በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እሳት የሚሰጠው ጥቅምና የሚያስከትለው ጉዳት

እሳት የሚሰጠው ጥቅምና የሚያስከትለው ጉዳት

እሳት የሚሰጠው ጥቅምና የሚያስከትለው ጉዳት

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደ ጻፈው

እሳት ወዳጅም ጠላትም ሊሆን ይችላል። አንድን መሬት ለመመንጠር ወይም ለማጥፋት ሊያገለግል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል።

እሳት ምን ያህል ከባድ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በ1997 በኢንዶኔዥያ የደረሰውን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚያ ዓመት የተነሳው ሰደድ እሳት ሰፊ ክልል በማዳረስ በአገሪቷ ላይ፣ በሕዝቡ ጤናና በኢኮኖሚ ላይ ይህ ነው የማይባል ጉዳት አስከትሏል። እሳቱ ያስነሳው ጭስ አጎራባች ወደሆኑ ስምንት አገሮች ተዛምቶ 75 ሚልዮን በሚያህሉ ሰዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል። ሃያ ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች ከአስም፣ ከሳንባ፣ ከልብና ከደም ሥር ጋር በተያያዘ እንዲሁም በዓይናቸውና በቆዳቸው ላይ በተከሰተ ችግር ወደ ሕክምና ለመሄድ እንደተገደዱ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።

በሲንጋፖር ብክለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከተማዋ በጭስ ተሸፍናለች። አንዲት የከተማዋ ነዋሪ ንጹሕ አየር ከሚያገኙበት ቤት ለመውጣት እንደሚፈሩ ሲገልጹ “ቤታችን ውስጥ እሥረኞች ሆነን ተቀምጠናል” በማለት በምሬት ተናግረዋል። አንዳንድ ቀን ሰማዩ በጭጋግ ስለሚሸፈን ነዋሪዎቹ ፀሐይዋን ማየት አይችሉም።

በቀጣዩ ዓመት በ1998 በብሪታንያ፣ በኮሎምቢያና በካናዳ የሚኖሩ 8, 000 ነዋሪዎች እያስገመገመ ከሚመጣው ሰደድ እሳት ለማምለጥ መኖሪያቸውን ለቅቀው ለመሸሽ ተገድደው ነበር። በዚያ ዓመት በካናዳ ከተነሱት አንድ ሺህ ከሚጠጉ ሰደድ እሳቶች መካከል ይህ እሳት አንደኛው ብቻ ሲሆን 115 የሚሆኑት ከቁጥጥር ውጭ እንደነበሩ ተነግሮላቸዋል። በካናዳ፣ በሰሜን አልበርታ የተነሳ አንድ እሳት 35, 000 ሄክታር የሚሸፍን ጫካ አውድሟል። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ አንድ ሰው “ከአናታችን እንደ ደመና የሸፈነንን ጥቁር ጭስ ስንመለከት የኑክሌር ቦምብ የፈነዳ ነበር የመሰለን” በማለት ተናግረዋል።

እሳት ያለው አሉታዊ ገጽታ

እሳት አንዱ የተፈጥሮ ኃይል ነው። በድንገት የተነሳ ሰደድ እሳት የአንድን መሬት ገጽ ሊያጠፋ፣ በተክሎች መካከል ያለውን የተፈጥሮ ሚዛን ሊያዛባ፣ የዱር አራዊትን አኗኗር ሊቀይርና በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ከባድ እሳት የመሬት መሸርሸር ሊያስከትል ይችላል። የተራቆተ መሬት የበጋውን ፀሐይ ተከትሎ ለሚመጣ ከባድ ዝናብ ከተጋለጠ አፈሩ ተጠርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም በእጽዋት ዝርያዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ የእጽዋት ዝርያዎች ሁኔታውን ተቋቁመው መኖር ቢችሉም ሌሎች ደካማ ተክሎች ግን ይሞታሉ። ይህ አጋጣሚ ለአረሞች ጥሩ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ በአገር በቀሎቹ እጽዋት ምትክ አካባቢውን ሊሞሉት ይችላሉ።

ይህም አገር በቀሎቹን እጽዋት በሚመገቡ እንስሳት ላይ አደጋ እንዲጋረጥባቸው ያደርጋል። ኮዋላ እና ብሩሽ ቴይልድ በአውስትራሊያ ብቻ የሚገኙ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ ብርቅዬ እንስሳት ሲሆኑ መኖሪያቸው በከባድ እሳት ከወደመ ዝርያቸው ሙሉ በሙሉ በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል። ባለፉት 200 ዓመታት የአውስትራሊያ አሕጉር 75 በመቶ ደኗን፣ ደኑ የሚሸፍነውን 66 በመቶ አካባቢ፣ 19 ዓይነት የእንስሳት ዝርያዎችንና በሌላ በየትም ቦታ የማይገኙ 68 ዓይነት አገር በቀል ተክሎችን አጥታለች።

ከተሞች እየተስፋፉ አቅራቢያቸው ወደሚገኙት ገጠራማ አካባቢዎች እየተጠጉ ሲሄዱ ሰዎች ለሰደድ እሳት ይበልጥ እየተጋለጡ ይሄዳሉ። ታኅሣሥ 1997 ከ250, 000 ሄክታር የሚበልጥ አካባቢ በእሳት ሲወድም፤ በሲድኒ፣ አውስትራሊያና በብሉ ማውንቴን አካባቢ የሚኖሩ በርካታ መንደሮች ከመቶ ጊዜ በላይ በእሳት ተቃጥለዋል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያህሉትን መቆጣጠር አልተቻለም ነበር። የእሳት መከላከያ ኮሚሽነር ባለፈው 30 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ሰደድ እሳት አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል። በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ለመሄድ የተገደዱ ሲሆን የአንዳንዶቹም በእሳቱ ጋይተዋል። ሁለት ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከታኅሣሥ 2001 አጋማሽ አንስቶ ወንጀለኞች ለኩሰዋቸዋል ተብለው የሚገመቱ ሰደድ እሳቶች 753, 000 ሄክታር መሬት አውድመዋል።

የእሳት አደጋ በሚጋረጥበት ጊዜ

የእሳት አደጋዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው የተፈጥሮ ምክንያት ኤል ኒኞ የተባለውና በየጊዜው በመላው ዓለም ደረቅና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንዲስፋፋ የሚያደርገው ክስተት ነው። በጣም ሞቃት ለሆነው የኤል ኒኞ ክስተት የሚጋለጥ ማንኛውም አገር ለእሳት ቃጠሎ መነሳት የሚያመቹ ሁኔታዎች ይኖሩታል።

አብዛኛውን ጊዜ ለሰደድ እሳት መነሳት ምክንያት የሚሆነው የሰዎች ግድየለሽ እንቅስቃሴ ነው። ሆን ብሎ ሰደድ እሳት ማቀጣጠል በብዙ አገሮች ወንጀል ነው። በአውስትራሊያ፣ በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት በመንግሥት ደኖች ላይ ከተነሱት ሰደድ እሳቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት የተቀጣጠሉት በድንገት ወይም ሆን ብለው እሳት በለኮሱ ወንጀለኞች እንደሆነ ይገመታል።

ከባድ ቃጠሎ ሊያስነሳ የሚችል ሌላ ምክንያት ደግሞ የአካባቢ መራቆት ነው። በዛፍ ቆረጣና በደን መጨፍጨፍ ምክንያት ብዙ ደኖች ለሰደድ እሳት መቀጣጠል የተመቻቹ ሆነዋል። ዛፎች በሚቆረጡበት ጊዜ እሳት በቀላሉ እንዲቀጣጠል የሚያደርጉ ደረቅ ጭራሮዎችና የእንጨት ስብርባሪዎች ይበዛሉ። በተጨማሪም ትላልቅ ዛፎች ሲቆረጡ ለመሬቱ እንደጥላ ሆኖ ያገለግል የነበረው ቅጠል ስለሚወገድ የፀሐይ ጨረር በቀጥታ ወርዶ መሬት ላይ ያሉትን ጭራሮዎችና የእንጨት ስብርባሪዎች ያደርቃል። እነዚህ የደረቁ እንጨቶች በቀላሉ ሊቀጣጠሉ ስለሚችሉ አንዲት የእሳት ፍንጣሪ ካገኙ በቀላሉ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ እሳት ሊፈጥሩ ይችላሉ።

በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ለሰደድ እሳት መስፋፋት መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ። በኢንዶኔዥያ ለእርሻ የሚያገለግል መሬት ለማስፋፋት ለብዙ መቶ ዓመታት ደኖች ሲመነጠሩና ሲቃጠሉ ኖረዋል። በተፈጥሮ ሚዛን ላይ ግን ብዙም መዛባት አላስከተለም ነበር። ገበሬዎች እሳቱን በጥንቃቄና በተወሰነ መጠን ቢጠቀሙ ከተፈጥሮ እሳት የከፋ ውጤት አያስከትልም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባሕላዊው ምንጣሮና ቃጠሎ በመጠን ጨምሮ ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኗል። እንደ ዘንባባ ዘይት ያሉት የደን ውጤቶች ተፈላጊነት በመላው ዓለም እየጨመረ በመሄዱ ብዙ ደኖች ተመንጥረው ብዙ ትርፍ የሚያስገኙ ተክሎች ተተክለውባቸዋል። ደኖቹን ለመመንጠር ደግሞ የተፈጥሮ እጽዋትን ከማቃጠል የቀለለና የረከሰ ዘዴ አይገኝም። በዚህ መንገድ ሰዎች በቂ ስፋት ያለው ደን መኖሩ ለሚያስገኘው የረዥም ጊዜ ጥቅም ደንታቢስ በመሆን በሺህ ሄክታር የሚቆጠር ደን አውድመዋል።

እሳት ያለው ጠቃሚ ገጽታ

እሳት አውዳሚና አጥፊ ሊሆን ቢችልም ለብዙ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክት ይችላል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

ከሰው ልጅ የጥንት ወዳጆች አንዱ አሳት ነው። የሰው ልጅ እሳትን ሙቀትና ብርሃን ለማግኘት እንዲሁም ምግቡን ለማብሰል ሲገለገልበት ኖሯል። የአውስትራሊያ የጥንት ሠፋሪዎች ለበርካታ ምዕተ ዓመታት እሳትን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ማከናወኛ አድርገው ሲገለገሉበት ኖረዋል። ያኝዩዋ የተባለው ጎሣ አባላት ለእሳት የሚሰጠው ቦታ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ የእሳት ዓይነቶችንና የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች ለይተው የሚያመለክቱባቸው ከደርዘን የሚበልጡ ቃላት አሏቸው። ለምሳሌ ያህል ሰደድ እሳትን ወይም በቁጥቋጦዎች ላይ የሚደርስን ቃጠሎ ለማመልከት ካምባምባራ በሚል ቃል ይጠቀማሉ። በደንብ ተቃጥሎ ለአደን ምቹ የሆነን መሬት ለማመልከት ወርማን በሚል ቃል ይጠቀማሉ። ወደላይ እየተምዘገዘገ የሚወጣ ጥቅጥቅ ያለ ጭስ ሩማሪ ይባላል።

እነዚህ የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ሕዝቦች የሚኖሩበትን መሬት የሚቆጣጠሩት ጭራሮ መማገድ በተባለ የግብርና ዘዴ ነበር። ለሰደድ እሳት መነሳት ምክንያት የሚሆነውን የደረቅ ጭራሮዎችና ጉቶዎች ክምችት ለመቀነስ አነስተኛ መጠን ባለው እሳት ይጠቀማሉ። ይህ ዓይነቱ ተገቢ ቁጥጥር የተደረገበት የእሳት አጠቃቀም አቦርጅኖች የእጽዋትንና የእንስሳትን ሚዛን ሳያዛቡና መሬታቸውን ሳያራቁቱ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም አደገኛ በሆነ ሰደድ እሳት የሰዎች ሕይወት እንዳይጠፋ ተከላክሏል።

ቁጥጥር የተደረገበት የደን ቃጠሎ

ከሁለት መቶ ዓመት ብዙም ከማይበልጥ ዘመን በፊት አውሮፓውያን ሰፋሪዎች ወደ አውስትራሊያ በመጡ ጊዜ ለብዙ ዘመናት ተጠብቆ የኖረው የሰው፣ የተፈጥሮና የእሳት ሚዛን መዛባት ጀመረ። በአውሮፓውያኑ አመለካከት እሳት ሁልጊዜ ተዳፍኖ መኖር ያለበት ነገር ነበር። ቃጠሎ እንዳይደርስ ብዙ ቁጥጥር ይደረግ ስለነበረ ብዙ ደረቅ ጭራሮና የእንጨት ስብርባሪ ተከማቸ። በዚህም ምክንያት በጣም ከባድ የሆነና ለመቆጣጠር የሚያስቸግር ሰደድ እሳት መፈጠር ጀመረ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግሥታት የአውስትራሊያ የጥንት ተወላጆች ይከተሉ ከነበረው ልማድ ትምህርት ስላገኙ ሆን ተብሎ የሚደረግ የደን ቃጠሎ ማካሄድ ጀምረዋል። በዚህ ዘዴ ቁጥጥር የተደረገበት ቃጠሎ በየጊዜው ስለሚካሄድ አደገኛ የሆነ ከባድ ቃጠሎ እንዳይነሣ መከላከል ተችሏል። ሰደድ እሳት ከሚነሳበት ወቅት በፊት መጠነኛ የሆነ ቃጠሎ እንዲካሄድ ይደረጋል። እነዚህ ቃጠሎዎች ብዙ ፍጥነት የሌላቸውና አነስተኛ መጠን ያላቸው ስለሆኑ ትላልቆቹን ዛፎች ሳይጎዱ ከታች ያሉትን ጭራሮዎች ይመነጥራሉ። አብዛኛውን ጊዜም የማለዳ ጤዛ ያጠፋቸዋል።

ሆን ተብሎ በሚቀጣጠል እሳት አማካኝነት ሰደድ እሳት እንዳይነሳ ጥረት የሚደረግበት ዓላማ የአገር በቀል እጽዋትና እንስሳት ሕልውና ሳይነካ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ መከላከል ነው። በተጨማሪም ሆን ተብሎ የሚደረገው ቃጠሎ አንዳንድ መጤ አረሞች እንዳይዛመቱ ይከላከላል። ከዚህም በላይ ለነባር እንስሳት ሕልውና አስፈላጊ የሆነው የአካባቢ ብዝሐ ሕይወት ተጠብቆ እንዲኖር ይረዳል።

አንዳንድ የእጽዋት ዝርያዎች ዘሮቻቸው መብቀል የሚጀምሩት እሳት ሲያገኙ ብቻ ይመስላል። አንዳንድ ዘሮች ጠንካራ ሽፋን ስላላቸው እርጥበት እንዲገባባቸው ይህ ውጪያዊ ሽፋን በእሳት መከፈት ይኖርበታል። በተጨማሪም ከቃጠሎ የሚወጣው ጭስ ዘሮች እንዲበቅሉ እንደሚረዳ ጥናቶች ያመለክታሉ። በጭስ ውስጥ ዘሮች እንዲበቅሉ ያደርጋሉ ተብለው የሚታሰቡ 70 ዓይነት ቅመሞች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ ነው።

ከቃጠሎ በኋላ መሬቱ እንደ ናይትሮጅንና ፎስፈረስ ባሉ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ለም አፈር ይሆናል። እሳቱ በርጋፊ ቅጠሎች ውስጥ የተከማቸው አልሚ ንጥረ ምግብ ከአፈር ጋር እንዲዋሃድ ከማድረጉም በላይ ፀሐይ ወደ መሬት ዘልቆ እንዲገባ ስለሚያስችል ለአዳዲስ እጽዋት የሚያቆጠቁጡበት ምቹ መደብ ይፈጥራል። ለምሳሌ እንደ ግራር ያሉት ዛፎች ዘር ከቃጠሎ በኋላ የሚያፈሩ ሲሆን ከቃጠሎ በኋላ የሚኖረው ሁኔታ በጣም ምቹ የሆነ አካባቢ ይፈጥርላቸዋል።

ከቃጠሎ በኋላ የሚኖረው ሁኔታ ለእንስሳትም በጣም አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። በተለይ አዲስ የሚያቆጠቁጡት እጽዋት በጣም ለስላሳና እርጥበት ያዘሉ ይሆኑላቸዋል። አንዳንድ የካንጋሩ ዘሮች ተደጋግሞ የተቃጠለ ደን በጣም እንደሚወዱና ደን ካልተቃጠለ መኖር እንደማይችሉ ይነገራል። ምክንያቱም ለምግብነትና ለመጠለያነት የሚያስፈልጓቸው እጽዋት እሳት ካላገኙ መብቀልና ማደግ የማይችሉ ናቸው።

አሁንም ገና ያላወቅናቸው ብዙ ነገሮች አሉ

ስለ ሁለቱ የእሳት ገጽታዎች ያለን ግንዛቤ እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጂ እሳት ከአካባቢያችን ጋር ያለው መስተጋብር በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ገና ያላወቅናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በአንዳንድ የተለዩ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ላይ እሳት ምን ዓይነት ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ገና መጠናት ያለበት ነገር ነው። በተጨማሪም እሳት ከሥነ ምህዳራችን ጋር ያለው መስተጋብር ብዙ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ነው። መልስ ማግኘት ከሚገባቸው ጥያቄዎች አንዳንዶቹ ‘ቃጠሎ የከባቢ አየር ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋልን? ከቃጠሎዎች የሚወጣው ጭስ በአየር ንብረት መለዋወጥ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል? የቃጠሎዎች ባሕርይ ምንድን ነው? የሚሉት ናቸው።

ባሁኑ ጊዜ የሰደድ እሳቶችን ባሕርይ ለመተንበይ የሚረዱ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ፕሮግራሞች የማገዶውን ብዛት፣ የአካባቢውን ሙቀት፣ የነፋሱን ፍጥነትና የአየሩን ሁኔታ በማስላት የሰደድ እሳቶችን ባሕርይና አካሄድ ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ባሁኑ ጊዜ እነዚህ ፕሮግራሞች ሁልጊዜ ትክክለኛውን ሁኔታ መጠቆም ካለመቻላቸውም በላይ ድንገት ስለሚነሱ እሳቶችና ስለመሳሰሉት ያልተለመዱ ክስተቶች ሊተነብዩ አይችሉም። በ1997 በሲድኒ ልምድ ያካበቱ ሁለት የእሳት አደጋ ተከላካዮች “የሞት ጣቶች” የሚል ስያሜ በተሰጣቸው የእሳት ወላፈኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በተለይ በጣም ትላልቅ ሰደድ እሳቶች የራሳቸው የሆነ ኃይለኛ ነፋስ፣ ደመናና ውሽንፍር ጭምር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል መተንበይ ያስቸግራል። ነፋሶቻቸው በድንገት አቅጣጫቸውን ወይም ፍጥነታቸውን ሊለውጡ ስለሚችሉ የሰደድ እሳቱን ሁኔታ መተንበይ አስቸጋሪ ይሆናል። ተመራማሪዎች እነዚህን ሁኔታዎች እንዲሁም እንደ መሬት አቀማመጥና የማገዶ ስርጭት የመሰሉትን ተጨማሪ መረጃዎች በማካተት የተሻለ ፕሮግራም ለማዘጋጀት እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ።

በዚህ ዓላማ ላይ ያተኮረ አንድ ፕሮጀክት ናሽናል ሴንተር ፎር አትሞስፈሪክ ሪሰርች በተባለ ድርጅት በኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በመካሄድ ላይ ነው። ይህ ድርጅት ሲ-130 በተባለ የመጓጓዣ አይሮፕላን ላይ በጣም የተራቀቁ ሳይንሳዊ መሣሪያዎችንና ሰባት ኮምፒውተሮችን እሳት በማይደፍረው ሽፋን ውስጥ ገጥሟል። አይሮፕላኑ በሚንቀለቀል እሳት ላይ እየበረረ በክንፎቹ ላይ በተገጠሙለት መሣሪያዎች አማካኝነት መረጃዎች ይሰበስባል። ከዚያ በኋላ መረጃዎቹ እንዲተነተኑ ወደ ኮምፒውተሮቹ ይላካሉ። በተጨማሪም ተርማካም የተባለ በኢንፍራሬድ ጨረር የሚሠራ ካሜራ ስላለው የእያንዳንዱን የእሳት ክፍል የግለት መጠን ያመለክታል። በዚህ መንገድ የኤን ሲ ኤ አር ሳይንቲስቶች ባሁኑ ጊዜ ያሉትን የሰደድ እሳት ባሕርይ መተንበያ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች እንዴት እንደሚያሻሽሉ እየተማሩ ነው።

እነዚህ የተሻሻሉ ፕሮግራሞች ሊቃውንቱን የተሻለ የእሳት ቃጠሎ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። በተጨማሪም የሰደድ እሳትን ባሕርይ በትክክል መተንበይ መቻል የእሳት አደጋ ተከላካዮች ማኅበረሰቡን ከአደጋ ለማዳን በሚጥሩበት ጊዜ የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ ያስችላል።

አዎን፣ እሳት ከቁጥጥር ውጭ በሚሆንበት ጊዜ አጥፊና አውዳሚ ጠላት ሊሆን ቢችልም ጥሩ ወዳጅ የሚሆንበትም ጊዜ አለ። ፈጣሪያችን ምድርን ለማለምለምና የእንስሳትና የእጽዋት ሚዛን ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ባቋቋመው የተፈጥሮ ኡደት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚና ይጫወታል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተደናገጠች ኤልክ በሞንታና በሚገኘው የቢተርሩት ወንዝ ሸለቆ ውስጥ ከተቀጣጠለው ሰደድ እሳት ስትሸሽ

[ምንጭ]

John McColgan, BLM, Alaska Fire Service

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአውስትራሊያ ቁጥጥር ተደርጎበት እንዲቀጣጠል የተደረገ እሳት

[ምንጭ]

Photo provided courtesy of Queensland Rural Fire Service