህነት። ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ መሆናቸው ለኤድስ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በበለጸጉ አገሮች እንደ መሠረታዊ ነገር ተደርገው የሚታዩ ነገሮችን በአብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ሆነ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አይገኝም። በአብዛኞቹ ገጠራማ ቦታዎች በቂ መንገዶች የሉም ወይም ከናካቴው መንገድ የሚባል ነገር የለም። ብዙዎቹ ነዋሪዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ከመሆኑም በላይ በቂ የሕክምና መስጫ ተቋማት የሉም።

ኤድስ በንግዱና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። በርካታ ሠራተኞች በኤድስ እየተጠቁ በመሆኑ የማዕድን ማውጫ ኩባንያዎች ምርታቸው እየቀነሰ ነው። አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ተጨማሪ መሣሪያዎችና ማሽኖች በመትከል ያጡትን የሰው ኃይል ለማካካስ እያሰቡ ነው። በ2000 በአንድ የፕላቲንየም ማዕድን ማውጫ በኤድስ የተያዙት ሠራተኞች ቁጥር በእጥፍ ገደማ እንደጨመረ የተገመተ ሲሆን 26 በመቶ የሚሆኑት በበሽታው ተጠቅተዋል።

በኤድስ ሳቢያ የተከሰተው ሌላው አሳዛኝ ሁኔታ ደግሞ በበሽታው ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ ነው። እነዚህ ልጆች ወላጆቻቸውን ከማጣታቸውና በኑሮ ከመደቆሳቸውም በተጨማሪ ኤድስ የሚያስከትለውን ጠባሳ ተሸክመው ለመኖር ይገደዳሉ። ዘመዶቻቸው ወይም የሚኖሩበት ማኅበረሰብ በአብዛኛው እነሱን ለመርዳት የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም ወይም ለመርዳት ፈቃደኛ አይሆኑም። ብዙዎቹ ልጆች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የሚገደዱ ሲሆን አንዳንዶቹ በዝሙት አዳሪነት ይሰማራሉ። ይህም በሽታው ይበልጥ እንዲዛመት በር ይከፍታል። በርከት ያሉ አገሮች እነዚህን ልጆች ለመርዳት መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ፕሮግራሞችን ሥራ ላይ አውለዋል።

አለማወቅ። በኤች አይ ቪ የተያዙ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አያውቁም። ብዙዎቹ በሽታው የሚያመጣባቸውን ነቀፋ ስለሚፈሩ ምርመራ ለማድረግ አይፈልጉም። የተባበሩት መንግሥታት የተቀናጀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም (ዩ ኤን ኤድስ) ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ “ኤች አይ ቪ ያለባቸው ወይም እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ሊነፈጉ፣ መኖሪያ ቤትና ሥራ ሊያጡ፣ ጓደኞቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው ሊያገሏቸው፣ የኢንሹራንስ ዋስትና ሊነፈጉ ወይም ወደ ሌላ አገር እንዳይገቡ ሊከለከሉ ይችላሉ” ይላል። እንዲያውም አንዳንዶች ኤች አይ ቪ እንደያዛቸው በመታወቁ ብቻ ተገድለዋል።

ባሕል። በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ባለው ባሕል በአብዛኛው ሴቶች የትዳር ጓደኛቸው ከሌላ ሴት ጋር ስላለው ግንኙነት የመጠየቅ፣ የጾታ ግንኙነት መፈጸም አልፈልግም የማለት ወይም በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ለበሽታ የማያጋልጡ ዘዴዎችን የመጠቀም ሐሳብ የማቅረብ መብት የላቸውም። ባሕላዊ እምነቶችን የሚከተሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ኤድስ ግንዛቤ የሌላቸው ከመሆኑም በላይ የኤድስን መኖር አያምኑም። ለምሳሌ ያህል በሽታውን ከጥንቆላ ጋር ሊያያይዙትና እርዳታ ማግኘት የሚችሉት ከጠንቋዮች እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ።

የሕክምና ተቋማት እጥረት። ያሉት የተወሰኑ የሕክምና ተቋማት በሕሙማን የተጨናነቁ ሲሆኑ ከሕሙማኑም መካከል ብዙዎቹ የኤድስ ሰለባዎች ናቸው። ሁለት ትልልቅ ሆስፒታሎች አልጋ ከያዙት ታካሚዎቻቸው መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በኤች አይ ቪ የተያዙ መሆናቸውን ሪፖርት አድርገዋል። በክዋዙሉ-ናታል ግዛት የሚገኝ የአንድ ሆስፒታል የሕክምና ክፍል ዋና ኃላፊ የሆኑ ሰው የሕክምና ክፍሎቻቸው አቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ 140 በመቶ ለመሥራት እንደተገደዱ ገልጸዋል። አንዳንድ ጊዜ በአንድ አልጋ ላይ ሁለት ታካሚዎች እንዲተኙ የሚደረግ ሲሆን ሌላ ሦስተኛ ታካሚ ደግሞ ከታች ወለሉ ላይ እንዲተኛ ይደረጋል!—ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ሲሆን ወደፊት ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያሉት ሁኔታዎች ይጠቁማሉ። የዩ ኤን ኤድስ ባልደረባ የሆኑት ፒተር ፓዮ “ወረርሽኙ አሁንም ቢሆን ገና ጀመረ እንጂ በደንብ አልተስፋፋም” ብለዋል።

በአንዳንድ አገሮች የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ጥረት በመደረግ ላይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሰኔ 2001 ላይ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ ለመነጋገር ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ስብሰባ አካሂዶ ነበር። የሰው ልጅ እያደረገ ያለው ጥረት ግቡን ይመታ ይሆን? የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኤድስ የሚገታውስ መቼ ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኔቫይረፒን የተሰኘው የኤድስ መድኃኒትና በደቡብ አፍሪካ የተፈጠረው ውዝግብ

ኔቫይረፒን ምንድን ነው? ኒኮል ኢታኖ የተባሉት ጋዜጠኛ እንዳሉት ኔቫይረፒን “ፀረ ሬትሮቫይረስ መድኃኒት ሲሆን ኤድስ [ከእናት] ወደ ልጅዋ ሊተላለፍ የሚችልበትን አጋጣሚ በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል የምርመራ ውጤቶች አረጋግጠዋል።” አንድ የጀርመን ኩባንያ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መድኃኒቱን ለደቡብ አፍሪካ በነፃ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም እስከ ነሐሴ 2001 ድረስ መንግሥት የቀረበለትን ሐሳብ አለመቀበሉ ታውቋል። ችግሩ ምንድን ነው?

ደቡብ አፍሪካ በኤድስ ሕሙማን ቁጥር ከዓለም ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘች ሲሆን 4.7 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎቿ በኤች አይ ቪ ተጠቅተዋል። የለንደኑ ዚ ኢኮኖሚስት በየካቲት 2002 እትሙ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ “ኤች አይ ቪ የኤድስ በሽታ ያመጣል የሚለውን በስፋት ተቀባይነት ያገኘ አመለካከት ያላመኑበት” ከመሆኑም በላይ “ፀረ ኤድስ በሆኑ መድኃኒቶች ዋጋ፣ አስተማማኝነትና ጠቀሜታ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። በመድኃኒቶቹ ላይ እገዳ ባይጥሉም የደቡብ አፍሪካ ዶክተሮች መድኃኒቶቹን እንዳይጠቀሙባቸው ለማሳመን ጥረት ተደርጓል” ሲል ዘግቧል። ይህ ጉዳይ ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? በደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በኤች አይ ቪ ተይዘው ስለሚወለዱና ነፍሰ ጡር ከሆኑ ሴቶች መካከል 25 በመቶዎቹ የቫይረሱ ተሸካሚ በመሆናቸው ነው።

እንዲህ ያለ የአመለካከት ልዩነት በመፈጠሩ መንግሥት መድኃኒቱን እንዲያከፋፍል ጫና ለመፍጠር ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተመርቷል። የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውሳኔውን በሚያዝያ 2002 አስተላልፏል። ራቪ ኔስማን ዘ ዋሽንግተን ፖስት ላይ እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ብያኔ “መንግሥት መድኃኒቱን መስጠት በሚችሉ የጤና ተቋማት ሁሉ እንዲያቀርብ” የሚያዝዝ ነው። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቀደም ሲልም መድኃኒቱ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት መጀመሪያ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ 18 ጣቢያዎች ላይ እንዲሞከር ያደረገ ቢሆንም ይህ አዲስ ውሳኔ በኤች አይ ቪ ለተያዙ ነፍሰ ጡር ሴቶች ጥሩ ተስፋ ፈንጥቋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሴሎችን የሚያታልል መሠሪ ቫይረስ

እስቲ ለጥቂት ደቂቃዎች ቆም እንበልና የሰውን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክመውን ረቂቅ ቫይረስ (ኤች አይ ቪ) እንመርምር። አንዲት ሳይንቲስት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “የቫይረስ ቅንጣቶችን ለብዙ ዓመታት በኤሌክትሮን አጉሊ መነጽር ስመረምር የኖርኩ ቢሆንም በዚህ እጅግ በጣም ትንሽ በሆነ ነገር ውስጥ የሚታየው ፍጹም ትክክለኛ የሆነና የተወሳሰበ ንድፍ አሁንም ድረስ በጣም ያስገርመኛል።”

ቫይረስ ከባክቴሪያ ያነሰ ሲሆን ባክቴሪያ ደግሞ ከሰው ልጅ ሴል በእጅጉ ያነሰ ነው። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው ከሆነ ኤች አይ ቪ በጣም ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ “በዚህ አረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ ከምናገኘው አራት ነጥብ ውስጥ አንዷ 230 ሚልዮን [የኤች አይ ቪ ቅንጣቶችን] ልትይዝ ትችላለች።” አንድ ቫይረስ፣ ሴል ውስጥ ሰርጎ በመግባት የሴሉን ክፍሎች መቆጣጠር እስካልቻለ ድረስ መባዛት አይችልም።

ኤች አይ ቪ የአንድን ሰው አካል በሚያጠቃበት ጊዜ በቀላሉ የማይገመቱትን የሰውነት የመከላከያ ኃይሎች መቋቋም ይኖርበታል። * በነጭ የደም ሴሎች የተዋቀረው ይህ የመከላከያ ኃይል የሚመረተው በመቅኒ ውስጥ ነው። ነጭ የደም ሴሎች ሁለት ዓይነት ዋና ዋና የሊምፍ ሴሎችን ያቀፉ ሲሆን እነዚህም ቲ ሴሎችና ቢ ሴሎች በመባል ይታወቃሉ። ፋጎሳይት ወይም “ሴል በሊታዎች” በመባል የሚታወቁ ነጭ የደም ሴሎችም አሉ።

ቲ ሴሎች በተለያዩ ክፍሎች የሚከፈሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የሥራ ድርሻ አላቸው። ጠቋሚ ቲ ሴሎች ከእነዚህ አንዱ ሲሆኑ በውጊያው ስልት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ጠቋሚ ቲ ሴሎች የውጪ ወራሪዎችን ለይቶ በማወቅና እነዚህን ወራሪዎች የሚያጠቁና የሚደመስሱ ሴሎች እንዲመረቱ መመሪያ በመስጠት ያገለግላሉ። ኤች አይ ቪ ዋነኛ የጥቃት ዒላማው የሚያደርገው እነዚህን ጠቋሚ ሴሎች ነው። ገዳይ ቲ ሴሎች ወረራ የተፈጸመባቸውን ሴሎች እንዲያጠፉ ጥቆማ ይደርሳቸዋል። ቢ ሴሎች ደግሞ በሽታን የሚከላከሉ ፀረ እንግዳ አካላት ያመርታሉ።

የረቀቀ ስልት

ኤች አይ ቪ ሬትሮቫይረስ በመባል ከሚታወቁት ቫይረሶች መካከል የሚመደብ ሲሆን ጀነቲካዊ ንድፉ ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) ሳይሆን አር ኤን ኤ (ራይቦኑክሊክ አሲድ) ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኤች አይ ቪ ከባድ የበሽታ ምልክቶች ሳይታዩ ረዘም ላለ ጊዜ ተደብቆ ሊቆይ የሚችል በመሆኑ ሌንቲቫይረስ በመባል በሚታወቀው የሬትሮቫይረሶች ንዑስ ክፍል ውስጥ ይመደባል።

ኤች አይ ቪ አንድ ሴል ውስጥ ከገባ በኋላ ዓላማውን ለማሳካት የሴሉን የአሠራር ዘዴ መጠቀም ይችላል። ኤች አይ ቪው በሰውነት ውስጥ መባዛት ይችል ዘንድ የሴሉን የዲ ኤን ኤ “ፕሮግራም ይለውጠዋል።” ይሁን እንጂ ይህን ከማድረጉ በፊት አንድ ለየት ያለ “ኮድ” መጠቀም ይኖርበታል። የሴሉ ክፍሎች ኤች አይ ቪው የሚያስተላልፈውን መልእክት መረዳት እንዲችሉ የራሱን አር ኤን ኤ ወደ ዲ ኤን ኤ መለወጥ አለበት። ይህን ለማከናወን ደግሞ ሪቨርስ ትራንስክሪፕቴስ የተባለውን በቫይረሶች ውስጥ የሚገኝ ኤንዛይም ይጠቀማል። ሴሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ የኤች አይ ቪ ቅንጣቶችን ሲያመርት ከቆየ በኋላ ይሞታል። የተባዙት የኤች አይ ቪ ቅንጣቶች ሌሎች ሴሎችን ማጥቃት ይጀምራሉ።

የጠቋሚ ቲ ሴሎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ሲመጣ ሌሎች ኃይሎች በኤች አይ ቪ የተዳከመውን ሰውነት ያላንዳች ችግር ሊወርሩት ይችላሉ። ክፉኛ የተጠቃው ሰውነት ለተለያዩ በሽታዎችና ኢንፌክሽኖች የተጋለጠ ይሆናል። ከዚህ በኋላ በቫይረሱ በተያዘው ሰው ላይ የኤድስ በሽታ ምልክቶች ሙሉ በሙሉ መታየት ይጀምራሉ። ኤች አይ ቪው የሰውነቱን የመከላከያ ኃይል በማሽመድመድ ግቡን መታ ማለት ነው።

ይህ ቀለል ባለ መንገድ የቀረበ ትንተና ነው። ተመራማሪዎች ስለ ሰውነታችን ተፈጥሯዊ የመከላከያ ኃይልም ሆነ ስለ ኤች አይ ቪ አሠራር ገና ብዙ የማያውቁት ነገር እንዳለ ማስታወስ ይኖርብናል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታዋቂ የሕክምና ተመራማሪዎች ላለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ማለት ይቻላል፣ አእምሯቸውንና ጉልበታቸውን በዚህ ረቂቅ ቫይረስ ላይ ለሚደረገው ጥናት ያዋሉ ሲሆን ለዚህ የምርምር ሥራም በቀላሉ የማይገመት ገንዘብ ፈስሷል። በውጤቱም ስለ ኤች አይ ቪ ብዙ ግንዛቤ ማግኘት ተችሏል። ቀዶ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሸርዊን ቢ ኑላንድ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተው ነበር:- “የሰውን ልጅ በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያዳክመው ቫይረስ በተደረጉት ምርምሮች . . . የተገኙት በርካታ መረጃዎችና ለቫይረሱ መከላከያ ለማግኘት በተደረጉት ጥረቶች የታየው እመርታ በእርግጥም አድናቆት የሚቸረው ነው።”

ያም ሆኖ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኤድስ አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት ላይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.26 የካቲት 8, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 13-15 ተመልከት።

[ሥዕል]

ኤች አይ ቪ፣ በሽታ ተከላካይ የሆኑትን የሊምፍ ሴሎች የሚያጠቃ ከመሆኑም በላይ በውስጣቸው ያለውን ፕሮግራም በመለወጥ ተጨማሪ ኤች አይ ቪዎችን እንዲያመርቱ ያደርጋቸዋል

[ምንጭ]

CDC, Atlanta, Ga.

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ደንቦች ይከተላሉ