በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ድክመቶቻችንን ችላ ብሎ ያልፋል?

አምላክ ድክመቶቻችንን ችላ ብሎ ያልፋል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ ድክመቶቻችንን ችላ ብሎ ያልፋል?

‘ያሉብኝን መጥፎ ልማዶች ለመተው ያላደረግሁት ጥረት የለም። ከአቅሜ በላይ ሆኖ እንጂ መጥፎ ሰው ሆኜ አይደለም!’

አንተም እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ወይም ደግሞ እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማው ሰው ታውቅ ይሆናል። ብዙ ሰዎች ሥር የሰደደ የሥነ ምግባር ድክመትን ማሸነፍ የማይቻል ነገር ነው ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች የአልኮል መጠጦች፣ የትምባሆ ወይም የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች ሱሰኞች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸው በስግብግብነት የተሞላ ነው። የጾታ ስሜታቸውን ፈጽሞ ሊቆጣጠሩት እንደማይችሉ በማሰብ የጾታ ብልግና ውስጥ የሚዘፈቁ ሰዎችም አሉ።

ኢየሱስ በማቴዎስ 26:​41 ላይ የተናገረው ሐሳብ የሰዎችን ድክመት የሚረዳ መሆኑን ያሳያል። * እንዲያውም መላው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ መሐሪ መሆናቸውን ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 103:​8, 9) ነገር ግን አምላክ ድክመቶቻችንን በሙሉ ችላ ብሎ ያልፋል ብለን ማሰብ ይኖርብናል?

ሙሴና ዳዊት

እስቲ የሙሴን ታሪክ እንመርምር። ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት” የነበረ ሲሆን ይህንን ጥሩ ባሕርይ ይዞ ለመኖር ጥረት አድርጓል። (ዘኍልቁ 12:​3) እስራኤላውያን በምድረ በዳ ይጓዙ በነበረበት ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜያት የማይገባ ነገር በማድረግ ለይሖዋም ሆነ እርሱ ለሾማቸው ሰዎች ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል። በዚህ ሁሉ ወቅት ሙሴ በትሕትና መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ጥሯል።​—⁠ዘኍልቁ 16:​12-14, 28-30

ይሁን እንጂ ይህ አድካሚ ጉዞ የሚገባደድበት ጊዜ እየተቃረበ በመጣበት ወቅት ሙሴ በመላው የእስራኤል ብሔር ፊት በቁጣ ገንፍሎ የይሖዋን መመሪያ ጣሰ። ይሖዋ ይቅር ቢለውም ድርጊቱን ችላ ብሎ አላለፈውም። “በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋችሁ ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም” ብሎት ነበር። ሙሴ ተስፋይቱ ምድር አልገባም። ያንን ልዩ የሆነ መብት ለማግኘት ከ40 ዓመት በላይ የደከመ ቢሆንም ሰብዓዊ ጉድለቱ የበረከቱ ተካፋይ እንዳይሆን አድርጎታል።​—⁠ዘኍልቁ 20:​7-12

ንጉሥ ዳዊትም ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው ቢሆንም እንኳ ድክመት ነበረበት። በአንድ ወቅት የሌላ ሰው ሚስት በመመኘት ምንዝር ፈጸመ። ከዚያም ባሏን በማስገደል የሠራውን ሥራ ለመሸፋፈን ሞክሯል። (2 ሳሙኤል 11:​2-27) የኋላ ኋላ ግን በፈጸመው ድርጊት በጣም በመጸጸቱ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። ይሁንና ዳዊት አንድ ቤተሰብ በማፍረሱ ከመጣበት መቅሠፍት ይሖዋ አልጠበቀውም። የወለደው ልጅ በጣም በመታመሙ ልጁን እንዲያድንለት ወደ ይሖዋ ቢጸልይም ይሖዋ እጁን ጣልቃ ለማስገባት ፈቃደኛ አልሆነም። ልጁ ከመሞቱም በላይ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የዳዊት ቤት የተለያዩ መከራዎች ደርሰውበታል። (2 ሳሙኤል 12:​13-18፤ 18:​33) ዳዊት በሥነ ምግባር መውደቁ ብዙ መከራ አምጥቶበታል።

አምላክ፣ ሰዎች ለሚፈጽሙት ድርጊት ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው እነዚህ ምሳሌዎች ያሳያሉ። እሱን ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑባቸውን ጎኖች ማጠናከርና የተሻሉ ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች እንዲህ አድርገዋል።

ከኃጢአት ዝንባሌ ጋር መዋጋት

ሐዋርያው ጳውሎስ በጥሩ ክርስቲያናዊ አኗኗሩ በምሳሌነት የሚጠቀስ ቢሆንም ከድክመቶቹ ጋር የማያቋርጥ ትግል ያደርግ እንደነበረ ታውቃለህ? ጳውሎስ በሮሜ 7:​18-25 ላይ በግልጽ ተጠቅሶ የምናገኘውን ይህን ትግል ወይም ቁጥር 23 እንደሚገልጸው ይህን ‘ውጊያ’ ያለማቋረጥ ያደርግ የነበረው የኃጢአት ዝንባሌ በቀላሉ የማይወገድ መሆኑን ስላወቀ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​26, 27

በጥንቷ ቆሮንቶስ ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ቀደም ሲል የኃጢአት ድርጊቶችን የመፈጸም ልማድ ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴሰኞች፣ አመንዝሮች፣ ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ፣ ሌቦች፣ ገንዘብን የሚመኙና ሰካሮች’ እንደነበሩ ሆኖም ‘ታጥበው እንደነጹ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9-11) ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ትክክለኛ እውቀት መቅሰማቸው፣ ከክርስቲያኖች ጋር መገናኘታቸውና መሰብሰባቸው እንዲሁም የአምላክን መንፈስ ማግኘታቸው መጥፎ ድርጊቶቻቸውን እንዲተዉ ብርታት ሰጥቷቸዋል። በመጨረሻም አምላክ በክርስቶስ ስም ጸድቃችኋል ሊላቸው ችሏል። በእርግጥም አምላክ ንጹሕ ሕሊና በመስጠት ምሕረት አሳይቷቸዋል።​—⁠ሥራ 2:​38፤ 3:​19

ጳውሎስም ሆነ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የኃጢአት ዝንባሌያቸውን አቅልለው አልተመለከቱትም። ከዚህ ይልቅ አጥብቀው በመዋጋት በይሖዋ እርዳታ ድል አድርገውታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚህ የይሖዋ አምላኪዎች ከራሳቸው የኃጢአት ዝንባሌ በተጨማሪ በዙሪያቸው ያለው ዓለም መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድርባቸው የነበረ ቢሆንም የሚያስመሰግን ሥነ ምግባር ነበራቸው። እኛስ?

አምላክ ድክመቶቻችንን እንድንዋጋ ይጠብቅብናል

እርግጥ ድክመታችንን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችል ይሆናል። ያለብን አለፍጽምና እንዲያሸንፈን መፍቀድ ባይኖርብንም እንኳ ከናካቴው ልናጠፋው እንደማንችል የታወቀ ነው። አለፍጽምና በቀላሉ ማስወገድ የማንችላቸው ድክመቶች ሊያመጣብን ይችላል። ሆኖም ለድክመቶቻችን እጅ መስጠት የለብንም። (መዝሙር 119:​11) ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ምክንያቱም አምላክ ለምንፈጽማቸው መጥፎ ድርጊቶች ሁሉ አለፍጽምናን ማሳበቢያ እያደረግን እንድናቀርብ ስለማይፈቅድ ነው። (ይሁዳ 4) ይሖዋ ሰዎች ጥሩ ሥነ ምግባር በመከተል ራሳቸውን በሚገባ እንዲያነጹ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት” ይላል። (ሮሜ 12:​9) አምላክ እንዲህ ዓይነት ጥብቅ አቋም የያዘው ለምንድን ነው?

አንደኛው ምክንያት ላለብን ድክመት እጅ መስጠታችን ጉዳት ያለው በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 6:​7 ላይ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” ይላል። ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን በሱስ ያስጠመዱ፣ ስግብግብና ሴሰኛ የሆኑ ሰዎች የኋላ ኋላ አሳዛኝ ውጤት ማጨዳቸው አይቀርም። ነገር ግን ከፍ ያለ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ምክንያት አለ።

ኃጢአት አምላክን ያስቆጣዋል እንዲሁም በእኛና በይሖዋ መካከል ‘መለያየት’ ይፈጥራል። (ኢሳይያስ 59:​2) ኃጢአትን የሚያደርጉ ሰዎች ሞገሱን ማግኘት ስለማይችሉ “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ . . . ክፉ ማድረግን ተዉ” በማለት አጥብቆ ያሳስባቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 1:​16

ፈጣሪያችን አፍቃሪና መሐሪ ነው። ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ (2 ጴጥሮስ 3:​9) ሁልጊዜ ለድክመቶቻችን የምንሸነፍ ከሆነ የአምላክን ሞገስ እንዳናገኝ እንቅፋት ይሆንብናል። አምላክ ድክመቶቻችንን ችላ እንደማይል ሁሉ እኛም ችላ ማለት አይኖርብንም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ኢየሱስ “መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” ብሏል።