ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
‘ባለጠጋ የመሆን ቅዠት’
ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማግኘት ያለው ዕድል በጣም አነስተኛ ሆኖ ሳለ ብዙ ድሃ ሰዎች ከባድ ተጽዕኖ በሚያሳድረው የማስታወቂያ ዘመቻ በመታለል በቁማር አማካኝነት ከድህነታቸው ሊያመልጡ እንደሚችሉ አድርገው እንደሚያስቡ ታይምስ ኦቭ ዛምቢያ ዘግቧል። ይህ ጽሑፍ እንዳለው “የሎተሪ ማስታወቂያዎች ቅጽበታዊ ብልጽግና፣ ቅንጦትና ከችግር ነጻ የሆነ ኑሮ የማግኘት ቅዠት ውስጥ ያስገባሉ። ዕጣውን የማሸነፍ ዕድል በጣም ጠባብ መሆኑ ግን አይነገርም።” ጋዜጣው ሲያጠቃልል “ምንም ዓይነት ምክንያት ቢቀርብ ቁማር በጠራራ ፀሐይ የሚፈጸም ሥርቆት በመሆኑ በማንኛውም ቀና ሥነ ምግባር ያለው ማኅበረሰብ ውስጥ በሕግ ሊከለከል የሚገባ ድርጊት ነው” ብሏል።
ጨለማን መፍራት
በለንደኑ ዘ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳለው “በዛሬው ጊዜ ልጆች በሰው ሠራሽ መብራት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ጨለማ በሆነ አካባቢ የሚቆዩበት ጊዜ በጣም አነስተኛ ስለሆነ ለጨለማ ያላቸው ፍርሃት ወላጆቻቸው ሕፃናት ሳሉ ይሰማቸው ከነበረው ፍርሃት የበለጠ ነው።” የሥነ ልቦና ባለሙያና ደራሲ በሆኑት አሪክ ሲግማን የምርምር ውጤት መሠረት ከአሥር ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት መብራት እንደበራ መተኛት ይፈልጋሉ። ልጆችና ወጣቶች ማታ በሚተኙበት ጊዜ እንኳን ሙሉ በሙሉ ጨለማ በሆነ አካባቢ አለመሆናቸው የምናብ ችሎታቸው እንደቀነሰባቸው ባለሙያው ይናገራሉ። “የልጆች የምናብ ችሎታ ሊዳብር የሚችልበት አጋጣሚ ማግኘት አለበት” ይላል ሪፖርቱ። “ጨለማ ውስጥ ሲሆኑ በምናባቸው የሚስሉት ሥዕል በዓይነቱ ልዩ ስለሚሆን በጨለማ ውስጥ መዝናናትና መጫወት በጣም ሊያስደስታቸው ይችላል።” ባሁኑ ጊዜ ግን “በቴሌቪዥን፣ በፊልምና በኮምፒውተር ጨዋታዎች ታይተው በልጆች አእምሮ ውስጥ የሚቀረጹ ምስሎች” ያስፈሯቸዋል። ዶክተር ሲግማን “ብዙ ቴሌቪዥን አለማየትና ብዙ ማንበብ ዘመን ያለፈበት ምክር ሊመስል ቢችልም አሁንም ይህንን ምክር መድገም አስፈላጊ ሆኗል” በማለት ተናግረዋል።
ጉድፍ ትላልቅ ሰዎችን ይገድላል
“በጣም ከተለመዱት የልጆች በሽታዎች አንዱ የሆነው ጉድፍ ትላልቅ ሰዎችን በመግደል ላይ ነው” ይላል የለንደኑ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ። ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጉድፍ ከሞቱ ሰዎች መካከል 48 በመቶ የሚሆኑት ትላልቅ ሰዎች ሲሆኑ በ2001 ይህ አኃዝ 81 በመቶ ደርሷል። የለንደን የሐይጂንና የሐሩር አገሮች ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኖኣ ኖርማን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል:- “ይህ ጥናት ጉድፍ የማይናቅ ቁጥር ያላቸውን ትላልቅ ሰዎች ለሞት የሚዳርግ በሽታ መሆኑን አረጋግጧል። . . . በአገራችን [በእንግሊዝና በዌልስ] በየዓመቱ 25 ሰዎች ይሞታሉ መባሉ አነስተኛ ግምት ይመስለኛል። . . . ትላልቅ ሰዎች ጉድፍ ከያዛቸው በልጅነት ከሚይዘው በሽታ የተለየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። አደገኛ ሊሆንባቸው ስለሚችል ቶሎ ብለው በሐኪም መታየት ይኖርባቸዋል።” በአብዛኛው እንዲህ ላለው አስጊ ሁኔታ የሚጋለጡት ከ15 እስከ 44 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ናቸው።
በስሎቫኪያ የአማኞች ቁጥር ጨምሯል?
በስሎቫኪያ በ2001 የተደረገው ቆጠራ ከአገሪቱ ዜጎች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት ሃይማኖት አለን እንደሚሉ አመልክቷል። የማህበራዊ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ያን ቡንቻክ ይህ የሚያመለክተው “ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት መኖሩን ነው” ብለዋል። በኮምኒስቶቹ ዘመን በሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ጫና ይደረግ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን “ተገቢ” እና “የተለመደ” ነገር ሆኗል። ይሁን እንጂ “ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በአምላክ ጨርሶ የማያምኑ ናቸው” ይላሉ ቡንቻክ። በአውሮፓ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ አስተያየት ሲሰጡም “አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖት እንዳላቸው ይናገራሉ። . . . ሃይማኖት አለን እያሉ ግን ሃይማኖታቸው አኗኗራቸውን እንዲነካባቸው አይፈልጉም” ብለዋል።
በ2050 የረሀብተኞች ቁጥር አራት ቢልዮን ይደርሳል
በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ስለሚሄድ የዓለም ሕዝብ ብዛት በ2050 ወደ 9.3 ቢልዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ድርጅት ያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል 4.2 ቢልዮን የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው እንደ ምግብና ውኃ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ባልተሟሉባቸው አገሮች ነው። ይህ አሐዝ ባሁኑ ጊዜ በቂ ምግብ ከማያገኘው ሕዝብ በእጥፍ ይበልጣል። የድርጅቱ ዋና ዲሬክተር የሆኑት ቶራያ ኦቤድ “የሕዝብ እድገትና ድህነት ሲቀናጅ በጣም አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል” ብለዋል። “እንደ መሬት፣ እንጨትና ውኃ የመሰሉት የተፈጥሮ ሀብቶች ለድሃ ሕዝቦች መተዳደሪያ የግድ አስፈላጊ ናቸው። በአካባቢ መመናመን በጣም የሚጠቁት ደግሞ እነዚሁ ድሃ ሕዝቦች ናቸው። . . . አንዳንዶቻችን የተፈጥሮ ሀብቶችን አለመጠን ስናባክን ሌሎች ደግሞ በሕይወት የሚያቆያቸውን እንኳን ማግኘት ተስኗቸዋል።”
ወንዶች ቀድመው የሚሞቱት ለምንድን ነው?
“የወንዶች ሕይወት ጎስቋላ ሕይወት ነው። ወንዶች ቀድመው ታመው ቀድመው ይሞታሉ።” ይህን ተስፋ አስቆራጭ አስተያየት የሰጡት በቪየና፣ ኦስትሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የዓለም የወንዶች ጤና ጉባኤ አዘጋጆች ናቸው። ዙትዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ወንዶች በአማካይ ከሴቶች በአምስት ዓመት ቀድመው የሚሞቱ መሆናቸው ተሰብሳቢዎቹን እጅግ እንዳስደነገጣቸው ዘግቧል። ወንዶች ከሴቶች ቀድመው የሚሞቱት ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር አብዛኛውን ጊዜ የሚያጨሱትና ከመጠን በላይ የሚጠጡት ወንዶች ናቸው። አለመጠን መብላትና በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግም ሌላው ለአደጋ የሚያጋልጣቸው ምክንያት ነው። በመካከለኛ ዕድሜ ከሚገኙ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በጣም ወፍራሞች ናቸው። በተጨማሪም ብዙዎቹ የሥራና የቤተሰብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲጣጣሩ ብዙ ውጥረት ይደርስባቸዋል።
ብዙ ወንዶች ሲታመሙም ሆነ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ወደ ሐኪም አይሄዱም። ከስብሰባው አዘጋጆች አንዱ የሆኑት ዜግፍሪት ሜሪን “በጤና ረገድ ወንዶች የተጎዱ ናቸው” በማለት አጠቃልለዋል።በስፔይን ፍቺና መለያየት በጣም በዝቷል
የማህበራዊ ኑሮ አማካሪና ላ ኑዌቫ ፋሚሊያ ኤስፓኞላ (አዲሱ የስፓኝ ቤተሰብ) የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ኢኔስ አልበርዲ “መላ ሕይወታችንን በአንድ የትዳር ጓደኛ ታስረን መኖር አይኖርብንም” ብለዋል። ኤል ፓኤስ በተባለው ጋዜጣ ላይ እንደተዘገበው እንዲህ የሚሰማቸው የስፓኝ ባለትዳሮች ቁጥር ጥቂት አይደለም። የፍትሕ ሚኒስቴር በቅርቡ ያደረገው አንድ ጥናት በስፔይን ከሁለት ጋብቻዎች አንዱ በፍቺ ወይም በመለያየት ያከትማል። ይህ ዓይነቱ የትዳር መፍረስ ሰዎች ስለ ጋብቻ ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ በሄደና የሴቶች የኢኮኖሚ ነጻነት እየጨመረ በሄደ መጠን እየበረከተ እንደሚመጣ ሊቃውንቱ ይተነብያሉ። የስፓኝ የቤተሰብ ጉዳይ ጠበቆች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሉዊስ ሳራሉኪ “ባለትዳሮች ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የላቸውም። ወጣቶች ደግሞ ምንም ነገር ችሎ ለማሳለፍ የተዘጋጁ አይደሉም” ብለዋል። “በዕድሜ በገፉት መካከልም ቢሆን፣ በተለይ ጡረታ ዕድሜ ላይ በደረሱት ላይ፣ የፍቺ ቁጥር ጨምሯል።” ባሕላዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ እምነቶች ይህን አዝማሚያ ሊገቱ አልቻሉም። ከስፔናውያን መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊክ ነን የሚሉ ቢሆኑም ባለፉት 20 ዓመታት መለያየትና ፍቺ 500 በመቶ ጨምሯል።
ጨርሶ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው አንበሶች
ኒው ሳይንቲስት መጽሔት “አንበሶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ፈጽመው ሊጠፉ ይችላሉ” ሲል ዘግቧል። መቶ የሚያክሉ የሚዋለዱ ጥንዶች ለማስገኘት ከ500 እስከ 1,000 የሚደርሱ አንበሶች መኖር አለባቸው። ከዚህ ካነሰ ግን የቅርብ ዝምድና ያላቸው ይዋለዱና ዘራቸው ይበላሻል። የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ማኅበር እንደሚለው በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ የአንበሶች ቁጥር ከዚህ በጣም አንሷል። በኔዘርላንድ የላይደን ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ሃንስ ባወር “በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ነው” ይላሉ። “ሕልውናቸው አስተማማኝ ነው የምንልበት አንድም አካባቢ የለም።” ለአራዊቱ ቁጥር መመናመን ምክንያት ከሆኑት ነገሮች ዋነኛው የመኖሪያ አካባቢያቸው በሰዎች መወረሩ ነው። አንበሶች በጣም ሠፊ የሆነ የማደኛ አካባቢ ያስፈልጋቸዋል። ለአንድ ወንድ አንበሳ ብቻ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለው አካባቢ ያስፈልጋል። “የአንበሶች መኖር ለሌሎች የዱር አራዊት ሕልውና መሠረት ነው” በማለት ባወር ተናግረዋል። “ይህ ማስጠንቀቂያም ነው። ዛሬ የአንበሶች ሕልውና አደጋ ላይ መውደቁ ሌሎች ዝርያዎችም ከ20 እና ከ30 ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ አደጋ ይደቀንባቸዋል ማለት ነው።”
የአልኮል ሱሰኛነት
ባሁኑ ጊዜ በብሪታንያ ከ13 ሰዎች አንዱ አለአልኮል መንቀሳቀስ አይችልም በማለት የለንደኑ ዚ ኢንዲፐንደንት ዘግቧል። በዚህ መሠረት የአልኮል ሱሰኞች ብዛት “በሕገ ወጥም ሆነ በሐኪም ከሚታዘዙ መድኃኒቶች ሱሰኞች ብዛት በእጥፍ ይበልጣል።” ከ1994 እስከ 1999 ባለው ጊዜ ውስጥ የልብ በሽታን፣ የጉበት በሽታንና በአልኮል መመረዝን ጨምሮ አልኮል አላግባብ በመውሰድ ጠንቅ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 43 በመቶ ያህል ጨምሯል። ሰክሮ በማሽከርከር ምክንያት የሚደርሰው አደጋ ብዛት በ1998 ከነበረው 10,100 በ2000 ወደ 11,780 ከፍ ብሏል። በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ሰባት ሰዎች መካከል አንዱ የሚሞተው በስካር ጠንቅ በሚፈጠር አደጋ ነው። ስድሳ በመቶ የሚሆኑ አሠሪዎች አለመጠን በሚጠጡ ሠራተኞች ይቸገራሉ። አምባጓሮ ከሚፈጥሩ ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት እንዲህ ላለው ወንጀል የሚነሳሱት በአልኮል ተገፋፍተው ነው። አልኮል ኮንሰርን የተባለው የብሪታንያ በጎ አድራጎት ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ኤሪክ አፕልቢ እንዲህ ብለዋል:- “አልኮል የመንግሥት ተቋማት ለሕዝብ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዳለ ሆኖ፣ በሰዎች ጤና፣ ግንኙነትና የገንዘብ ወጪ ላይ የሚያደርሰው ችግር ስፋትና መጠን ብቻውን . . . አስቸኳይ የሆነና የተቀናጀ እርምጃ እንድንወስድ ያስገድደናል።”