በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከ30 ዓመት በኋላ የተከሰተ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ

ከ30 ዓመት በኋላ የተከሰተ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ

ከ30 ዓመት በኋላ የተከሰተ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ

በ1967 ሁለት ወጣቶች በአጋጣሚ ይገናኛሉ። ወጣቶቹ በዩናይትድ ስቴትስ ሚቺጋን የሚገኘው የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው እንዲኖሩ ተመድበው ነበር። ከሊማ ኦሃዩ የመጣው ዴኒስ ሺትስ በዚያን ጊዜ የ18 ዓመት ወጣት ሲሆን የአንደኛ ዓመት የደን አያያዝና ጥበቃ ሳይንስ ተማሪ ነበር። ከቡፋሎ ኒው ዮርክ የመጣው የ22 ዓመቱ ማርክ ሩጅ ደግሞ የሦስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ ነበር።

ይሁን እንጂ በወቅቱ ጓደኝነታቸው ብዙ አልዘለቀም። ሁለቱም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው የየራሳቸውን ግብ ለማሳካት ተለያዩ። ይህ ከሆነ በኋላ ሦስት አሥርተ ዓመታት አለፉ። ከዚያም አንድ ቀን በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ ሁለቱ ሰዎች እንደገና በዓይን ለመተያየት በቁ። እንደዚህ ባለ አስገራሚ መንገድ እንደገና መገናኘታቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ቢሆንም እንዲገናኙ አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላም ነገር ነበር። ይህ ምን ይሆን? መልሱን ለማግኘት ሁለቱ ሰዎች ያሳለፉትን ሕይወት እስቲ መለስ ብለን እንመልከት።

ዴኒስ ወደ ጦር ሜዳ ዘመተ

ዴኒስ በኮሌጅ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ ወደ ትውልድ ሥፍራው ይመለሳል። ከዚያም በታኅሣሥ ወር 1967 በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግል ይመለመልና ሰኔ 1968 ወደ ቪየትናም ይላካል። በዚያም ጦርነት የሚያስከትለውን ሰቆቃ ተመልክቷል። በ1969 ግዳጁን ከተወጣ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይመለስና በኦሃዮ በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ ሥራ ይቀጠራል። ያም ሆኖ ደስተኛ አልነበረም።

ዴኒስ “የልጅነት ሕልሜ አላስካ ሄጄ በግብርና መተዳደር ነበር” ይላል። ስለዚህ በ1971 ከአንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር በመሆን ሕልሙን ለማሳካት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ሆኖም ያሰበው ስላልተሳካለት ዝቅተኛ የሚባሉ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ተገደደ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሰደድ እሳት እንዳይነሳ በመጠበቅ በድንኳን ኖሯል። በዚህ ጊዜ ጺሙንና ፀጉሩን አሳድጎና ማሪዋና ማጨስ ጀምሮ ነበር።

በ1972 ዴኒስ በሉዊሲያና፣ ኒው ኦርሊንስ በሚከበረው የማርዲ ግራስ በዓል ላይ ለመገኘት ሲል አንኮሬጅን ለቅቆ ሄደ። ከዚያም በአርካንሳስ ጫካ ውስጥ አነስ ያለች ጎጆ ሠራና ቤቶችን በመገንባት ሙያ ተሠማርቶ መሥራት ጀመረ። በ1973 ሰኔ ላይ ዴኒስ በሕይወቱ ውስጥ አንድ ትርጉም ያለው ነገር ለማከናወን በማሰብ ባገኘው መኪና እየተሳፈረ በአገሪቷ ውስጥ ይዘዋወር ጀመር።

ማርክ በፀረ ጦርነት እንቅስቃሴ ውስጥ

ዴኒስ ዩኒቨርሲቲውን ለቅቆ ከሄደ በኋላ ማርክ ለጥቂት ሴሚስተሮች ቆይቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን ጦርነትን የሚደግፈው ማኅበረሰብ አባል መሆን እንደሌለበት በማሰብ ወደ ቡፋሎ ተመልሶ በአንድ የብረታ ብረት ፋብሪካ ውስጥ የሠራተኞች ተቆጣጣሪ ሆኖ መሥራት ጀመረ። እዚያም ቢሆን ለጦርነት በሚደረገው ድጋፍ ቅሬታ የተሰማው ማርክ ሞተር ብስክሌት ይገዛና ሥራውን ትቶ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርንያ ይሄዳል። ዴኒስና ማርክ በወቅቱ ባይገነዘቡትም ለተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ሳን ፍራሲስኮ ውስጥ ኖረዋል።

እንደ ዴኒስ ሁሉ ማርክም ጺሙንና ፀጉሩን አጎፍሮና ማሪዋና ማጨስ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ማርክ በፀረ ጦርነት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ተውጦ የነበረ ሲሆን በተቃውሞ ሰልፎችም ይካፈል ነበር። የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ በግዳጅ ለጦርነት ሊመለምለው ይፈልገው ስለነበር ለተወሰኑ ዓመታት ያህል እንዳይያዝ የሐሰት ስሞችን ይጠቀም ነበር። ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ የሂፒዎች ዓይነት ሕይወት ይመራ ጀመር። እዚያም ሳለ በ1970 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ ይመጣሉ።

ማርክ እንዲህ ይላል:- “ፍላጎት እንዳለኝ ተሰምቷቸው ነው መሰለኝ ሌላ ቀን ተመልሰው መጡ። ሆኖም እቤት ስላልነበርኩ አንድ አረንጓዴ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሦስት መጻሕፍት ትተውልኝ ሄዱ።” ሆኖም ማርክ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና በመዝናኛ ተጠምዶ ስለነበር መጽሐፎቹን አላነበባቸውም። ከዚህም በላይ የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ በጥብቅ እየተከታተለው ነበር። ስለዚህ በሌላ የሐሰት ስም ተጠቅሞ ወደ ዋሽንግተን ዲ ሲ ሄደ። እዚያም በዩኒቨርሲቲ እያለ ካወቃት ካቲ ያኒስኪቪስ የተባለች የሴት ጓደኛው ጋር ይገናኛል።

በመጨረሻም በ1971 የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ ማርክን ይይዘዋል። ሁለት የፌደራል ምርመራ ቢሮ ሠራተኞች ከዋሽንግተን ዲ ሲ እስከ ኒው ዮርክ ድረስ ከሸኙትና ወደ ቶሮንቶ፣ ካናዳ መሄዱን ካረጋገጡ በኋላ ተመለሱ። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ለማኅበረሰቡ እንደሚያሰጋ ሰው አድርገው አልተመለከቱትም። ከአገር መውጣቱ ብቻ በቂ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። በቀጣዩ ዓመት ከካቲ ጋር ተጋቡና በብሪቲሽ ኮሎምቢያ፣ ካናዳ በምትገኘው በጋብሪኦላ ደሴት መኖር ጀመሩ። ይህን ያደረጉት ከማኅበረሰቡ ርቀው ለመኖር በማሰብ ቢሆንም ሕይወት የተሻለ ዓላማ እንዳለው ይሰማቸው ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ዴኒስ በሕይወቱ ትርጉም ያለው ነገር ለመሥራት ጉዞ ጀምሮ ነበር። በዚህ መሃል ወደ ሞንታና ይሄድና ከሺኑክ ከተማ ወጣ ብሎ ለአንድ ገበሬ ተቀጥሮ ሰብል የመሰብሰብ ሥራ ያገኛል። የሰውየው ሚስትና ሴት ልጁ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ለዴኒስ ንቁ! መጽሔት ሰጡት። ብዙም ሳይቆይ ምሥክሮቹ እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ ተገነዘበ።

ዴኒስ እርሻውን ይተውና መጽሐፍ ቅዱሱን ይዞ ወደ ካለሰፔል፣ ሞንታና ይሄዳል። በዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑት ጠየቀ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ፀጉሩን ተቆረጠ፣ ጺሙንም ተላጨ። ጥር 1974 ለመጀመሪያ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ተካፈለ፤ ከዚያም መጋቢት 3, 1974 በፖልሰን ከተማ፣ ሞንታና በውኃ ገንዳ ውስጥ ተጠመቀ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋብሪኦላ ደሴት የሚኖሩት ማርክና ካቲ ጊዜ ስላላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ይወስናሉ። ኪንግ ጀምስ ቨርሽን የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይጀምሩና እንግሊዝኛው ለመረዳት ከባድ ይሆንባቸዋል። በዚህ ጊዜ ማርክ ምሥክሮቹ ከዓመታት በፊት የሰጡትን መጽሐፍ ቅዱስና መጻሕፍት ያስታውሳል። ማርክና ካቲ መጽሐፍ ቅዱስንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነውን? የተባሉትን መጻሕፍት ሲያነቡ በጣም ተነኩ።

ማርክ እንዲህ ይላል:- “በምንም ዓይነት በጦርነት የማይካፈሉ ክርስቲያኖች እንዳሉ የሚገልጸው በእውነት መጽሐፍ ላይ ያለው ሐሳብ ልቤን ነካኝ። እነዚህ ሰዎች እውነተኛውን ክርስትና እንደያዙ ተሰማኝ።” ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ማርክና ካቲ ሊያዙ እንደሚችሉ ቢያውቁም የካቲን ወላጆች ለመጠየቅ ወደ ሚሺጋን፣ ሃውተን ተመለሱ። በዚያም እንደዚያው ሂፒ እንደመሰሉ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኙ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙና ሚሺጋን በቆዩበት የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሲያጠኑ ቆዩ።

ወደ ጋብሪኦላ ደሴት ከተመለሱ በኋላ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ፣ በናናይሞ ጎዳና ላይ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ያገኙና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደሚፈልጉ ይነግሯታል። በዚያው ቀን ምሥክሮቹ በጀልባ መጥተው ማርክና ካቲን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኗቸው ጀመር። ከሦስት ወራት በኋላ ማርክና ካቲ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመሩ። ይህ ከሆነ ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ መጋቢት 10, 1974 ሁለቱም ተጠመቁ። ይህም ዴኒስ በተጠመቀ በሳምንቱ ማለት ነው!

ዴኒስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ

መስከረም 1974 ዴኒስ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። እንዲህ ይላል:- “በአቅኚነት በማገልገሌ ደስተኛ ብሆንም አገልግሎቴን ይበልጥ ለማስፋት ስለፈለግሁ ሐምሌ 1975 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገል አመለከትሁ። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር በቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ።”

ዴኒስ መጀመሪያ የተሰጠው ሥራ የቀድሞውን ታወርስ ሆቴል ለዋና መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች መኖሪያ እንዲሆን በማስተካከሉ ሥራ ማገዝ ነበር። በዚያም ሸክላ የሚያነጥፈውን ቡድን በበላይነት በመከታተል ለዓመታት ሠራ። በኋላም ማግባት ስለፈለገ ወደ ካሊፎርኒያ ሄደ። በ1984 በካቴድራል ሲቲ በሚገኘው ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ እያለ ካቲ ኤንስ የተባለችውን አቅኚ እህት አገባ።

ዴኒስና ካቲ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደም ስለፈለጉ ኑሯቸውን ቀላል ለማድረግ ቆርጠው ነበር። በመሆኑም ዴኒስ በደቡባዊ ካሊፎርኒያ በጣም ተፈላጊ በነበረው የግንባታ ሥራ ብዙ ገንዘብ ማግኘት የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ቢቀርቡለትም አልተቀበላቸውም። በ1988 እሱና ካቲ በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች የግንባታ ሥራ ለመካፈል አመለከቱ። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር በቦነስ አይረስ፣ አርጀንቲና በሚካሄደው የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ እንዲሠሩ ተመደቡ።

በ1989 ዴኒስና ካቲ በይሖዋ ምሥክሮች የግንባታ ሥራ ቋሚ በሆነ መንገድ እንዲካፈሉ ተጋበዙ። በዚህ ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው በሱሪናምና በኮሎምቢያ ሁለት ጊዜ አገልግለዋል። እንዲሁም በኢኳዶር፣ በሜክሲኮና በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ሥራ ተካፍለዋል።

ማርክ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ

በ1976 የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ለማርክና ወታደራዊ ምልመላውን በመሸሽ ወደ ካናዳ ለተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች አሜሪካውያን ወንዶች ምሕረት አደረገላቸው። ማርክና ሚስቱም በአገልግሎታቸው የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ ሕይወታቸውን ቀላል ማድረግ ይፈልጉ ነበር። በመሆኑም ማርክ በቀያሽነት የትርፍ ሰዓት ሥራ እየሰራ እሱና ካቲ ከመጠመቃቸው በፊት የተጠራቀመባቸውን ዕዳ ቀስ በቀስ ከፍለው ጨረሱ።

በ1978 በካናዳ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ አቅራቢያ አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ለመሥራት ሲያቅዱ ማርክና ካቲ በሥራው እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነበሩ። ማርክ በቅየሳ ሥራ ልምድ ስለነበረው በግንባታው እንዲካፈሉ ተጋበዙ። በጆርጅታውን ፕሮጀክቱ ሰኔ 1981 እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ሠርተዋል። ከዚያም እንደገና ወደ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ተመልሰው ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ሲሠሩ ቆዩ። ሥራው ሲጠናቀቅ በካናዳ የሚገኘውን የቅርንጫፍ ቢሮ በማስፋቱ ሥራ እንዲካፈሉ እንደገና ተጋበዙ።

ማርክና ካቲ በጆርጅታውን ለጥቂት ወራት ከቆዩ በኋላ በ1986 የካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ቋሚ አባላት እንዲሆኑ ተጋበዙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በማገልገል ላይ ሲሆኑ በሌሎች በርካታ አገራትም በግንባታ ሥራ የመሳተፍ ሰፊ አጋጣሚ አግኝተዋል። ማርክ በቅየሳ ሥራ ልምድ ስላለው በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ እንዲሁም በካሪቢያን ደሴቶች በተከናወኑት የቅርንጫፍ ቢሮዎችና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ግንባታ በሙያው አገልግሏል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ ማርክና ካቲ በቬኑዝዌላ፣ ኒካራጓ፣ ሃይቲ፣ ጉያና፣ ባርባዶስ፣ የባሃማስ ደሴቶች፣ ዶሚኒካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ (ፍሎሪዳ)፣ እና ዶሚኒካን ሪፑብሊክ አገልግለዋል። ይህ ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስክ ማርክና ዴኒስ እንደገና እንዲገናኙ መንገድ ጠርጓል።

በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ እንደገና ተገናኙ

ማርክና ዴኒስ ሳያውቁት በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ እየሠሩ ነበር። አንድ ቀን በሳንቶ ዶሚንጎ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በድንገት ይገናኛሉ። እንደገና በመገናኘታቸው በጣም እንደተደሰቱ መገመት አይከብድህም። ደግሞም የተገናኙት ከ33 ዓመት በኋላ ስለሆነ ስላሳለፉት ሕይወት ብዙ የሚያወሩት ነገር ነበራቸው። ባብዛኛው እስካሁን ያነበብከውን ታሪክ የሚጫወቱት በግርምት ተውጠው ነበር። ይሁን እንጂ ለእነሱም ሆነ ታሪካቸውን ለሰማ ሁሉ በጣም አስገራሚ የሆነው ሕይወታቸው በብዙ ነገሮች መመሳሰሉ ነው።

ሁለቱም የሂፒ አኗኗር ኖረዋል፤ እንዲሁም በፍቅረ ነዋይ የተጠመደው ዘመናዊ አኗኗር ከሚያስከትላቸው በርካታ ጭንቀቶች ለመገላገል ሲሉ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ሄደዋል። ዴኒስም ሆነ ማርክ ያገቧቸው ሴቶች ካቲ ይባላሉ። ሁለቱም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኙ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማምተዋል። ሁለቱም የተጠመቁት በመጋቢት ወር 1974 ነው። ዴኒስ በዩናይትድ ስቴትስ ማርክ ደግሞ በካናዳ የይሖዋ ምሥክሮች የቅርንጫፍ ቢሮ ቤተሰብ አባላት ሆነዋል። ሁለቱም መንፈሳዊ ግቦችን ለመከታተል ሲሉ ሕይወታቸውን ቀላል ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። (ማቴዎስ 6:22) ሁለቱም በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ የተካፈሉ ሲሆን በተለያዩ አገሮች ውስጥ ሠርተዋል። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በአጋጣሚ እስከተገናኙበት ጊዜ ድረስ አንዳቸውም ከቀድሞ ጓደኞቻቸው መካከል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለ ሰው አላጋጠማቸውም።

ማርክና ዴኒስ ይህ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ የዕድል ጉዳይ እንደሆነ ይሰማቸዋልን? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጊዜና አጋጣሚ [ሁላችንንም]” እንደሚያገኘን በሚናገረው መሠረት አንዳንድ ጊዜ በጣም አስገራሚ የሆኑ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። (መክብብ 9:11 NW) ይሁን እንጂ ሁለቱም ሕይወታቸውን ትርጉም ባለው መንገድ ለመምራት የነበራቸው ፍላጎትና ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንደገና እንዲገናኙ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ይገነዘባሉ።

የዴኒስና የማርክ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚማሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የሚያጋጥሟቸውን ሌሎች ነገሮችም ያጎላል። ዴኒስ እንዲህ ይላል:- “ማርክና እኔ ያጋጠመን ሁኔታ ይሖዋ የሰዎችን ሁኔታ እንደሚከታተልና ልባቸው ለእውነት ዝግጁ ሲሆን ወደ ራሱ እንደሚስባቸው ያሳያል።”—2 ዜና መዋዕል 16:9፤ ዮሐንስ 6:44፤ ሥራ 13:48

ማርክም እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “የእኛ ተሞክሮ ሌላም ነገር አስተምሮናል። አንድ ሰው ራሱን ከይሖዋ የአቋም መሥፈርቶች ጋር ካስማማ፣ ሕይወቱን ለእሱ ከወሰነና ራሱን ካቀረበ ይሖዋ ሕዝቦቹን በሚጠቅም መንገድ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የግለሰቡን ችሎታ ሊጠቀምበት ይችላል።”—ኤፌሶን 4:8

የእነርሱ ተሞክሮ ይሖዋ አምላክ ሕዝቦቹ በሙሉ ነፍስ የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንደሚባርከውም ያሳያል። ዴኒስና ማርክ በእርግጥ ይሖዋ እንደባረካቸው ይሰማቸዋል። ዴኒስ እንዲህ ይላል:- “በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል የመንግሥቱን ፍላጎቶች ማስቀደም ትልቅ መብት ነው። በዓለም ዙሪያ ካሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር መሥራታችን እርስ በእርስ የምንበረታታበትን አጋጣሚ ፈጥሮልናል።”

ማርክም አክሎ እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ መንግሥቱን የሚያስቀድሙትን እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም። የካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ቤተሰብ አባል ሆኜ ለማገልገልና በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ ለመካፈል መቻሌን እንደ ልዩ በረከት እቆጥረዋለሁ።”

አስገራሚ ግጥምጥሞሽ አይደለም? አዎን፣ ማርክ ሁኔታውን ልዩ ያደረገው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እንደገና መገናኘታችን ያን ያህል አስደሳች የሆነው ሁለታችንም ልዩ የሆነውን አምላክ ይሖዋን ማወቅ፣ መውደድና ማገልገል በመቻላችን ነው።”

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዴኒስ በ1966

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርክ በ1964

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዴኒስ በደቡባዊ ዳኮታ፣ 1974

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርክ በኦንታሪዮ፣ 1971

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዴኒስ እና ማርክ ከነሚስቶቻቸው በ2001 እንደገና ከተገናኙ ከጥቂት ጊዜ በኋላ