በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ

ከአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ

ከአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ

ቶሺያኪ ኒዋ እንደተናገረው

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦች ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ለመሰንዘር ሰልጥኖ የነበረ አንድ የቀድሞ የጃፓን የጦር አውሮፕላን አብራሪ የሞት ተልዕኮውን የሚወጣበትን ቀን እየተጠባበቀ ሳለ ምን እንደተሰማው ይተርካል።

ጃፓን፣ ሰኔ 1942 በተደረገው የሚድዌይ ጦርነት ላይ በደረሰባት ከባድ ሽንፈት የፓስፊክ ይዞታዋን ለማስፋፋት ታደርግ የነበረው ግስጋሴ ተገታ። ከዚያ በኋላ ጃፓን ከዩናይትድ ስቴትስና ከጦር አጋሮቿ ጋር በምታደርጋቸው ጦርነቶች ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠማት ሲሆን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋቸው የነበሩትን አንዳንድ ቦታዎች አሳልፋ ለመስጠት ተገደደች።

መስከረም 1943 የጃፓን መንግሥት ከወታደራዊ አገልግሎት ነጻ የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለጦርነት እንዲመለመሉ መግለጫ አወጣ። በታኅሣሥ ወር በ20 ዓመት ዕድሜዬ ዩኒቨርሲቲውን ለቅቄ ከባሕር ኃይሉ ጋር ተቀላቀልኩ። ከአንድ ወር በኋላ በባሕር ኃይል የበረራ ክፍል በአብራሪነት መሰልጠን ጀመርኩ። ታኅሣሥ 1944 ዜሮ የተባለ ተዋጊ አውሮፕላን ለማብረር የሚያስችለኝን ስልጠና አገኘሁ።

የካሚካዚ ልዩ አጥቂ ዕዝ

ጃፓን ወደ ሽንፈት እያመራች ነበር። በየካቲት 1945 ቢ-29 የሚባሉት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በጃፓን ላይ የሚሰነዝሩትን የአየር ጥቃት አፋፋሙት። በዚሁ ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል የተውጣጣ ልዩ ግብረ ኃይል ወደ ጃፓን በመጠጋት ከአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች በሚነሱ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መደብደብ ጀመረ።

ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ የጃፓን የጦር መኮንኖች የአጥፍቶ መጥፋት የውጊያ ስልት በመጠቀም የመጨረሻ ፍልሚያ ለማድረግ ወስነው ነበር። ምንም እንኳ ጃፓን ጦርነቱን በድል መወጣት እንደማትችል በወቅቱ ግልጽ የነበረ ቢሆንም ውሳኔው ጦርነቱን ከማራዘሙም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።

የካሚካዚ ልዩ አጥቂ ዕዝ የተመሠረተው በዚህ ወቅት ነበር። ዕዙ ይህን ስያሜ ያገኘው ካሚካዚ ከተባለው መለኮታዊ ነፋስ ሲሆን ይህ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በ13ኛው መቶ ዘመን ጃፓንን ለመውረር የመጡትን የሞንጎሊያን መርከቦች እንዳወደመ በአፈ ታሪክ ይነገርለታል። የመጀመሪያው የካሚካዚ ጥቃት የተደረገው እያንዳንዳቸው 250 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብ የተጠመደባቸው አምስት ዜሮ ተዋጊ አውሮፕላኖች ዒላማቸው ካደረጉት መርከብ ጋር እንዲላተሙ በማድረግ ነበር።

እኔ የነበርኩበት የያታቤ የባሕር ኃይል የበረራ ዕዝ አንድ ልዩ የአጥፍቶ ጠፊ ቡድን እንዲያደራጅ ትእዛዝ ደረሰው። ለሁላችንም የዚህ ቡድን አባል ሆነን ለመዝመት የምንፈልግ መሆን አለመሆናችንን የምንገልጽበት ቅጽ እንድንሞላ ተሰጠን።

ሕይወቴን ለአገሬ መሠዋት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ሆኖም ለዚህ ተልዕኮ ሕይወቴን በፈቃደኝነት ባቀርብም ከዒላማዬ ጋር ከመላተሜ በፊት ተመትቼ ልወድቅና በከንቱ ልሞት እችላለሁ። ቤተሰቤ የጣለብኝን ኃላፊነት ሳልወጣ ብሞት እናቴ ቅር ትሰኝብኝ ይሆን? ሕይወቴን ልጠቀምበት የምችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ በዚህ ተልዕኮ በመካፈል እንደሆነ ራሴን ለማሳመን በጣም ተቸግሬ ነበር። ሆኖም ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ።

መጋቢት 1945 የያታቤ ልዩ አጥቂ ጓድ የመጀመሪያው ቡድን ተመሠረተ። ከበረራ ጓዶቼ ውስጥ 29 የሚያህሉት በዚህ ቡድን ውስጥ ቢመረጡም እኔ ግን ሳልመረጥ ቀረሁ። ልዩ ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በሚያዝያ ወር የአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኳቸውን ለመፈጸም በካጎሺማ አውራጃ ከሚገኘው የካኖያ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር እንዲነሱ ፕሮግራም ተያዘላቸው። ወደ ካኖያ የጦር ሰፈር ከመዛወራቸው በፊት ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ተልዕኮ ሲያስቡ ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ወደ ጓደኞቼ ሄድኩ።

ከመሃከላቸው አንዱ ረጋ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ:- “እኛ ለመሞት ቆርጠናል። አንተ ግን ለመሞት አትጣደፍ። ከመካከላችን አንዱ ቢተርፍ ሰላም ምን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት እንደሚገባ ለሰዎች መናገርና ሰላምን ለማምጣት መጣር አለበት።”

ሚያዝያ 14, 1945 ጓደኞቼ ተልዕኳቸውን ለመወጣት በረሩ። ከሰዓታት በኋላ የጦርነቱን ውጤት ለመስማት ሁላችንም ጆሯችንን ራዲዮ ላይ ተክለን ስናዳምጥ ማስታወቂያ ተናጋሪው “በካሚካዚ ልዩ አጥቂ ኃይል ውስጥ የመጀመሪያው የሆነው የሾዋ ቡድን ከኪካይ ሺማ [ደሴት] በስተ ምስራቅ በሚገኝ የጠላት ግብረ ኃይል ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ያደረሰ ሲሆን የቡድኑ አባላት በሙሉ በውጊያው ላይ ተሠውተዋል” ብሎ ሲናገር ሰማን።

ኦካ—ሰብዓዊ ቦምብ

ከሁለት ወራት በኋላ የጂንራይ ልዩ አጥቂ ቡድን አባል ሆኜ ወደ ኮኖይኬ የባሕር ኃይል የበረራ ዕዝ ተዛወርኩ። ጂንራይ “መለኮታዊ ነጎድጓድ” ማለት ነው። ቡድኑ ተዋጊና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን የሚያጅቡ (አታከር የሚባሉ) አውሮፕላኖችን ያቀፈ ነበር።

በእያንዳንዱ ባለ ሁለት ሞተር አታከር አውሮፕላን ላይ አንድ ኦካ ይጠመዳል። “እምቡጥ አበባ” የሚል ትርጓሜ ያለው ኦካ የሚለው መጠሪያ ሕይወታቸውን ለመሠዋት ፈቃደኛ የሆኑትን ወጣት አብራሪዎች የሚያመለክት ነበር። ከአንደኛው የክንፉ ጫፍ እስከ ወዲያኛው ጫፍ አምስት ሜትር የሚያህል ርዝመትና 440 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት ያለው ኦካ አውሮፕላን አንድ ሰው ብቻ የሚይዝ ሲሆን አፍንጫው ላይ አንድ ቶን ገደማ የሚመዝን ፈንጂ ይጠመድበታል።

አታከር አውሮፕላኑ ወደ ዒላማው ሲቃረብ አንድ አብራሪ ኦካው ላይ ይሳፈርና ከዋናው አውሮፕላን ተገንጥሎ ለብቻው መብረር ይጀምራል። እያንዳንዳቸው ለአሥር ሴኮንድ ያህል ኃይል በሚሰጡት ሦስት ሮኬቶች በመታገዝ የተወሰነ ርቀት ከተምዘገዘገ በኋላ ዒላማው ላይ ይሰካል። ይህ በእውነት ሰብዓዊ ቦምብ ሊባል ይችላል። አንዴ ከተወነጨፉ በኋላ መመለስ የሚባል ነገር የለም።

በልምምድ ወቅት አንድ የኦካ አብራሪ በአንድ ዜሮ ተዋጊ አውሮፕላን ላይ ይሳፈርና ከ6,000 ሜትር ከፍታ ላይ ወደ ዒላማው ይምዘገዘጋል። በእነዚህ ልምምዶች ብዙ አብራሪዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ አይቻለሁ።

በዚህ የአየር ኃይል ቡድን ውስጥ ከመመደቤ በፊት በ19 ተዋጊ አውሮፕላኖች የሚታጀቡና ኦካዎች የተጠመዱባቸውን 18 አታከር አውሮፕላኖችን ያቀፈው የመጀመሪያው ቡድን ዘምቶ ነበር። አታከር አውሮፕላኖቹ ግዙፍና ፍጥነት የሌላቸው ነበሩ። ከእነርሱ መሃል አንዱም ወደ ዒላማው አልደረሰም። እነርሱም ሆኑ አጃቢዎቻቸው በዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ አውሮፕላኖች ተመትተው ወድቀዋል።

የጂንራይ ቡድን ተዋጊ አውሮፕላኖቹ በማለቃቸው ቀሪ ተልዕኮዎቹን ለመወጣት ያለ አጃቢ መብረር ነበረበት። ከዚያ በኋላ ለውጊያ የሄዱት በሙሉ አልተመለሱም። ሁሉም በኦኪናዋ የውጊያ ሜዳ ላይ አልቀዋል።

የጦርነቱ የመጨረሻ ቀናት

ነሐሴ 1945 ወደ ኦትሱ የባሕር ኃይል የበረራ ዕዝ ተዛወርኩ። የጦር ሰፈሩ የሚገኘው በኮዮቶ ከተማ አቅራቢያ ባለው የሄዛን ተራራ ግርጌ ነበር። በጃፓን ዋነኛ ደሴት ላይ የሚያርፉ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎችን ለመመከት በጠላት መርከቦች ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት የሚያደርሱ ኦካዎች ከተራራው ላይ ለማስወንጨፍ ታቅዶ ነበር። ኦካዎቹ የሚወነጨፉበት ሃዲዶች በተራራው አናት ላይ ተዘርግተው ነበር።

እንድንበር ትእዛዝ እስኪሰጠን ድረስ መጠባበቅ ጀመርን። ሆኖም ትእዛዙ ሳይመጣ ቀረ። ነሐሴ 6 እና 9 ሂሮሺማና ናጋሳኪ በአቶሚክ ቦምብ ከወደሙ በኋላ ነሐሴ 15 ጃፓን ለዩናይትድ ስቴትስና ለአጋሮቿ ሙሉ በሙሉ ተንበረከከች። ጦርነቱ በዚህ ተጠናቀቀ። እኔም ለጥቂት ተረፍኩ።

በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ወደ ትውልድ መንደሬ ወደ ዮኮሃማ ተመለስኩ፤ ይሁን እንጂ ቤቴ ቢ-29 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በፈጸሙት የቦምብ ድብደባ ሙሉ በሙሉ አመድ ሆኖ ነበር። ቤተሰቦቼ ተስፋ ቆርጠውና በሐዘን ተቆራምደው ነበር። እህቴና ልጅዋ በእሳቱ ተቃጥለው ሞተዋል። ይሁንና ታናሹ ወንድሜ ከጦርነቱ በሕይወት ተርፎ መመለሱ በመጠኑም ቢሆን አጽናናን።

አካባቢው በፍርስራሽ የተሞላና ከባድ የምግብ እጥረት የነበረ ቢሆንም ትምህርቴን ለማጠናቀቅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለስኩ። ለአንድ ዓመት ያህል ከተማርኩ በኋላ ተመርቄ ሥራ ያዝኩ። በ1953 ከሚቺኮ ጋር ተጋባንና ከጊዜ በኋላ የሁለት ወንዶች ልጆች አባት ሆንኩ።

ሰላምን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

በ1974 ሚቺኮ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ በስብሰባዎቻቸው ላይ ትገኝና በስብከቱ ሥራቸው ትሳተፍ ጀመር። ውጪ ውጪ ማለቷን እንዳልወደድኩት ስነግራት ክርስቲያናዊ አገልግሎት እውነተኛ ሰላምና ደስታ እንደሚሰጥ ነገረችኝ። እንደዚያ ከሆነስ መተባበር እንጂ መቃወም አይገባኝም ብዬ አሰብኩ።

በዚሁ ወቅት ማታ ማታ መሥሪያ ቤቴን የሚጠብቁልኝ ጥቂት ወጣት የይሖዋ ምስክሮች ቀጠርኩ። ወጣቶቹ ምሥክሮች ሲመጡ ስለ ድርጅታቸውና ስለ አገልግሎት ጠየቅኋቸው። የእነርሱ እኩዮች ከሆኑት ከሌሎች ወጣቶች በተለየ ሁኔታ ዋነኛ ትኩረታቸው ያረፈው በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንደሆነና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዳላቸው ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ። እነዚህን ባሕርያት የተማሩት ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበር። በዓለም ዙሪያ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት የዘር መድልዎ እንደማያደርጉና አምላክንና ጎረቤታቸውን እንዲወድዱ የሚያዝዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ አጥብቀው እንደሚከተሉ ነገሩኝ። (ማቴዎስ 22:36-40) በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ የአምልኮ አጋሮቻቸውን እንደ ወንድምና እህት አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።—ዮሐንስ 13:35፤ 1 ጴጥሮስ 2:17

‘እነዚህ በቅዠት ዓለም የሚኖሩ ናቸው’ ስል አሰብኩ። አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች እርስ በእርስ እየተዋጉ እያለ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌላው የተለዩ ናቸው ብሎ ለማመን ከበደኝ።

ይህንኑ ጥርጣሬዬን ገለጽኩላቸው። ወጣቶቹ በጀርመን የነበሩ ምሥክሮች በሂትለር አገዛዝ ሥር የገለልተኝነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት እንደታሰሩ ከዚያም አልፎ እንደተገደሉ ከይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ አሳዩኝ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን አመንኩ።

ይህ በእንዲህ እያለ ታህሣሥ 1975 ሚስቴ በውኃ በመጠመቅ ራስዋን ለአምላክ መወሰንዋን አሳየች። በእርሷ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቼ ሳለሁ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ግብዣ ቀረበልኝ። ይሁን እንጂ ለልጆቼ የትምህርት ቤት ወጪዎችን መሸፈንንና የቤታችንን የቁጠባ ብድር መክፈልን የመሰሉ ያሉብኝን ገንዘብ ነክ ኃላፊነቶች አሰብኩና ግብዣውን ሳልቀበል ቀረሁ። በጉባኤው ውስጥ የነበሩት ባለ ትዳር ወንዶች ለመንፈሳዊ ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት በሰብዓዊ ሥራዎቻቸው ላይ የፕሮግራም ማስተካከያ ያደርጉ ነበር። እኔም እንደዚህ እንዳደርግ ይጠበቅብኛል ብዬ አሰብኩ። ክርስቲያናዊ ሕይወትንና ሰብዓዊ ሥራን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዴት ማስኬድ እንደሚቻል ከነገሩኝ በኋላ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰንኩ።

የሰላም አምላክን ለማምለክ ያደረግሁት ውሳኔ

ለሁለት ዓመት ያህል ካጠናሁ በኋላ አስጠኚዬ ራሴን ለአምላክ ስለ መወሰን አስቤ አውቅ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔ ግን ይህን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አልነበርኩም፤ ይህ ደግሞ ይረብሸኝ ነበር።

አንድ ቀን በምሠራበት ቦታ በደረጃ ላይ በፍጥነት እየወረድኩ ሳለሁ ተደናቅፌ ወደቅሁ። ስወድቅ ጭንቅላቴን ከኋላ አንድ ነገር መታኝና ራሴን ሳትኩ። ራሴን ሳውቅ ከባድ ራስ ምታት ይሰማኝ ስለነበር በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ። ጭንቅላቴ ከኋላ በጣም ቢያብጥም የአጥንት መሰንጠቅም ሆነ በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ አላጋጠመኝም ነበር።

በዚያ ጊዜ ይሖዋ የሰጠኝ ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወቴን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ መጠቀም እንዳለብኝ አሰብኩና ራሴን ለእርሱ ወሰንኩ። ሐምሌ 1977 በ53 ዓመት ዕድሜዬ ተጠመቅኩ። ታላቁ ልጄ ያሱዩኪም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረና ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠመቀ።

ከተጠመቅኩ ከ10 ዓመት ገደማ በኋላ ጡረታ ወጣሁ። በእነዚያ ዓመታት ክርስቲያናዊ ሕይወቴን ከሰብዓዊ ሥራዬ ጋር በሚዛናዊነት ስመራ ኖሬአለሁ። በአሁኑ ወቅት በዮኮሃማ በሽማግሌነት እያገለገልኩ ሲሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎትም ሰፋ ያለ ጊዜ አሳልፋለሁ። ታላቁ ልጄም በአጎራባች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ ያገለግላል።

ከነበርኩበት የልዩ አጥቂ ቡድንና ከአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮው በሕይወት ተርፌ ለዚህ በመብቃቴ በጣም አመስጋኝ ከመሆኔም በላይ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበኩ ሥራ መካፈሌንም እንደ ትልቅ ክብር እቆጥረዋለሁ። (ማቴዎስ 24:14) ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ ከአምላክ ሕዝቦች እንደ አንዱ ሆኖ መመላለስ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተገንዝቤአለሁ። (መዝሙር 144:15) በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ ስለማያነሳና፣ ሰልፍም ከዚያ ወዲያ ስለማይማሩ’ ጦርነት የሚባል ነገር ፈጽሞ አይኖርም።—ኢሳይያስ 2:4

የአምላክ ፈቃድ ከሆነ በጦርነቱ ከሞቱት መሃል በትንሣኤ የሚነሱትን ለማግኘት እፈልጋለሁ። በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የጽድቅ አገዛዝ ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚያገኙት ሰላማዊ ሕይወት ለእነርሱ መናገር ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል!—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ሥራ 24:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:19

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባሕር ኃይሉ የበረራ ጓድ ውስጥ እያለሁ

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ኦካ”—ሰብዓዊ ቦምብ

[ምንጭ]

© CORBIS

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ከመላካቸው በፊት ከበረራ ጓዶቼ ጋር፤ እኔ በግራ በኩል ሁለተኛው ስሆን በሕይወት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነበርኩ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከሚቺኮና ከትልቁ ልጄ ከያሱዩኪ ጋር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. National Archives photo