በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁጥሮች የሰዎችን ትኩረት የሚስቡት ለምንድን ነው?

ቁጥሮች የሰዎችን ትኩረት የሚስቡት ለምንድን ነው?

ቁጥሮች የሰዎችን ትኩረት የሚስቡት ለምንድን ነው?

ቁጥሮች ባይኖሩ ኖሮ ዓለማችን ምን ሊመስል እንደሚችል አስብ። ገንዘብ የሚባል ነገር አይኖርም። ንግድ ዕቃ በዕቃ ከመለዋወጥ ያለፈ አይሆንም። ስፖርትስ? ቁጥሮች ባይኖሩ ኖሮ ነጥብ ለመያዝ አለመቻል ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ቡድን ምን ያህል ተጫዋቾች መኖር እንዳለባቸው እንኳን መወሰን አይቻልም ነበር።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ቁጥሮች ከሚሰጡት ተግባራዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ የምሥጢራዊነት ባሕርይ አላቸው ብለው ያምናሉ። ይህ ሊሆን የቻለው እውን የሆኑ ግዑዛን ነገሮች ስላልሆኑ ነው። ቁጥሮችን መንካት፣ መዳሰስ ወይም ማየት አይቻልም። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አንድ ብርቱካን የተለየ ቀለም፣ መጠን፣ ቅርጽ፣ መዓዛና ጣዕም አለው። በእርግጥ ብርቱካን እንጂ ሎሚ ወይም ኳስ አለመሆኑን ለማረጋገጥ እነዚህን ባሕርያት መፈተሽ ይቻላል። ቁጥር ግን እንዲህ ያለ ነገር አይደለም። አንድ የሰባት ነገሮች ስብስብ ከሌላ ሰባት ነገሮች ስብስብ ጋር ሲወዳደር ሁለቱም ሰባት ከመሆናቸው በስተቀር አንድም የሚመሳሰሉበት መንገድ ላይኖር ይችላል። ስለዚህ የቁጥሮችን ትርጉም ለመረዳት፣ ለምሳሌ በስድስትና በሰባት መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት እውን ያልሆነን ረቂቅ ነገር ማስተዋል ይጠይቃል። ለቁጥሮች ምትሐታዊ ትርጉም መስጠት የተጀመረው በዚህ ምክንያት ነው።

ከፓይታጎረስ ዘመን አንስቶ የኖረ የሐሰት ሳይንስ

በጥንት ዘመን የነበሩ ኅብረተሰቦች ለቁጥሮች ልዩ ትርጉም የመስጠት ልማድ ነበራቸው። በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ፓይታጎረስ የሚባለው ግሪካዊ ፈላስፋና የሂሣብ ሊቅ “ማንኛውም ነገር በቁጥር ሊገለጽ ይችላል” ሲል አስተምሯል። እርሱም ሆነ ተከታዮቹ መላው አጽናፈ ዓለም ሥርዓትና ሚዛናዊነት የተንጸባረቀበት ዓይነተኛ ምሳሌ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ታዲያ ሁሉም ነገሮች በአኃዝ የተቀመሩ ናቸው ማለት ነው?

ከፓይታጎረስ ዘመን ጀምሮ ለቁጥሮች የሚሰጡ ትርጉሞች ለመተንበይ፣ ሕልም ለመፍታት እንዲሁም ለማስታወሻነት ሲያገለግሉ ኖረዋል። ግሪኮች፣ ሙስሊሞችና የሕዝበ ክርስትና አባላት ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል። አይሁዳውያን ደብተራዎች ጀሜትሪያ የሚባል የስሌት ሥርዓት በመጠቀምና ለ22ቱ የዕብራይስጥ ሆሄያት የተለያየ ቁጥር በመስጠት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሰወረ ምሥጢር አግኝተናል ይሉ ነበር።

ዘመናዊው የዐውደ ነገሥት ገለጣም ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግለው ስምህና የተወለድክበት ቀን ነው። በስምህ ውስጥ ላሉት ለእያንዳንዱ ሆሄያት ቁጥር ይሰጣል። አንድ መጽሐፍ ገላጭ እነዚህን ቁጥሮች ከተወለድክበት ቀንና ወር ጋር በመደመር የኮከብህን ቁጥር ያገኛል። ለዚህ ቁጥር የሚሰጠው ልዩ ትርጉም ጠባይህን፣ ስውር ፍላጎቶችህን፣ የወደፊት ዕጣህን፣ በጠቅላላ አንተነትህን የሚገልጽ ይሆናል።

የዐውደ ነገሥት ገለጣ ተፈላጊነት ያገኘበት ዋናው ምክንያት የሚሰጠው ትንታኔ በጣም ትክክል መስሎ መታየቱ ሳይሆን አይቀርም። ኤድዋርድ አልበርትሰን ፕሮፌሲ ፎር ዘ ሚልየንስ በተባለው መጽሐፋቸው “ብዙ ሰዎች በዐውደ ነገሥት ማመን የጀመሩት የሚሰጠው ትንታኔ ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ከመረመሩ በኋላ ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ የዐውደ ነገሥት ገለጣ የሐሰት ሳይንስ የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። ለምን? የዐውደ ነገሥት ገለጣን በጥርጣሬ የምትመለከትበት ምክንያት ይኖራል?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስውር መልእክቶች ይገኛሉን?

ማይክል ድሮዝኒን የተባሉ ጋዜጠኛ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በኮምፒውተር የታገዘ ጥልቅ ምርምር ካደረጉ በኋላ ስውር መልእክቶችን እንዳገኙ ዘ ባይብል ኮድ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል። ድሮዝኒን እንዳሉት ይሳቅ ራቢን ከሚለው ስም ጋር በተያያዘ ያገኙት “ኮድ” ወይም የምሥጢር ጽሑፍ “የሚገድል ነፍሰ ገዳይ” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። ይህ የተገኘው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ራቢን ከመገደላቸው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

ዘ ባይብል ኮድ የተሰኘው መጽሐፍ ብዙ ጭቅጭቅ አስነስቷል። የሂሣብና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ዴቭ ቶማስ የትኛውም ጽሑፍ በኮምፒውተር ቢተነተን ምሥጢራዊ መልእክት እንዳለው የሚያስመስል ውጤት ማስገኘቱ እንደማይቀር በተግባር አሳይተዋል። ቶማስ የድሮዝኒን ጽሑፍ ራሱን በመተንተን “ኮድ”፣ “ጅል” እና “አታላይ” የሚሉትን ቃላት አግኝተዋል። ቶማስ “ጊዜህን ለመሠዋትና ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ እስከሆንክ ድረስ ከየትኛውም ጽሑፍ የተሰወረ መልእክት የምታገኝበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው” ብለዋል።

ብዙ ስሌቶችን ለመሥራት የአቅም ገደብ የሌለበት ኮምፒውተር ለአንድ ዓይነት ትንበያ ሊያገለግል የሚችል የሆሄያት ቅንብር ማስገኘቱ አይቀርም። ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው በአጋጣሚ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የተሰወሩ መልእክቶች ስለሚገኙበት አይደለም። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚያዝያ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29-31 ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓይታጎረስ ሁሉም ነገር አኃዛዊ ቀመር አለው ሲል አስተምሯል

[ምንጭ]

Courtesy National Library of Medicine