በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ

የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ

የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሁለት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች በአንድ የሕዝብ መናፈሻ ውስጥ ሆነው ሲያወሩ በቪዲዮ ይቀረጻሉ። ምን እየተነጋገሩ እንደነበር ማንም ሰው መስማት ባይችልም ፖሊሶች ይይዟቸውና የረዥም ዓመታት እስር ይበየንባቸዋል። ይህ የሆነው የከንፈር እንቅስቃሴ በማንበብ ችሎታዋ በብሪታንያ የተመሰከረላትና የብሪታንያ ፖሊስ “ምስጢራዊ መሣሪያ” በመባል የምትታወቅ አንዲት ሴት በቪዲዮ የተቀረጸውን ፊልም በማየት ሁለቱ ሰዎች ስላደረጉት ውይይት በመመስከሯ ነው።

የከንፈር እንቅስቃሴን የማንበብ ችሎታን በተመለከተ የበለጠ ለማወቅ ማይክንና ክርስቲናን አነጋገርኩ። ክርስቲና የመስማት ችሎታዋን ያጣችው በሦስት ዓመቷ ነው። በኋላ ላይ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በተዘጋጀ ትምህርት ቤት ገብታ የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ ተምራለች። ማይክ የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ የተማረው ክርስቲናን ካገባ በኋላ በራሱ ጥረት ነው።

የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ ምን ያህል ከባድ ነው? ማይክ “የከንፈርን፣ የምላስን እንዲሁም የታችኛውን መንጋጋ ቅርጽና እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል ያስፈልጋል” ይላል። ክርስቲናም እንዲህ ስትል አክላ ትናገራለች:- “የሚያነጋግርህን ሰው በትኩረት ልትመለከተው ይገባል፤ የከንፈር እንቅስቃሴን የማንበብ ችሎታህ እያደገ ሲሄድ በፊት ላይ የሚታዩ መግለጫዎችንና አካላዊ እንቅስቃሴዎችንም ማንበብ ትችላለህ።”

ተናጋሪው ሰው በፍጹም መጮኽ ወይም ከንፈሩን ከልክ በላይ ማንቀሳቀስ እንደሌለበት ተምሬያለሁ። እንደዚህ ዓይነት መግለጫዎች መልእክቱን ስለሚያዛቡት ግራ ሊያጋቡና የታሰበላቸውን ዓላማ ሊስቱ ይችላሉ። የከንፈር እንቅስቃሴን በማንበብ ረገድ ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው እንደየአካባቢው የሚለያዩትን የአነጋገር ዘይቤዎችንም ጭምር መለየት ይችላል። እርግጥ ነው ይህን ሁሉ ማድረግ ቀላል አይደለም! የከንፈር እንቅስቃሴን የማንበብ ችሎታን የሚያስተምር ሂሪንግ ኮንሰርን የተባለ አንድ ድርጅት በግልጽ እንዳስቀመጠው “የከንፈር እንቅስቃሴን የማንበብ ችሎታ ለማዳበር ሳይታክቱ ደግሞ ደጋግሞ መለማመድ ይጠይቃል።”

ክርስቲና አንዳንድ ጊዜ በአውቶቡስ ወይም በባቡር ስትሄድ ሳታስበው የሌሎችን ውይይት “በማዳመጧ” የምታፍርበት ጊዜ እንዳለ ሳትሸሽግ ተናግራለች። በዚህ ጊዜ ቶሎ ብላ ፊቷን ታዞራለች። ሆኖም ይህ ችሎታዋ ጥበቃም ሆኖላታል። ክርስቲና በቴሌቪዥን በሚተላለፉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች የሚጠቀሙትን ጸያፍ ንግግር ላለማየት ስትል ጨዋታ አትመለከትም።

የብሪታኒያ ፖሊስ “ምሥጢራዊ መሣሪያ” እንደተባለችው ሴት ዓይነት ችሎታ ማዳበር የሚችሉት ጥቂቶች ናቸው። ያም ሆኖ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በመጠኑም ቢሆን የከንፈር እንቅስቃሴን የማንበብ ችሎታ ቢያዳብሩ ይጠቀማሉ።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲና

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማይክ