በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግዝና ምክንያት የሚደርሱ ችግሮችን መቀነስ

በእርግዝና ምክንያት የሚደርሱ ችግሮችን መቀነስ

በእርግዝና ምክንያት የሚደርሱ ችግሮችን መቀነስ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደ ጻፈው

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ድርጅት እንዳለው በየዓመቱ ከግማሽ ሚልዮን የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከእርግዝና ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ። በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በየዓመቱ ከ60 ሚልዮን የሚበልጡ ሴቶች በእርግዝና ምክንያት አጣዳፊ የሆነ የጤና መታወክ እንደሚደርስባቸውና ይህም የጤና እክል አንድ ሦስተኛ በሚሆኑት ላይ ዕድሜ ልክ የሚቆይ ጉዳት ወይም የጤና ችግር እንደሚያደርስ አመልክቷል። በታዳጊ አገሮች ብዙ ሴቶች እርግዝና፣ ወሊድና የሰውነት መጎሳቆል በተደጋጋሚ ስለሚፈራረቅባቸው የተጎሳቆለና የተጎዳ ሰውነት ይኖራቸዋል። አዎን፣ እርግዝና ጎጂ ከዚያም አልፎ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ታዲያ አንዲት ሴት በእርግዝና ምክንያት የሚደርሱባትን ችግሮች ለመቀነስ ማድረግ የምትችላቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን?

ከእርግዝና በፊት ለጤንነት እንክብካቤ ማድረግ

የቤተሰብ እቅድ። ባልና ሚስቱ ስንት ልጆች እንዲኖሯቸው እንደሚፈልጉ መነጋገር ያስፈልጋቸው ይሆናል። በታዳጊ አገሮች ጡት ያልጣለ ልጅ ያላት እናት ሌላ ልጅ ለመውለድ ተቃርባ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። እቅድ ማውጣትና በጉዳዩ ላይ በቁም ነገር ማሰብ በሚወለዱት ልጆች መካከል በቂ የዕድሜ መራራቅ እንዲኖር ያስችላል። ይህም ሴቲቱ ፋታና በቂ የማገገሚያ ጊዜ እንድታገኝ ያስችላታል።

አመጋገብ። ካኦሊሽን ፎር ፖዘቲቭ አውትካምስ ኢን ፕረግናንሲ የተባለው ድርጅት እንዳለው አንዲት ሴት ከማርገዟ እጅግ ቢያንስ ከአራት ወራት በፊት እንደ መድኃኒት፣ ሲጋራና አልኮል ካሉት ጎጂ ነገሮች መራቅና በቂ የንጥረ ምግቦች ክምችት ሊኖራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ነፍሰ ጡር የሆነችው ሴት ፎሊክ አሲድ የተባለውን ንጥረ ምግብ በበቂ መጠን ካገኘች ጽንሱ የነርቭ ቱቦው በአግባቡ ሳይዘጋ በመቅረቱ ምክንያት በሚመጣ ስፒና ባይፊዳ በተባለ የነርቭ እክል እንዳይጠቃ ማድረግ ትችላለች። የሽሉ የነርቭ ቱቦ የሚዘጋው በተጸነሰ ከ24ኛው እስከ 28ኛው ቀን ባለው ጊዜ ማለትም ብዙ ሴቶች ማርገዛቸውን ከማወቃቸው ከብዙ ቀን በፊት በመሆኑ ለማርገዝ የፈለጉ አንዳንድ ሴቶች ቀደም ብለው ፎሊክ አሲድ መውሰድ ይጀምራሉ።

ሌላው በጣም አስፈላጊ ንጥረ ምግብ ደግሞ ብረት ነው። አንዲት ሴት በምታረግዝበት ጊዜ የሚያስፈልጋት ብረት በእጥፍ ያድጋል። ቀድሞውኑ በቂ ክምችት ካልነበራት የደም ማነስ ችግር ያጋጥማታል። በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሴቶች የብረት ክምችት አይኖራቸውም። ቶሎ ቶሎ የምትወልድ ከሆነ ደግሞ የብረት ክምችቷን ለመጨመር በቂ ጊዜ ስለማታገኝ ችግሯ ይባባሳል። *

ዕድሜ። በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች ቁጥር በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች በ60 በመቶ ይበልጣል። በሌላው በኩል ደግሞ ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ዳውንስ ሲንድሮም እንደሚባለው ያለ እክል ያለባቸው ልጆች የመውለድ ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። በዕድሜ ለጋ የሆኑ ወይም ብዙ የገፉ ነፍሰ ጡሮች ፕሪኤክላምፕስያ በተባለው በሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ጽንሱ 20 ሳምንት ከሆነው በኋላ በሚደርስ የደም ግፊት፣ በሕብረ ሕዋስ ውስጥ ፈሳሽ በመብዛቱና በሽንት ውስጥ የሚኖረው ፕሮቲን መጠን በመብዛቱ የሚታወቀው ይህ በሽታ እናቲቱንም ሆነ ሕፃኑን ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

ኢንፌክሽኖች። የፊኛና የኩላሊት፣ የማህጸን አፍ፣ የጨጓራና የአንጀት ኢንፌክሽኖች በእርግዝና ወቅት ሊባባሱ ይችላሉ። እነዚህም ችግሮች ያለ ጊዜ መውለድና ፕሪኤክላምፕስያ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ማንኛውም ዓይነት ኢንፌክሽን ከእርግዝና በፊት ሙሉ በሙሉ እንዲድን ቢደረግ ጥሩ ይሆናል።

በእርግዝና ጊዜ የሚደረጉ የጤና እንክብካቤዎች

በእርግዝና ወቅት የሚደረግ ክትትል። በእርግዝና ጊዜ በሙሉ አዘውትሮ የሐኪም ክትትል ማግኘት በወሊድ ምክንያት የመሞትን አጋጣሚ በጣም ይቀንሳል። ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች እንደልብ በማይገኙባቸው አገሮችም ቢሆን ተገቢ ሥልጠና ያገኙ አዋላጆች ሊኖሩ ይችላሉ።

በእርግዝና ወቅት የሕክምና ክትትል ማድረግ ባለሞያዎቹ ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ሁኔታ መኖሩን በቅድሚያ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ልዩ ጥንቃቄ ከሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች መካከል መንታ ጽንስ፣ የደም ግፊት መጨመር፣ የልብና የኩላሊት ችግር እንዲሁም የስኳር በሽታ ይገኙባቸዋል። በአንዳንድ አገሮች አዲስ የሚወለደው ሕፃን ቴታነስ እንዳይዘው ለነፍሰ ጡር ሴቶች የቴታነስ ቶክሶይድ ክትባት ይሰጣል። በተጨማሪም አንዲት ሴት ካረገዘች በ26ኛውና በ28ኛው ሳምንት መካከል የግሩፕ ቢ ስትሬፕቶኮከስ ምርመራ ሊደረግላት ይችላል። ይህ ባክተሪያ በደንዳኔ አንጀት አካባቢ ከኖረ ልጁ በሚወለድበት ጊዜ ሊይዘው ይችላል።

ነፍሰ ጡርዋ ሴት ጤንነቷን የሚመለከቱ መረጃዎችን በሙሉ ለጤና ባለሞያዎቹ መንገር ይኖርባታል። እርሷም ጥያቄዎች ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይኖርባትም። ከማህጸኗ ደም የሚፈሳት ከሆነ፣ በድንገት ፊቷ የሚቆጣ ከሆነ፣ ኃይለኛ ወይም ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ራስ ምታት ወይም በጣቶቿ ላይ ሕመም የሚሰማት ከሆነ፣ በድንገት ዐይኗን የሚከልላት ወይም ብዥ የሚልባት ከሆነ፣ ሆዷን በኃይል ካመማት፣ የማያቋርጥ ትውከት ከኖራት፣ ትኩሳት ወይም ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ከኖራት፣ የሽሉ እንቅስቃሴ ከወትሮው የተለወጠ ከሆነ፣ የማህጸን ፈሳሽ ከኖራት፣ ስትሸና ሕመም ከተሰማት ወይም ሽንቷ በጣም ካነሰ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርባታል።

የአልኮል መጠጥና ሱስ የሚያስይዙ ዕፆች። አንዲት ነፍሰ ጡር የአልኮል መጠጥ የምትጠጣና ትንባሆን ጨምሮ ሱስ የሚያስይዝ ዕፅ የምትወስድ ከሆነ የምትወልደው ልጅ አእምሮ ዘገምተኛ፣ የአካል ጉዳተኛ ወይም የባሕርይ መዛባት ያለበት የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። የዕፅ ሱሰኛ ከሆኑ እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት የሱሰኝነት ምልክቶች ታይተውባቸዋል። አልፎ አልፎ አንድ ብርጭቆ የወይን ጠጅ መጠጣት ጉዳት የለውም ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም ሊቃውንት በእርግዝና ጊዜ ጨርሶ ከመጠጥ መራቅ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም ነፍሰ ጡር ሴቶች ሌሎች በሚያጨሱት የትንባሆ ጭስ እንዳይበከሉ መጠንቀቅ ይገባቸዋል።

መድኃኒቶች። ስለ እርግዝናው የሚያውቅ ሐኪም ጉዳቱንና ጥቅሙን በጥንቃቄ አመዛዝኖ ያዘዘው ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም መድኃኒት መውሰድ ተገቢ አይደለም። አንዳንድ ቪታሚኖች ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ቪታሚን ኤ ከበዛ በጽንሱ ላይ የአካል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

ውፍረት። ነፍሰ ጡር ሴት ከመጠን በላይ መክሳትም ሆነ መወፈር አይኖርባትም። ክራውሰስ ፉድ፣ ኒውትርሽን ኤንድ ዳየት ቴራፒ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው አነስተኛ ክብደት ኖሮት የተወለደ ሕፃን የመሞት አጋጣሚው ትክክለኛ ክብደት ከነበረው ሕፃን 40 እጥፍ ይበልጣል። በሌላ በኩል ደግሞ የሁለት ሰው ድርሻ መብላት ከመጠን በላይ ከማወፈር ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አንዲት ነፍሰ ጡር ከሦስተኛው ወር በኋላ ትክክለኛ የሆነ ውፍረት መጨመሯ ጥሩ አመጋገብ እንዳላት ያሳያል። *

የግል ንጽሕናና ሌሎች ጥንቃቄዎች። እንደወትሮው ገላን መታጠብ የሚያስከትለው ጉዳት ባይኖርም ማጸንን በኃይል በሚፈስስ ውኃ መታጠብ ተገቢ አይሆንም። ነፍሰ ጡር ሴት ከማንኛውም እንደ ጉድፍ ያለ የቫይረስ ኢንፌክሽን ከያዘው ሰው መራቅ ይኖርባታል። ከዚህም በላይ ቶክሶፕላዝሞሲስ የተባለው በሽታ እንዳይዛት በደንብ ካልበሰለ ሥጋና ከድመቶች ዓይነ ምድር መራቅ ይገባታል። እጅ እንደመታጠብና እሳት ሳይነካቸው የሚበሉ ምግቦችን እንደማጠብ ያሉ መሠረታዊ የንጽሕና ሥርዓቶችን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ሳምንታት ካልሆነ ወይም ደም መፍሰስ ወይም ቁርጠት ካልኖራት፣ ወይም ውርጃ አጋጥሟት የሚያውቅ ካልሆነ ምንም ጉዳት አያስከትልባትም።

በተሳካ ሁኔታ መውለድ

በእርግዝና ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄና እንክብካቤ ያደረገች ሴት በምትወልድበት ጊዜ ብዙም ችግር አይገጥማትም። እቤቷ ወይም ሆስፒታል መውለድ እንደምትፈልግ መወሰን እንደሚኖርባት የታወቀ ነው። በተጨማሪም ይነስም ይብዛ ምን እንደሚጠበቅባትና የአዋላጅዋን ወይም የዶክተሯን ጥረት ለማገዝ ምን ማድረግ እንደሚገባት ታውቃለች። አዋላጅዋና ዶክተሮችም የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አወላለዷን በሚመለከቱ (በምን መንገድ እንዲያዋልዷት እንደምትፈልግ፣ ቶሎ እንድትወልድ ለማድረግ የሚወሰዱ እርምጃዎችን፣ ጽንስ መጎተቻ መሣሪያ መጠቀምን፣ ሥቃይ ማስታገሻ መድሐኒቶችን መውሰድንና ጽንስ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ስለመሳሰሉ) ጉዳዮች ያሏትን ምርጫዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በቅድሚያ ሊስማሙባቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች ይኖራሉ። እቤቷ ሊያዋልዷት ሲሞክሩ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ችግር ቢያጋጥማቸው የሚወስዷት ወደየትኛው ሆስፒታል ወይም ክሊኒክ ይሆናል? ብዙ ደም ቢፈስሳት ምን ይደረጋል? ብዙ ወላጆች ብዙ ደም ፈስሷቸው ስለሚሞቱ ደም ለማይወስዱ ነፍሰ ጡሮች የደም ምትክ የሆኑ መድኃኒቶች መዘጋጀት አለባቸው። በተጨማሪም በቀዶ ሕክምና ማዋለድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ምን እንደሚደረግ አስቀድሞ ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የአምላክ በረከት፣ የእርሱም “ስጦታ” እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 127:​3) አንዲት ሴት ስለ እርግዝናዋ በተቻለ መጠን ብዙ እውቀት ማግኘቷ ብዙም ሳትቸገር እንድትወልድ ይረዳታል። ከማርገዟ በፊትና በእርግዝናዋ ወቅት በቂ ጥንቃቄ ብታደርግና በአወላለዷ ረገድ ሊያጋጥሟት ስለሚችሉ የተለያዩ ችግሮች አስቀድማ ብታስብ በእርግዝና ወቅት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ብዙ ችግሮች ትድናለች።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ፎሊክ አሲድና ብረት የሚገኝባቸው አንዳንድ ምግቦች ጉበት፣ ጥራጥሬዎች፣ አረንጓዴ ተክሎች፣ ኦቾሎኒ የመሰሉ ምግቦችና ንጥረ ምግቦች የተጨመሩባቸው የእህል ዘሮች ናቸው። በብረት የበለጸጉ ምግቦች ከሰውነት ጋር እንዲዋሃዱ ለመርዳት በቪታሚን ሲ የበለጸጉ ፍራፍሬዎችን አብሮ መመገብ ጥሩ ሊሆን ይችላል።

^ አን.16 ከማርገዟ በፊት ጤናማ ውፍረት የነበራት ሴት በእርግዝናዋ መጨረሻ ላይ ከ9 እስከ 12 ኪሎ ግራም ብትጨምር ጥሩ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙና ከሲታ ሴቶች ከ12 እስከ 15 ኪሎ ግራም መጨመር ሲኖርባቸው ወፍራም የሆኑ ሴቶች ግን ከ7 እስከ 9 ኪሎ ቢጨምሩ በቂ ይሆናል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለነፍሰ ጡር ሴቶች የሚጠቅሙ ምክሮች

አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት የተለየ ችግር ከሌለባት በስተቀር በየቀኑ ፍራፍሬና አትክልት (በተለይ አረንጓዴ፣ ብርቱካንማና ቀይ ቀለም ያላቸውን)፣ ጥራጥሬዎችን (እንደ ባቄላ፣ አኩሪ አተር፣ ምስርና ሽንብራ ያሉትን)፣ የእህል ዘሮችን (ስንዴን፣ በቆሎን፣ አጃንና ገብስን ይጨምራል፤ ያልተፈተገና በፋብሪካ ያልተዘጋጀ ቢሆን ይመረጣል)፣ ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦችን (ዓሣ፣ ዶሮ፣ የበሬ ሥጋ፣ እንቁላል፣ አይብና ቅባቱ የወጣለት ቢሆን ይመረጣል ወተት) መመገብ ይገባታል። ቅባት፣ ስኳርና ጨው በመጠኑ ብቻ ቢወሰድ ይመረጣል። ብዙ ውኃ መጠጣት አስፈላጊ ነው። እንደ ቡናና ሻይ ያሉትን ካፌይን ያላቸው መጠጦችንም ሆነ ሰው ሠራሽ ማጣፈጫዎችና ቅመሞች የተጨመሩባቸውን ምግቦች ማስወገድ ጥሩ ይሆናል።

ለኤክስሬይ ጨረር ወይም መርዛማ ለሆኑ ኬሚካሎች እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ ይገባቸዋል። በቤት ውስጥ የሚረጩ መድኃኒቶችንና መርዞችን በጣም መቀነስ ያስፈልጋል። ብዙ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ወይም ብዙ ለፀሐይ በመጋለጥ ምክንያት ከሚመጣ ከፍተኛ ሙቀት መራቅ ይገባል። ብዙ መቆም ወይም በጣም አድካሚ የሆነ ሥራ መሥራት ተገቢ አይደለም። የመኪና ቀበቶ አመቺ ቦታ ላይ ማሠርም አስፈላጊ ነው።