በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መኪና ጥንትና ዛሬ

መኪና ጥንትና ዛሬ

መኪና ጥንትና ዛሬ

የሰው ልጅ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ጥሩ የመጓጓዣ መሣሪያ ለማግኘት ሲደክም ኖሯል። በመጀመሪያ ከቦታ ወደ ቦታ ለመጓጓዝ ይገለገል የነበረው በእንስሳት ነበር። ይሁን እንጂ ከእንስሳት የተሻለ መጓጓዣ ማግኘት አስፈላጊ እየሆነ መጣ። በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተውና በፈረስ ለሚጎተት ጋሪና ሠረገላ መፈልሰፍ መንገድ ጠራጊ የሆነው የተሽከርካሪ ጎማ መሠራት ነው። ይሁን እንጂ የ19ኛው መቶ ዘመን ግኝቶች የመጓጓዣ መሣሪያዎች ከዚያ በፊት ሊታሰብ እንኳን በማይችል መጠን እንዲሻሻሉ አድርገዋል።

የተሻሻሉ ሞተሮች

በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ኒኮላውስ ኦውገስት ኦቶ የሚባል ጀርመናዊ በአየር ግፊት የሚንቀሳቀስ ባለ አራት ኡደት ሞተር ሠራ። ከጊዜ በኋላም በእንፏሎትና በኤሌክትሪክ በሚንቀሳቀስ ሞተር ተተክቷል። ካርል ቤንዝ እና ጎትሊፕ ዳይምለር የተባሉ ጀርመናውያን ለአውሮፓ የአውቶሞቢል ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በ1885 ቤንዝ ባለ ሁለት ኡደት በሆነና በደቂቃ 250 ጊዜ ሊሽከረከር የሚችል ባለ አንድ ሲልንደር ሞተርና ባለ ሦስት ጎማ መኪና ሊያሽከረክር ችሏል። ዳይምለር ከ1872 ጀምሮ አንድ ቦታ ላይ የሚተከልና የማይንቀሳቀስ የጋዝ ሞተር ሲሠራ ቆይቶ ነበር። ከአሥር ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ከቪልኸልም ማይባኽ ጋር ሆኖ በቤንዚን ነዳጅነት የሚንቀሳቀስ ካርቡረተር የተገጠመለትና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ሞተር ሠራ።

ብዙም ሳይቆይ ዳይምለር እና ማይባኽ በደቂቃ 900 ሽክርክሪት የሚደርስ ፍጥነት ያለው ሞተር ሠሩ። በኋላም ሁለተኛ ሞተር ሠርተው ብስክሌት ላይ ከገጠሙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዳር 10 ቀን 1885 ሊነዱት ችለዋል። በ1926 የዳይምለር እና የቤንዝ ኩባንያዎች አንድ ሆኑና ምርታቸውን መርሴድስ-ቤንዝ በሚል ስም መሸጥ ጀመሩ። * የሚያስገርመው ግን እነዚህ ሁለት ሰዎች ዓይን ለዓይን ተያይተው የማያውቁ መሆናቸው ነው።

በ1890 ኤሚል ለቫሰር እና ረነ ፓንሃር የተባሉ ፈረንሳውያን በሻሲው መሐል ላይ ሞተር የተገጠመለት ባለ አራት ጎማ መኪና ሠሩ። በሚቀጥለው ዓመት መኪናው አስፋልት ባልተነጠፈለት መንገድ ላይ ሲሽከረከር አቧራና ጭቃ እንዳያስቸግረው ሞተሩ ከፊት እንዲገጠም አደረጉ።

መኪና ተራው ሰው እጅ እንዲገባ ማስቻል

የመጀመሪያዎቹ መኪናዎች በጣም ውድ ስለነበሩ አብዛኛው ሰው እጅ ሊገቡ አልቻሉም። ይሁን እንጂ ሄንሪ ፎርድ በ1908 ሞዴል ቲ የተባለውን መኪና በመገጣጠሚያ ፋብሪካ ማምረት ሲጀምር ይህ ሁኔታ ተለወጠ። ይህ መኪና በመኪና ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል። ርካሽ፣ ለብዙ ዓይነት አገልግሎት የሚውልና ለመጠገን የማያስቸግር ነበር። መጠነኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎች እንኳን ሊገዙ የሚችሉት መኪና ነበር። * ግሬት ካርስ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሰንቸሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “አሜሪካን፣ ብሎም መላውን ዓለም ባለ ተሽከርካሪ ሊያደርግ የቻለው ሞዴል ቲ ነው።”

መኪና ከተሠራ አንድ መቶ ዓመት ያህል የሞላው ቢሆንም መኪና አስፈላጊ ነገር እንጂ ቅንጦት አይደለም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ብዙ ናቸው። እንዲያውም ኢንድፐንደንት ዴይሊ በተባለው የለንደን ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳለው ከአንድ ኪሎ ሜትር ለማይበልጥ ርቀት እንኳን መኪናቸውን የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ።

የቴክኖሎጂ እድገት መኪናዎች ይበልጥ ፈጣኖች እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን የመኪና አደጋዎች እንዲቀንሱ አስችሏል። እንዲያውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበርካታ አገሮች በመኪና አደጋ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል። ብዙዎች መኪና በሚመርጡበት ጊዜ የሚመለከቱት ከመኪናው መልክ ይልቅ በቂ የአደጋ መከላከያዎች ያሉት መሆኑን ነው። ለምሳሌ መኪናዎች በቀላሉ የሚኮማተር የአካል ክፍል ያላቸው በመሆኑ ግጭት በሚደርስበት ጊዜ የግጭቱ ኃይል በአንዳንዶቹ የሻሲ ክፍሎች ይዋጥና በአሽከርካሪውና በተሳፋሪዎች አካባቢ ያለው አካል ብዙ ጉዳት ሳይደርስበት ይቀራል። በሚያንሸራትት መንገድ ላይ ፍሬን አልይዝም እንዳይል የሚከላከልና የኤሌክትሮኒክ ቁጥጥር የሚደረግለት መሣሪያ አለ። በሦስት ማዕዘናት ላይ የሚወጠሩ የአደጋ መከላከያ ቀበቶዎች በደረትና በሽንጥ አካባቢ አደጋ እንዳይደርስ ሲከላከሉ የአየር ከረጢቶች በግጭት ጊዜ ጭንቅላት ከመሪ ወይም ከመኪና ፊተኛ አካል ጋር እንዳይጋጭ ይጠብቃሉ። *

እርግጥ ነው፣ በጥንቃቄ መንዳትን የሚተካ ነገር ሊኖር አይችልም። በሜክሲኮ ከተማ የሚታተመው ኤል ኢኮኖሚስታ “አነዳዳችን ካልተስተካከለ ምንም ዓይነት የአደጋ መከላከያ መሣሪያ ቢሠራ በጣም የተራቀቀ ነው የሚባለው ቴክኖሎጂ እንኳን የተፈጥሮ ሕጎችን ብንጥስ ከሚደርስብን አደጋ ሊያድነን አይችልም” ብሏል።

አንዳንዶቹ የዘመናችን መኪናዎች ተሽከርካሪ ቤቶች ይመስላሉ። ብዙ መኪናዎች የሲዲ ማጫወቻ፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክና ለመኪናው የፊትና የኋላ ክፍል ለየብቻ የሙቀትና የድምፅ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ተገጥሞላቸዋል። በተጨማሪም አሽከርካሪዎች ካሰቡበት ቦታ ለመድረስ ይበልጥ አመቺው መንገድ የትኛው እንደሆነ የሚያሳይ በሳተላይት የሚታገዝ ጠቋሚ መሣሪያ የተገጠመላቸው መኪናዎች አሉ። አንዳንዶቹ መሣሪያዎች በመንገድ ላይ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮች መረጃ ያቀብላሉ። እርግጥ፣ የተራቀቁ ዘመን አመጣሽ መሣሪያ ያላቸውና በቅርብ የወጡ ሞዴሎችን መግዛት ለብዙዎች የኑሮ ደረጃ ማሳያ ሆኗል። የመኪና አምራቾችና አስተዋዋቂዎችም በዚህ የሰዎች ፍላጎት በሚገባ ተጠቅመዋል።

እንደተመለከትነው መኪና ከተሠራበት ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ብዙ እድገት አድርጓል። በጥንቃቄና በአግባቡ ከተጠቀምንበትም ለሥራም ሆነ ለመዝናኛ በጣም ጥሩ አገልግሎት የሚያበረክት መሣሪያ ሊሆን ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የዳይምለር ኩባንያ ዋነኛ ባለአክስዮን የነበረው አሚል የሊነክ አዲሱ መኪና በሴት ልጁ ስም መርሴድስ ተብሎ እንዲጠራ ሐሳብ አቀረበ። ይህን ያደረገው ዳይምለር የሚለው የጀርመንኛ ስም መኪናው በፈረንሳይ አገር ገበያ እንዳያገኝ እንቅፋት ይሆንበታል ብሎ ስለሰጋ ነበር።

^ አን.8 ሞዴል ቲ ገና እንደተሠራ ዋጋው 850 ዶላር ቢሆንም በ1924 አንድ አዲስ ፎርድ መኪና በ260 ዶላር መግዛት ይቻል ነበር። ሞዴል ቲ ለ19 ዓመታት ሲመረት የቆየ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ15 ሚልዮን የሚበልጥ መኪና ተመርቷል።

^ አን.10 የአየር ከረጢቶች ብቸኛ የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች ከሆኑ በተለይ ለሕፃናትና ለአጫጭር ሰዎች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

[በገጽ 22-25 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሰንጠረዥ]

ዓመቶቹ መኪናዎቹ የተሠሩባቸውን ዓመታት የሚያመለክቱ ናቸው

1885 የቤንዝ መኪና

በዓለም የመጀመሪያው አውቶሞቢል

1907-25 ሮልስ ሮይስ፣ ሲልቨር ጎስት

የተባለው ሞዴል ፈጣን፣ ኃይለኛ፣ ምቹና አስተማማኝ ነበር

1908-27 ፎርድ ሞዴል ቲ

መኪና በብዛት መመረት የጀመረበት፣ ከ15,000,000 የሚበልጡ መኪናዎች ተሽጠዋል

ከበስተጀርባ:- የፎርድ መገጣጠሚያ ፋብሪካ

1930-7 ካዲላክ ቪ16 7.4-ኤል

በዓለም የመጀመሪያው ባለ 16 ሲሊንደር ሞተር

1939–ዛሬ ቮልስዋገን ቢትል

ከ20,000,000 በላይ ተመርቷል። በ1998 የተመረተው አዲሱ ቢትል (ከታች በስተግራ)

1941–ዛሬ ጂፕ

የዚህን ያህል በዓለም የታወቀ መኪና የለም

1948-65 ፖርሸ 356

የቮልስዋገን ቢትልን መሠረት በማድረግ የተሠራ መኪና

1952-7 መርሴድስ-ቤንዝ 300 ኤስ ኤል

ጉልዊን የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አካሉ ከአሉምኒየም ውህዶች የተሠራና ያለ ካርቡሬተር የሚሠራ ሞተር ሆኗል

1955-68 ሲትሮይን ዲ ኤስ 19

መሪውና ፍሬኑ በሃይድሮሊክ ኃይል የሚሠራ፣ አራት የፊት ማርሽ ያለውና፣ በራሱ ከፍና ዝቅ የሚል ሰስፔንሽን ያለው

1959–ዛሬ ሚኒ

ይህ ዘመናዊና ብዙ ተወዳጅነት ያተረፈ መኪና በውድድሮችም ላይ ውጤታማ ሆኗል

1962-4 ፈራሪ 250 ጂ ቲ ኦ

ባለ 300 ፈረስ ጉልበት ቪ-12 ሞተር ያለውና ኃይለኛ የሆነ የውድድር መኪና

1970-3 ዳትሰን 240ዜድ

አስተማማኝና ርካሽ የሆነ የስፖርት መኪና

1970–ዛሬ ሬንጅ ሮቨር

ከዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ባለ ሁለት ዲፈረንሲያል መኪና እንደሆነ ይታሰባል

1984–ዛሬ ክራይስለር ሚኒባሶች

በጣም ተወዳጅ እንዲሆኑ ያስቻለ ሚኒባስ

ትረስት ኤስ ኤስ ሲ

ጥቅምት 15 ቀን 1997 በዩ ኤስ ኤ ኔቫዳ የሚገኘውን የብላክ ሮክ ምድረ በዳ በማቋረጥ በሰዓት የ1, 228 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ልታስመዘግብ ችላለች

[ምንጭ]

Benz-Motorcar: DaimlerChrysler Classic; background: Brown Brothers; Model T: Courtesy of VIP Classics; Rolls-Royce: Photo courtesy of Rolls-Royce & Bentley Motor Cars

Jeep: Courtesy of DaimlerChrysler Corporation; black Beetle: Courtesy Vintage Motors of Sarasota; yellow Beetle: VW Volkswagen AG

Citroën: © CITROËN COMMUNICATION; Mercedes Benz: PRNewsFoto

Chrysler Minivan: Courtesy of DaimlerChrysler Corporation; Datsun: Nissan North America; Thrust SSC: AP Photo/Dusan Vranic