በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስሎቫኪያ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

በስሎቫኪያ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

በስሎቫኪያ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና

ያን ባሊ እንደተናገረው

ታኅሣሥ 24, 1910 አሁን በምሥራቃዊ ስሎቫኪያ በምትገኝ ዛሆር የተባለች መንደር ውስጥ ተወለድኩ። በወቅቱ መንደራችን በኦስትሪያና በሃንጋሪ ጥምር መንግሥት በሚተዳደረው ክልል ውስጥ ነበረች። በ1913 እናቴ ቀደም ብሎ ዛሆርን ለቅቆ ከነበረው ከአባቴ ጋር ለመኖር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይዛኝ ሄደች። እኔና እማማ በኢንዲያና ግዛት በምትገኘው ጌሪ ከተማ ከደረስን ከሁለት ዓመት በኋላ ታናሽ እህቴ አና ተወለደች። ከዚያም በ1917 አባባ ታመመና በሞት ተለየን።

ትምህርቴን በትጋት መከታተል ጀመርኩ። በተለይ ለሃይማኖት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። የሰንበት ትምህርት በምማርበት የካልቪኖች ቤተ ክርስቲያን አስተማሪው ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዳለኝ አስተዋለ። ይህንኑ ፍላጎቴን ለማርካት 4, 000 የሚያህሉ ጥያቄዎችና መልሶች የያዘውን የሆልማን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሰጠኝ። ስለዚህ ገና በ11 ዓመቴ ሰፊ እውቀት ሊያስጨብጠኝ የሚችል መጽሐፍ አገኘሁ።

‘እውነት ይህ ነው’

በእነዚያ ዓመታት እኛ በምንኖርበት አካባቢ የነበሩት አንዳንድ ስሎቫካውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነው ነበር። ከእነዚህም አንዱ አጎቴ ሚካኤል ባሊ ሲሆን ለእኛ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የነገረን እሱ ነበር። ይሁን እንጂ በ1922 እማማ እኔንና እህቴን ይዛ በወቅቱ የምሥራቃዊ ቼኮዝሎቫኪያ ክፍል ወደሆነችው ወደ ዛሆር ተመለሰች።

ከዚያም ብዙ ሳይቆይ አጎቴ ሚካኤል በቻርልስ ቴዝ ራስል የተዘጋጀውን ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለውን መጽሐፍ ሙሉ ጥራዞችና በሐምሌ 1, 1879 ከወጣው የመጀመሪያ እትም ጀምሮ ያሉትን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች በሙሉ ላከልኝ። ሁሉንም ከዳር እስከ ዳር ያነበብኳቸው ሲሆን አንዳንዶቹንም ደጋግሜ አነበብኳቸው። ከዚያም ስፈልገው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ።

በዚህ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የስሎቫክ ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ትውልድ አገራቸው ተመለሱና የመጀመሪያውን የስሎቫክ ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን በቼኮዝሎቫኪያ መሠረቱ። በዚያን ጊዜ እኔና እናቴ በመንደራችን በዛሆርና በአቅራቢያችን ባሉ ቦታዎች በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንገኝ ነበር።

እነዚህ ስብሰባዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይደረጉ ከነበሩት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአንዱ ቤት ውስጥ የምንሰበሰብ ሲሆን ፋኖስ ባለበት ጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጥ ነበር። እኔ የሁሉም ታናሽ ስለነበርኩ ከኋላ ጨለማ ውስጥ ተቀምጬ አዳምጣለሁ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሐሳብ እንድሰጥ ይጋብዙኝ ነበር። በስሎቫክ ቋንቋ የተጻፈ ጽሑፍ ግልጽ ካልሆነላቸው “ያን እስቲ እንግሊዝኛው ምንድን ነው የሚለው? ብለው ይጠይቁኛል። ወደ ፋኖሱ ቀርቤ የእንግሊዝኛው ጽሑፍ ምን እንደሚል እተረጉምላቸዋለሁ።

በዩናይትድ ስቴትስ እውነትን ሰምተው ወደ ቼኮዝሎቫኪያ ከተመለሱት ውስጥ አንዱ ሚካኤል ሻላታ ነበር። በአቅራቢያችን ወዳለው የድሮ መንደሩ ወደ ሴቾቭትሲ ተመለሰና በቼኮዝሎቫኪያ ውስጥ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በማደራጀቱ ሥራ መርዳት ጀመረ። ወንድም ሻላታ ለስብከት በሚጓዝበት ወቅት ይዞኝ ይሄድ ነበር። ከዚያም በ1924 የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ እንዲያጠምቀኝ ጠየቅሁት። ምንም እንኳን እናቴ እንዲህ ዓይነቱን ከባድ እርምጃ ለመውሰድ ገና ልጅ እንደሆንኩ ተሰምቷት የነበረ ቢሆንም በውሳኔዬ እንደቆረጥኩ አሳመንኳት። ስለዚህ በዚያው ወር በኦንዳቫ ወንዝ አጠገብ በተደረገ የአንድ ቀን ስብሰባ ላይ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በወንዙ ውስጥ በመጠመቅ አሳየሁ።

ውድ የአገልግሎት መብቶች

የ17 ዓመት ወጣት እያለሁ እኔ ከምሰብክበት መንደር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ አንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚፈጸም ሰማሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአካባቢው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲያከናውኑ ይህ የመጀመሪያቸው ነበር። በቀብሩ ቦታ ስደርስ በማንነቴ ግራ በተጋቡት መንደርተኞች መሃል አልፌ ወደ ተናጋሪው አመራሁ። አጠገቡ ስደርስ ወደ እኔ ዞረ አለና “መጀመሪያ እኔ ልናገርና ከዚያ በኋላ አንተ ትቀጥላለህ” አለኝ።

ያቀረብኩት ንግግር “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል” በሚለው በ1 ጴጥሮስ 4:​7 ላይ የተመሠረተ ነበር። መከራና ሞትም የሚያከትምበት ጊዜ መቅረቡን ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስኩ ያስረዳሁ ሲሆን ስለ ትንሣኤ ተስፋ አብራራሁ። (ዮሐንስ 5:​28, 29፤ ሥራ 24:​15) ምንም እንኳን ሲያዩኝ ገና ልጅ የምመስል ብሆንም [ምናልባትም ልጅ መምሰሌ ሳይረዳኝ አልቀረም] በቀብሩ ላይ የተገኙት ሁሉ በጥሞና ያዳምጡ ነበር።

የመስከረም 15, 1931 መጠበቂያ ግንብ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚለው ወይም በሌላ በየትኛውም ስም መጠራት እንደማንፈልግ የሚገልጽ አስደሳች ዜና ይዞ ነበር። በአካባቢያችን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ዜና ካነበቡ በኋላ አንድ ለየት ያለ ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት አደረጉ። ወደ 100 የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በፖዝዲሾቭሲ መንደር ተሰበሰቡ። በዚያ ስብሰባ ላይ “አዲሱ ስም” በሚል ርዕስ ከላይ በተጠቀሰው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ላይ የተመሠረተ ንግግር የማቅረብ መብት አገኘሁ።

በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉት የእምነት አጋሮቻቸው ያወጡትን የአቋም መግለጫ መደገፋቸውን እንዲያሳዩ ሲጠየቁ በታላቅ ደስታ እጃቸውን አነሱ። ከዚያም ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚከተለውን ቴሌግራም ላክን:- “እኛ በዛሬው ዕለት በፖዝዲሾቭሲ የተሰበሰብን የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን ስማችንን አስመልክቶ በመጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው ማብራሪያ ሙሉ በሙሉ የምንስማማ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲሱን ስማችንን መቀበላችንን ለመግለጽ እንወዳለን።”

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የቼኮዝሎቫኪያ ክፍል የነበረው ሰፊው የስሎቫኪያና የትራንስካርፓቲያ አካባቢ ለክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ፍሬያማ መስክ ነበር። ይህን ሰፊ ክልል የምንሸፍነው በእግር፣ በባቡር፣ በአውቶቡስና በብስክሌት እየተጓዝን ነበር። በወቅቱ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተሰኘው ከድምፅ ጋር የተቀናበረ የተንቀሳቃሽ ፊልምና የስላይድ ትዕይንት በበርካታ ከተሞች ውስጥ ይታይ የነበረ ሲሆን ፊልሙ ከቀረበ በኋላ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አድራሻ ሁልጊዜ ይሰበሰባል። ለእነዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠይቅ የሚያደርጉ ምሥክሮችን እንዳደራጅ አብዛኞቹ አድራሻዎች ለእኔ ይሰጡኛል። በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ አዳራሽ ተከራይተን ፊልሙን ካሳየን በኋላ ልዩ ንግግር አቀርብ ነበር።

በ1930ዎቹ ዋና ከተማ በሆነችው በፕራግ በተካሄዱት ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ልዑክ ሆኜ የመገኘት መብት አግኝቼ ነበር። በ1932 በቼኮዝሎቫኪያ የመጀመሪያውን ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት ተደረገ። ስብሰባው የተደረገው በቫሬቲ የቲያትር አዳራሽ ነበር። ወደ 1, 500 የሚጠጉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን “አውሮፓ ከመውደሟ በፊት” በሚል ጭብጥ የቀረበው የሕዝብ ንግግር የተሰብሳቢዎቹን ትኩረት ስቦ ነበር። በ1937 በፕራግ ሌላ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን ከንግግሮቹ ውስጥ አንዱን የማቅረብ መብት አግኝቻለሁ። ከበርካታ የአውሮፓ አገሮች ልዑካን መጥተው የነበረ ሲሆን ሁላችንም ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትለው የመጡትን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት የሚያስፈልገንን ማበረታቻ አግኝተናል።

ትዳርና ከባድ ፈተናዎች

እማማና እኔ ወደ ቼኮዝሎቫኪያ ከተመለስን በኋላ በፖዝዲሾቭሲ አቅራቢያ ከሚኖሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ሆነን እንሰብክ ነበር። በዚያ መንደር አና ሮሃሎቫ ከተባለች አንዲት ውብ ልጃገረድ ጋር ተዋወቅሁ። እያደግን ስንሄድ የነበረን ቅርርብ እንዲሁ የወንድምነትና የእህትነት ብቻ እንዳልሆነ ተገነዘብን። በ1937 ተጋባን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አና ትደግፈኝ የነበረ ሲሆን ከፊታችን ይጠብቁን በነበሩት ‘አመቺ ያልሆኑ ጊዜያት’ እንኳን ከጎኔ አልተለየችም።​​—⁠⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​2 አ.መ.ት 

ከተጋባን በኋላ ብዙም ሳይቆይ አውሮፓ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተዘጋጀች እንዳለች በግልጽ ይታይ ጀመር። በኅዳር 1938 የናዚ ጀርመን አጋር የነበረችው ሃንጋሪ የትራንስካርፓቲያን ደቡባዊ ክፍልና ስሎቫኪያን ጠቀለለቻቸው። የሃንጋሪ ፖሊሶች ስብሰባዎችን እንዳናደርግ የከለከሉን ሲሆን ዘወትር ፖሊስ ጣቢያ እየሄድን ሪፖርት ማድረግ ነበረብን።

መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር በዛሆር ከነበርነው ወንዶችና ሴቶች ምሥክሮች ውስጥ በርከት ያልነውን በቁጥጥር ሥር አዋሉንና አሁን በዩክሬይን ይዞታ ሥር በምትገኘው በሙካቾቭ ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ አሮጌ የግንብ ቤት ውስጥ አጎሩን። በዚያም በትራንስካርፓቲያ ካሉ ጉባኤዎች ከመጡ ብዙ የእምነት አጋሮቻችን ጋር ተገናኘን። ለሦስትና አራት ወራት ያህል ምርመራ የተደረገብን ሲሆን ብዙ ጊዜ እንደበደብ ነበር። በመጨረሻም ወደ አንድ ልዩ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀረብን። ለሁላችንም “ከሃንጋሪ ጎን ቆማችሁ ሶቪየት ሕብረትን ለመውጋት ፈቃደኛ ናችሁ?” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ቀረበልን። ፈቃደኛ አለመሆናችንን በመግለጻችን እስራት ተፈረደብንና በቡዳፔስት ሃንጋሪ ውስጥ ሞርጊት ቦሊቫርድ በሚገኝ ወኅኒ ቤት ውስጥ ታሰርን።

በወኅኒ ቤቱ ያሉት እስረኞች በሙሉ በረሃብ የተጎዱ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ተላላፊ በሽታ ተነሳና እስረኞች ይሞቱ ጀመር። በዚህ ወቅት ባለቤቴ እኔን ለማየት ከዛሆር ድረስ ስትመጣ ምንኛ እንደተደሰትኩ ገምቱ! በወኅኒ ቤቱ የብረት ፍርግርጎች በኩል እየተያየን የተነጋገርነው ለአምስት ደቂቃ ያህል ብቻ ቢሆንም እርሷን የመሰለ ታማኝ አጋር በማግኘቴ ይሖዋን አመሰገንኩት። *

ከወኅኒ ቤት የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ

ከወኅኒ ቤት በቀጥታ 160 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚገኙበት በሃንጋሪ ውስጥ ወደሚገኝ ያስቤራን የተባለ ከተማ ተወሰድኩ። በዚያ እያለን አንድ የሃንጋሪ መኮንን መንግሥቱን ወክሎ የመጨረሻ እድል ሰጠን። “በሠራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆናችሁ ወደ ፊት ውጡ።” ማንም ካለበት አልተንቀሳቀሰም። ከዚያ መኮንኑ እንዲህ አለ:- “በውሳኔያችሁ ባልስማማም ታማኝነታችሁን ለመጠበቅ ያላችሁን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ።”

ከጥቂት ቀናት በኋላ በዳንዩብ ወንዝ ላይ በመርከብ አድርገን ቦር በምትባለው የዩጎዝላቭ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ጉዞ ጀመርን። በጉዞ ላይ እያለን ወታደሮቹና አዛዣቸው ሐሳባችንን እንድንለውጥ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጉ ነበር። አዛዡ ወታደሮቹ በጠመንጃቸው እንዲደበድቡን፣ በወታደር ጫማቸው እንዲረግጡንና በሌሎች መንገዶችም እንዲያሰቃዩን ያደርግ ነበር።

በቦር የጉልበት ሥራ ማሠሪያ ካምፕ አዛዥ የነበረው ሌተና ኮሎኔል አንድራሽ ቦሎግ ሲረከበን “ስለ እናንተ የሰማሁት እውነት ከሆነ በቃ አለቀላችሁ” አለን። ይሁን እንጂ ከመንግሥት ባለስልጣናት የተላከለትን የታሸገ መልእክት ካነበበ በኋላ በአክብሮት አስተናገደን። ቦሎግ ከሌሎች የተሻለ የመንቀሳቀስ ነጻነት የሰጠን ሲሆን የራሳችንንም መኖሪያ እንድንገነባ ፈቀደልን። ምንም እንኳን የነበረው የምግብ አቅርቦት በጣም አነስተኛ ቢሆንም የራሳችን ማብሰያ ቤት ስለነበረን የተገኘችዋን እኩል እንከፋፈላት ነበር።

በመጋቢት 1944 ጀርመን ሃንጋሪን መውረር ጀመረች። ከዚያም ቦሎግ ኢዲ ሞራኒ በተባለ የናዚዎች ደጋፊ አዛዥ ተተካ። አዲሱ አዛዥ የካምፑ ሥነ ሥርዓት ልክ እንደ ማጎሪያ ካምፕ ጥብቅ እንዲሆን አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ግን የሩሲያ ሠራዊት እየተቃረበ ስለመጣ በቦር የነበረውን ካምፕ ለቅቀን ጉዞ ጀመርን። በጉዟችን ወቅት በቼርቬንኮ በነበሩ አይሁዶች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በዓይናችን ተመልክተናል። የእኛ በሕይወት መትረፍ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነበር።

ሃንጋሪ ከኦስትሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ስንደርስ መትረየስ የሚጠመድባቸው ምሽጎች እንድንቆፍር ታዘዝን። መጀመሪያውኑም የታሰርነው በማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አንሳተፍም በማለታችን መሆኑን ተናገርን። የቆምኩት በቡድኑ ፊት ለፊት ስለነበር አንድ የሃንጋሪ ወታደር አፈፍ አድርጎ ያዘኝና ይደበድበኝ ጀመር። “እገድልሃለሁ! አንተ አልሠራም ካልክ ሌሎቹም ያንተን መጥፎ አርኣያ ይከተላሉ” ሲል አንባረቀብኝ። በስብከቱ ሥራችን ግንባር ቀደም የነበረ አንድራሽ ባርታ የተባለ አንድ አረጋዊ ምሥክር በድፍረት ጣልቃ ባይገባ ኖሮ አልቆልኝ ነበር። *

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጦርነቱ አበቃና ወደ ቤታችን ለመመለስ ጉዞ ጀመርን። እኛ ከመለቀቃችን ቀደም ብሎ ከቦር ካምፕ የተለቀቁ አብረውን የነበሩ ሌሎች እስረኞች ሁላችንም ወደ ቼርቬንኮ ተወስደን እንደተገደልን አውርተው ነበር። ስለዚህ ባለቤቴ ለስድስት ወራት ያህል ራስዋን መበለት እንደሆነች አድርጋ ትቆጥር ነበር። አንድ ቀን ድንገት እቤት ከተፍ ስል ምን ያህል እንደተደሰተች ልትገምቱ ትችላላችሁ! ከዓመታት መለያየት በኋላ ስንገናኝ ተቃቅፈን በደስታ አለቀስን።

የስብከቱን ሥራ ዳግመኛ ማደራጀት

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ስሎቫኪያና ቼኪያ ተቀላቀሉና ቼኮዝሎቫኪያ ተመሠረተች። ከጦርነቱ በፊት በአብዛኛው በቼኮዝሎቫኪያ ሥር ይተዳደር የነበረው የትራንስካርፓቲያ አካባቢ ግን የሶቪየት ሕብረት አካል ለነበረችው ለዩክሬይን ተሰጠ። በ1945 እኔና ሚካኤል ሞስካል አሁን የስሎቫኪያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ብራቲስላቫ ሄድንና የስብከቱን ሥራ በድጋሚ ማደራጀትን በሚመለከት ኃላፊነት ከነበራቸው ወንድሞች ጋር ተነጋገርን። በአካልም ሆነ በስሜት ተዳክመን የነበረ ቢሆንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ ለመወጣት በጣም ጓጉተን ነበር።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ ማቴዎስ 28:​18-20

ከጦርነቱ በኋላ ትላልቅ ስብሰባዎች ለሥራችን እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተው ነበር። በመስከረም 1946 በመላ አገሪቱ ውስጥ ለመካሄድ የመጀመሪያ የሆነው ስብሰባ በበርኖ ከተማ ተካሄደ። በዚህ ስብሰባ ላይ “መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው” በሚል ጭብጥ ንግግር የማቅረብ መብት አግኝቼ ነበር።

በ1947 በበርኖ ሌላ አገር አቀፍ ስብሰባ ተደረገ። በዚህ ስብሰባ ላይ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጡት ናታን ኤች ኖር፣ ሚልተን ጂ ሄንሽልና ሃይደን ሲ ኮቪንግተን የሚያበረታቱ ንግግሮች አቅርበው የነበረ ሲሆን በአስተርጓሚነት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ምንም እንኳን በወቅቱ በቼኮዝሎቫኪያ የነበሩት ምሥክሮች 1, 400 ገደማ ቢሆኑም ሕዝብ ንግግሩን ለማዳመጥ 2, 300 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።

በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር የነበረ ስደት

በ1948 ኮሚኒስቶች ሥልጣን ያዙ። ብዙም ሳይቆይ በስብከቱ ሥራችን ላይ ለ40 ዓመታት የዘለቀ እገዳ ተጣለ። በ1952 ባለሥልጣናት እንደ ሥራው መሪዎች አድርገው ያዩን ከነበርነው ውስጥ ብዙዎቻችን ታሰርን። አብዛኞቹ የተከሰሱት መንግሥት ለመገልበጥ አሲራችኋል በሚል ሲሆን ጥቂቶቻችን ግን አገርን በመክዳት ተወነጀልን። ለ18 ወራት ታስሬ ምርመራ ተደረገብኝ። አገሬን የከዳሁት እንዴት እንደሆነ ስጠይቅ ዳኛው እንዲህ አሉኝ:- “ስለ አምላክ መንግሥት ትሰብካለህ። እንዲሁም የአምላክ መንግሥት መጥቶ የዓለምን አገዛዝ እንደሚያጠፋ ትናገራለህ። የዓለም መንግሥታት ደግሞ ቼኮዝሎቫኪያንም ይጨምራል።”

“እንደዚያ ከሆነ የጌታን ጸሎት እየጸለዩ ‘የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ’ የሚለምኑትን ሁሉ አገርን በመክዳት ልትወነጅሏቸው ይገባል” ስል መለስኩላቸው። እንዲያም ሆኖ የአምስት ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደብኝና በያኬሞፍ ወደሚገኘው በአስከፊነቱ የታወቀ የኮሚኒስት ወኅኒ ቤት ተላክሁ።

አብዛኛውን የእስራት ጊዜዬን ካጠናቀቅሁ በኋላ ተፈታሁ። ባለቤቴ አና ደብዳቤዎች በመጻፍና በአካል መጥታ በመጠየቅ እንዲሁም ሴት ልጃችንን ማሪያን በመንከባከብ በታማኝነት ትደግፈኝ ነበር። በመጨረሻም ከእስር ተፈትቼ ከቤተሰቤ ጋር ተቀላቀልኩና ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን በድብቅ ማካሄድ ቀጠልን።

ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እርካታ

ባለፉት ከ70 የሚበልጡ ዓመታት በአካባቢያችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፉት በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ነበር። ምንም እንኳ እድሜዬ ቢገፋና አቅሜ ቢደክምም በ98 ዓመት እድሜው ላይ እንደሚገኘው እንደ ያን ኮርፓ-ኦንዶ ከመሳሰሉ ታማኝ ምሥክሮች ጋር በዛሆር በሚገኝ ጉባኤ በሽማግሌነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። * የይሖዋ ስጦታ የነበረችው ውዷ ባለቤቴ በ1996 በሞት ተለየችኝ።

በ1924 በታተመው ዘ ዌይ ቱ ፓራዳይዝ በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 228 እስከ 231 ላይ የቀረበው ምናባዊ ትዕይንት አሁንም በአእምሮዬ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ይህ መጽሐፍ አንባቢው ገነት ውስጥ እንዳለና በትንሣኤ የተነሱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የት እንዳሉ ግራ ገብቷቸው ሲነጋገሩ እንደሚሰማ አድርጎ በዓይነ ሕሊናው እንዲስል ግብዣ ያቀርባል። ከዚያም ከአርማጌዶን በሕይወት የተረፈ አንድ ሰው ለሁለቱ ሰዎች በገነት ውስጥ ትንሣኤ ማግኘታቸውን ይነግራቸዋል። (ሉቃስ 23:​43) እኔም ከአርማጌዶን በሕይወት ከተረፍኩ ባለቤቴ፣ እናቴና ሌሎች የምወዳቸው ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ እንዲህ የመሳሰሉ ሁኔታዎችን መንገር እፈልጋለሁ። አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት ከሞትኩ ግን በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ትንሣኤ ሳገኝ አንድ ሰው እኔ ከሞትኩ በኋላ ስለተከናወኑት ነገሮች ሲነግረኝ ለመስማት እናፍቃለሁ።

እስከዚያው ግን ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር ለመነጋገርና እርሱን የቅርብ ወዳጄ ለማድረግ ያገኘሁትን ልዩ መብት ከፍ አድርጌ መመልከቴን እቀጥላለሁ። በሮሜ 14:​8 ላይ ከሚገኙት “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፣ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን” ከሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ጋር ተስማምቼ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጌአለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.22 በሚያዝያ 22, 2002 ንቁ! ገጽ 19-23 (እንግሊዝኛ) ላይ የሰፈረውን የአንድሬ ሃናክ ታሪክ ተመልከት። በታሪኩ ላይ በዚህ ወኅኒ ቤት የነበረው ሁኔታና በኋላ በሚጠቀሰው በቼርቬንኮ የተፈጸሙት ሁኔታዎች ተገልጸዋል።

^ አን.28 ስለ አንድራሽ ባርታ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሐምሌ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11⁠ን ተመልከት።

^ አን.39 የወንድም ያን ኮርፓ-ኦንዶን የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24-28 ላይ መመልከት ትችላለህ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአና ጋር፣ ከሠርጋችን ከአንድ ዓመት በኋላ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1947 በበርኖ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ከናታን ኤች ኖር ጋር