በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እኩዮች የሚያሳድሩብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

እኩዮች የሚያሳድሩብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

እኩዮች የሚያሳድሩብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“በየትኛውም ቦታ የእኩዮች ተጽዕኖ ያጋጥማል።”​—⁠እሴይ የተባለ የ16 ዓመት ወጣት

“በወጣትነት ዕድሜዬ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑብኝ ነገሮች አንዱ አብረውኝ የሚማሩት ልጆች የሚያሳድሩብኝን ተጽዕኖ ተቋቁሜ መኖር ነበር።”​—⁠ዮናታን የተባለ የ21 ዓመት ወጣት

እኩዮች ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ግን ልትቋቋመው እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። እንዲያውም እኩዮች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልታሸንፍና ከዚያም አልፎ ጥቅም ልታገኝበት ትችላለህ። እንዴት?

በዚህ አምድ ሥር ከዚህ በፊት በወጣው ርዕስ ላይ እኩዮች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዳ አንዱን ጠቃሚ የሆነ የመጀመሪያ እርምጃ ተመልክተን ነበር፤ ይህም እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ኃይል እንዳለውና በአንተም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አምኖ መቀበል ነው። * ከዚህ በተጨማሪ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ? የአምላክ ቃል ጠቃሚ የሆነ መመሪያ ይሰጥሃል። ምሳሌ 24:​5 ‘አዋቂ ሰው ኃይሉን ያበዛል’ ይላል። እኩዮችህ የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ለማግኘት የሚረዳህ ምን ዓይነት እውቀት ነው? ወደዚህ ጥያቄ መልስ ከመሄዳችን በፊት በእኩዮች ተጽዕኖ እንድትሸነፍ የሚያደርገውን አንዱን ችግር እንመልከት።

በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት አደገኛ ነው

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣቶች ስለ እምነታቸው ለሌሎች የመናገር ኃላፊነት ስላለባቸው ከሌሎች ወጣቶች ለየት ባለ መንገድ ከእኩዮቻቸው ተጽዕኖ ያጋጥማቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) አንዳንድ ጊዜ፣ ለምታገኛቸው ወጣቶች ስለ እምነትህ መናገር ያስፈራሃል? ከሆነ እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። የ18 ዓመቷ ሜላኒ እንዲህ ብላለች:- “የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩ አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መናገር ካሰብኩት በላይ ከባድ ነበር። እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ልነግራቸው አስብና እንደገና ፈርቼ እተወዋለሁ።” እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ስለ እምነትዋ እንዳትናገር እንቅፋት ሆኖባት ነበር።

ታማኝ የነበሩ ወንዶችና ሴቶች እንኳን ስለ አምላክ ለመናገር እንዳመነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ወጣቱ ኤርምያስ አምላክ እንዲናገር ያዘዘውን መልእክት ቢናገር ፌዝና ስደት እንደሚደርስበት ያውቅ ነበር። ከዚህም በላይ ኤርምያስ ሥራውን ለማከናወን ስለመቻሉ እርግጠኛ አልነበረም። ለምን? “እነሆ፣ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም” ብሎ ነበር። አምላክ ኤርምያስ ልጅ በመሆኑ ምክንያት መናገር እንደማይችል ተሰምቶት ነበር? በፍጹም። ይሖዋ ነቢዩን “ብላቴና ነኝ አትበል” በማለት አበረታቶታል። ከዚያም ይሖዋ እያመነታ ለነበረው ወጣት አንድ አስፈላጊ ሥራ ሰጠው።​​—⁠⁠ኤርምያስ 1:​6, 7

በራስ መተማመን ጎድሎን አንድን ሥራ ማከናወን እንደማንችል ሆኖ ከተሰማን እኩዮች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መቋቋም በጣም ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ጥናቶችም ይህንን አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል በ1937 ሙዛፈር ሸሪፍ የተባሉ ሳይንቲስት አንድ ሙከራ አካሂደው ነበር። በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች እንዲቀመጡ ካደረጉ በኋላ አንድ የብርሃን ጨረር አሳዩአቸው፤ ከዚያም ጨረሩ ከነበረበት ቦታ ምን ያህል እንደተንቀሳቀሰ ጠየቋቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ የብርሃኑ ጨረር እየተንቀሳቀሰ እንዳለ እንዲመስላቸው ተደረገ እንጂ ወዴትም አልተንቀሳቀሰም። ሰዎቹ ለየብቻ ሲጠየቁ የየራሳቸውን የተለያየ ግምት ይሰጡ ነበር። ሆኖም በቡድን ሆነው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መልሳቸውን እንዲናገሩ ተጠየቁ። ውጤቱ ምን ሆነ? አንዳቸው የሌላውን መልስ ሲሰሙ የራሳቸውን መልስ መጠራጠር ጀመሩ። ሙከራው ሲደጋገም መልሶቻቸው ይበልጥ እየተቀራረቡ ሄዱና በመጨረሻም “ብዙሃኑ” የተስማሙበት አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ከዚያ በኋላ እንደገና ለየብቻቸው ቢጠየቁም ቀደም ሲል በቡድን እያሉ የሰጡትን መልስ ይመልሱ ነበር።

ይህ ሙከራ አንድ ጠቃሚ ነጥብ ያስተላልፋል። በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት እኩዮች ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ በቀላሉ ያጋልጣል። ይህ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ አይደለም? እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ሰዎች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ስለመፈጸም ወይም አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ስለመውሰድ ያላቸውን አመለካከትና ሌላው ቀርቶ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያወጧቸውን ግቦች እንኳን ሳይቀር ሊነካ ይችላል። በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የ“ብዙሃኑን” አመለካከት ብንከተል የወደፊት ሕይወታችንን አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። (ዘጸአት 23:​2) ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?

ቀደም ሲል በተገለጸው ሙከራ ላይ ብርሃኑ እንደማይንቀሳቀስ አውቀህ ቢሆን ኖሮ ለጥያቄው ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር? ምናልባት የሌሎቹ መልስ ተጽዕኖ አያሳድርብህ ይሆናል። አዎን፣ በራሳችን የመተማመን መንፈስ ማዳበር ያስፈልገናል። ሆኖም በራስ መተማመን ሲባል ምን ማለት ነው? እንዴትስ ልናዳብረው እንችላለን?

በይሖዋ ተማመን

በራስ የመተማመንን መንፈስ ስለማዳበር ብዙ ሲባል ሰምተህ ይሆናል። ይህንን ባሕርይ እንዴት ማዳበር እንደሚቻልና ምን ያህል በራስ የመተማመን መንፈስ ሊኖርህ እንደሚገባ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ግን እርስ በርስ የሚጋጩ የተለያዩ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ሚዛናዊ የሆነ ምክር ይዟል:- “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ . . . እናገራለሁ።” (ሮሜ 12:​3) ይህንኑ ጥቅስ አንድ ሌላ ትርጉም እንዲህ ብሎታል:- “ማንም ስለ ራሱ ዋጋማነት በልክ እንዲያስብ እንጂ የተጋነነ አመለካከት እንዳይኖረው እላለሁ።”​​—⁠ቻርለስ ቢ ዊልያምስ

ስለ ራስህ “ዋጋማነት” “በልክ” ማሰብ ግብዝ፣ ትምክህተኛ ወይም ትዕቢተኛ ከመሆን እንድትቆጠብ ይረዳሃል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚህ ያለው ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት ለማሰብ፣ በምክንያት ለማስረዳትና ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ለማድረግ ባለህ እውነተኛ ችሎታ የመተማመን መንፈስ እንድታዳብር ያስችልሃል። ፈጣሪህ ድንቅ የሆነ “የማመዛዘን ችሎታ” ሰጥቶሃል። (ሮሜ 12:​1 NW ) ይህንን በአእምሮህ መያዝህ ሌሎች ለአንተ ውሳኔ እንዲያደርጉልህ የሚደረግብህን ግፊት እንድትቋቋም ይረዳሃል። ይሁን እንጂ እኩዮች የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ በመቋቋም ረገድ ከዚህ የበለጠ እርዳታ ማግኘት የምትችልበት ሌላም መንገድ አለ።

ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት “አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 71:​5) አዎን፣ ዳዊት ከወጣትነቱ ጀምሮ በሰማያዊ አባቱ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመን ነበር። ጎልያድ የተባለ ግዙፍ ፍልስጤማዊ አንድ እስራኤላዊ ወታደር ወጥቶ እንዲገጥመው በጠየቀ ጊዜ ዳዊት “ገና ብላቴና” ምናልባትም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ወጣት ነበር። የእስራኤል ወታደሮች በጣም ፈሩ። (1 ሳሙኤል 17:​11, 33) በመካከላቸው ወኔ የሚሰልብ ወሬ ተዛምቶ ሊሆን ይችላል። ስለ ጎልያድ ግዙፍነትና ወታደራዊ ችሎታ እያነሱ ያበደ ካልሆነ በስተቀር ከእርሱ ጋር ለመፋለም የሚደፍር ሰው ሊኖር እንደማይችል አሉታዊ በሆነ መንገድ እርስ በርስ ተነጋግረው ሊሆን ይችላል። ዳዊት እንደዚህ ላለው ተጽዕኖ አልተንበረከከም። ለምን ይሆን?

ዳዊት ለጎልያድ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ልብ በል:- “አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።” (1 ሳሙኤል 17:​45) ዳዊት፣ ጎልያድ ግዙፍና ጠንካራ መሆኑን አያውቅም ወይም የታጠቀውን የጦር መሣሪያ ማየት ተስኖት ነበር ማለት አይደለም። ሆኖም በእርግጠኝነት የሚያውቀው አንድ ነገር ነበር። ከይሖዋ አምላክ ጋር ሲወዳደር ጎልያድ ከቁጥር የማይገባ መሆኑን ያውቅ ነበር። ይሖዋ ከእሱ ጋር ከሆነ ጎልያድን የሚፈራበት ምን ምክንያት አለው? ዳዊት እንዲህ ያለውን ትምክህት በአምላክ ላይ ማሳደሩ ልበ ሙሉ እንዲሆን ረድቶታል። እኩዮቹ ምንም ያህል ተጽዕኖ ቢያሳድሩበት ፈጽሞ ወደኋላ እንዲል ሊያደርጉት አልቻሉም።

አንተስ በይሖዋ ላይ እንደዚህ ዓይነት ትምክህት አለህ? ይሖዋ አሁንም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:​6፤ ያዕቆብ 1:​17) ስለ ይሖዋ ይበልጥ እየተማርክ በሄድክ መጠን በቃሉ አማካኝነት የሚነግርህ ሁሉ ትክክል ስለመሆኑ ይበልጥ እርግጠኛ እየሆንክ ትሄዳለህ። (ዮሐንስ 17:​17) በቃሉ ውስጥ ሕይወትህን ለመምራት የሚያስችሉህና እኩዮችህ የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚረዱህ የማይለዋወጡና ትምክህት ሊጣልባቸው የሚችሉ መመሪያዎች ታገኛለህ። ይሖዋን መታመኛህ ከማድረግም በተጨማሪ ልታደርገው የሚገባህ ሌላም ነገር አለ።

ጥሩ መካሪዎች ይኑሩህ

የአምላክ ቃል ጥሩ መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ምሳሌ 1:​5 “አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል” ይላል። ወላጆችህ ስለ አንተ ደህንነት ከልባቸው የሚያስቡ በመሆናቸው ጥሩ መመሪያ ሊሰጡህ ይችላሉ። ይህንን በሚገባ የተገነዘበችው ኢንዲራ እንዲህ ትላለች:- “አሁን በእውነት መንገድ ልመላለስ የቻልኩት ወላጆቼ በቅዱሳን ጽሑፎች ተጠቅመው ዘወትር መመሪያ ስለሰጡኝና ይሖዋ በሕይወቴ ውስጥ እውን እንዲሆንልኝ ስላደረጉ ነው።” ብዙ ወጣቶችም እንደዚህ ይሰማቸዋል።

የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆንክ በጉባኤ ውስጥ የተሾሙትን የበላይ ተመልካቾች ማለትም ሽማግሌዎችንና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችን የማማከር ግሩም አጋጣሚ አለህ። ናድያ የተባለችው ወጣት እንዲህ ትላለች:- “በጉባኤዬ ውስጥ ያሉትን ሽማግሌዎች በጣም አደንቃቸዋለሁ። በአንድ ወቅት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ወጣቶችን በማስመልከት ያቀረበውን ንግግር አልረሳውም። በንግግሩ ውስጥ ያቀረበው ሐሳብ እኛ እያጋጠመን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ስለነበር ስብሰባው ሲያበቃ እኔና ጓደኛዬ በጣም ተደስተን ነበር።”

እኩዮች የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል ሌላው ኃይለኛ መሣሪያ በጎ የሆነ ተጽዕኖ ነው። ጓደኞችህን በጥበብ የምትመርጥ ከሆነ ጥሩ ግቦችንና ትክክለኛ መሥፈርቶችን ይዘህ እንድትቀጥል ሊረዱህ ይችላሉ። ጥሩ ጓደኞች መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? የሚከተለውን ምክር አስታውስ:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” (ምሳሌ 13:​20) ናድያ በትምህርት ቤት ጥሩ ጓደኞች በመምረጥ ረገድ ጠንቃቃ ነበረች፤ ጓደኞቿ እሷ የምትከተላቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚከተሉ የእምነት ባልንጀሮቿ ነበሩ። “ትምህርት ቤት ያሉት ወንዶች ልጆች ‘ሊያነጋግሩን’ ፈልገው ወደ እኛ ሲመጡ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር” ስትል ታስታውሳለች። ጥሩ ጓደኞች መልካም ባሕርያቶቻችንን የበለጠ እንድናጠናክራቸው ሊረዱን ይችላሉ። ጥሩ ጓደኞች ለማግኘት የሚደረገው ጥረት መልሶ የሚክስ ነው።

እንግዲያው በይሖዋ ከታመንህ፣ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች መመሪያ ለማግኘት ጥረት ካደረግህና ጓደኞችህን በጥበብ ከመረጥህ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ ማሸነፍ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። እንዲያውም በጓደኞችህ ላይ በጎ ተጽዕኖ ልታሳድርና በሕይወት መንገድ ላይ አብረውህ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ልትረዳቸው ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በታኅሣሥ 2002 ንቁ! ላይ የወጣውን “እኩዮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ያን ያህል ከባድ ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንደ አንተው አምላክንና እርሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች የሚወድዱ ጥሩ ጓደኞች ምረጥ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል”—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​33

“ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል”—⁠ምሳሌ 13:​20