በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርኪኦሎጂ ማስረጃ ለክርስቲያኖች እምነት የግድ አስፈላጊ ነውን?

የአርኪኦሎጂ ማስረጃ ለክርስቲያኖች እምነት የግድ አስፈላጊ ነውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የአርኪኦሎጂ ማስረጃ ለክርስቲያኖች እምነት የግድ አስፈላጊ ነውን?

በ1873 እንግሊዛዊው ቄስ ሳሙኤል ማኒንግ ስለ ኢየሩሳሌም እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር:- “ስሜት በሚማርከው እይታ የተሳቡ ተሳላሚዎች ራቅ ካሉ ቦታዎች ጭምር ወደ ኢየሩሳሌም ይጎርፋሉ። በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈራረሱ ግንቦቿን፣ የቆሸሹ መንገዶችዋንና የፍርስራሹን ክምር በምድር ላይ ከሚገኝ ከየትኛውም ቦታ በላቀ ጥልቅ አክብሮታዊ ስሜት ይመለከቱታል።”

ቅድስቲቱ ምድር ቢያንስ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት ከቆስጠንጢኖስ ዘመን ጀምሮ ለብዙዎች መስህብ ሆና ቆይታለች። * ለ1,500 ዓመታት ያህል ተሳላሚዎች ወደ ቅድስቲቱ ምድር ሃይማኖታዊ ጉዞ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ምሁራን ቅድስቲቱን ምድር መጎብኘት የጀመሩት በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሲሆን በዚህ ወቅት ስለ ጥንታዊቷ ቅድስት ምድር ቅርጻ ቅርጾች፣ ስለ ሕዝቧ፣ ስለ ቦታዎቹና በዚያ ይነገሩ ስለነበሩት ቋንቋዎች ማጥናት በመጀመራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር የተያያዘ አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ተጀመረ።

አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበሩት አብዛኞቹ ነገሮች ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማዳበር እገዛ አድርገዋል። ከዚህም በላይ አርኪኦሎጂያዊው ዘገባ ባብዛኛው ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር የሚስማማ ሆኖ ተገኝቷል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ለክርስቲያኖች እምነት የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነውን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችል ዘንድ ብዙ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች የተካሄዱባትን የኢየሩሳሌም ከተማና የቤተ መቅደሷን ታሪክ እንመርምር።

“ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ . . . አይቀርም”

በአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 11 ቀን 33 እዘአ የፀደይ ወቅት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥቂት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ዳግም ላይመለስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለቅቆ ሄደ። ወደ ደብረ ዘይት ተራራ በመውጣት ላይ ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር ሆይ፣ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ” አለው።—ማርቆስ 13:1

እነዚህ ታማኝ አይሁዳውያን ለአምላክ እና ለቤተ መቅደሱ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። እጹብ ድንቅ በሆነ መንገድ በተገነቡትና ለ1,500 ዓመታት የቆየ ባህል ተምሳሌት በሆኑት ሕንፃዎች ኩራት ተሰምቷቸው ነበር። ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ ግን የሚያስደነግጥ ነበር። እንዲህ አለ:- “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም።”—ማርቆስ 13:2

ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መጥቶ እያለ አምላክ ቤተ መቅደሱ እንዲጠፋ እንዴት ይፈቅዳል? ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደነበረ ሙሉ በሙሉ የተገነዘቡት ከጊዜ በኋላ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ሲያገኙ ነበር። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር በተያያዘ ከሚደረገው አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?

አዲስ “ከተማ”

በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ እለት የአይሁድ ሕዝብ የአምላክን ሞገስ አጣ። (ማቴዎስ 21:43) ይህም ላቅ ያለ ነገር እንዲከናወን ማለትም ለሰው ልጆች በሙሉ በረከት የሚያመጣ ሰማያዊ መንግሥት እንዲቋቋም መንገድ ከፈተ። (ማቴዎስ 10:7) ከኢየሱስ ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ በ70 እዘአ ተደመሰሱ። ስለዚህ ክንውን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አርኪኦሎጂም ይደግፈዋል። ሆኖም የክርስቲያኖች እምነት የዚያ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ በመገኘቱ ላይ የተመሠረተ አይደለም። እምነታቸው የተመሠረተው በሌላኛዋ ኢየሩሳሌም ላይ ሲሆን ይችኛዋ ኢየሩሳሌም ለየት ያለች ከተማ ናት።

ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደስዋ መጥፋት የተናገረውን ትንቢት የሰማውና ትንቢቱ ሲፈጸም የተመለከተው ሐዋርያው ዮሐንስ በ96 እዘአ የሚከተለውን ራእይ ተመለከተ:- “ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ . . . ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።” ከዙፋኑ የወጣ አንድ ድምፅ እንዲህ አለ:- “ከ[ሰዎች] ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”—ራእይ 21:2-4

ይህቺ “ከተማ” ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ነገሥታት ሆነው የሚያገለግሉ ታማኝ ክርስቲያኖችን ያቀፈች ስትሆን ኢየሱስና እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች አንድ ላይ በመሆን ሰማያዊውን የአምላክ መንግሥት ይመሠርታሉ። ይህ መንግሥት በምድር ላይ ሲገዛ በሺህ ዓመት ውስጥ የሰውን ልጅ ሕብረተሰብ ወደ ፍጽምና ይመልሰዋል። (ማቴዎስ 6:10፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የዚህ ቡድን አባላት የሚሆኑ የመጀመሪያው ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በዚያ የአይሁድ ሥርዓት ውስጥ ያላቸው ማንኛውም ነገር ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ከመግዛት መብት ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ተገንዝበው ነበር።

ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ሲል በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥ ስለነበረው ከፍ ያለ ቦታ ሲጽፍ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጒዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፣ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጒዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ።”—ፊልጵስዩስ 3:7, 8

ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ሕግና ለቤተ መቅደሱ ዝግጅት ከፍ ያለ አክብሮት ስለነበረው ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ሲናገር እነዚህ መለኮታዊ ዝግጅቶች ዝቅ ተደርገው ሊታዩ ይገባል ማለቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። * (ሥራ 21:20-24) ከዚህ ይልቅ የክርስትና ዝግጅት ከአይሁድ ሥርዓት እንደሚበልጥ ማመልከቱ ነበር።

ጳውሎስና ሌሎቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በአይሁድ ሥርዓት ውስጥ ስለነበሩት ትኩረት የሚስቡ ብዙ ዝርዝር ነገሮች ያውቁ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ስላለፉት ዘመናት ለማወቅ ስለሚያስችል በአሁኑ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች መካከል አንዳንዶችን መረዳት ችለዋል። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱ ጢሞቴዎስ ትኩረቱን ምን ላይ ማሳረፍ እንዳለበት ሲመክረው የተናገረውን ልብ በል:- “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን [ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች] አስብ፣ ይህንም አዘውትር።”—1 ጢሞቴዎስ 4:15

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ የተመሠረተው አርኪኦሎጂያዊ ምርምር በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበረው ሁኔታ ያለንን ግንዛቤ ስላሳደገልን ሊደነቅ ይገባዋል። ያም ሆኖ ግን ክርስቲያኖች እምነታቸው የተመሠረተው ሰዎች ቆፍረው ባወጡት መረጃ ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—1 ተሰሎንቄ 2:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ቆስጠንጢኖስም ሆነ እናቱ ሄለና የኢየሩሳሌም ቅዱስ ቦታዎች ተለይተው እንዲታወቁ ማድረግ ይፈልጉ ነበር። እሷ በግሏ ኢየሩሳሌምን ጎብኝታለች። በቀጣዮቹ መቶ ዘመናትም ሌሎች ብዙ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ጎብኝተዋል።

^ አን.15 በኢየሩሳሌም የነበሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለተወሰነ ጊዜ ያህል በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተቱትን የተለያዩ ሥርዓቶች ያከብሩ ነበር። ይህንን ያደረጉት በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ ይመስላል። ሕጉን የሰጠው ይሖዋ ነበር። (ሮሜ 7:12, 14) ሕጉ በአይሁድ ሕዝብ መካከል ሥር የሰደደ ልማድ ሆኖ ነበር። (ሥራ 21:20) የአገሪቱ ሕግም የነበረ በመሆኑ ሕጉን መቃወም በክርስትና መልእክት ላይ አላስፈላጊ ተቃውሞ ማስነሳት ይሆን ነበር።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ:- ኢየሩሳሌም በ1920፤ 43 እዘአ፣ አይሁዳውያን ይጠቀሙበት የነበረ የሮማውያን ሳንቲም፤ ስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ፣ ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ የተገኘ እንደሆነ የሚገመት ከዝሆን ጥርስ የተሠራ የሮማን አበባ

[ምንጮች]

ገጽ 2 እና 16:- ሳንቲም:- Photograph © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority; የሮማን አበባ:- Courtesy of Israel Museum, Jerusalem