በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መኮረጅ ምን ስህተት አለው?

መኮረጅ ምን ስህተት አለው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

መኮረጅ ምን ስህተት አለው?

“መኮረጅ ስህተት እንደሆነ ሁሉም ያውቃል፤ ሆኖም የሚቀላቸው እንደዚያ ማድረግ ነው።”​—የ17 ዓመቱ ጂሚ

ፈተና ላይ እያለህ አጠገብህ ከተቀመጠው ተማሪ ለመኮረጅ ቃጥቶህ ያውቃል? ከሆነ እንደዚህ የምታስበው አንተ ብቻ አይደለህም። የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ጄና አብረዋት የሚማሩት አብዛኞቹ ወጣቶች በመኮረጃቸው እንደማያፍሩ ስትናገር “እንዴት እንደሚኮርጁ በጉራ ያወራሉ። እናንተ የማትኮርጁ ከሆነ እንደ ልዩ ፍጥረት ይመለከቷችኋል!” ብላለች።

በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት በክፍል ውስጥ “ጥሩ ውጤት” ከሚያመጡት ተማሪዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት እንደሚኮርጁ ሲያምኑ ከእነዚህ መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት ሲኮርጁ ተይዘው አያውቁም። የጆሴፍሰን የግብረገብ ተቋም ከ20, 000 በሚበልጡ የመለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ “ሐቀኝነትን ማጉደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ያለ ችግር ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። መምህራን ኩረጃ ምን ያህል እንደተስፋፋ ሲመለከቱ በጣም ይገረማሉ። እንዲያውም ጋሪ ጄ ኒልስ የተባሉ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር “ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ይኮርጃሉ” እስከማለት ደርሰዋል።

አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ሐቀኞች እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ ወጣቶች ፈተና ላይ ስለሚኮርጁ ሐቀኞች ሳይሆኑ ይቀራሉ። ተማሪዎች ለኩረጃ የሚጠቀሙባቸው ምን አዳዲስ ዘዴዎች አሉ? አንዳንድ ወጣቶች የሚኮርጁት ለምንድን ነው? ይህንን ልማድ ማስወገድ የሚኖርብህስ ለምንድን ነው?

የተራቀቀ ኩረጃ

ዛሬ ተማሪዎች በተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶች ይጠቀማሉ። እንዲያውም ከሌሎች ተማሪዎች የቤት ሥራ መገልበጥ ወይም በወረቀት ላይ መልስ ጽፎ ለፈተና መቅረብ ዛሬ ካሉት በቴክኖሎጂ የተራቀቁ የኩረጃ ዘዴዎች አንጻር ሲታዩ እንደ ተራ የሚቆጠሩ ሆነዋል። ለኩረጃ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል በሌላ ቦታ ካለ ሰው የፈተናውን መልስ ለመቀበል የሚያስችል መሣሪያ (ፔጀር)፣ “ተጨማሪ” መረጃ የያዙ የስሌት ማሽኖች፣ መልስ ለሚነግራቸው ሰው የፈተናውን ጥያቄ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ በልብስ ውስጥ የሚደበቁ አነስተኛ ካሜራዎች፣ አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆች በጨረር አማካኝነት መልእክት ለማስተላለፍ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ይገኙባቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ በማንኛውም ርዕስ ላይ የተዘጋጁ የመመረቂያ ጽሑፎችን እንኳን ከኢንተርኔት ማግኘት ይቻላል!

መምህራን ይህንን አስደንጋጭ አዝማሚያ ለመግታት እየታገሉ ቢሆንም ሥራው እንዲህ የዋዛ አልሆነላቸውም። ደግሞም በኩረጃ ሥር የሚፈረጁት ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው በሚለው ነጥብ ላይ ራሱ ሁሉም ተማሪዎች ወይም መምህራን ተመሳሳይ አመለካከት የላቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ ተማሪዎች በቡድን የሚሠሩት ሥራ በሚሰጣቸው ጊዜ የትኞቹ ተማሪዎች በሐቀኝነት ተባብረው እንደሠሩና የትኞቹ ግን በተወሰኑ ተማሪዎች ብቻ እንዳሠሩ መለየት አዳጋች ይሆናል። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ደግሞ ሆን ብለው በማልመጥ ሥራውን ሁሉ ለሌሎቹ የቡድኑ አባላት ይተዉታል። ዩጂ የተባለ አንድ የኮሌጅ ተማሪ እንዲህ ብሏል:- “ከእነዚህ ወጣቶች አንዳንዶቹ በጣም ሰነፎች ከመሆናቸው የተነሳ አንዲት ነገር አይሠሩም! ያም ሆኖ ግን ሥራውን ከሠሩት ተማሪዎች እኩል ውጤት ያገኛሉ። እንደኔ ከሆነ ይህም ከኩረጃ ተለይቶ አይታይም።”

ተማሪዎች የሚኮርጁት ለምንድን ነው?

አንድ ጥናት እንዳመለከተው አብዛኞቹ ተማሪዎች የሚኮርጁበት ዋነኛው ምክንያት ስለማያጠኑ ነው። ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ቤት ያለው የፉክክር መንፈስ ወይም ወላጆቻቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርጉባቸው ግፊት ከመኮረጅ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። የ13 ዓመቱ ሳም “ወላጆቼ ለውጤት ያላቸው አመለካከት በጣም ከፍተኛ ነው” ብሏል። “‘በሒሳብ ፈተናህ ስንት አገኘህ? በእንግሊዝኛስ?’ እያሉ ይጠይቁኛል። ይህ ደግሞ በጣም ያናድደኛል!”

አንዳንዶች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ የሚደረግባቸው የማያቋርጥ ግፊት እንዲኮርጁ ያነሳሳቸዋል። ዘ ፕራይቬት ላይፍ ኦቭ ዘ አሜሪካን ቲንኤጀር የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ተማሪዎች፣ ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ የሚደረግባቸው ግፊት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ መማር የሚያስገኘውን እርካታ ከማጣታቸውም በላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ሲሉ ለመኮረጅ ይገደዳሉ።” ብዙ ወጣቶች በዚህ አባባል ይስማማሉ። ደግሞም ማንም ተማሪ ቢሆን በአንድ ትምህርት ይቅርና በአንድ የመልመጃ ፈተና እንኳን መውደቅ አይፈልግም። ጂሚ የተባለ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ “አንዳንዶች እንዳይወድቁ በጣም ይሰጋሉ። መልሱን ቢያውቁትም እንኳን እርግጠኛ ለመሆን ሲሉ ይኮርጃሉ” ብሏል።

ለሐቀኝነት ብዙም ግድ የሌላቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸው ኩረጃ ምንም ጉዳት የሌለው ድርጊት እንዲመስል አድርጎታል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል። የ17 ዓመቱ ግሬግ እንዲህ ብሏል:- “ትናንት ፈተና ስንፈተን አንደኛው ልጅ ሲኮርጅ አየሁት። ዛሬ የፈተና ወረቀቱ ሲመለስልን የእሱ ውጤት ከእኔ ይበልጥ ነበር።” ኩረጃ በጣም መስፋፋቱ ብዙዎች አቋማቸውን እንዲለውጡ ያደርጋቸዋል። ዩጂ “አንዳንድ ወጣቶች ‘ሌሎች የሚኮርጁ ከሆነ እኔም እኮርጃለሁ’ ብለው ያስባሉ” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ይህ ትክክል ነውን?

አታላይ የሆነ ሱስ

እስኪ ኩረጃን ከስርቆት ጋር እናወዳድረው። ብዙ ሰዎች የሚሰርቁ መሆኑ ስርቆትን ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርገዋል? ‘በፍጹም አያደርገውም’ ትል ይሆናል፤ በተለይ ደግሞ የተሰረቀው የአንተ ገንዘብ ከሆነ እንደዚህ ብለህ መመለስህ የማይቀር ነው። ስንኮርጅም እኛ ያልለፋንበትን ነገር ለማግኘት እየሞከርን ነው፤ ምናልባትም በሐቅ የሚሠሩትን ተማሪዎች እየጎዳናቸው ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 4:28) በቅርቡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ቶሚ እንዲህ ብሏል:- “መኮረጅ ፈጽሞ ትክክል ያልሆነ ድርጊት ነው። የማታውቁትን ነገር ‘አውቀዋለሁ’ ያላችሁ ያህል ነው። ይህ ደግሞ ውሸት ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ያለውን አቋም “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ” በማለት በግልጽ አስቀምጦታል።​—⁠ቆላስይስ 3:9

መኮረጅ፣ ለማቆም አስቸጋሪ ከሆነ ሱስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጄና እንዲህ ብላለች:- “የሚኮርጁ ተማሪዎች ፈተናውን ለማለፍ ማጥናት እንደማያስፈልጋቸው ስለሚያውቁ መኮረጃቸውን ይቀጥላሉ። ከዚያም ራሳቸውን በሚችሉበት ጊዜ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚኖርባቸው ግራ ይገባቸዋል።”

በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ልብ ልንለው የሚገባ ነው። መኮረጅ ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል የሕሊና ወቀሳ፣ በጓደኞች ዘንድ እምነት ማጣት እንዲሁም የመማር አጋጣሚህን ሳትጠቀምበት በመቅረትህ የመማር ችሎታ መቀነስ ይገኙበታል። ልክ አደገኛ እንደሆነ የካንሰር በሽታ ሁሉ እንደዚህ ዓይነቱ የማታለል ዝንባሌም ሌሎች የሕይወትህን ክፍሎች ሊነካና ከፍ አድርገህ የምትመለከታቸውን ዝምድናዎች ሊያበላሽብህ ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ማታለልን ከሚጠላው አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ያበላሽብሃል።​—⁠ምሳሌ 11:1

የሚኮርጁ ተማሪዎች የሚያታልሉት ራሳቸውን ነው። (ምሳሌ 12:19) በዚህ ድርጊታቸው በጥንቷ እስራኤል እንደነበሩት “ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፣ በሐሰትም ተሰውረናልና” እንዳሉት በሥነ ምግባር የተበላሹ መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 28:15) ሐቁ ሲታይ ግን አታላይ የሆነ ሰው ተግባሩን ከአምላክ መሰወር አይችልም።​—⁠ዕብራውያን 4:13

አትኮርጁ!

ለመኮረጅ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉና ዘዴ የሚጠቀሙ በርካታ ወጣቶች ይህን ችሎታቸውን በሐቀኝነት ለመማር ቢያውሉት የተሻለ ውጤት ማግኘት ይችሉ ነበር። የ18 ዓመቷ አቢ “ለመኮረጅ የሚበረቱትን ያህል ለማጥናት ቢበረቱ ኖሮ የት በደረሱ ነበር” ብላለች።

እንድትኮርጅ የሚደረግብህ ግፊት ቀላል እንደማይሆን አይካድም። ይሁን እንጂ ይህንን የሥነ ምግባር ወጥመድ ማስወገድ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 2:10-15) እንደዚህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትሄደው ለመማር መሆኑን አትዘንጋ። እርግጥ ነው መቼም የማትጠቀምበትን እውቀት መሰብሰብህ እምብዛም ትርጉም የሌለው ሊመስልህ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ይህን ጊዜ በመኮረጅ ቢያሳልፍ አዳዲስ ነገሮችን የመማርና እውቀቱን ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ እንዳያዳብር ያደርገዋል። ምንጊዜም ቢሆን እውቀት ያለ ጥረት አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነትን ግዛ አትሽጣትም፣ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም” ይላል። (ምሳሌ 23:23) በእርግጥም ጥናትንና አስቀድሞ መዘጋጀትን አክብደህ ልትመለከተው ይገባል። ጂሚ “ከፈተና በፊት ማጥናት አለብህ። እንደዚህ ማድረግህ በራስህ ተማምነህ ፈተናውን እንድትሠራ ይረዳሃል” በማለት ይመክራል።

አልፎ አልፎ ሁሉንም መልሶች ባለማወቅህ ዝቅተኛ ውጤት ልታገኝ እንደምትችል እሙን ነው። ያም ሆኖ ግን ሐቀኝነትህን ካላጎደልህ ውጤትህን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንዳለብህ ታውቃለህ።​—⁠ምሳሌ 21:5

ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ዩጂ የይሖዋ ምሥክር ነው። አብረውት የሚማሩት ልጆች እንዲያስኮርጃቸው ሲጠይቁት ምን እንደሚያደርግ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በመጀመሪያ ደረጃ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን እነግራቸዋለሁ። የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኞች መሆናቸውን ስለሚያውቁ እንዲህ ማድረጌ በጣም ይረዳኛል። በፈተና ወቅት አንድ ሰው መልስ እንድሰጠው ቢጠይቀኝም እሺ አልለውም። ከዚያም ለምን እንደዚያ እንዳደረግሁ በኋላ ላይ አስረዳዋለሁ።”

ዩጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጻፈው “በሁሉም መንገድ በመልካም [“በሐቀኝነት፣”NW ] ለመኖር እንመኛለን” ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ዕብራውያን 13:18 የ1980 ትርጉም ) ከፍ ያሉትን የሐቀኝነት መሥፈርቶች መጠበቅህና አለመኮረጅህ የልፋትህን እውነተኛ ዋጋ እንድታገኝ አስተዋጽዖ ያደርጋል። በታማኝነት የምታገኘው ውጤት ለወላጆችህ ልትሰጠው የምትችለው ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ውድ ስጦታ ነው። (3 ዮሐንስ 4) ከዚህም በላይ ንጹህ ሕሊና ይኖርሃል እንዲሁም የይሖዋ አምላክን ልብ ደስ እንደምታሰኝ በማወቅህ እርካታ ታገኛለህ።​—⁠ምሳሌ 27:11

እንግዲያው ኩረጃ የቱንም ያህል የተለመደ ቢሆን ላለመኮረጅ ጥንቃቄ አድርግ! እንደዚህ በማድረግ ከሌሎች ጋር፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የእውነት አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ያለህን ጥሩ ዝምድና ለመጠበቅ ትችላለህ።​—⁠መዝሙር 11:7፤ 31:5

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሚኮርጅ ሰው ድርጊቱ ስርቆት መሆኑን አይገነዘብ ይሆናል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መኮረጅ አብዛኛውን ጊዜ ይበልጥ ከባድ ወደሆኑ የማጭበርበር ድርጊቶች ይመራል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሚኮርጅ ሰው ድርጊቱን ከአምላክ መሰወር አይችልም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፈተና በፊት በደንብ ማጥናትህ በራስህ እንድትተማመን ይረዳሃል