በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ያን ያህል ከባድ ነውን?

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ያን ያህል ከባድ ነውን?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ያን ያህል ከባድ ነውን?

“እኩዮቼ ተጽዕኖ የሚያደርጉብኝ አይመስለኝም።”—ፓሜላ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ

“አሁን አሁን የእኩዮች ተጽዕኖ ብዙም አያስቸግረኝም። በአብዛኛው ተጽዕኖ የሚያሳድርብኝ የራሴ ስሜት ነው።”—ሮቢ የተባለ ወጣት

እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” እንደሚል ታውቅ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሆኖም ‘እንዲያው ወላጆችና ትላልቅ ሰዎች አጋንነው ስለሚመለከቱት ይሆናል እንጂ እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ያን ያህል ከባድ ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

አልፎ አልፎ እንደዚህ ዓይነት ጥርጣሬ የሚሰማህ ከሆነ እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ሆኖም እኩዮችህ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች እንድትመረምር ልናበረታታህ እንወዳለን። እኩዮችህ አንተ ከምታስበው በላይ ተጽዕኖ እያሳደሩብህ ይሆን? ብዙ ወጣቶች እኩዮቻቸው የሚያሳድሩባቸው ተጽዕኖ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘቡ ተገርመዋል። ለምሳሌ ያህል አንጂ ከምታስበው በላይ ያለችበትን ማኅበረሰብ መስላ ለመኖር እየሞከረች ሊሆን እንደሚችል ሳትሸሽግ ተናግራለች። እንዲህ ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ማኅበረሰቡ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ተጽዕኖ እየተደረገብህ እንዳለ እንኳን ላትገነዘብ ትችላለህ። ተጽዕኖ እያደረገብህ ያለው የራስህ ውስጣዊ ስሜት እንደሆነ አድርገህ ማሰብ ትጀምራለህ።”

በተመሳሳይም መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሮቢ ከሁሉ ይበልጥ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት የራሱ ውስጣዊ ስሜት እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም በትላልቅ ከተሞች ውስጥ መኖር ከባድ መሆኑን ያምናል። ለምን? በፍቅረ ነዋይ ከተያዘው ዓለም የሚመጣው ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ ነው። “በእንዲህ ያሉ ከተሞች ውስጥ ሃብት በጣም ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል” ብሏል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በቸልታ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ይህ ከሆነ ታዲያ ብዙ ወጣቶች እኩዮቻቸው ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው እንደማይችሉ የሚያስቡት ለምንድን ነው?

በጣም አታላይ ነው

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አታላይ ከመሆኑ የተነሳ ልብ ላንለው እንችላለን። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በባህር ወለል ከፍታ ላይ በሚገኝ ቦታ የምንኖር ከሆነ ከእኛ በላይ ያለው አየር በእያንዳንዱ ስኩዌር ሴንቲ ሜትር አንድ ኪሎ የሚመዝን ግፊት ያሳድርብናል። * በየዕለቱ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትኖር ቢሆንም እንኳን አየሩ የሚያሳድርብህን ግፊት ላታስተውለው ትችላለህ። ለምን? ስለለመድኸው ነው።

እርግጥ፣ ከባቢ አየር የሚፈጥረው ግፊት ሁሉ ጉዳት ያስከትላል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ሰዎች ስውር በሆነ መንገድ ተጽዕኖ ሲያሳድሩብን ቀስ በቀስ እንድንለወጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች “በዙሪያችሁ ያለው ዓለም በራሱ መልክ እንዳይቀርጻችሁ ተጠንቀቁ” ብሏቸዋል። (ሮሜ 12:2ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ) ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

እኩዮች ተጽዕኖ የሚያሳድሩበት መንገድ

በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ያስደስትሃል? አብዛኞቻችን እንደዚህ ዓይነት ፍላጎት አለን። ሆኖም ይህ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ጠቃሚም ጎጂም ሊሆን ይችላል። የምንፈልገውን ተቀባይነት ለማግኘት የምንሞክረው እስከምን ድረስ ነው? በራሳችን በኩል ጎጂ ለሆነ ተጽዕኖ እንደማንሸነፍ እርግጠኞች መሆን ብንችል እንኳን በአካባቢያችን ስላሉት ወጣቶችስ ምን ማለት እንችላለን? ከእኩዮቻቸው የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ እየተቋቋሙት ነው ወይስ እንዲቀርጻቸው እየፈቀዱለት?

ለምሳሌ ያህል፣ ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ እንዳለፈባቸውና በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ብዙዎች አምላክን እሱ ባዘዘው መንገድ ማምለክ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። (ዮሐንስ 4:24) እንደዚህ የሚያስቡት ለምንድን ነው? ለዚህ አንዱ ምክንያት እኩዮቻቸው የሚያሳድሩባቸው ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል። በኤፌሶን 2:2 ላይ ጳውሎስ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኝ “መንፈስ” ወይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር አመለካከት እንዳለ ተናግሯል። ይህ መንፈስ ሰዎች አስተሳሰባቸውን ይሖዋን ከማያውቀው ዓለም ጋር እንዲያስማሙ ግፊት ያሳድርባቸዋል። ይህ በእኛ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?

እንደ ትምህርት ቤት፣ ጥናት፣ የቤተሰብ ኃላፊነቶች እና ሥራ ያሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን እኛ ከምንከተለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የተለየ አቋም ካላቸው ሰዎች ጋር ያገናኙናል። ለምሳሌ ያህል በትምህርት ቤት ታዋቂ ለመሆን ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ፣ ከሥነ ምግባር ውጪ በሆኑ የጾታ ግንኙነቶች የሚካፈሉ ወይም አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን እንዲሁም የአልኮል መጠጦችን አለአግባብ የሚወስዱ ብዙ ወጣቶች ይኖሩ ይሆናል። በእንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ከሚካፈሉ ወይም እንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት የተለመደ እንደሆነና እንዲያውም ከፍተኛ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባ ከሚሰማቸው ሰዎች ጋር የጠበቀ ጓደኝነት ብንመሠርት ውጤቱ ምን ይሆናል? ሳይታወቀን ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት ማዳበር እንጀምራለን። የዓለም “መንፈስ” ወይም “አየር” ተጽዕኖ ያሳድርብንና በራሱ መልክ ይቀርጸናል።

በዘመናዊው የማኅበራዊ ሳይንስ መስክ የተሠማሩ ባለሙያዎች ያካሄዱት ጥናት እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች የሚደግፍ ነው። አሽ የተባሉ ባለሙያ ያካሄዱትን ሙከራ እንመልከት። አንድ ግለሰብ አንድ ላይ ከተቀመጡ ሰዎች ጋር እንዲቀላቀል ይጋበዛል። ዶክተር አሽ ቀጥ ያለ መስመር የተሰመረበት አንድ ትልቅ ካርድ ያሳዩአቸዋል፤ ከዚያም በግልጽ የሚታይ ልዩነት ያላቸው ሦስት ቀጥታ መስመሮች የተሰመሩበት ሌላ ካርድ ያሳዩአቸዋል። ቀጥሎም በቡድኑ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ግለሰብ ከሦስቱ መስመሮች ውስጥ ከመጀመሪያው መስመር ጋር የሚመሳሰለው የትኛው እንደሆነ ይጠይቁታል። መልሱ ቀላል ነው። መጀመሪያ ላይ ሁሉም ተመሳሳይ መልስ ይሰጣሉ። በሦስተኛው ሙከራ ላይ ግን ለየት ያለ ሁኔታ ይፈጠራል።

በዚህም ጊዜ ቢሆን ተመሳሳይ ርዝመት ያላቸውን መስመሮች መለየት አያስቸግርም። ሆኖም ሙከራ እየተካሄደበት ያለው ግለሰብ ሳያውቅ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት አንድ ዓይነት መልስ እንዲሰጡ የተከፈላቸው በመሆኑ ሁሉም የተሳሳተ መልስ ሰጡ። በዚህ ጊዜ ምን ሆነ? ሙከራ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል ትክክለኛውን መልስ በመስጠት በአቋማቸው የጸኑት 25 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። የተቀሩት በሙሉ ቢያንስ አንድ ጊዜ በዓይናቸው ከሚያዩት በተቃራኒ አብረዋቸው ካሉት ሰዎች ጋር የሚስማማ የተሳሳተ መልስ ሰጥተዋል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰዎች አብረዋቸው ባሉት ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እውነት እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር እንኳን ሊክዱ ይችላሉ። ብዙ ወጣቶች ተጽዕኖው የሚያሳድረውን ውጤት በራሳቸው ላይ ተመልክተውታል። የ16 ዓመቱ ዳንኤል እንዲህ ሲል ሐቁን ተናግሯል:- “እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንድትለወጥ ሊያደርግህ ይችላል። በብዙ ሰዎች መካከል ስትሆን ደግሞ ተጽዕኖው ከባድ ይሆናል። እነሱ እያደረጉ ያሉት ነገር ትክክል እንደሆነ ማሰብ ትጀምራለህ።”

ቀደም ብላ የተጠቀሰችው አንጂ እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ በትምህርት ቤት ሊያጋጥም የሚችልበትን ሁኔታ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትማር የምትለብሰው ልብስ በጣም ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል። የታዋቂ ዲዛይነሮች ስም ያለበት ልብስ ሊኖርህ ይገባል። እውነቱን ለመናገር ለአንድ ሸሚዝ 50 የአሜሪካ ዶላር ማውጣት አትፈልግም፤ ማንስ ቢሆን እንዲህ ለማድረግ የሚፈልግበት ምን ምክንያት አለ?” አንጂ እንዳመለከተችው አንዳንድ ጊዜ ተጽዕኖ እየተደረገብህ እንዳለ ለማስተዋል ሊከብድ ይችላል። ይሁን እንጂ እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከዚህ ከበድ ባሉ ነገሮችም ሊነካን ይችል ይሆን?

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አደገኛ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት

በውቅያኖስ ውስጥ እየዋኘህ እንዳለህ አድርገህ አስብ። የማዕበሉን አቅጣጫ ተከትለህ በውኃው ግፊት እየታገዝህ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ስትዋኝ ውስጥ ውስጡን የሚሄድ ሌላ ኃይለኛ ውኃ ደግሞ ቀስ እያለ ወደ ጎን ይገፋሃል። በመጨረሻም የባሕሩን ዳርቻ በዓይኖችህ ስትቃኝ ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ ከእይታህ እንደራቁ ትገነዘባለህ። ውስጥ ውስጡን የሚሄደው ውኃ ሳታውቀው ወደ ጎን ብዙ አርቆሃል። በተመሳሳይም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ተጠምደን እንዳለን በአስተሳሰባችንና በስሜታችን ላይ የማያቋርጥ ተጽዕኖ ይደረግብናል። እነዚህ ተጽዕኖዎች አጥብቀን እንደያዝናቸው ከምናስባቸው መሥፈርቶች ሳናውቀው ሊያርቁን ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጴጥሮስ ደፋር ሰው ነበር። ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ላይ በጠላቶቹ መሃል በድፍረት ሰይፍ በመምዘዝ ጥቃት ሰንዝሯል። (ማርቆስ 14:43-47፤ ዮሐንስ 18:10) ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ እኩዮቹ ያሳደሩበት ተጽዕኖ አድሎአዊ ተግባር እንዲፈጽም አድርጎታል። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ክርስቶስ አሕዛብን ርኩስ እንደሆኑ አድርጎ እንዳይመለከት በራእይ የነገረው ቢሆንም አሕዛብ ክርስቲያኖችን አገለላቸው። (ሥራ 10:10-15, 28, 29) ጴጥሮስ ከሰይፍ ይልቅ ሌሎች እንዳይንቁት ፈርቶ ነበር። (ገላትያ 2:11, 12) በእርግጥም እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አደገኛ ሊሆን ይችላል።

እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ኃይል እንዳለው ማመን ያስፈልጋል

የጴጥሮስ ምሳሌ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። በአንድ አቅጣጫ ጠንካራ ነን ማለት በሁሉም አቅጣጫ ጠንካራ ነን ማለት አይደለም። እንደ ማንኛውም ሰው ጴጥሮስም ደካማ ጎኖች ነበሩት። ሁላችንም ደካማ ጎናችንን ልናስተውለው ይገባል። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን በሐቀኝነት ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ደካማ የሆንኩት በየትኛው አቅጣጫ ነው? እጅግ የተደላደለ ሕይወት ለማግኘት እጓጓለሁን? ከልክ ያለፈ ኩራት ይሰማኛልን? አድናቆት፣ ክብር ወይም ታዋቂነት ለማግኘት ስል ተገቢ ያልሆነ ነገር ለማድረግ ይዳዳኛልን?’

ምናልባት አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ከሚወስዱ ወይም ርካሽ የጾታ ሥነ ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር በመወዳጀት ሆን ብለን ራሳችንን ለአደጋ አናጋልጥ ይሆናል። ሆኖም ይበልጥ ስውር ስለሆኑት ድክመቶቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? በደካማ ጎናችን ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የምንመሠርት ከሆነ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትልብን ለሚችል የእኩዮች ተጽዕኖ ራሳችንን እያጋለጥን ነው።

ደስ የሚለው ግን እኩዮች የሚያሳድሩት ሁሉም ዓይነት ተጽዕኖ ጎጂ አይደለም። እኩዮች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልንቋቋምና ከዚያም አልፎ ጥቅም ልናገኝበት እንችላለንን? ጎጂ የሆኑ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የምንችለውስ እንዴት ነው? በሚቀጥለው እትም ላይ የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ . . .” አምድ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 የአየር ግፊት መኖሩን ለማወቅ ቀላል የሆነ ሙከራ ማካሄድ ይቻላል። አንድ ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙስ ወደ አንድ ተራራ ጫፍ ወስደህ በአየር ከሞላኸው በኋላ ጥርቅም አድርገህ ብትከድነው ከተራራው ስትወርድ ጠርሙሱ ምን ይሆናል? ጭርምትምቱ ይወጣል። ከውጪ ያለው አየር የሚፈጥረው ግፊት ጠርሙሱ ውስጥ ያለው አየር ከሚፈጥረው ግፊት እንደሚበልጥ ከዚህ ማየት ይቻላል።

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ዓለም ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ ይችላል